
ባለፉት ተከታታይ እትሞቻችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ ፣ ማህበራዊ ፣ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ዲፕሎማሲያዊ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ለተነሱ ጥያቁዎች ሰፊ ምላሽ እና ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል ። በዛሬው እትማችን የቃለ መጠይቁን የመጨረሻ ክፍል እንደሚከተለው አቅርበነዋል ።
ኢቲቪ ፦ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ፓርቲያዊ ጉዳይ ልውሰድዎት ኢትዮጵያ በታሪኳ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳተፉባቸው ሂደቶችን አሳልፋለች እና ብልፅግና ከእነዚህ ካለፍንባቸው ፓርቲዎች ለየት የሚያደርገው ምንድነው?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፦ ብልፅግና ታምራዊ ፓርቲ ነው:: ብልፅግና በብዙ መንገድ እስካሁን ከነበሩ ፓርቲዎች ይለያል በሳይዙ፤ በአደረጃጀቱ፤ በእሳቤው በሚያስገኛቸው ውጤቶች በሚኖረው ቆይታ ሁሉ ይለያል:: አንደኛ ኢትዮጵያዊንን በሙሉ በሰፈር ሳይከፋፈል አቅፎ የያዘ ብቸኛ ፓርቲ ነው:: ሁለተኛ በዚህ ጥቂት ወራት ውስጥ ከጉባዔው በኋላ ባለው ጊዜ እንኳን ጨምሮ ዛሬ 16 ነጥብ 3 ሚሊዮን አባል ያለው ፓርቲ ነው:: በአፍሪካ ትልቁ ፓርቲ ነው:: ሁሉን ያቀፈ መሆኑ በሳይዙ ትልቅ መሆኑ ብቻ ግን አይደለም::
ትልቅ ራዕይ ያለው፤ ግልጥ ያለ ፕሮግራም ያለው ግልጥ ያለ ሥርዓት ያለው እያንዳንዱ ፖሊሲዎቹ በፓርቲ ብቻ ሳይሆን በመጻፍ መልክ የተገለጹ በራሱ እሳቤዎች ላይ አባላት በሃሳብ ተግባብተው ወደ ሥራ ተሰማርተው በውጤት የሚለኩበት ሥርዓት ያለ:: በግምገማ እና በጭቅጭቅ ሳይሆን በውጤት ላይ ያተኮረ ፓርቲ ነው::
ብልፅግና ስያሜው በራሱ መጤን ይኖርበታል:: ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የፓርቲ ሥርዓት ስለፓርቲው ተክለ ሰውነት የሚያወራ ስያሜ እንጂ ስለሚያመጣው ውጤት የሚያወራ አልነበረም:: የሠራተኞች ፓርቲ፤ የማን የሠራተኞች፤ የእንትን ብሄር ፓርቲ፤ የሶሻሊስት ንቅናቄ ፓርቲ አይነት የነበረ ነው:: ድርጊቶቹም ፓርቲዎቹም ወይ በዘር ወይ በሆነ መንገድ ስለ እነሱ የሚናገሩ እንጂ ስለሚያመጡት ጉዳይ አይናገሩም::
ለምሳሌ የኦሮሞ ድርጅት ፓርቲ የአማራ ድርጅት ፓርቲ፤ ትግራይ ድርጅት ፓርቲ የሚለው ጉዳይ የማን እንደሆ ስለራሱ ይገልጻል እንጂ ምን ሊያደርግ፤ ምን ሊያመጣ እንደሆነ ስያሜው በራሱ አይገልጽም:: ራዕይውን አያመላክትም፤ ብልፅግና ግን ግቡን ነው የሚያሳየው በእያንዳንዱ፤ ቅድም ከትርክት ጋር ያያያዝኩልሽ ነገር አለ::
ብልፅግና ፓርቲ፤ ብልፅግና የሚያመጣ ብልፅግና ለማምጣት እያልን የምናደርገው የትርክት ግንባታ በራሱ እራያችንን ስለሚያስታውሰን፤ ግባችንን ስለሚያስታውሰን፤ መርህ መልህቃችን ስለሚሆን፤ ግን መልህቃችን ስለሚሆን አንስትም ማለት ነው::
ብዙ ፓርቲዎች እንደዛ አይነት የስያሜ አጠቃቀም አይጠቀሙም፤ በጣም ክፍት ፓርቲ ነው:: ከውጭ ሀገር መጥተው የተቀላቀሉ ሰዎች አሉ:: ፓስፖርታቸውን ቀይረው የእኛ ፓርቲ አባል የሆኑ ሰዎች አሉ:: የተቃዋሚ ፓርቲ የነበሩ ሰዎች የመንግሥታችን አካል የሆኑ አሉ:: ከተቃዋሚ ፓርቲ አባላችን የሆኑ ሰዎች አሉ:: ክፍት ነው ለወጣቱ በተለያዩ ዓለም ላሉ ሰዎች ክፍት ሆነ ፓርቲ ነው::
ምክንያቱም በሥርዓቱ፤ በሂደቱ ነው ሰው እየነጠረ የሚወጣው ብሎ ስለሚያስብ:: አዲስ ደም ለመቀበል ያለው ዝግጅት በጣም ለየት ያደርገዋል:: በኢትዮጵያ ታሪክ እኮ እንደ ብልፅግና በከፍተኛ ድምጽ አሸንፎ የለም ብቻዬን አልመራም ትፎካከሩና አብረን መንግሥት እናስተዳድር ያለ ማን አለ እስካሁን እኮ ሰምተን አናውቅም ብልፅግና እንደዚህ አይነት የተከፈተ ልብ ያለው ፓርቲ ነው::
ይሄ የእኔ የግል ውሳኔ አይደለም:: የብልፅግና ፓርቲ ውሳኔ ነው:: የሚፎካከሩ ፓርቲዎች እናስገባ ስንል በእነሱ ምትክ የሚወጡ የብልፅና አመራሮች አሉ:: እኔ አልወጣሁም ወጥተው ነው እነሱ ይግቡ ያሉት:: የእነዛ የጀግና የብልፅግና አመራሮች ውሳኔ ጭምር ነው ይሄ ውጤት የግል ወጤት አይደለም::
እና ብልፅግና ክፍት መሆኑ፤ አቃፊ መሆኑ፤ አካታች መሆኑ ከብሔር ጽንፈኝነት የጸዳ መሆኑ፤ ለብሔራዊ ትርክት የሚተጋ መሆኑ፤ የኢትዮጵን ትልቁን ጥላ የኢትዮጵያን ትልቁን አቅም፤ የኢትዮጵያን ትልቁን ማሰብ የሚያምን መሆኑ፤ ዳር የነበሩትን የተረሱትን መሃል ያመጣ መሆኑ፤ ለዲሞክራሲ ቀናኤ መሆኑ::
ብልፅግና ተፈጥሮ በሚድህበት ዘመን የተደረገው ምርጫ ሌሎች ፓርቲዎች ተፈጥረው በጣም ብዙ ቆይተው ካደረጉት ምርጫ ይሻላል:: ለዲሞክራሲ ቀናኢነት አለው፤ አቃፊ ነው፤ ብዙ አባላት አሉት:: ብዙ አስደማሚ ጉልበት ከጀርባው ይዟል እና በብዙ መንገድ ብልፅግና ተስፋ ሚጣልበት ለአፍሪካ ምሳሌ ሚሆን የራሱ ሃሳብ ግልጽ ሃሳብ ያፈለቀ በማንም አይዶሎጂ ያልታሰረ ከሰዎች የተማረ ግን የራሱን የገነባ ሀገር በቀል አልኩት ቅድም ማለት ነው::
ፍልስፍናችን ቀድተን አይደለም ተምረናል ግን ሀገር በቀል ሃሳብ ነው ያለን:: በሃሳብ በተግባሩ በአደረጃጀቱ በሳይዙ በራዕይው በመጠሪያውም ጭምር ከሌሎች ፓርቲዎች የተለየ እና የሚያጓጓ ፓርቲ ነው:: የዚህ ፓርቲ አባል ባለመሆንሽ በጣም ነው የማዝንልሽ::
ኢቲቪ ፦ ወደ መንግሥታዊ ሥራ ጉዳይ እንመለስና ከመንግሥት ሥራ ኃላፊነት ጋር በተገናኘ በማህበረሰቡ ዘንድ የሚነሱ አንዳንድ ችግሮች አሉ:: በተለይ ከሙስና እና ብልሹ አሠራር ጋር የተገናኙ የሚነሱ ብዙ ቅሬታዎች አሉ፤ የሚነሱ ሃሳቦች አሉና እዛ ላይ መንግሥት ምን ያህል ቁርጠኛ ሆኖ እየሠራ ነው ብሉሹ አሠራርን እና ሙስናን ከማስተካከል እረገድ?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፦ ሌብነት ኢትዮጵያ ውስጥ ልክ እንደ ርዳታው አንዱ ስብራት የምንለው፤ አንዱ ጥፋት መንገድ ምንለው ካልተገራ በቀር ያ ቅድም ያልኩት ራዕይ ለማሳካት እንቅፋት ነው የምንለው ጉዳይ ነው:: ሌብነት በጣም አደገኛ ስብራት ነው:: ገንዘብም ሌብነት፤ የጊዜም ሌብነት፤ የማልመጥም ሌብነት በመትጋት ላይ ባለች ሀገር ውስጥ እንቅፋት ነው::
ነገር ግን ሌብነት ኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥት የሚለው ጉዳይ ቆይቶ የጋራ ባህል እየሆነ መጥቷል:: እሴት ሸርሽሯል ሞራል ሸርሽሯል ፤ እምነት ሸርሽሯል እንደሚገባ ነገር ተወስዷል ሰዎች ሰርቀው ህንጻ ቢገነቡ እንደ በለጡ የሚያስብ ማህበረሰብ ሰፊ ነው:: አንድ ጊዜ ስብሃት ገብር እግዚያብሄር ምናለ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ እኮ ይገርማል ፖሊስ ሌባ እያሯሯጠ ወደ ግራ ወደ ቀኝ እያለ ሌባውን ያስመልጣል:: ፖሊሱን አግዞ ሌባውን እንደመያዝ ፖሊሱ ሌባውን ደርሶ እንዳይዝ አስመላጭ ነው::
ዛሬ ዛሬ ታክሲ ውስጥ እዚህ ከተማ ታክሲው ትርፍ ጭኖ ቢሄድ ትራፊክ ከሩቅ ሲያይ ተሳፋሪ ምን ያደርጋል አጎንብሶ የሌብነት ተባባሪ ሆኖ፤ የሕገ ወጥነት ተባባሪ ሆኖ የታክሲ ሹፌሩ ያን ሕገ ወጥ ተግባር እንዲቀጥልበት ያድርገዋል:: ትርፍ ቢያስከፍል ትራፊክ ቢይዝ ትራፊክ ፖሊስ ብይዝ ከፍያለው የሚል ሰው አለ እንዴ አልከፍልንም ነው የሚለው:: ሰራቂው ብቻ ሳይሆን የሚሰረቀውም የሚተባበርበት ባህል ተገንብቷል::
አለመስረቅ ተገቢ አይደለም የሚል እሳቤ በግለሰብ አለማሰብ ብቻ ሳሆን ማህበረሰቡም እየተቀበለው መጥቷል:: እንደዚህ አይነት ስር የሰደደ ስብራት በንግግር፣ በፖሊሲ ብቻ የምንቀርፈው ጉዳይ አይደለም:: ስር ሰዷል እኛ በሶስት የከፈልነው ይህንን ጉዳይ በኮሚቴ፤ በጥናት፤ በጸረ ሙስና ምናምን ሞክረናል ብዙ አስረናል፤ ብዙ አባረናል፤ ብዙ ቀይረናል ሰዎች፤ ግን አንዱ ይቀየራል አንዱ ይመጣል፤ ባህሉ እስካልተቀየረ ድረስ የሚሸረሸር ሆኖ አላየነውም፤ እና ለሦስት ከፈልነው::
የመጀመሪያው ምዕራፍ መንግሥታዊ ሌብነት፣ ተቋማዊ ሌብነትን ማስቆም ነው:: ይሄ መንግሥታዊ ሌብነት የለም ጠፍቷል ሲል ብዙ ግራ የሚገባቸው ሰዎች አሉ:: አሁንም በእርግጠኝነት የምናገረው ኢትዮጵያ ውስጥ መንግሥታዊ ሌብነት የለም:: ምን ማለት ነው አንድ ኩባንያ የብልፅግና ብዬ ፈጥሬ ምንም እንዳልነበረው፣ ታሪክ እንዳልነበረው እየታወቀ ኮንትራት ስጡት ብድር ስጡት ብዬ ቢሊየነር የማደርገው ኩባንያ የለኝም::
አላደርግም እንደሱ፤ እኔ ከከንቲባ፤ ከክልል አስተዳደር፣ ከሚኒስትር ጋር ተነጋግሬ ይሁነኝ ብዬ የምደብቀው ወርቅ የማሸሸው ወርቅ የለም:: በመንግሥት ደረጃ የተገኘችውን እያንዳንዷን ሰሙኒ የምናውለው ለኢትዮጵያ ልማት ነው:: ይሄ ጥፋቱም ቶሎ አይታይም፤ ስብራቱም ከፍተኛ ነው ሰውም ግን አይገነዘበውም፤ ለኮሌክቲቭ ጥቅማችን ለናሽናል ኢንተረስት ከፍተኛ ጉዳት ያለው ግራንድ ኮራፕሽን ነው::
አደገኛ ነገር ነው፤ ለዚህ ነው ቅድም የማነሳልሽ ኤክስፖርት የቡናው የምኑ እኮ የሚያያዝ ነገር አለው:: ባለመመረት ብቻ የሚሆን አይደለም ወርቁም ሌላውም ነገር፤ የተቀናጀ ዘረፋ፣ ፓወር ያላቸው ሰዎች ዘረፋ የሚደረግበት፤ በግል አይደለም በቡድን በሚደረግበት ሰዓት በከፍተኛ ደረጃ የሀገር ዕድገት ያዳክማል::
በዚያ ደረጃ መቶ ፐርሰንት ኢትዮጵያ ውስጥ ኮራፕሽን የለም፤ መንግሥት ተደራጅቶ መክሮ ዘክሮ እንትናን እጠቅማለሁ እንትናን እጎዳለሁ ብሎ አይሠራም እርግጠኛ ነኝ በዚህ:: ይሄን እንደ ትልቅ ድል እወስደዋለሁ፤ ይሄ ማለት ግለሰብ ሌባ የለም ማለት አይደለም:: በግሉ የሚሰጥ ሰው የለም፤ የሚደራደር የለም ማለት አይደለም፤ የግሉ ውሳኔ ነው እሱ፤ ያም ሆኖ በአመራር ደረጃ ራዕይ ለማጋራት ተሞክሯል::
