የያዝነው 2012 ዓ.ም ከመጠናቀቁ በፊት በኢትዮጵያ ይካሔዳል ተብሎ የሚጠበቀውን ምርጫ በቁጥር ረገድ ሥድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ ነው። በዴሞክራሲያዊነት ግን ከሂደቱ እስከ ውጤቱ ድረስ ወደ ፊት ምናየው ቢሆንም ካለው የውክቢያ ሂደትና በጊዚያዊነት ከተቆረጠው የምርጫ ቀን አንጻር በአይነቱ ልዩ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ይካሄዳል ብዬ አላምንም። ሀገሪቱ ካሁን ቀደም በርካታ ምርጫዎች በዴሞክራሲ ስም አካሒዳች። በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጊዜ ምርጫ ነበር። በኮለኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምም ጊዜ የብሔራዊ ሸንጎ አባላት ተመርጠዋል ውስጡን ለቄስ የሚባሉ ነበሩ እንጂ። በኢፌዴሪ ሕገመንግሥት መሠረትም አምስት ጊዜ ምርጫ ተደርጓል- ውስጡን ለሌላ ቄስ ብለን አለፍነው እንጂ። እናም ከእንደራሴ ሰጠንህ እስከ ዝሆንን ካልመረጥክ ፀረ አብዮት ነህ እና ንቢቱን ካልመረጥክ ትነደፋለህ ሁሉ ምርጫ ተብለው አልፈዋል።
ይህ አሁን ባለው ሕገመንግሥት መሠረት ዘንድሮ በነሃሴ ወር የሚከናወነው ምርጫ ዴሞክራሲያዊ መሆን አለመሆኑ ምርጫው ሲካሔድ የምንለየው ነው። እኔን ግን ያሳሰበኝ የምርጫው ዴሞክራሲያዊ መሆን አለመሆን ሳይሆን ምርጫው በሰላም ተጀምሮ በሰላም መጠናቀቁ እና የምርጫው ወቅት አመቺ አለመሆኑ ነው።
በሀገሪቱ እየተካሔዱ ያሉ ግጭቶች እልባት የማያገኙና ከምርጫው ጋር ተያይዞም የበለጠ ጡዘት የሚፈጠር ከሆነ ደግሞ ግጭቶቹ ወደ እርስ በርስ ጦርነት አምርተው እንደ ሶርያ፣ እንደ ሊቢያ እንዳንሆን እፈራለሁ መርዶ ነጋሪ ለመሆን ሳይሆን ያበራሽን ጠባሳ ያየ የሚለው ብሂል ትዝ ብሎኝ ነው- አያምጣብን አንጂ! የግጭት ኩሬን አድርቀን ሰላም ካላሰፈንን።
በሌላ በኩል ደግሞ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ከፍል በተለይ ሕዝብ ጥቅጥቅ ብሎ ሰፍሮ ባለበት አካባቢ ነሀሴ የዝናብ ወቅት ነው። የነሐሴ ዝናብ በተለመደው ገጽታው የሐምሌን ያህል ባይጠነክርም ጎርፍ እና የወንዝ ሙላት ሥራና እንቅስቃሴን ግን ማወኩ አይቀርም። ከዚህ አንፃር በሀገራችን በኢትዮጵያ በነሐሴ ብሔራዊ ምርጫ መደረጉ ሒደቱ እንዲጓተት፣ ድምጽ ሰጪው እንዲንገላታ፣ 50 ሚሊዮን ከሚገመተው መራጭ አነስተኛ ቁጥር ያለው ድምጽ ሰጪ እንዲወጣ ያደርገዋል። ለመራጩ ብቻ ሳይሆን 300 ሺህ ለሚሆኑት ምርጫ አስፈጻሚዎች እና ታዛቢዎችም ያስቸግራል። ኤሌክትሮኒክ ድምጽ አሰጣጥ (እንደነ ሩስያ) ለማድረግ ደግሞ የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን መሠረተ ልማቱ ብቁ አይመስልም።
ከምርጫ ሒደቶች አንዱ የእጩ ግለሰቦች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ ነው። የምርጫ ቅስቀሳ በክረምት አስቸጋሪ መሆኑ አይቀርም በብዙ የሀገሪቱ ክፍሎች። ለወትሮው እኝኝ እያለ የሚጥለው የነሀሴ ዝናብ ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት በዋነኝነት የሚጎዳው ምረጡኝ እያሉ የሚቀሰቅሱ ዕጩ ተወዳዳሪዎችን እና መራጮችን ነው። ሰዎች በተፈጥሮ ምቾት ፈላጊዎች በመሆናችን ቀስቃሹም ሆነ ተቀስቃሹ ዝናብ ውስጥ ቆመው ስለ ምርጫው ለመነጋገር፣ ለመቀስቀስ ለመንቀሳቀስ አዳጋች ነው። ምንአልባት በከተሞች ይህንን በአዳራሾች ማካሔድ ይቻል ይሆናል። አዳራሹ ለመድረስም ዝናብ እና ጭቃ ታልፎ ነው እንግዲህ። የምርጫ ቁሳቁስ ማጓጓዝም በእንደዚህ አይነት አየር ንብረት ከባድ ይሆናል። ከሀገሪቱ ሦስት አራተኛ ህዝብ በላይ በሚኖርበት ገጠርም ከዝናብ እና ጭቃ በተጨማሪ የጎርፍ እና ውሃ ሙላት ስጋትም በክቡር አቶ ከበደ ሚካኤል ‘’አዝማሪ እና የውሃ ሙላት’’ ግጥም እንደተጠቀሰው ለተወሰነ ጊዜ ቆመው የሚያሳልፉት አይደለም-ጊዜና ምርጫ ቆመው የሚጠብቁት አይደለምና።
እንደ 1997ዓ.ም ብሔራዊ ምርጫ አይነት ጊዜ ዐውድ ቢኖርም በክረምት እና ጸጥታ ጉድለት ምክንያት መራጩ ህዝብ በከፍተኛ ቁጥር ወጥቶ ድምጽ ይሠጣል ብዬም አላስብም፤ እስካሁን ካየኋቸው በመነሳት። በዚህ ላይ ክረምት፣ ብርድ፣ ጭቃ፣ ጎርፍ፣ የወንዝ ሙላት፣ የእርሻ ሥራ (የአረም ወቅት ነው በክረምት ዝናብ ተጠቃሚ የሀገሪቱ ክፍሎች) ሲጨመርበት እንኳን ዘንቦብህ ድሮም ጤዛ ነህ እንዲባል ወትሮውን አነስተኛ ቁጥር የነበረውን መራጭ የበለጠ እንዳያሳንሰው እሰጋለሁ። ስለዚህ በምርጫው ሰፊ የሕዝብ ተሳትፎ ከተፈለገ በዝናባማው ወቅት ነሐሴ መካሔዱ ትክክል ነው ብዬ አላምንም።
ይህን ለማስተካከል ሁለት ሦስት አማራጮች ሊኖሩ ይችላሉ። የመጀመሪያው ምርጫውን ክረምት ሳይገባ ማካሔድ ነው። ይህ እንዳይሆን ደግሞ ምርጫ ቦርዱም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲሁም ለመወዳደር የሚያስቡ ግለሰቦች በቂ ዝግጅት አላደረጉም። ለዚህ ዋነኛ ኃላፊነት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነው። የምርጫ የጊዜ ሰሌዳውን ቀደም ብሎ ቢያወጣ በአሁኑ ጊዜ የተጧጧፈ የምርጫ ክርክር ተደርጎ በሕዝብ የተሻለ ተቀባይነት ያለውን ፓርቲ ከወዲሁ ባመላከተ ነበር። ፓርቲዎቹ፣ ግለሰቦቹም ሆነ ቦርዱ እና ታዛቢዎች ዝግጅት ሳያደርጉ ምርጫ መደረጉም ቀደም ሲል እንደተባለው አሳታፊነቱን ያደበዝዛል።
ሁለተኛው አማራጭ ምርጫውን ማራዘም ነው። ምርጫ ማራዘምም ቀላል አይደለም። ያለውን ሕገመንግሥት እንደመጣስ ይቆጠራል። ባለው ሕገመንግሥት መሠረት ምርጫ በየአምስት ዓመቱ መካሔድ ይኖርበታል። በተራዘመ ቁጥር በሌሎች የአፍሪካ እና የሌሎች አህጉራት ሀገሮች እንደሚታየው ወደ ምርጫ ቅብ አምባገነንነት ሊያመራም ይችላል።
ሌላው አማራጭ አሁን ያለውን ሕገ መንግሥት ሰርዞ አዲስ ሕገመንግሥት አርቅቆ ሥራ ላይ በማዋል ምርጫ ማካሔድ ነው። ይህም የራሱ ውስንነቶች አሉት።
ሀገሪቱን በዋነኝነት ሲመራ የነበረው ፓርቲ ፈርሶ እና ከአባላት ድርጅቶቹ ሦስቱ በሌላ ፓርቲ ታቅፈው መደረጉ፣ ለውድድሩ እንደ 1997ዓ.ም ብሔራዊ ምርጫ አይነት ዐውድ መኖሩ የዘንድሮውን ምርጫ ይበልጥ ተጠባቂ ያደርጉታል። በሌላም በኩል በሀገሪቱ ያለው የጸጥታ አለመረጋጋት እና አዳዲስ ፊቶች ወደ ፊት ለፊት መምጣትም ተጠባቂነቱን ይበልጥ ያግሙታል። እነዚህ ሁኔታዎች የዘንድሮውን ብሔራዊ ምርጫ በአህጉረ አፍሪካ በዓመቱ ከሚካሔዱ ምርጫዎች ይበልጥ አጓጊ ከሆኑት ውስጥ እንዲቆጠር ያደርጉታል።
በአፍሪካ ዘንድሮ ከሚካሔዱ ምርጫዎች መካከል ቶጎ፣ ቡሩንዲ፣ ካሜሩን (ሰሞኑን ተካሒዷል)፣ ማሊ እና ግብጽ የሚካሔዱት ይገኙባቸዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 7/2012
መልካሙ ተክሌ
(melkamutekle@gmail.com)