በሌብነት አይደለም የሚሳክልን ሠርተን ጥረን ግረን ኢትዮጵያን ስንቀይር ነው ችግራችን የሚቀረፍ የሚለው እምነት በከፍተኛ እምነት ከፍተኛ አመራር ደረጃ በስፋት በውይይት በሥልጠና የራዕይ መጋራት ሥራ ሠርተናል፤ መቶ ፐርሰንት እያንዳንዱ ሰው ምንም እንከን የለበትም ብዬ ደፍሬ መናገር ባልችልም አብዛኛው ከፍተኛ አመራር በእርግጠኝነት ሌብነት ውስጥ የለበትም::
በከፍተኛ ደረጃ ያሉ አመራሮች ብዙ በዚህ ሥጋት የለኝም:: ውሏቸውን ሥራቸውን በቅርበትም ስለማይ፣ ግን አመራሩ ሰፊ ነው፤ ቅድም እንዳልኩት 16 ሚሊዮን አባል ያለው ነው፤ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ሰዎች ያሉበት ነው፤ ስለለሁሉ ሰው መናገር እሱ ደግሞ በምን ያህል ራዕይ ተጋርቶ በተደራጀ ሌብነት ውስጥ ምን ያህል ቀነሰ የሚለው ገና ረጅም ሥራ የሚጠይቅ ይሆናል:: በቅርበት ባሉት ግን ሥጋት ብዙም የለኝም::
ሁለተኛው ምዕራፍ ፒቲ ኮራብሽን የሚለው፤ ቅድም እንዳልሽው ለሰርቪስ ሰው መታወቂያ ሲያወጣ አንዳንድ ሰርቪስ ሲያገኝ የሚከፍለው ነገር ማለት ነው ሰጪውም ተቀባዩም ባለው ነገር፤ ይሄ እውነት ለመናገር በጣም አስቸጋና ሕዝብ የሚያስመርረው ነገር ነው:: ያኛው ሰው ብዙ አያውቀውም ግራንዱ ጉዳቱ እየቆየ ሰባሪ ቢሆንም ቶሎ አይታወቅም፤ ይሄኛው ግን ይታወቃል::
ሰው ለመደ በቃ፤ መደራደር ኮሚሽን መውሰድ ልማድ አደረገው:: ይሄን ለመፍታት አማራጩ መንገድ ሲስተም መዘርጋት ብቻ ነው፤ ለምሳሌ፤ አንዱ ሌብነት መሬት ነው፤ እኔ ራሴ ኤክስፐርት ሆኜ ኢንሳ ሆኜ አዲስ አበባ ላይ አዳማ ላይ በጂኦስፓሻል አውቶሜት ለማድረግ ሞክሬያለሁ አልተሳካልኝም፤ ሲስተሙ እያሉ አልተሳካልኝም አልፈቀደልኝም ሲስተሙ ሥርዓቱ::
አሁን አዲስ አበባ ኦውቶሜትድ ነው እያንዳንዷ ትታወቃለች፤ ቢሾፍቱ አዳማ ሸገር ዋና ሌብነት አለበት የሚባለው አካባቢ መቶ ፐርሰንት በጂኦስፓሻል ሲስተም ውስጥ ገብቷል፤ እያንዳንዱ ከንቲባ የትኛዋ መሬት የማን ምን መቼ እንደሆነች ያውቃል:: ይሄ ግን ሌብነቱን ዜሮ አያደርገውም፤ ሰው ሲስተም ስንዘረጋ ሲስተሙን የሚሻገርበትን ይፈጥራል፤ ሙቪንግ ታርጌት ነው ሌብነት እዚህ ጋ ሲዘጋ እዚህ ጋ፤ ቋሚ አይደለም፤ በዘጋነው በር ብቻ የሚቆም አይደለም:: ያንን እየተከተሉ መዝጋት ያስፈልጋል::
ሁለተኛው መሶብ፣ መሶብ ለኢትዮጵያ ለኤፌሺየንሲ፣ ለቅልጥፍና ለዕድገት በእጅጉ የሚያግዝ ሥርዓት ነው፤ መሶብ ማለት ድሮ ወታደር ቤት እያለሁኝ የሲዊዝ ቢላ የሚባል ነበር፤ የሲዊዝ ቢላ አንድ ናት ትንሽ ናት ግን ከውስጣ መቁረጫ አለ መስፊያ አለ ከውስጡ እየቀጣ መቁረጫ አለ ይመዘዛል ከውስጡ አንዷ እዚህ ጋ የምትያዘዋ ቢላዋ በውስጧ ግን በርካታ ሥራዎች የሚሠሩ ቢላዎች አሉ::
እሱን እየመዘዘ አንዱ ስቃጥላ ይቆርጥበታል፣ አንዱ ጨርቅ ይቀድበታል፣ አንዱ እንጨት ይቆርጥርበታል ለበርካታ ሥራ የሚውል ማለት ነው:: መሶብ እንደዚያ ነው አንድ ሰው ቀበሌ ሄዶ መታወቂያ ከሚያወጣ ኢሚግሬሽን ሄዶ ፓስፖርት ከሚያወጣ ኢንቨስትመንት ሄዶ ላይሰንስ ከሚያወጣ ባንክ ሄዶ ብር ከሚያወጣ ቴሌ ሄዶ ሲም ካርድ ከሚያወጣ ሁሉን ሰርቪስ በአንድ ጣሪያ ሥር ማግኘት ማለት በጊዜ በገንዘብ ያለው አንደምታ ከፍተኛ ነው::
ለእያንዳንዱ ታክሲ ለእያንዳንዱ ጊዜ ስለነበረ፣ ከዚያ ባሻገር ሥርዓቱ ከኤ እስከ እዚህ በሲሰተም ክትትል ውስጥ ስለሆነ ያለው በቀላሉ ለድርድርና ለሌብነት አይመችም፤ ሰውን መከታተል ይቻላል:: በእርግጥ መሶብ አንድ ሳምፕል ናት፤ መስፋት አለበት፤ አዲስ አበባ ላይ ከጀመርን በኋላ በፌዴራል ደረጃ የአዲስ አበባ ከተማ፣ የአዳማ ከተማ የአርባ ምንጭ ሐዋሳ ባህር ዳር ሻሸመኔ በጣም በርካታ ከተሞች እየተዘጋጁ ነው፤ በሚቀጥሉት አራት አምስት ወራት ይጀምራሉ እነርሱም፤ እስፍተን ሁሉ ቦታ በአንድ ቤት ውስጥ በአንድ ሰፈር መሥራት ስንጀምር ሰው እየተደራደረ የሚያደርጋትን ነገር መቀነስ እንጀምራለን፤ ብዙ ሀገራትም የሚሆነው ይኸው ነው::
በህንድ አጋጥሟል፤ ሲንጋፖር አጋጥሟል:: ሲስተም ሲጠቀሙ ሌብነት ቀንሷል፤ ሲስተም ሲጠቀሙ ኤፊሸንሲ አድጓል:: ለዚያ ደግሞ ሲስተም መዘርጋት ብቻ ነው መፍትሔው፤ ሰው አይቀመስ! ሶ አስቸጋሪ ነገር ስለሆነ በሲስተም ነው የምንፈታው፤
ሦስተኛው ምዕራፍ ሌብነት የሚጠየፍ ባህል መገንባት ነው:: እንደ ሰው እኔ የተፈጠርኩት ሰርቪ ቫልዩ አድ ለማድረግ ነው:: ሰርቼ ለመጥቀም ነው ለመርዳት ነው የሚል በራሱ የሚኮራ የሚተማመን በውጤት የሚያምን ሰው ለመፍጠር ደግሞ የባህል ግንባታው ሰፊ ጊዜ ይወስዳል፤ ይሄም የትርክቱ ውጤት ነው::
ትርክት እያደገ ሲሄድ፣ ትርክር እየሰረጸ ሲሄድ፣ የኢትዮጵያ ዕድገት እያደገ ሲሄድ ሙቪንግ ታርጌት ስለሆነ ሌብነት ዜሮ ባይሆንም የምንማረርባቸው ጉዳዮች በእጅጉ እየቀነሱ ይሄዳሉ:: ለምሳሌ፤ ያደጉ ሀገራት ትላልቆቹ ስም ሳልጠራ ይሄ የየዕለት ኮራፕሽን ብዙ የላቸውም:: ወጥተዋል ከእሱ፤ ለመታወቂያ ለመንጃ ፈቃድ ሌብነት የላቸውም::
ግን የሌብነት አውራ ናቸው፤ ከፍ ሲባል ከፍተኛ ሌብነት ነው ያለው፤ አይቀርም ይቀያየራል ቦታው፤ ከፍተኛውም ዝቅተኛውም አደገኛ ስለሆነ በሥርዓት ትርክት እየገነባን ስናጠፋው ያ ለኢትዮጵያ ዕድገትና ብልፅግና መረጋገጥ እጅጉን ጠቃሚ ይሆናል:: አሁን ግን እንደ አንድ ትልቅ ስብራት ልክ እንደ ልመናው አይተን በምዕራፍ ከፍለን እየሠራንበት ያለ ጉዳይ እንደሆነና ሕዝቡም ተባባሪ እንዲሆን ሌቦች ማጋለጥ አለመተባበር፣ ታክሲም ትሁን ቦታዋ፣ በትንሽ ያልታመነ በትልቅ አይታመንም:: በትንሽ ላይ ስርቆት የጀመረ ከፍ ሲል አያቋርጥም::
ለዚህ ነው ተረትም እኮ አለ በሀገራችን እናቴ በቀጣሽኝ የሚለው እኮ እሱን ነው:: በትንሹ ነው መቅጣት የሚያስፈልገው እና ሕዝቡ ተባብሮ ትርክቱን ገንብተን እድገት እየመጣ ሲሄድ ይሄ ሰው የሚያስመርረው አደገኛ የሆነው የሌብነት ልምምዳችን እየቀነሰ፤ በሲስተም ሚታገዝ የፈጠነ አገልግሎት እየሰጠን ሕዝባችን እፎይታ የሚያገኝበት ዘመን እየተፈጠረ እንደሚሄድ በእጅጉ ተስፋ አደርጋለሁ::
ኢቲቪ ፦ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የኮሪዶር ልማት እየተከናወነ እንደሆነ ይታወቃል፤ክብር ጠቅላይ ሚኒስትር እና የኮሪዶር ልማትን አጀንዳ ማድረግ ያስፈለገው እዛ ላይ መሥራት ያስፈለገው እንደ ሀገር ለምንድነው?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፦ የኮሪዶር ልማትን አጀንዳ አድርጎ እንደ መንግሥት አቅዶ መሥራት ያስፈለገበት በጣም በርካታ ምክንያቶች አሉ:: ሁሉን ከምዘረዝር ጥቂቶቹን ብቻ እንደ ማሳያ ብገልጽ በቂ ሊሆን ይችላል:: የመጀመሪያው ስለኮሪዶር ስናስብ ማሰብ መጠየቅ ያለብን ጥያቄ የጤና ዋጋው ስንት ነው? አንድ ሰው ስለ ጤናው በምን ተመን ነው የሚያሰላው? ከተማ ውስጥ በእግር መሄድ የማይቻልበት፤ ትንሽዬ ጉድጓድ ካለ፣ ውሃ ካለ፣ ወንዝ ካለ የቆሸሸ የሸተተበት፤ ትንሽየ ከዘነበ የዝናቡ ሪስፖንስ ከተማውን በሙሉ በሽተኛ የሚያደርግበት ሁኔታ ባለበት ከተማ ውስጥ እንዴት ነው ጤናውን በጸዳ ቦታ በንጹህ ቦታ መዋል ማደርን፤ ልጆቹ ማደራቸውን በምን ግምት ነው የሚያሰላው ፤ የኢኮኖሚ ጥቅሙ እንደተጠበቀ ሆኖ::
ሰው ካልጸዳ፣ ጥርሱ ካልጸዳ፣ ሰውነቱ ካልጸዳ፣ ጸጉሩ ካልተበጠረ በቀር እንዲህ በጋራ በሚሠሩ ሥራዎች ውስጥ ይረብሻል:: ለራሱም ጤና ለወንድምና እህቶቹ ምቾት ሲባል ሰው መጽዳት አለበት:: ከተማም እንደሱ ነው:: በጋራ ቆሽሸን የሚቆሽሽ ከባቢ ላይ የሚንኖር ከሆነ ጤናችን አደጋ ውስጥ ነው ያለው::
ይሄን እንዴት ነው የምናየው ነው አንዱ ጥያቄ? ሁለተኛ በበርካታ ጥናቶች መሠረት እስከ 2050 ድርስ የከተማ ነዋሪ ከ48 ከ50 እስከ 60 በመቶ ያድጋል ከተሜነት እየሰፋ ይሄዳል፤ እያደገ ይሄዳል፤ ለምሳሌ አዲስ አበባ ከለውጡ በፊትና ከለውጡ በኋላ ያለው ሕዝብ አንድ አይደለም:: ሰው ከተለያየ አካባቢ እየመጣ ሰው እየበዛ ነው ከተማው ያው ነው::
ቤቱ ያው ነው፤ አስፓልቱ ያው ነው፤ የውሃ መሠረተ ልማቱ ያው ነው፤ ኢነርጂው ያው ነው:: ሰው ግን እየጨመረ ነው ሰው እየጨመረ ሲሄድ ከተማ መልኩ ካልተቀየረ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የነበረው በሽታ ላይ በሽታ እየታከለበት ፕላኒንግ ከሌለ ምን አይነት ተስፋና ነገ ነው ያለን ብሎ መጠየቅ ለማንም ሰው የሚከብድ አይመስለኝም::
ከተማ ለሁሉም ከተማ ለጤና መሆን አለበት:: ከተማ ለሁሉም ስንል ከዚህ ቀደምም ቢሆን ከተማ ውስጥ ሳይዙ ቢያንስ ቢበዛ መንገድ ይሠራል:: ከዚህ ቀደም ብዬዋለሁ:: ለስንት መኪና ነው መንገድ የሚሠራው ነው፤ ስንት ሰው ነው መኪና ያለው? በርካታው ሰው በእግር ነው ሚሄደው፤ እግረኛ መንገድ ስለማይሠራለት መኪና ጋር ይጋፋል:: ከዛን አደጋ ያጋጥማል ሰው ይሞታል::
ከተማ ለሁሉም ሰው መሆን አለበት፤ ለባለ መኪናውም ለባለ እግረኛውም፤ ለባለ ሳይክሉም ይሄን አመቻችተን ካልገነባን በቀር ባለመኪኖች መንገድ ያላቸው፤ እግረኞች መንቀሳቀሻ ቦታ የሌላቸው ከሆኑ መሻማታቸው አይቀርም:: ሲሻሙ ደግሞ አደጋ ያጋጥማል ሕግ ይጣሳል:: ለሁሉም መሆን አለበት::
ከተማ ለጤና ሲባል ንጽህናው ብቻ አይደለም አሁን ለምሳሌ ቤቱ ቦሌ የሆነ ሰው የሚሠራው አራት ኪሎ ቢሆን፤ የሚሠራው ስድስት ኪሎ ቢሆን፤ አንድ ስድስት ኪሎ ያለ መምህር ክላስ ከጨረሰ በኋላ ካለምንም ችግር እተራመደ ቦሌ መሄድ ይችላል:: ካለምንም ችግር ሰፊ መንገድ ነው፤ ንጹህ ነው መብራት አለው አይሸትም አያስጠላም :: እስፖርትም እየሠራ ነው፤ ዋጋም እየቀነሰ ነው ለራሱም ጊዜ እየሰጠ ነው ከጤናም አንጻር ከማንኛውም መስፈርት አንጻር ጠቃሚ ነገር ነው ለጤናው ማለት ነው::
ይሄንን ለእግረኛ ለሳይክል ለተሽከርካሪ በተመቸ መንገድ መሥራት እየባሰ ከመጠው ሕዝብ አንጻር ሥራውን አሁን ካልጀመርን የባሰ አደጋ ከፊታችን አለ ማለት ነው:: የበለጠ እየተበላሸ ይሄዳል ማለት ነው:: እንግዲህ ሁላችንም ውጭ ሀገር ስንሄድ የማይቀና ሰው የለም:: መቼ ነው ኢትዮጵያ እንደዚህ ሆና የማይል ሰው ብዙ ያለ አይመስለኝም::
እኔ የዛሬ 20 ዓመት ገደማ ሻንጋይ ሄጄ ነበር:: ሻይንጋይ የሄድኩበት ጊዜ ሻንጋይን ያየሁበት እይታ ተስፋ አስቆራጭ ነበር የነበረው:: ከህንጻው ብዛት፤ ከከተማው ስፋት፤ ከመንገዱ ብዛት መቼ ነው ሀገሬ እንደዚህ አይነት መልክ ምትይዘው ይቻላልስ ወይ ብዬ እንድሰጋ ነበር ያደረገኝ:: በቅርቡ ሻንጋይ ሄጄ ነበር፤ ሻንጋይ በጣም ምርጥ ከተማ ነው፤ በጣም ትልቅ ከተማ ነው:: ያ የነበረኝ ድንጋጤ ግን የለኝም አሁን እንደሚቻል ደርሽያለሁ ማለት አይደለም ፤እንደሚቻል ምልክት አይችያለሁ:: ብዙ ሰዎች ውጭ ሀገር ሲሄዱ ይቀናሉ:: በብዙ ነገር ሀገራችን ቢመጣ ይላሉ ያ ቅናታቸውን ሲሠራ ደግሞ የለም ብለው ይቃወማሉ:: ይሄ እንግዲህ የእኛ ልምምድ ነው፤ ባህል ነው:: ጠንከር ያለ ሥራ ብዙም ስላለመደን ሊሆን ይችላል:: ሥነ ውበት ግን እሳቤ ነው:: ስለውበት ስለ ኤቲክስ ማሰብ፤ ስለ ኢቲኬት ማሰብ ስለ ፤ድሬሲንግ ኮድ ማሰብ በጣም ጠቃሚ ነገር ነው፡ ውበትን ማድነቅ የማይችል ሰው ተፈጥሮን ማድነቅ አይችልም፤ ተፈጥሮን ማድነቅ ማይችል ሰው መፍጠር አይችልም ::
ማስተዋል፣ ማሰብ፣ በጥልቀት መጓዝ የሚቻለው በጥልቀት መጓዝ የሚቻለው ተፈጥሮን ማድነቅ ከሚሹ ሰዎች ነው:: አብዛኛው የተፈጠረው ነገርም ከዛ ጋር የሚያያዝ ነው:: የሚያስቡ ሚያስተውሉ ከተፈጥሮ ጋር የሚጓዙ ሰዎች ናቸው:: እና ውበትን ከተፈጥሮ ሳንለይ መፍጠር ማድነቅ ማስዋብ ያስፈልጋል:: በግልም በማህበረሰብ ደረጃም :: ለምሳሌ ወንዝ ዳርቻን እንውሰድ በነገራችን ላይ አዲስ አበባ ከተሠሩ ሥራዎች እየተሠሩ ካሉ ሥራዎች በኢትዮጵያ እየተሠሩ ካሉ ሥራዎች እንደ አዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልቤን የሚያሞቅ ሥራ የለም::
ብዙ ሰው አያውቀውም :: አልቆም በደንብ ስላልታየ ከተሠራው ሥራ ሁሉ ግን ይልቃል:: የሚጀምረው ከእንጦጦ ነው ከዚህ ቀደም እንጦጦ ባህር ዛፍ ስላለ መንገድ ሠርተን ፓርክ ነው ያለው:: አሁን ግን የለም ባህር ዛፉ አፈራችንን እየሸረሸረብን ነው:: ሀገር በቀል ዛፎች እየጠፋብን ነው መተካት አለብን ስንል እየሠራን ያለነው እርከን ያ ተራራ ሁሉ በእርከን እየታጠረ ነው ያለው::
እርከን ምን ማለት ነው አፈር እንዳይሸረሸር ያደርጋል:: አፈር አንዴ ከተሸረሸረ በሺህ ዓመታት አይመለስም፤ ስለ ትውልድ እያሰብን ትውልድ ትውልድ የሚበላበትን አፈር ካልጠበቅን በምን ይበላል:: ተሸርሽሮ ይሄዳል አፈር አላቂ ሀብት ነው ቋሚ ሀብት አይደለም መጠበቅ አለበት:: ወርቅ ብቻ አይደለም የሚጠበቀው አፈር መጠበቅ አለበት እናም እርከን ምንሠራው ባህር ዛፍ ቆርጠን ሀገር በቀል ዛፍ የምንተክለው አፈራችን እንዲጠበቅ ውበቱ እንዲጨምር ነው፤ ጫካው ሞር ዴንስ እንዲሆን ነው::
ዛሬ ነው ወይ? አይደለም አሁንማ ተቆራትጧል እንጦጦ ሲታይ አያምርም:: ከሶስት ዓመት በኋላ ተመልሰሽ ተመልከቺው፤ ጉለሌ ፓርክ ያለው ውበት እንጦጦ ይደገማል:: ጉለሌ ፓርክ ያምራል በጣም ሰው አይገባበትም እንጂ፤ እንጦጦ ይደገማል፤ ጫካ ላይ ያለውም እንደዛው ነው:: ይቆረጣል ይተከላል ከአምስት ከአስር ዓመት በኋላ ኢንዲጂነስ የሆነ የሚያምር አፈሩን ሚጠብቅ በእርከን የተደገፈ ውሃ የሚቋጥር አካባቢ አለን ማለት ነው::
ከእንጦጦ ይነሳና እስከ ፒኮክ 20 ምናምን ኪሎ ሜትር ውስጥ ለውስጥ ለሳይክል፤ ፣ ለመንገድ የሚሠራው የሽታ ማስወገጃው፤ የድሬኔጅ የተሠራው ሥራ፣ መንገዱ፣ የሚተከለው ዛፍ እውነት ለመናገር በጣም በጣም በጣም ሰፊ ሥራ ነው:: ምናልባት በሚቀጥለው መስከረም ጥቅምት አብዛኛው ለጥቅም ስለሚውል ይታያል ብዬ አስባለሁ:: ክረምቱን አብዛኛውን ተክለን መስከረም ጥቅምት ላይ ብዙ ሰው ያየዋል::
እናንተ የሚዲያ ሰዎች ብታዩት ጥሩ ነው:: አስደማሚ ሥራ ነው:: አፈርን እንታደጋለን፣ ወንዙን ከሽታ እንታደጋለን፣ ዛፍ እንተክላለን፣ ሰው እንዲንቀሳቀስበት እንዳርጋለን:: እዚያ አካባቢ ፕሮፐርቲ ያላቸው ፎቅ የሠሩ ሰዎች፣ ዛሬ ዋጋው አስር ከሆነ ነገ ጥርጥር የለውም መቶ ይደርስላቸዋል::
ምንም ጥርጥር የለውም የፕሮፐርቲ ዋጋ ያድጋል:: ውብ ስለሆነ ፣ በየትኛውም መስፈርት:: የወንዝ ዳርቻ ላይ እንጦጦ ላይ ከምንሠራው ሥራዎች ውጪ ግን አንቺን፣ እኔን፣ እሱን፣ እሷን ስለሚነካ ጉዳይ ደግሞ እንየው:: ከተማው ውስጥ ስንቀሳቀስ ትራፊክ ጃም ለሥራ አያንቀሳቅስ፣ በሽተኛ አያንቀሳቅስ ሰው ይሰቃያል::
ትራንስፖርት ችግር ነው፣ ከችግሮቹ አንዱ ትራፊክ ጃም ነው:: ሲ ኤም ሲ ዘመድ የለሽም? ሲ ኤም ሲ የዛሬ ስድስት ወር፣ የዛሬ ዓመት ያለው የትራፊክ ጃም ችግር እና ዛሬ አንድ ነው? የዛሬ ዓመት እኮ ከሲ ኤም ሲ ሰዎች ጠዋት ሥራ ለመግባት አንድ ሰዓት መንገድ ላይ ይቆሙ ነበር፣ ከዛም በላይ:: አልጠፋም ቀንሷል:: ቢያንስ ሰላሳ ደቂቃ ቀንሷል::
አሁንም አማራጭ መንገድ አበራክተን ያንን መቀነስ አለብን:: ለምን ከቤት ተነስቶ መንገድ ላይ የሚቆመው ሰውዬ ነዳጅ እየበላ ነው:: ጊዜ እየበላ ነው፣ በዛ ውስጥ ደግሞ አላስፈላጊ ስልኮች እያወራ ነው:: ሀብት ነው የሚወድመው:: ፈጥኖ ቢደርስ ቢሮ፣ በጊዜ ቢሠራ፣ በጊዜ ሁለተኛ ሥራ ቢሠራ አንድ ሥራ ስለማይበቃ፣ ሁለተኛ ሥራ ቢሠራ ፕሮዳክቲቪቲ እያደገ ይሄዳል::
በእኔ እምነት አማራጭ መንገድ በቪአይፒ መንገድ በጎሮ የሚወጣ እየሠራን ስለሆነ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ሕግ ማውጣት አለብን:: ጠዋት ከአስራ ሁለት ሰዓት ጀምሮ እስከ ሁለት ሰዓት ከሲ ኤም ሲ አቅጣጫ ለሚመጡ መኪናዎች አንደኛውን ሳይሆን ሁለቱንም መንገድ መጠቀም አለባቸው:: ምክንያቱም 95 ፐርሰንት መኪና ከዛ ነው የሚመጣው:: የሚሄዱ አሉ ለነሱ አማራጭ ካበጀንላቸው ከአስራ ሁለት ሰዓት እስከ ሁለት ሰዓት ከፈቀድን በአስራ አምስት ደቂቃ፣ በሃያ ደቂቃ ያ የምናየው መኪና ጸጥ ይላል ማለት ነው::
ማታስ ከአስራ አንድ ሰዓት በኋላ? የሚመጣው ብዙ ስላልሆነ አማራጭ መንገድ ሰጥተነው የሚሄደው ሁለቱንም ይጠቀም ብንልስ:: በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል:: ሰው በጊዜ ቤቱ ገብቶ ከልጆቹ ጋር ያጠናል፣ ያስጠናል:: ቤት የሚሠራውን ሥራ ይሠራል ማለት ነው:: ትራፊክ ጃም ችግር የለውም ሊባል አይችልም፤ ችግር አለው::
መብራት ከለውጡ በፊት ሬሽን ነበር አዲስ አበባ:: አንድ ሳምንት እዛ ሰፈር፣ አንድ ሳምንት እዛ ሰፈር ተብሎ በአዋጅ ነበር የሚሠራው:: አሁን ይሄ ቀርቷል:: ግን መጥፋት አልቀረም ምክንያቱም መስመሩ ችግር ስላለባቸው በወጉ ስላልተሰሩ መብራት ሃይል እየደወልን መብራት ጠፋ፣ ተቋረጠ እንላለን::
መስመር ካልዘረጋን እና ካልቀበርን በስተቀር ያ ችግር አይፈታም:: ኮሪዶር ማለት መብራት መንገድ፣ የስልክ መስመር፣ የስዌሬጅ ድሬኔጅ መስመሮች የሚቆፈሩበት የሚቀበሩበት ማለት ነው:: ኮሪዶር ማለት እያንዳንዱ የሻገተ ቤት ፌት ለፊት አድርጎ የተሻለ ቫልዩ እንዲያወጣ ማድረግ ማለት ነው::
ኮሪዶር ማለት የተደበቁ ሰፈሮች ተገላልጠው የቢዝነስም የመዝናኛም ሰፈር እንዲሆኑ ማድረግ ማለት ነው:: መዝናኛ አንድ ሰፈር ሳይሆን፤ ሁሉም ቦታ መዝናኛ መፍጠር ማለት ነው:: ኮሪዶር ማለት እያንዳንዱ ውጪ ሀገር ለማየት እድል ያገኘ ሰው የቀናበት፣ የተቆጨበትን ነገር በሀገሩ ማየት ማለት ነው:: ይሄ ደግሞ እየሆነ ነው::
አንድ ወዳጄ ከአሜሪካ ይመላለሳል፤ እና እዚህ መጥቶ ኮሪዶር እና አጠቃላይ ልማቶችን ተንቀሳቅሶ ያያል የማየት፣ የመገምገም፣ የማድነቅ አቅም ያለው ሰው ነው:: እዚህ መጥቶ ሳምንት ከቆየ በኋላ፤ ለእኛ እና ለሠሪዎቹ ሥራውን ያስተምረናል:: እንደዚህ እኮ ነው እንደዛ እኮ ነው እያለ ይነግረናል በመደነቅ:: እሱ ነው አስረጂው እኛ ተረጂዎች ነን:: አልገባችሁም እኮ እናንተ፤ ይሄ ማለት እኮ በእኛ ሀገር እያለ ይነግረናል የተሠራውን ሥራ:: ከቆየ በኋላ ወደሀገሩ ሲሄድ የመጀመሪያ ሳምንት፣ ሁለት ሳምንት፣ ሶስት ሳምንት አንደኛ አስረጂ ነው::
ለቤተሰቦቹ፣ ለጓደኞቹ አንደኛ አስረጂ ነው:: ኢትዮጵያ እኮ ያለው፣ አዲስ አበባ እኮ ያለው ለውጥ ብሎ መስካሪ ነው:: ወር ሲሞላው ይደውላል ‹‹ሰላም ናችሁ? ሀገር ሰላም ነው? የምንሰማው እውነት ነው?››:: ይላል እዛ በሚሰማው ወሬ ተወጥሮ፤ ያየውን፣ ያስተማረውን፣ የሚመሰክረውን ነገር ይዘነጋል::
ከዛ ውጪ ግን ማንም ሰው የፖለቲካ ባያዝ ሳይኖርበት የመደገፍ፣ የመቃወም ጉዳይ ትቶ፤ ሀገሩን የሚያውቅ ሰው የዛሬ ሶስት ዓመት፣ አምስት ዓመት፣ አስር ዓመት የመጣ ሰው ኢትዮጵያ ቢመጣ የሚጨበጥ፣ የሚዳሰስ፣ የሚያኮራ ውጤት ያያል:: ንግግር አይደለም የሚታይ ነው:: አስረጂ አይፈልግም:: ኮሪዶር እንደሱ ነው::
ይሄን ከአዲስ አበባ አውጥቶ በበርካታ ከተሞች ማስፋት ያስፈልጋል:: አዲስ አበባ ብቻ ከሆነና ሰው ወደዚህ ከተከማቸ ችግር ስለሆነ፤ ጅማ ላይም፣ አርባምንጭ ላይም፣ ሃዋሳ ላይም፣ ድሬዳዋ ላይም፣ ጅጅጋ ላይም፣ ሀረር ላይም፣ ባህር ዳር ላይም፣ ጎንደር ላይም፣ ደሴ ላይም ሌሎችም ከተሞች እየሰፋ መሄድ አለበት:: በገጠርም፣ በከተማም እየሰፋ መሄድ አለበት:: ያንን ስናደርግ ኢኮኖሚክ ፋይዳ ደግሞ አለው:: ቱሪዝም በ2023 የሰሜን አሜሪካ ሀገራት ከቱሪዝም መስክ ሴክተር 2 ነጥብ 7 ትሪሊዮን ዶላር አግኝተዋል::
2 ነጥብ 7 ትሪሊዮን ዶላር የሰሜን አሜሪካ ሀገራት አግኝተዋል:: የሩቅ ምስራቅ ሀገራት ግን 2 ነጥብ 5 ትሪሊዮን አግኝተዋል:: አውሮፓ ሀገራት ወደ 2 ነጥብ 4 ትሪሊዮን አግኝተዋል:: አውሮፓ 2 ነጥብ 4 ትሪሊዮን አግኝተዋል:: ሩቅ ምስራቅ 2 ነጥብ 5 አግኝቶ፣ አሜሪካ 2 ነጥብ 7 አግኝቶ፤ የእነዚህ ሶስቱን ስንደምር በጣም በጣም ትልቅ ሀብት በዛ ሴክተር እንዳለ ያሳያል::
አፍሪካ ሲመጣ ግን 192 ቢሊዮን ገደማ ቱሪስት የመጣው:: አፍሪካ በሳይዙ ከአውሮፓ ስለሚያንስ ነው ወይ? ከአሜሪካ ስለሚያንስ ነው ወይ? በታሪኩ ስለሚያንስ ነው ወይ? የሚታይ ቦታ ስለሌለው ነው ወይ? አይደለም:: ሎጀስቲክ የለም:: ትራንስፖርት የለም:: ሆቴል የለም:: ሰርቪስ የለም:: በትክክል የሠራነውን የሚሸጥ ሰው የለም:: በዛ ምክንያት ሀብት እያጣን ነው::
አዲስ አበባን ሠርተን እኮ እኛ ሃምሳ፣ ስልሳ፣ ሰባ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ አዘጋጅተናል ዘንድሮ:: ይሄ አዲስ አበባ የጎረፈው ኮንፍረንስ በሁለት ሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይወጣል ከከተማ:: ቢሾፍቱ ላይ፣ ባህር ዳር ላይ፣ ጅማ ላይ ይሄዳል ኮንፍረንስ ጥርጥር የለውም:: እነሱም ያምራሉዋ:: በዛ ውስጥ ሥራ ይፈጠራል:: በዛ ውስጥ ሀብት ይመጣል:: በዛ ውስጥ እውቀት ይሸጋገራል:: በዛ ውስጥ ኢንተርናሽናል ሰዎች ጋር መገናኘት እየሰፋ ይሄዳል:: እና ኢኮኖሚክ ጥቅም አለው:: የጤና ጥቅም አለው:: ለሚመለከቱን ሰዎች የእኛን ልክ ለማሳየት አቅም አለው::
መቆሸሽን ባህል አድርገን፣ አለመሥራትን ባህል አድርገን፣ የሚጸዳ ነገር ሲመጣ ተቃውመን፣ ተጸይፈን አይሆንም:: አሁን ኮሪዶር ቅድሚያ ይሰጠዋል ወይ? ምን ቅድሚያ ይሰጡታል ታዲያ? ከመቆሸሽ በላይ፣ ከጤና በላይ፣ ተንቀሳቅሶ ውሎ ከመግባት በላይ፣ ይሄ ሰው ያለው ጅቡቲ፣ ኬንያ ሊሆን ይችላል? ግን ሲኤምሲ ያለች እናት ልጇ ታሞ ሆስፒታል ለማድረስ አንድ ሰዓት መንገድ ላይ የምትቆም ከሆነ እና ልጇ አደጋ ላይ የሚወድቅ ከሆነ የምታውቀው እሷ ናት እሱ አያውቀውም ችግሩን::
ትራፊክ ካልቀነሰ፣ የሚጠፋ የሚበራውን መብራት ካልቀነስን፣ አንድ ሰው ቤቱ መብራት አለ ብሎ፣ ኢንተርኔት አለ ብሎ፣ እቅድ አቅዶ፣ ሰርግ ሰርጎ፣ ተዘጋጅቶ፣ ሰው ጠርቶ፣ መብራት አልም ብሎበት ያበላሽበታል ፕሮግራም:: መብራት ሃይልም ልኳል ኢነርጂውን፣ በመስመር ምክንያት ይሄን ካልፈታን ታዲያ ምን ልንፈታ ነው? አዲስ አበባን መቀየር የሚያስችል ሥራ ከሠራን ሌሎች ከተሞች ይቀየራሉ:: ከተቀየሩ ከተሞች ደግሞ የኢትዮጵያ ልምድ ለአፍሪካ ይተርፋል::
አፍሪካ ከተማ ላይ ደካማ ናት:: ይሄን የሚቀይር ታሪክ ይፈጠራል፤ እና የኮሪዶር ልማት ያልነው የእያንዳንዱን ሰው ቤት መንካት አለብን ነው:: ከተማ ብቻ አይደለም ገጠር የእያንዳንዱን ጎረቤት መንካት አለብን:: የእያንዳንዱን ሰፈር መንካት አለብን:: ሁሉም በልኩ በጸዳ አካባቢ መኖር አለበት:: ይሄን ነው በአዲስ አበባ የገለጥነው:: ፒያሳ ላይ ግራ ተጋብተን ሊሆን ይችላል፣ ካሳንቺስን ስናይስ? ግራ እንጋባለን? ማንም ሰው ካሳንቺስ ተወልዶ ያደገ አሁን ያለውን ነገር ቢያይ ይኮራል እንደሆን እንጂ፤ የሚያፍርበት ነገር የለም:: ሰፈሬ ለማለት የሚያኮራ ሆኗል::
ኮሪዶር እንደሱ ነው:: ተጠናክሮ መቀጠል አለበት:: ያም ሆኖ ግን አዲስ አበባ ብዙ ሀገራት የፌዴራል ሀገራት፣ ስቴት ያላቸው ሀገራት፣ ክልሎች ከፍተኛ ብድር አለባቸው:: የሚታወቅ እውነታ ነው:: አዲስ አበባ የኮሪዶር ሥራ ለመሥራት አንድ ብር ከፌዴራል መንግሥት አልተበደረም:: የታገዘባቸው ኤርያዎች ይኖራሉ:: አንድ ብር አልተበደረም:: መቶ ፐርሰንት በራሱ ኢንካም ነው ይሄንን ሥራ የሠራው::
ባለፉት ሃያ ዓመታት በራሱ ኢንካም አዲስ አበባ ይሄን ሰርቶ ቢሆን ኖሮ ምን አይነት ከተማ ይኖረን ነበር:: በዚም ይሁን በዚያ ወጪ መውጣቱ አይቀርም መቼም:: ኮሪዶርም ባይሠራ በሆነ መንገድ ይጠፋል ገንዘብ:: አሁን ከተማችንን እየገነባንበት ያለንው ሀብት ከውጪ ተበድረን እንኳን ቢሆን፣ ከፌዴራል ተበድሮ እንኳን ቢሆን አዲስ አበባ የሚያዋጣን ነገር ነው:: ነገር ግን ምንም አይነት ብድር ሳንበደር ገንዘባችንን፣ ጊዜአችንን አጣጥመን በኤርያ ከፍለን ከተማችንን መቀየራችን ለሁላችን ደስታ ነው መሆን ያለበት::
በዚያ ውስጥ የተገኘ እውቀት፣ የተገኘው ልምድ፣ የተገኘው ሥራ፣ ስንት ኮንትራክተር፣ ስንት ወጣት ሥራ እንዳገኘ ደግሞ ቤቱ ይመስክረው ማለት ነው:: እና ይሄ ሥራ በጣም ጠቃሚ ነው:: ውጤት እያየንበት ነው:: ዓለም እየመሰከረ ያለው ጉዳይ ነው የሚታይ ነገር ስለሆነ ብዙ የሚያከራክር አይደለም:: ይሄንን ግራ ቀኝ ሳንል ተባብረን አስፍተን ሀገራችንን ማስዋብ አለብን:: ውብ ሀገር ነው ያለችን የእኛ የእጅ ሥራ ሲጎድል ትቆሽሻለች::
የእኛ የእጅ ሥራ ሲታከል ግን የተሰጠን ውብ ነገር እኛም የምንጠቀምበት ዓለምም የሚያደንቀው አድርገን መሥራት እንችላለን:: በዚያ እሳቤ ሥነ-ውበት ገብቶን ከተማ ገብቶን አብሮ ሰው ሲኖር ያለው ጥቅም እንደተጠበቀ ሆኖ ጉዳቱም ገብቶን በዕቅድ በዲዛይን በእውቀት የሚሠራ ሲሆን ደግሞ ኑሮን ኢዚ ያደርገዋል ያቀለዋል ያመቻቸዋል ማለት ነው:: በዚያ መንገድ ነው ኮሪዶርን የምናየው በጣም በጣም ጠቃሚ ሥራ ነው ኮሪዶር::
ኢቲቪ ፡- መልካም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ጋር የተገናኘ ጥያቄ እስኪ ልሰንዝርልዎ:: በተለያየ የሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የሚታዩ ግጭቶች አሉ:: እነዚህ ግጭቶች መንስኤያቸው ምንድን ነው ይላሉ ከዚያ ባሻገር መንግሥት እነዚህን ግጭቶች በሰላም እንዲቋጩ በማድረግ ረገድ ምን ያህል ቁርጠኛ ነው ?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፦ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ግጭቶች በኃይል ፍላጎትን የማሳካት ዝንባሌዎች ፕራይመርሊ መንስኤ ተብለው የሚወሰዱት የንቅል ልሂቃን የሥልጣን ሽኩቻ እና ስሁት ትርክት ነው:: ሥልጣን የሚገኘው በኃይል ብቻ ነው፤ ሥልጣን የሚገኘው በመሣሪያ ጉልበት ብቻ ነው ብለው የሚያስቡ ሥልጣን ሥልጣን የሚሆነው እኔ ከያዝኩት ብቻ ነው ብለው የሚያስቡ የስሁት ትርክት ውጤት እሱ ነው::
በምርጫ በሕዝብ ይሁንታ ማንም ሰው ሕዝብ ከፈቀደለት መሆን ይችላል የሚል እምነት እስካልፈጠርን ድረስ እኔ ከሆንኩ ትክክል፤ እኔ ካልሆንኩ ይበላሻል ብለው የሚያስቡ ስሁት ትርክት ባለበት ቦታ ግጭቶች ይበራከታሉ:: የእኛም ችግር እሱ ነው:: የክራብ ሜንታሊቲ የሚባል ነገር አለ:: ክራቦች በጃር ውስጥ ቢቀመጡ እንደ ጉንዳን ተጋግዘው የመውጣት አቅም የላቸውም:: አንዱ ሲወጣ አንዱ ሲጎትት አንዱ ሲወጣ አንዱ ሲጎትት ተያይዘው ይቀራሉ ፤ እዚያ ውስጥ:: የእኛም የፖለቲካ ሽኩቻችን ያ ባህሪ አለው::
የወጣን ከትክተን መስበር የወጣን ከትክተን ማድቀቅ ነው እንጂ ተጋግዘን መቆም እንቸገራለን:: በዚህ ምክንያት ነው እንደ መንስኤ የሚወሰደው:: የስሁት ትርክት ውጤት ነው ሮንግ የሆነ የሥልጣን ሽኩቻና ሥልጣን የሚገኝበት መንገድ ሃሳብ ሳይሆን ክላሽ አድርገው ከሚያስቡ ኃይሎች የሚመነጭ ነው:: እኛ በለውጡ ጊዜ በውስጥና ሰላማዊ ትግል ነው ለውጥ የሚመጣው ብለን ስንታገል መከራ ስላልደረሰብን አይደለም፤ ቤተሰብ ተሰድዶብናል ተባረናል ተሰቃይተናል::
በሰላማዊ መንገድ ከውስጥ ሪፎርም ነው ለውጥ የሚመጣው ብለን የቆየነው ተመችቶን አይደለም:: በግጭት በጦርነት ያ ነገረ ሊሳካ እንደማይችል ስለምናውቅ ነው:: አሁንም ያሉት ሙከራዎች 99 አይደለም መቶ ፐርሰንት አይሳኩም:: በዚያ መንገድ የሚሳካ ህልም የለም:: ህልም ማሳኪያ መንገዱ እሱ አይደለም::
አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር የሆነው በጥባጩ፤ረባሹ ፤ ክላሽ አንጋቹ ፤ ጦርነት ጠማቂው ደግሞ መልሶ ሲሸነፍ የሰላም ሰባኪ ይሆንና ከሳሽ ይሆናል:: ራሱ አደፍራሹ ከሳሽ ሆኖ ሰላም እንዴት ነው መንግሥት ስለሰላም ምን ያስባል ይላል:: መንግሥት ስለሰላም ያለው እሳቤ ግልጽ ያለ ነው::
ከፕሪቶሪያ በላይ የመንግስትን የሰላም ኮሚትመንት የሚያሳይ ምን አለ ? በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ታሪክ መመርምር የሚፈልግ ሰው ይመርምር፤ በየትኛውም ዘመን መንግስት ተገዳዳሪ ኃይሎችን እያሸነፈ 24 ሰዓት 48 ሰዓት ውስጥ ከተማ ሊቆጣጠር በደረሰበት ሰዓት ቆሞ በድርድር ሰላም ይሁን ብሎም አያውቅም ፤ተብሎም አያውቅም :: የመጀመሪያ ታሪክ ብልጽግና ነው ያደረገው:: እኛኮ መቀሌ ልንገባ አንድ ቀን ሁለት ቀን ነው የቀረን:: አሸንፈናል ጦርነቱን፣ ያለቀ ጦርነት መሆኑን እኮ እናውቀዋለን፤ ግን ጦርነት ማሸነፍ ዘላቂ ድል አይደለም ሰላም ይልቃል ብለን ነው ወደ ፊርማ የገባነው::
ቤኒሻንጉል ላይ ጋምቤላ ላይ አማራ ክልል በጣም በርካታ ኃይሎች ኦሮሚያ በጣም በርካታ ኃይሎች በቅርቡ አንድ ሴክት እኮ ኦሮሚያ ክልል ተደራድሮ ገብቶ እየሁ ስልጣን ተካፍሎ እየሠራ አይደለም እንዴ:: እኛ ከቲፒኤልኤፍ ጋር በነበረው ግጭት ስንደራደርና ወደ እርቅ ስንገባ የፕሪቶሪያው ስምምነት ባለቤት አንዱ አንኳር ተደራዳሪኮ ጌታቸው ረዳ ነው:: ሁለተኛው ጻድቃን ነው፤ እነዚህ ናቸው ዋና ተደራዳሪዎች በዲቴል ድርድሩን የሚያውቁት እነሱ ናቸው::
ከእነኚህ ሰዎች ጋር መታረቅ ብቻ አይደለም ተባብረን እየሰራን ነው:: ሰላምማ እኛ የምንፈልገው ነገር ነው:: ከኦነግም፣ አማራ ክልል ላይ ከሚንቀሳቀሱትም፣ በቲፒኤልኤፍ ካሉትም፣ ቤንሻንጉል ካሉትም፣ ጋምቤላ ካሉትም፣ አፋር ላይ፣ ሶማሌ አካባቢ ላይ በግልጽ ታይቷል የእኛ አቋም ሰላም እንፈልጋለን:: ሰላም ግን ዋጋ አለው ያን ዋጋ ለመክፈልም ዝግጁ ነን እኛ:: አደፍራሹ ራሱ መልሶ ደግሞ የሰላም ባለቤት ሆኖ ሲመጣ እሱ የትርክት ሁነትነትን ያስከትላል::
በንግግር በድርድር በውይይት ችግር መፍታት የኢትዮጵያ ባህል አይደለም:: በመዝመት ነው፤በመውጋት ነው የሚታለፈው:: ያ ይቅር አደገኛ ታሪክ ስለሆነ በንግግር ይፈታ ብለንኮ ኢንኩልሲቭ ናሽናል ዲያሎግ ስንል፣ ኢንኩልሲቭ ናሽናል ዲያሎግ የሚባል ነገር መንግስት ቀርቶ ኢትዮጵያ ውስጥ በተቃዋሚዎች እንኳን ፈራ ተባ እያሉ የሚያነሱት ጥያቄ እኮ ነው:: ማን ፈቅዶ ያውቃል እንወያይ ብሎ ? ማን ተጋጨ ነው እኮ የሚባለው:: እንወያይ ችግሮቻችንን በንግግር እንፍታ ያለ መንግስትኮ ነው:: ይሄ ታይቶ አይታወቅም በኢትዮጵያ ታሪክ:: ችግር አለብንና እንወያይ እንምከር መክረንስ እናስተካክል እኛ ነንኮ ያልነው::
አሁን ኢንኩልሲቭ ናሽናል ዲያሎግ ከ1200 በላይ ወረዳዎች ህዝብ ተወያይቷል:: በሺህ የሚቆጠር ህዝብ ተወያይቷል፤ በርካታ ኢሹዎች ተነስተዋል ከግራ ከቀኝ:: በርግጥ የሚነሳ ጥያቄ ሁሉ ትክክል ነው ማለት አይደለም:: አንዳንዱ ከራሱ ወረዳ ከራሱ ሰፈር ተነስቶ የሚያነሳው ጥያቄ አለ:: ያ ደግሞ እንዴት በሀገር ደረጃ ከናሽናል ኢንተረስት ጋር ተሳስሮ ይተገበራል የሚለው ሌላ ውይይት ይፈልጋል::
ግን ሰዎች ስሜቶቻቸውን ፤ጥያቄዎቻቸውን ቁርሾዎቻቸውን ፍላጎቶቻቸውን ሳይፈሩ ሳይሰጉ በነጻነት የሚገልጹበት መድረክ ተፈጥሯል:: ይሄ ትልቅ እምርታ ነው፤ አልነበረም:: ይህ ውይይት ለምንገነባው የሰላም መንገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተስፋ አደርጋለሁ:: የሁሉ ነገር መቋጫ ሊሆን አይችልም:: ተወያየንና ነገር ሁሉ ተፈታ ማለት አይደለም ፤ግን ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል:: እና በእኛ በኩል መንስኤው ሮንግ የሆነ እሳቤ ነው:: ስልጣን ሀሳብን ሽጦ በህዝብ ሲገዛ ብቻ ነው የሚገኘው::
ከዚህ ውጭ ያሉ ወንድሞቻችን ጊዜ ባያባክኑ ጥሩ ነው፤ ድካም ስለሆነ:: ድካም ስለሆነ ቶሎ ሰብሰብ ብሎ ይቅርታ ጠይቆ ተስማምቶ ፓርቲ ሆኖ ሀሳብ ሽጦ በሆነ ደረጃ አሸንፎ ተስማምቶ አብሮ መቀጠል ይቻላል::ኦነጎች መጥተው ከእኛ ጋር ከሠሩ፤ ከተለያየ ክልል ሲጋጩ የነበሩት ከእኛ ጋር ከሠሩ የቀሩትም ከዚያ ውጭ የሚያደርጋቸው ምንም ምክንያት አይኖርም:: ከዚያ ውጭ ያለው እሳቤና ምክንያት ግን በቃ ዝም ብሎ ባዶ ምኞት ነው:: ባዶ ምኞት ደግሞ የሚጮህ ድምጽ ሊሰማ ይችላል ግን ውጤት አያመጣም::
አሁን አይሳካም በዚህ መንገድ ብዬ የማስበው ዝም ብዬ አይደለም:: ድምጽ ጩኸት ስለሌለ አይደለም:: ባዶ ገረወይና እና ባዶ በርሜል ሲነኩት በጣም ነው የሚጮኽው:: ውሃ ያለው እህል ያለው በርሜል ቢደበደብ ያለው ድምጽና ባዶ ገረወይና ሲደበደብ ያለው ድምጽ እኩል አይደለም:: ውስጡ ባዶ የሆነ ውስጡ የቀለለ ፤ብዙ ሊጮህ ይችላል ድምጸቱ ሊሰማ ይችላል ግን ውስጡ ባዶ ነው:: በደምብ ያልጮኸ ሁሉ ደግሞ ስላልተሰማ ምንም ማለት አይደለም:: በውስጡ የተሸከመው ነገር አለ:: እና በጩኸት በእንደዚህ አይነት መንገድ የሚሳካ ነገር ያለ አይመስለኝም:: በእኔ ዘመን ሳይሆን ከእኔ ዘምን በኋላም የሚሳካ አይመስለኝም::
የሚያዋጣው በሰላም በውይይት በምክክር በሃሳብ ብልጫ ፍላጎትን እየተገበሩ መሄድ ነው የሚሻለው፤ ኢትዮጵያን ወደዚያ ማምጣት አለብን:: በእርግጥ ይሄ ነገር ከጊዜ ወደጊዜ በጣም እየቀነሰ ነው ያለው:: ወሬው ነው የገነነ ስፍራ ያለው እንጂ በአክቹዋል ፕሮብሌሙ ያን ያህል ከዚህ ቀደም ከነበረው ጋር የሚወዳደር አይደለም:: ያም ሆኖ ግን ዜሮ መሆን አለበት:: እኛ እርስ በእርስ የሚያገዳድለን ምክንያት የለንም::
ዲሞክራሲያዊ ሀገር ነው:: እራስን በራስ ማስተዳደር ይቻላል:: ማንም ማንንም መግዛት አይችልም አሁን፤ ቅዠት ነው እሱ:: ኢምፓወር አድርገን ሁሉን ሰው አንተ አንደኛ፣ አንተ ሁለተኛ ሳንል ኢትዮጵያዊ መሆኑን አምነን፣ እኩል ዜጋ መሆኑን አምነን፣ አስተባብረን ለመሥራት የተሻለ ሀሳብ ካለን መድረኩ ግልጽ ነው:: ሀሳብ ኖሮን እንኳን በአንደኛው አመት በሙሉ ባይሳካልን አቅፎ ለመስራት የሚችል መንግስት ነው ያለው፤ ተሸንፈሀልና ወጊድ አይልም:: ተሸንፈሃልና አብረን እንሥራ ነው የሚለው፤ እና በዚያ መንገድ ቢታሰብ ጥሩ ይመስለኛል::
ኢቲቪ – የሰብአዊ መብትስ ጉዳይ የዜጎችን የሰብአዊ መብት በመጠበቅ ረገድ መንግስት ላይ የሚሰነዘሩ ትችቶች አሉ:: ስለዚህ ይሄንን ሥራ በተለይ የዜጎች ሰብአዊ መብታቸው የተከበረ እንዲሆን በማድረግ ረገድ መንግስት ምን እየሠራ ነው ያለው?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፦ ለሰብአዊ መብት መንግስት ከፍተኛ ኮሚትመንት አለው:: ምንም አሌ የሚባል ጉዳይ አይደለም:: ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ትልቁ ችግር ነጻነትን የማስተዳደር አቅም ውስን መሆኑ ነው:: ነጻነትን ማስተዳደር ፈተና ሆኗል፤ እኛ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ተፈትሸው በተቋም አቅም ተገንብተው ሁላችንም አውቀን እንድንገነባቸው ብዙ ርቀት ሄደናል:: ለምሳሌ ከንጉሱ ጊዜ በኋላ ትልቁ የህግ ማእቀፍ ማሻሻያ የተካሄደው በለውጡ ነው::
የሌጋል ኳሊፊኬሽን የተደረገው በእኛ ዘመን ነው:: በርካታ ህጎች ሳይቀየሩ ቆይተዋል፤ እሱን ሠርተናል:: በነጻነት የሚሠሩ ተቋማት ገንብተናል:: የኢትዮጵያ ሒዩማን ራይት ኮሚሽን በተዛባ መንገድም ቢሆን ላለፉት ሦስት፣ አራት የኢትዮጵያ መንግስት ላይ እዚሂቹ ተቀምጦ ሲያወጣው የነበረው ሪፖርት እያዳመጠ ዝም የሚል መንግስት መፍጠር መቻላችን እኮ ትልቅ እመርታ ነው:: አልነበረም እኮ፤ አይደፈርም::
እንኳን ውሸት፣ እንኳን ቅጥፈት፣ እንኳን ያልተስተካከለ ዳታ፣ የተስተካከለስ ቢሆን መንግስት ሳያውቀው መንግስትን መክሰስ እኮ አይቻልም:: ያን ያደረግንበት ምክንያት ጠፍቶን ሳይሆን፣ ያኛውማ እናውቀዋለን ኖረንበታል:: ጠፍቶን ሳይሆን ተቋም ለመገንባት መከፈል የሚገባው ዋጋ አካል አርገን ስላሰብን፤ ነጻ ሆነው ይሥሩ:: እኛ ነጻ ይሁኑ ስንላቸው ሌሎች የጠለፏቸው ቢሆንም ማለት ነው:: ነጻነትን ማስተዳደር ፈተና ቢሆንም፤ ተቋማት መገንባት አለባቸው የሚል እምነት ስላለን ነው::
በወንጀል የሚሳተፉ ሰዎች በተለይ ፖለቲከኛ ነን፣ አክቲቪስት ነን እንደዚህ ነን የሚሉ ሰዎች፣ በወንጀል ላይ ተሳትፈው በህግ አግባብ ሲጠየቁ ደግሞ የሰብአዊ መብት ጥያቄ የሚያነሱበትም አጋጣሚ ታይቷል:: እሱ ስህተት ነው:: ኢትዮጵያ ውስጥ ሀሳቡን ስለገለጸ የሚታሰር ሰው የለም:: ብዙ እኮ የሚሳደቡ ሰዎች አሉ በየሜዳው በዚያ የሚታሰር ሰው የለም::
ሰው የሚታሰረው አውድ አውጥቶ፣ ተደራጅቶ፣ ፋይናንስ ፈልጎ፣ አራት ኪሎ በኃይል እገባለሁ ሲል ከሕገመንግስት ከሕግ ውጪ ስለሆነ ይጠየቃል እሱ:: ጋዜጠኛ ይሁን፣ አክቲቪስት ይሁን፣ ፕሮፌሰር ይሁን፣ ሕግ አክብሮ እስካልተንቀሳቀሰ ይጠየቃል:: ሥልጣንን በኃይል፣ ፍላጎትን በኃይል፣ መሻትን በኃይል፣ መተግበር ከፈለገ::
ለምሳሌ መሬት ከዚህ ቀደም በሆነ መንገድ አጥሮ መያዝ ይቻላል:: አሁን የሚያረግ ሰው ካለ ማንም ቢሆን ይታሰራል:: ደግሞ እናውቀዋለን፣ መሬቶቻችንን በሕግ ይጠይቃል እንጂ ማጠር አይችልም:: ሕገወጥነትን ኢንተርቴይን የሚያደርግ ሥርዓት አንፈጥርም:: ጋዜጠኝነት ወይም ፖለቲከኝነት ፓሽን ነው:: እናንተ ጋዜጠኛ የሆናችሁት ውስጣችሁ ስላለ ነው::
ስለምትፈልጉት ነው እንጂ ጋዜጠኛ ሆኜ እንደፈለኩ እሳደብና ብጠየቅ ጋዜጠኛ እኮ ነኝ እላለሁ ብላችሁ አይደለም:: ፖለቲከኝነት ፓሽን ነው:: ሕዝብ የማገልገል፣ የሕዝብን ኑሮ የማሻሻል፣ የመቀየር ፓሽን ነው:: ፖለቲከኛ ስለሆንኩ እንዳሻኝ አይባልም:: በሕግና ሥርዓት ውስጥ ሎው ኤንድ ኦርደር የሌለው ማንኛውም ነገር ጥፋት ነው::
ይሄ ጋዜጠኝነትና ፖለቲከኝነት የወንጀለኞች ካባ መሆን አይገባውም፤ የለበትም:: ሞያ ነው፣ የተከበረ ሞያ ነው:: ያን ሞያ አክብረው የሚሰሩ ሰዎች የሚከበሩበት፣ ያን ሞያ አክብረው ሲሰሩ ቢስቱ እንኳን የሚተዉበት፣ በድግግሞሽ ልምምድ ሲያደርጉት ግን የሚጠየቁበት መንገድ ደግሞ ያስፈልጋል:: ብዙ እኮ የምንተዋቸው አሉ:: ብዙ፣ ብዙ ቅጽፈቶች እኮ አሉ የምንተዋቸው፤ መስመር አልፎ ሲሄድ ግን መገራት ይኖርበታል::
ወንጀለኞች በመልካም እሴቶች ውስጥ እንዲደበቁ አይፈለግም:: ጋዜጠኝነት መልካም እሴት ነው:: ያ መልካም እሴት መደበቂያ ካባ ከሆነ ጥፋት ያመጣል:: ያ በህግ መገራት አለበት:: በቅርቡ በአሜሪካ ሀገር ሕግ አውጥተዋል:: በኤአይ፣ በዲፕፌክ የሰውን ሥም የሚያጠፉ፣ የሚያጠለሹ ድምጽ የሚመስሉ ሥራዎች የሚሰሩ ሰዎች በሕግ ይጠየቃሉ ብሏል:: ኤአይን ጠልተው እኮ አይደለም፤ ኤአይ የሚፈለግ ነገር ነው፤ ፋይናንስ ያደርጉበታል::
ኤአይ ግን ለሕገወጥ ተግባር መዋል የለበትም ነው ያሉት እንጂ ኤአይ አያስፈልግም አላሉም:: ላይክ ዋይዝ ጋዜጠኝነት ይፈለጋል፣ ፖለቲካ ይፈለጋል፤ ለጥፋት ሳይሆን ለመልካም ለልማት መዋል አለበትና የሰብአዊ መብትና የዲሞክራሲ ባህል ዝቅተኛ በሆነበት ሀገር ውስንነት ባለበት ሀገር፤ ሁሉነገር አልጋበአልጋ ነው ባይባልም በአብዛኛው የሞራል ውድቀት ያለበት ሥርዓት አይደለም::
ዜጎች ለምሳሌ ከዚህ ቀደም ማእከላዊ በሚባለው ቦታ ገብተው የሚገረፉበት ሥርዓት የለም አሁን:: ታስረው የተገረፉት ሰዎች ለምን ተገረፍኩ አሁን አይሉም:: የለም እንደዛ አናደርግም:: በህግ ነው የምናስረው በህግ ነው የምንጠይቀው፣ ይም ሆኖ ግን እንደባህል ፖሊሱም፣ ወታደሩም፣ አቃቤህጉም ምንም አይነት እንከን የለውም ብዬ ደግሞ ልናገር አልችልም::
ምክንያቱም የኢትዮጵያ ባህል እራሱ ሌባ ተይዞ ዱላ ይጠየቃል ወይ የሚል ነው:: ሌባ ከያዝክ መደብደብ ተገቢ ነው ብሎ የሚያስብ ባህል ባለበት ሁኔታ ሰው ሲያዝ በሕግ አግባብ አክብሮ ማስተናገድ ላይ የሚቀሩ ጉዳዮች ይኖራሉ እያሻሻልን እንሄዳለን:: ዋና ዋናዎቹ መግረፉ መቁረጡ፣ ምግብ መከልከሉ አትጠየቅም ማለቱ እነዚህ ጉዳዮች ግን የሉም::
ተቋም ተገንብቷል፤ ለውጦች አሉ:: ኢምፕሩቭ አድርገናል የሚቀሩ ጉዳዮች ደግሞ እያረቅም፣ እያረምን እንሄዳለን:: ሰብአዊ መብት ማለት ሕግ እያከበርን፣ ግዴታችንን እየተወጣን፣ መብት ስንጠይቅ ብቻ የሚከበር ነገር መሆኑን አብሮ ማሰብ ጠቃሚ ይሆናል:: በእኛ በኩልም የሚታረመውን እያረምን፣ የሰውም ባህሪ እየተቀየረ ተቋም እየተጠናከረ ሲሄድ ደግሞ የተሻለ ውጤት እያመጣ ይሄዳል ብዬ አስባለሁ::
ኢቲቪ፡- መልካም እኔን ወደሚመለከት ጉዳይ የተያያዘ ጥያቄ ላንሳሎ:: እንደሚድያ ባለሙያነት የሚድያ ጉዳይ ነው ቀጣይ የምሰነዝረው ጥያቄ:: ባለፉት ሰባት ዓመታት ሚዲያው ነጻና ገለልተኛ ሆኖ እንዲሠራ በማድረግ ረገድ መንግሥት ምን አውዶችን ፈጥሯል?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፦ ሚዲያ ልክ እንደእሳት ነው:: ያጠፋል፤ ያለማል:: ወይ እንደ ቢላ ነው:: ይገድላል፣ ያበስላል:: ማብሰያ ይሆናል፣ ማገዣ ይሆናል:: ሚዲያን ለመልካም ነገር መጠቀም እስከቻልን ድረስ ውጤቱ ከፍተኛ ነው:: ለጥፋት ካዋልነውም በዚያው ልክ አደጋ ያስከትላል:: እኛ ሰዎች፣ ማህበረሰቦች ዝናብ ይቁም ብለን ማወጅ አንችልም:: ማስወገድ አንችልም:: ዝናብ ተፈጥሯዊ ኩነት ነው፤ ይዘንባል::
ያ የዘነበው ዝናብ ግን ፍሳሽ መስመር ካልተዘረጋለት በቀር ቤታችንን ሊያበላሽ ይችላል:: እንቅስቃሴያችንን ሊገታ ይችላል:: የእኛ ሥራ የፍሳሽ ማስተላለፊያ መዘርጋት ነው እንጂ ዝናቡን ማቆም አይደለም:: ሚዲያን በሚመለከትም ሚድያ በጣም ኢምፖርታንት ነገር ነው:: ሕግ አበጅተን በእውቀት፣ በሞራል፣ በሙያ የታነጹ ሰዎች በዝተው ለጥቅም እንዲውል ማድረግ ያስፈልጋል::
ባለፉት ሰባት ዓመታት ጥቂት ዳታ ለማንሳት ልክ ቅድም በኤክስፖርት እንዳነሳሁልሽ፣ በርዳታ እንዳነሳሁልሽ በጣም ኢምፕረሲቭ የሆነ ዳታ ደግሞ ያለው አንዱ ሚዲያ ላይ ነው:: ይሄ ደግሞ ቀጥታ ከሙያሽ ጋር ስለሚያያዝ ቼክ ማድረግ ይኖርብሻል አንቺም:: ቅድም ባነሳኋቸው በኤክስፖርት ጉዳዮች ከሚመለከታቸው ተቋማት ማረጋገጥ አለባችሁ:: ከሀገር ውስጥም ከውጭም፤ ተረጅነት ላይም ማረጋገጥ አለባችሁ:: እያንዳንዱ ዳታ አኪውሬት ነው:: ምንም ይሄ ዝም ብሎ ለንግግር የመጣ ዳታ አይደለም::
ሚዲያን በሚመለከት ባለፉት ስድስት ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ 160 ያልነበሩ ሚዲያዎች ተጨምረዋል:: በለውጡ ጊዜ ኢትዮጵያ ያላት ቴሌቪዥን 4 ሚሊዮን ነበር:: በእርግጥ ይህ በእኔ ዕድሜ ያሉ ሰዎች ብዙ የሚገርማቸው ታሪክ አይደለም:: ምክንቱም ቴሌቪዥን ለማየት ስንት ሜትር ተጉዘን እንደምንሄድ፤ እንዴት በረንዳ ላይ ተቀምጠን እንደምናይ እናውቀዋለን::
ቲቪ በየቤቱ ያለ ነገር አልነበረም ኢትዮጵያ ውስጥ:: በለውጡ ጊዜ አራት ሚሊዮን ቲቪ ነበር፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው:: ዛሬ 20 ሚሊዮን ቲቪ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ:: ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የቲቪ ብዛት በሶስት ዕጥፍ አድጓል:: ምን ማለት ነው ይሄ ጎረቤት ተሰልፈን በረንዳ ተቀምጠን ከማየት ነጻ የወጡ ህጻናት በጣም ብዙ ናቸው::
በእኛ ጊዜ መከራው ብዙ ነበር፤ ማታ ቲቪ ለማየት ቀን ስንላክ እንውል ነበር:: ቲቪ ያላቸው ሰዎች በጣም ውስን ስለነበሩ:: አሁን በርካታ ቤተሰብ ቲቪ አለው:: ሁለት ሶስት ያላቸው፤ ዘመናዊ ቲቪ ያላቸው ሰዎች አሉ:: ሚዲያውም በዝቷል፤ ቲቪው በዝቷል::
የሚዲያ ቋንቋው 60 ደርሷል:: ኢትዮጵያ ውስጥ በ60 ቋንቋ ብሮድካስት ይደረጋል:: አማርኛ፤ ኦሮምኛና ትግርኛ ቋንቋዎች ብቻ ሳይሆን ብዙ ቋንቋዎች ማለት ነው:: የማህበረሰብ ሚዲያዎችን ጨምሮ በራሳቸው 60 ቋንቋ ብሮድካስት ያደርጋሉ:: ይህ ትልቅ ዕድገት ነው:: ሚዲያ ግን ሲፈጥረው ገለልተኛ የሚባል ሚዲያ የለም ዓለም ላይ::
ሁሉም ሚዲያ ከጀርባው የሚነዳው ሀሳብ አለ:: ሀሳቡን የሚደግፍ፤ የሚቃረን ሊኖር ይችላል:: ሁሉም ሚዲያ ሲቋቋም የሆነ ተልዕኮ ይዞ ነው:: ለሚዲያው ፋይናንስ የሚደርግ ሰው በዓላማ ነው:: እናም ገለልተኛ ባለመሆኑ ምክንያት 60ው ቋንቋ፤ 160ው ሚዲያ የበረከተው ቲቪ በሙሉ ለኢትዮጵያ ብልጽግናና እና ልማት እያገለገለ ነው ማለት አይደለም::
ሁሉም አላማ ስላለው ለራሱ ጥቅምና አላማ ስለሚሰራ፤ የሚዲያው ዕድገት ደግሞ በተለይ ባለፉት ሁለት ሶስት ዓመታት ወደ ድህረ እውነት ዓለም ተለውጧል:: ብዙ ውሸቶች ይደመጣሉ፤ እንዳንዱ ያስቃል፤ ያስደንቃል፤ ስለእኔ ከእኔ በላይ የሚነግረኝ ሚዲያ አለ፤ ስለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ከጽህፈት ቤቱ በላይ የሚናገር ሚዲያ አለ::
ግን ሀፍረት የለም፤ መረጃ አግኝቻለው ብሎ ይናገራል፤ ከየት አገኘህ ብሎ የሚጠይቅ ሰው የለም:: ማረጋገጥ የሚባል ነገር የለም፤ ‹‹ትሪያንጉሌት›› የሚባ ነገር የለም:: አንዱ አለ አለ ነው:: እናም ብዙ ውሸቶች፤ የሚፈጠሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል:: በመበራኩቱ ልክ በጣም ብዙ ውሸቶች፤ ብዙ የማይገቡ ዜናዎች፤ ትክክል ልሆኑ መረጃዎች ይሰራጫሉ::
ትንሽ ተስፋ ያለው ነገር መረጃው መስመር እየሳተ ሲመጣ፤ ህዝቡ ከዚያ እየተጎዳ ሲመጣ እንደከዚህ ቀደሙ የሰማውን የማመን ጉዳይ ሲታይ ደግሞ ለውጥ አለ:: የሰው ልጅ አንድም በሳር ሀ ብሎ አሊያም በአሳር ዋ ብሎ ነው የሚማረው የሚባለው አባባል ሰርቷል በሚዲያው::
ብዙ ጊዜ በአሳር ዋ ብሎ ሀ እያልን ቀምሰን ከፍዳ በመነሳት ብዙዎች የሰሙትን ወሬ ይህ ነገር እውነት ነው አጣርታችኋል፤ ከሌላ ሰውስ ሰምታችኋል ማለት ጀምሯል:: አላለቀም ግን ጀምሯል:: ይህ ደግሞ ጥሩ ዕድገት ነው:: የማጣራት ዝንባሌ እየተፈጠረ መጥቷል:: ይህንን ማጥራቱን እያሳደገ ህዝቡ ማህበራዊ ሚዲያ ሲባል የእውነት ምንጭ ሳይሆን የበርካታ ውሸቶች ምንጭ እንደሆነ አውቆ ወደ እውነት የሚያመሩ ሚዲያዎችን ለይቶ ሲያበላሹ ሲያሳስቱ የሚጠየቁ መሆናቸውን አውቆ እየመረጠ የሚጠቀም ከሆነ ውሸት እየቀነሰ ‹‹ኢንፎርማቲብ›› ሚዲያዎች እየበዙ ይሄዳሉ ብየ ተስፋ አደርጋለሁ::
በእኛ ሁኔታ በቁጥር በሳይዝም በአሠራር በከፍተኛ ሁኔታ ሚዲያው ተለቋል:: ወቀሳ ያለብን ለምንድነው ሚዲያው እንዳሻው እንዲናገር የፈቀዳችሁት የሚል ነው:: እኛ ደግሞ ያለን ሀሳብ ጀማሪዎች ነን ካሁኑ ማፈን ከጀመርን ፈጠራን ያጠፋል:: አሁን ከመቶ ሺ በላይ ይዘት ፈጣሪዎች( content creators) ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ:: ሁሉ ትክክል ላይሆን ይችላል፤ ሁሉ ባለሙያ ላይሆን ይችላል::
መከልከል ስንጀምር ግን ይገታልና እየሰፋ ቀስ እያልን እያስተማርን እየገራን ብንሄድ ይመረጣል በሚል ነው ለቀቅ ያደረግነውና ሚዲያው በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ ባልታወቀ ቁጥር፤ ስፋት እና ጊዜ የሚዲያው ብዛት የዜናው ብዛት አስቸጋሪ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ:: በዚያ ልክ ነው ያለው:: እየገራን፤ እያረቅን እያስተካከልን፤ ወደ እውነት፤ ወደ ልማት፤ ወደ ብልጽግና የሚወስደውን ደግሞ እያሰፋን፤ እሚዋሽ አይጠፋም ግን እየቀነስ መሄድ ይኖርብናል ብየ አምናለሁ::
ጥያቄ፡- ከምርጫ ጋር በተገናኘ ጉዳይ እናንሳ፤ ቀጣይ የምርጫ ጊዜ የተሻለ ሰላማዊ፤ ዲሞክራሲዊ መንገድ እንዲሄድ መንግስት ምን ያህል ቁርጠኛ ነው?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፦ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ከአንዱ ስርዓቶች እንደ ኢትዮጵያ ላለ ሀገር የተሻለ ስርዓት ተብሎ ይወሰዳል:: የተለያየ ፍላጎት የተለያየ ቋንቋ ባህል ያለበት ሀገር ስለሆነ ከዲሞክራሲ ውጭ ያለ አሠራር እምብዛም ጠቃሚ አይደለም:: ዲሞክራሲ ደግሞ አንዱ የሚገለጥበት መገለጫው ምርጫ ነው::
በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ስልጣን ያላቸው ሰዎች ስልጣን ቢይዙ ለህዝብ ገልጠው የህዝብ ይሁንታ ሲያገኙ ስልጣን የሚይዙበት መንገድ ደግሞ አንዱ የዲሞክራሲ መገለጫው ነው:: እናም ምርጫ ዲሞክራሲያዊ ማድረግ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ያለን ፍላጎት ለማሳካት የምንከውንበት መንገድ ነው::
ባለፈው የነበረው ምርጫ እስካሁን በኢትዮጵያ ታሪክ ከነበረው ምርጫ የተሻለ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል:: አሁን ደግሞ ምርጫ ቦርድ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመታጠቅ ሙከራ እያደረገ ነው:: ራሱን እንደተቋም እያሳደገ ነው:: ከባለፈው ምርጫ የተሻለ በሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ይደረጋል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ::
የችግር መፍቻ ግን ምርጫ አይደለም:: ውስብስብ ችግር ያለበት ወስብስብ መፍትሄ ነው የሚፈልገው፤ ለውስብስብ ችግር አቋራጭ የሆነ የቀለለ መፍትሔ የለም:: በአንድ ጊዜ ሁሉ ነገር እንደሚፈታ ማሰብ ተገቢ አይደለም:: ምርጫ ቦርድ ቢጠነክር መራጩ መጎበዝ አለበት:: መራጩ ቢጎብዝ ሚዲያው ያን ለመዘገብ ብቃት አለው ወይ፤ ሚዲያው ቢዘግብ በውጭ ያሰፈሰፉ ጠላቶቻችን እንዴት ይረዱታል፤ ብዙ ጫናዎች ነው ያለው:: እናም እንደ ማጅክ ቡሌት ሁሉነገር እንደሚፈታ ሳናስብ ነገር ግን ካለፈው የተሻለ ለማድረግ መንግስት በእጅጉ ይሠራል:: ምንም ጥርጥር የለውም:: በእኛ በኩል የተሳካ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማድረግ የቻልነውን ጥረት እናደርጋለን::
ይህ ምርጫ በመንግስት ጥረት ብቻ አይሳካም:: የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ፖለቲከኞች በዚያ መድረክ ውስጥ ሀሳባቸውን ሽጠው ለመወዳደር ዝግጁ መሆን አለባቸው:: ብቻችን ተወዳድረን ብቻችን ቆመን ዲሞክራሲያዊነቱን ለመለካት እንቸገራለን:: በሌላ መንገድ ደግሞ ፖለቲከኛው ለመወዳደር ፈቃደኛ አይደለም:: ፖለቲከኛ ነኝ፤ ፓርቲ ነኝ፤ ግን አልወዳደርም ማለት ልክ ባህር ዳር ወንዝ ዳር ቆሞ ውጭ ሆኖ ዋና እንደመዋኘት ማለት ነው:: ዋና ለመዋኘት ውሃ ውስጥ መግባት ያስፈልጋል:: ውሃ ሳይነካና ሳናምቦጫርቅ ዋና መዋኘት ከባድ ነገር ነው:: ፖለቲካል ፓርቲ ከሆን የምንለካበት አንዱ መንገድ በምርጫ ተወዳድረን በማሸነፍ ይሁንታ ስናገኝ መንግስት በመሆን ደግሞ የገባነው ቃል በመተግበር ነው::
ለዚያም ተፋላሚ፣ ተቃዋሚ ተከራካሪ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ማሰብ ይኖርባቸዋል:: ለምርጫ ትልቁ ቅስቀሳ ትልቁ ቅድመ ምርጫ ሥራ የሚባለው ተግባር ነው:: ቃልን በተግባር መፈፀም ነው:: እኛ ባለፉት አምስት ዓመታት እናሳካለን ብለን ቃል የገባናቸውን ጉዳዮች በበርካታው ጉዳይ እናሳካለን:: አሳክተን ነው ለምርጫ የምንቀርበው:: እንናገራለን፤ እንተገብራለን:: በንግግራችንም፤ በተግባራችንም የተሸነፈ ያመነ ሕዝብ ካለና ይሁንታ ካገኘን ደግሞ ስልጣን ይዘን እንቀጥላለን:: በዚህ አግባብ በተግባር የሚገለጥ የምርጫ ሥርዓት ይሆናል::
የተሻለ ፓርላማ ይፈጠራል:: የተሻሉ ሃሳቦች ይንሸራሸራሉ:: የተሻለ የፖለቲካል ካልቸር እየተፈጠረ ይሔዳል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ:: ናሽናል ዲያሎጉ አለ:: ሠላሙ ላይ እየመጣ ያለ ለውጥ አለ:: የኢኮኖሚ ዕድገቱ አለ:: ጉዳዮች መልክ እየያዙ የተሻለ ሰብሰብ ብለን ኢትዮጵያን የምናበለፅግበት መሠረታዊ ችግሮቿን የምንፈታበት ትልልቅ ስብራቶቿን የምንፈታበት ዘመን እንደሚሆን ነው የምጠብቀው እኔ::
ኢቲቪ ፡- ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እስከ አሁን ብዙ ጉዳዮችን አንስተናል:: የባለፉትን ዓመታት የወደፊቱንም ከኢኮኖሚው፤ ከአገልግሎት ዘርፉ በብዙ መልኩ የሀገሪቱን ሁኔታ ስንቃኝ ቆይተናል:: በዚህ መነሻነት የኢትዮጵያ የነገ ገፅታ ምን ሊመስል ይችላል ብለው ያስባሉ? ኢትዮጵያ ነገ ገፅታዋ ምን እንደሚሆን ይጠብቃሉ?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፦ አጓጊ! የኢትዮጵያ ነገማ የሚያጓጓ የሚያስመረቃ፤ የሚያስቀና ኢትዮጵያ እንዲህ ነበረች ? የሚያስብል እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለኝም:: ነገዋ በጣም የሠመረ አገር ነች ኢትዮጵያ :: ለዚያም ነው የምንተጋው:: የሠመረ ነገ ኖሯት፤ ልጆቻችን አሁን ስብራት መከራ ችግር ያልናቸውን ነገሮች መልሰው እንዳያዩዋቸው እንዲህ ነበር እኮ፤ ብለው እንደታሪክ ብቻ እንዲያወሷቸው ነው:: ፍላጎቱ የሠመረ የምታስቀና ውብ ሀገር ትሆናለች ኢትዮጵያ:: ይህ ደግሞ የሚሆነው የተጀመሩ ሥራዎች አሉ:: በርካታ ሥራዎች፤ ማብዛት ማፅናት ያስፈልጋል::
ሕዳሴን ጨርሰናል፤ ኮይሻን መጨረስ አለብን:: አዳዲስ ኢነርጂ ኢንቨስት ማድረግ አለብን:: መሰረተ ልማት /ኢንፍረስትራክቸሩን/ ማስፋት አለብን:: ከተሞችን ማበራከት አለብን:: ያን እያደረግን በገጠር ኮሪዶር የተሻለ ገጠር ሆኖ ሶላር የሚጠቀም፤ ባዮ ጋዝ የሚጠቀም ከከብት ጋር የማይተኛ አርሶ አደር መፍጠር አለብን::
ማዳበሪያ ከውጪ ነው የምናመጣው:: በሀገር ውስጥ ማምረት አለብን:: ማሳካት አለብን:: ማዳበሪያ አገር ውስጥ አምርተን አርሶ አደሩ ሳይቸገር ማዳበሪያ አግኝቶ በስፋት የሚያገኝበት ሁኔታ መፈጠር አለበት:: ማሽነሪ ማምረት አለብን:: ትራክተሩ የእርሻ መሣሪያዎቹ በሀገር ውስጥ ተመርተው ቅድም ያልናቸው ቆላማ አካባቢዎች በስፋት ማምረት አለባቸው::
ዘመናዊ ከተሞች መስፋት አለባቸው፤ ሎጀስቲክ ሥርዓታችን መሳለጥ አለበት:: እስረኛ የሆንባቸው በርካታ ጉዳዮች መፈታት አለባቸው:: ኢንዱስትሪው ማደግ አለበት:: ያድጋልም:: ቴክኖሎጂው በጣም የኢትዮጵያን ዕድገት ብልፅግና ለማገዝ የሚችል መሆን አለበት:: ኤ አይ ማምረት አለበት:: ሶሻል ሴኩሪቲው መሻገር አለበት:: ስፔስ ላይ ያለን ቁጥር እና ፕረዘንስ ማደግ አለበት:: እስከ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ሶፍት ዌር አምራች ኩባንያዎች አሉ:: ሶፍት ዌር አምራች ተቋማት አሉ:: ሃርድ ዌር መመረት አለበት::
ቴክኖሎጂው ላይ እኛ አክቲቭ ተሳታፊ መሆን አለብን:: ቅድም በዘመን ገበያ እንዳነሳሁት፤ በኢ ኮሜርስ ብዙ ጉዳዮችን ሶልቭ ማድረግ አለብን:: ነገሮችን ኢዚ ማድረግ አለብን:: ሰዎች ሳይቸገሩ በቀላሉ የሚያገኙበትን አግባብ መፍጠር አለብን:: የኢትዮጵያን ብልፅግና፣ የኢትዮጵያን ቀጣይነት፤ የኢትዮጵያን ሉዑላዊነት የኢትዮጵያን ቆሞ ከፍ ብሎ መታየት የሚያፀኑ ተቋማት መገንባት አለባቸው::
መከላከያ ብቻ ሳይሆን ውጪ ጉዳይ፤ ውጪ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ግብርና ሚኒስቴር፤ ግብርና ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን ትምህርት ሚኒስቴር፤ ትምህርት ሚኒስቴር ብቻ ሳይሆን ጤና፤ ሁሉም ተቋማት መዘመን መገንባት አለባቸው:: የሚገጥማቸውን ፈተና ለመሸከም የሚያስችል ብቃት እንዲፈጥሩ መደረግ አለበት::
ከዚህ ባሻገር በአለም አቀፍ መድረክ የምትረዳ ለማኝ ሀገር፤ በብድር የምታስቸገር ሀገር የሚለውን ታይትል ቀይሮ ተጽኖዋ ከፍ ያለ፤ የምትደመጥ በብዙ ሀገራት ውስጥ የመደመጥ አቅም ያላት፤ ክብር ያላት ሀገር ትሆናለች:: የነገዋ ኢትዮጵያ በጣም የምታጓጓ ናት:: የነገዋን የምታጓጓዋን ኢትዮጵያ እያየን ነው አሁን እንቅልፍ አልባ ሆነን የምንሠራው::
እንቅልፍ አልባ ሆነን ስንሠራ የነገዋ ኢትዮጵያ የምታጓጓን ምኞት ብቻ ደግሞ አለመሆኗን ያየናቸው ውጤቶች ያሳያሉ:: ኤክስፖርቱ ያሳያል፤ እድገቱ ያሳያል፤ ደህነት የተቀነሰበት መንገድ ያሳያል፤ብዙ ጉዳዮች ተስፋ እንዳለ ያሳያሉ:: መበርታት መሥራት ውጤት ላይ ማተኮር ካለ ምንም ጥርጥር የለውም ልጆቻችን ከእኛ የተሻለች ሀገር ይረከባሉ:: የነገ ኢትዮጵያም ለሁሉ ዜጎቿ የምታኮራ የማታሳፍር ሀገር እንድምትሆን ተስፋ አድርጋለሁ::
ኢቲቪ ፡-ይሄ ህልምዎት ይሆን ከመንግሥታዊ ሥራ ኃላፊነቱ ባሻገር በግል ገቢዎ ፕሮጀክቶችን እስከ መገንባት ያደረስዎት ነው ወይስ ምንድነው የሚያነሳሳዎት ይህንን ተግባር ለመፈጸም?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፦ ያው የግል ገቢ የሚባለው ነገር ህልም ነው፤ ራዕይ ነው:: ወደዚህ ቦታ ያመጣኝ፤ ማገልገል ነው፤ መለወጥ ነው:: ብዙ ዓመት አቅጄ አሰቤ ሰርቼ ያመጣሁት ነገር ነው::ድንገት የወደቀብኝ ነገር አይደለም:: ለዘመናት መሆን አለብኝ ብዬ አስቤ ተዘጋጅቼ ነው የሆንኩት:: ተዘጋጅቼ የሆንኩት ደግሞ ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት ነው::
እናም በዚህ የሚገኝ ማንኛውም ኦፖርቹኒቲ ካለ ማንኛውም እድል ካለ ጊዜም፣ ገንዘብም ጉልበትም ማንኛውም ነገር መዋል ያለበት ኢትዮጵያን ለመቀየር ለማበልጸግ መሆን አለበት::ለምሳሌ መጽሐፍ ነው የገቢ ምንጭና መጽሐፎች በኢትዮጵያ ታሪክ ከፍተኛ ሽያጭ ካስገኙ መጽሐፎች አንዱ የእኔ መጽሐፍ ነው:: ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ባልሆን ያ መጽሐፍ በዚያ ልክ ይሸጣል ወይ? በዚያ ልክ አንባቢ ያገኛል ወይ? ፣ ስለጻፍኩ ብቻ ነው ወይስ መጽሀፌ እና ያለሁበት ቦታ ነው ተደምረው ያንን ገንዘብ ያመጡት ? ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል::
ያ ገንዘብ መቶ ፐርሰንት የእኔ አይደለም ሀሳቡ ሰው ጋር ደርሷል በገንዘቡ ለድሀ ቤት ተሠርቷል ፣ ትምህርት ቤት ተገንበቷል ፣ በገንዘቡ በጣም ብዙ ሰዎች ከችግር ተገላግለዋል ፡ እኔ አንድም ብር ከዚያ የመጠቀም ፍላጎቱም የለኝም ወደፊትም አይደረግም በቅርቡም የሚወጣ መጽሐፍ አለኝ እየጨረስኩ ነው ያለሁት እሱ በተለመደው መንገድ ተሸጦ ሀሳቡ ሀሳብ ለሚገበዩ ሰዎች ገንዘቡ ደግሞ ለልማት ነው የሚውለው እና በልመናም ይምጣ በሽያጭም ይምጣ በሆነ መንገድ ይምጣ ማንኛውም ሪሶርስ (ሀብት) መዋል ያለበት ኢትዮጵያን ለማበልጸግ ብቻ ነው ብዬ ነው የማምነው ::
ከዚያ ውጪ የሚጠቀሙ ሰዎች የሉም ማለት አይደለም ::ብዙ የማውቃቸው ሰዎች አሉ ስልጣን ላይ ተቀምጠው በጎን የሚነግዱ ሰዎች አሉ:: እንደዚህ አይነት አፕሮች ትክክል ነው ብዬ እኔ አላምንም:: እነርሱም ባያደርጉት እመርጣለሁ :: በእኛ ተጨባጭ ሁኔታ ግን አንድ ሰው ስልጣን ላይ ሲወጣ ስልጣንን አስታኮ የሚገኝ ማንኛውም ጥቅም ለግል የሚውል ከሆነ ብዙ ጠቃሚ ነው ብዬ አላምንም::
በዚያ መንገድ ነው የምሠራው ውጤቱም እንደርሱ ነው :: እንግዲህ በመደመር 30 ገደማ ትምህርት ቤት ተሠርቷል ኢትዮጵያ ውስጥ ፤ 30 ሀይስኩል መገንባት እንደሰውስ መታደል አይደል እንዴ? ስለዚህ ያንን ማድረግ ከቻልን መልሶ ኢንቨስትመንት ነው :: ብዙ ድሀዎች እኮ እዚህ አዋሬ አላየሽም? ብዙ ድሀዎች እኮ የቤት ባለቤት ሆነዋል ፤ ብዙ እናቶች ከዚያ በላይ ምን ደስታ አለ ይሄ ወደፊትም ቀጥሎ ተጠናክሮ የሚቀጥል ጉዳይ እንደሚሆን ነው ተስፋ የማደርገው ::
ኢቲቪ ፡- ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እርሶን አግንቼ የግል ጉዳ አንድ ሁለት ጥያቄ ባልጠይቅ ምናልባት ተመልካቾች እንዳይቀየሙኝ ፤ እንዳይወቅሱኝ እፈራለሁኝ እና እርሶ የትዳር አጋር ኖት፤ አባት ኖት እና ደግሞ የሀገር መሪ ኖት በዚህ ሁሉ ሒደት አንድ ላይ ይህንን ሁሉ ማከናወን አይከብድም እንዴት ነው የሚያቻችሉት እነዚህን ጉዳዮች ?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፦ እነዚህ ጉዳዮች አንድ ላይ ባይመጡም እኮ ይከብዳሉ ቀላል የሚባል ነገር የለም እንዲሁ ትዳርም ብቻውን ቀላል አይደለም ፤የልጅ አባት መሆንም ብቻውን ቀላል አይደለም ፣ መሪ መሆንም ብቻውን ቀላል አይደለም፤ ጋዜጠኛ መሆንም ቀላል አይደለም ፤ሁሉም ነገር የራሱ ፈተና አለው ያንን ግን በሚዛን ባላንስ እያደረጉ መሄድ ያስፈልጋል እኔም በዛው አግባብ እያቻቻልኩ ነው የምኖረው ::
ኢቲቪ ፡- ትርፍ ጊዜ ይኖሮታል በትርፍ ጊዜዎ በብዛት ምን ቢያደርጉ ይወዳሉ? ትርፍ ጊዜ ድንገት እንኳን ሚኖሮት ከሆነ ምን በማድረግ ያሳልፉበታል?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፦ ጊዜ በጣም ውድ ነገር ነው ያው እንደሚታወቀው ያለኝን ጊዜ ሚታወቁ ሩቲን ስራዎች አሉኝ ምሰራቸው ፤ ፕሮጀክት ምከታተልባቸው ፣ ስፖርት ምሰራባቸው እንደዚህ እንደምታይው ላይብረሪ (ቤተ-መጽሀፍት) አለኝ ማነብባቸው ጊዜያቶች አሉ ::በዚህ ውስጥ ነው ጊዜዎቼ ሚያልፉት ፡ ብዙ ነገር ደስ የሚሉኝ ስራዎች ስለሆኑ ስፖርትም ስሰራ በደስታ ነው ፤ማነበውም ምጽፈውም ካለ በደስታ ነው ፣ ፕሮጀክት የማየውም ካለ በደስታ ነው ፤በዚህ አግባብ ነው ጊዜዬ ብዙም ሳያስቸግረኝ አቻችዬው ነው ምጠቀምበት ::
ኢቲቪ ፡- በዚህ ሀገር መደረግ አልነበረበትም ወይም ደግሞ መደረግ የለበትም ብለው የሚያስቡት ነገር ይኖራል?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፦ በዚህ ሀገር መደረግ አለበት፤ የለበትም ብዬ የማስባቸው ጉዳዮች አይጠፉም:: ባይሆኑ ባይኖሩ ቀድመን በሠራንባቸው ብዬ የማስባቸው ጉዳዮች የሚያስቆጩኝ ጉዳዮች ጥቂቶቹን ለማንሳት፤ አንዱ ድህነታችን ነው:: በጣም ያስቆጨኛል ድህነታችን ድህነትን አምርሬ ነው የምጠላው :: በድህነት ምክንያት ዝቅ ብለን ታይተናል፣ ተዋርደናል ፣ ለምነናል እና ድህነት መጥፎ ቀንበር ነው ፤መሰበር አለበት ይሄ ትውልድ ድህነትን መበቀል አለበት ብዬ በጽኑ አምናለሁ ::መሆን ነበረበት አሁንም መሰበር አለበት ብዬ አምናለሁ በጣም መጥፎ ነገር ስለሆነ ድህነት ::
ሁለተኛው ይሄ መጠፋፋት ፣ የመጠላላት ፣ የመከፋፈል ታሪካችን እንደዚሁ ያሳዝነኛል እኔ ካልሆንኩ እናንተ አትሆኑም ፣ እኔ ካልሆንኩ አንተ አትሆንም በሚል ፣ እኔ አንደኛ ነኝ በሚል እሳቤ ያለው መናናቅ፤ ያለው መጠላላት፤ ያለው መጠላለፍ ያሳዝነኛል ፡ ይሄ ድንበር የለውም በነገራችን ላይ ይሄ ድንበር የለውም በብሄር ብቻ አይደለም አንደኛው ብሄር በአንደኛው ብሄር፣አንደኛው እምነት በአንደኛው እምነት ሳይሆን በአንድ ብሄር ውስጥም አለ የእኛ ሰፈር የእኛ አካባቢ ይላል ደግሞ እና ይሄ አላስፈላጊ መጠፋፋቱ እና ጥቅምን ፍላጎትን ለማሳካት የምንሄድባቸው መንገዶች የተበታተኑ መሆናቸው ጎጂ አድርጌ አስባቸዋለሁ ::
ኢትዮጵያ ወደብ ያጣችበት መንገድ በጣም ያስቆጨኛል ፤ ኢትዮጵያ ባለፉት 30 አመታት ወደብ የላትም ይሄ የሆነበት መንገድ በጣም በጣም ያስቆጨኛል :: ያስቆጨኛል ስል አንዳንዶች ዘመን ያመጣው አጀንዳ ይመስላቸዋል ፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ከመሆኔ በፊት የዛሬ አስርም 15 አመት በይፋ በቪዲዮዬ ያለ ፤በጽሁፍ ያሉ አቋሞቼ ናቸው:: እነዚህ ትክክል ናቸው ብዬ አላምንም ማንንም ሳንጎዳ ግን የእኛን ጉዳት መቀነስ አለብን ብዬ አስባለሁ::
ኢትዮጵያ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያም ምንም ጥያቄ የለውም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባታል:: ይሄን ብታሳካ ግን ሌላ ሰው መጉዳት አይጠበቅባትም:: ሳንጎዳ በቂ ሪሶርስ ነው ፤በህግ እና በንግግር ማግኘት አለባት :: ያ ካልሆነ የተጎዳ የተሰበረ ሀገር በዘላቂነት የሰከነ ሰላም ያመጣል ብዬ አላስብም መቼም ይሁን መቼ በንግግር ይህ ጉዳይ መስመር መያዝ አለበት:: ግፍ ነው የተፈጸመው ትልቅ በደል ነው የተፈጸመው::
በአለም ወደብ አልባ ሀገራት ልምምድ የሌለ ነገር ነው ኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመው በታሪክም በፈለገው መስፈርት እና ይሄ ያስቆጨኛል፤ መፈታት አለበት ብዬ በጽኑ አምናለሁ :: ሌላው የሚያሳዝነኝ እና ቢቀር ብዬ የማስበው ነገር ኢትዮጵያውያን ስለራሳቸው ያላቸው ግምት ፤ ኢትዮጵያውያነ ስለእነርሱ ሰው ስለእነሱ ታሪክ ፤ ስለእነርሱ ሀብት፣ስለእነርሱ ሀገር፣ ስለእነርሱ ምድር የራስን የምናራክስበት ልክ ያሳዝነኛል ::
ከብዙ ሰዎች ባላነሰ ብዙ አለም የማየት እድል አለኝ ፤ ብዙ አለም ብቻ ሳይሆን የተከለከሉ ቦታዎች የማየት እድል አለኝ:: ኢትዮጵያ የምትራከስ ሀገር አይደለችም ፡ ኢትዮጵያውያን የሚራከሱ ሰዎች አይደሉም:: ኢትዮጵያውያን የራሳችንን አርክሰን አሳንሰን ሌላውን አግዝፈን የምናይበት የተሸጠ ማንነታችን ያሳዝነኛል :: በራሱ የሚተማመን፤ በሀገሩ የሚተማመን ፤የራሱን የሚያከብር ትውልድ እንዲፈጠር አብዝቼ እመኛለሁ ::
እና ድህነት የሚያስቆጨኝ ነገር ነው መጠፋፋት የሚያስቆጨን ነገር ነው:: ጂኦግራፊካል እስረኛ የሆነች ሀገር ዜጋ መሆኔ ፤የዚያ የጂኦግራፊክ እስረኛ የሆነች ሀገር መሪ መሆኔ በጣም የሚያስቆጨኝ ነገር ነው ፤ መቀየር ያለበት ነገር ነው እርስ በእርስ ማንከባበርበት የእኛን ቫልዩ የምናራክስበት የእኛ የሆነው ሁሉ ቆሽሾ ወድቆ የሚታይበት መንገድ የሚያሳዝነኝ ነገር ነው እና እነዚህ ጉዳዮች በየደረጃው በየጊዜው መልክ እየያዙ፤ መልስ እያገኙ እየተፈቱ እንዲሄዱ እመኛለሁ ለዚያም ነው አብዝቼ በትጋት መሥራት የምፈልገው ::
ኢቲቪ ፡- አንድ የመጨረሻ ጥያቄ ላንሳ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በእለት ተእለት ተግባሮ የሚያስደስቶት ተግባር ምንድነው?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፦ በእለት ተእለት ተግባሬ የሚያስደስተኝ ነገር ውጤት ነው:: የምንናገረውን ቃል የገባሁትን ነገር መፈጸሜን ማረጋገጥ እፈልጋለሁ:: ውጤት በትጋት በድካም እንደሚመጣ አምናለሁ :: በአቋራጭ የሚገኝ ድል እንደሌለ አውቃለሁ :: በየቀኑ የእርካታ ምንጬ ፤እንደ አዲስ ኢነርጂ (ሀይል) የማገኝበት፤ወጥቼ የምውልበት፤ የምዘረጋበት ነገን በብሩህ መንገድ የማስብበት ፤የተሻለ ነገር የምመኝበት ነገር ውጤት ነው:: አንድ ነገር እስቤ እርሱ ሲሳካልኝ የነገውን ቀጥዬ እንዳቅድ የሚያደርገኝ በየደረጃ የሚገኙ ውጤቶች ናቸው ::
እውነት ለመናገር ባለፉት ስድስት ሰባት አመታት የገጠሙን ፈተናዎች ፣ ችግሮች ወደግራ ወደቀኝ ያላጉን ጉዳዮች ቢኖሩም ከሞላ ጎደል ህልሜን እየኖርኩ ነው ፤ ከሞላ ጎደል መሻቴን እየከወንኩ ነው፣ ከሞላ ጎደል የማቅደውን የማስበውን ነገር እያሳካሁ ነው ፣ ከሞላ ጎደል ይሄን ሀገር የመምራት እድል ባገኝ ምን አደርጋለሁ ብዬ የማስበውን ነገር እውነት ለመናገር በሚያስደንቅ መንገድ ውጤት እያመጣሁ ነውና በጣም ከፍተኛ ደስታ እና ኢነርጂ ተሞልቼ ወደነገ እንድጓዝ ፤እንድዘረጋ የሚያደርገኝ ውጤት ነው ፡ መናገር ብቻ ሳይሆን መፈጸም ፈጽሞ ማየት ብቻ ሳይሆን መሻገር አልቆ መፈጸም እና ውጤት የእርካታ ምንጬ ጉልበቴ፤ ነገን ትልቅ ተስፋ እንዳይ የሚያደርገኝ ነገር ነው::
እስካሁን ያለውም ነገር በየሴክተሩ ስመዝነው የተናገሩትን እየተገበሩ ፤ የተመኙትን እየኖሩ ፣ የሠሩትን እየጨረሱ ፤ፍሬ እያዩ ፤ውጤት እያዩ በመከናወን ውስጥ ካሉ እድለኞች መካከል አንዱ ነኝ ብዬ ነው የማስበው ፤እና ውጤት ዋናው እርካታዬ ነው ::
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 3 ቀን 2017 ዓ.ም