በርካታ ስራ ፈላጊ ዜጎች ደጃቸውን ዘወትር ያንኳኳሉ፡፡ የተሻለ ስራና ደመወዝ ለማግኘት በመጓጓትም ደጅ ይጠናሉ – ወደ ስራ አስቀጣሪ ኤጀንሲዎች፡፡ ይሁንና ስራና ሰራተኛን በህጋዊ መንገድ በማስተሳሰር ከሚገኘው ጥቅም የበለጠ ማታለል በተሞላበት ተግባር የሚታፈሰው ረብጣ ንዋይ የሚያማልላቸው በዘርፉ የሚሰማሩ ተቋማት በርክተዋል፡፡ በህጋዊ መንገድ የሚሰሩትን ስም በማጠልሸት ተአማኒነት እንዲያጡም እያደረጉ ነው፡፡
ከአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በከተማዋ ባለፉት ሁለት አመታት የኤጀንሲ ፈቃድ አውጥተው በአገልግሎቱ ዘርፍ የተሰማሩት 454 ተቋማት ምዝገባ አካሂደዋል፡፡ በተደረገው ክትትል 128 ኤጀንሲዎች ህገ ወጥ ተግባር ሲፈጽሙ ተገኝተው ፈቃዳቸው ተሰርዟል፡፡ 81 ኤጀንሲዎች ፈቃድ ባወጡበት የመስሪያ ቦታ ያልተገኙ ሲሆን፤ሥራና ሠራተኛ በማገናኘት ብቻ የተሰማሩ 28 ኤጀንሲዎች በሕገ ወጥነት በርካታ ገንዘብ ከሥራ ፈላጊዎች ሰብስበው በመገኘታቸው እንዲታገዱ ተደርጓል፡፡
ስራ አጥቶ ወይም የተሻለ ስራ ፍለጋ በሚውተረተር ዜጋ የሚፈጸመው ደባና ተንኮል እየበዛ መጥቷል፡፡ ስራ እናስቀጥራችኋለን በማለት የመመዝገቢያ ገንዘብ ሰብስበው ቢሮ የሚቀይሩ፤ ከስራ ቀጣሪዎች ጋር በሚደረግ ምስጢራዊ ውል ለራሳቸው ዳጎስ ያለ የኮሚሽን ክፍያ በየወሩ እየተቀበሉ ለሰራተኛው ጥቂት ገንዘብ የሚወረውሩ፤ በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/96 መሠረት ከስራ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ ከሰራተኞች መሠረታዊ መብቶች መካከል የመደበኛ የስራ ሰዓት፣ የትርፍ ሰዓት ስራና የክፍያ ሁኔታ፣ የሳምንት ዕረፍትና የዓመት ዕረፍት፣ የወሊድ ፍቃድ፣ የጋብቻ ፍቃድ፣ የሀዘን ፍቃድ፣ የሙያ ደህንነትና ጤንነት አጠባበቅ…ወዘተ በተመለከተም ጉዳዬ የማይሉ አስቀጣሪ ኤጀንሲዎች በርካታ ናቸው፡፡
አለም አቀፍ ድንጋጌዎችም ሆኑ የኢትዮጵያ አሰሪና ሰራተኛ ህግ ሰዎች ለሚሰጡት አገልግሎት ተገቢውን ምንዳ እንዲያገኙ እንዲሁም ምቹ የስራ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው ይደነግጋሉ፡፡ ኢትዮጵያም ከሀገሯ አልፋ በውጭ የሚሰሩ ዜጎቿ የሚያፈሱትን ጉልበት የሚመጥን ክፍያ እንዲያገኙ ትግል እያደረገችና ውጤትም እያስመዘገበች ትገኛለች፡፡ ሰሞኑን ከሳዑዲ አረቢያ መንግስት ጋር በተደረገው ስምምነትም እዚያ በስራ የሚሰማሩ ዜጎቿ ዝቅተኛው የደመወዝ ጣሪያ 266 ዶላር እንዲሆን መደረጉ ተጠቃሽ ስኬት ነው፡፡ ይህ ዜጎችን ያከበረ ተግባር ተገቢውን የጉልበት ዋጋ ከማስገኘት ባሻገር በሰብአዊ መብት አያያዝና በሌሎችም ጉዳዮች በሌሎችም አገሮች እንደሚቀጥል ይጠበቃል፡፡
ከባህር ማዶ በመሻገር መብትን ማስከበር መጀመሩ እሰየው የሚያስብል ቢሆንም፤ በአገር ውስጥም ሁሉን አቀፍ የሰራተኞችን መብትና ጥቅም የማስከበሩ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ በተለይ በገዛ ወገኖቻቸው ላይ በስራ ማስቀጠር ስም ግፍና በደል የሚፈጽሙት ኤጀንሲዎች ህገ ወጥ ተግባር ጥብቅ ክትትል በማድረግ መግታት ለነገ የሚባል ስራ መሆን የለበትም፡፡
አሰሪና ሰራተኛ በማገናኘት በአስቀጣሪ ኤጀንሲ ስም ለራሳቸው በአካፋ ለለፍቶ አዳሪዎቹ በማንኪያ ብር የሚሰጡትን አካላት በፍጥነት ማስቆም ይገባል፡፡ በእነዚህ ተቋማት አማካኝነት በበርካታ የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማት ብዙ ሺ ዜጎች የስራ እድል ማግኘታቸው መልካም ቢሆንም፤ የልፋታቸው ዋጋ አንዴ ስራ በማገናኘት ብቻ ተልእኳቸውን በተወጡ አገናኞች በየወሩ መመዝበሩ ሊበቃ ይገባል፡፡ ለእዚህም አውቀውም ሳይሆን ተሳታፊ የሆኑ ስራ ቀጣሪ ተቋማት ትብብር ያስፈልጋል፡፡ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት መረጃ በመለዋወጥ ተግባሩ መገታት አለበት፡፡
ስራ እናስቀጥራችኋለን በማለት ከበርካታ ሰዎች በሌለ አቅማቸው ኪሳቸውን አሟጠው ገንዘብ እየሰበሰቡ የራሳቸውን ገቢ የሚያደልቡትንም መቆጣጠር አስፈላጊ ነው፡፡ በተለይ አማላይ ማስታወቂያዎችን በተለያየ መንገድ እያስነገሩ በስራ ታገኛላችሁ የሃሰት ዘዴ ገንዘብ ሰብስበው እብስ የሚሉትንና በቃላቸው የማይገኙት፤ ሰውን በጉጉት ከማስከራቸው፣ ሌብነታቸው ይቅር የማይባል ነውና ተከታትሎ እርምጃ መውሰድ ይገባል፡፡
በህገ ወጥ መንገድ ስራ በማገናኘት በተሰማሩ አካላት ላይም አስተማሪ የሆነ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ዛሬ ቀላል በሚመስሉ የማታለል ተግባር የተሰማሩ አካላት በህገ ወጥ መንገድ የሚገኘው ጥቅም እየጣማቸው ሲመጣ ከፍ ወዳለው የምዝበራ ድርጊት መሰማራታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ስለሆነም ‹‹በእንቁላሉ በቀጣሽኝ›› እንዳይባል ከሚሆን ከስር ከስር እየተከታተሉ በህጋዊ እርምጃ ማረቁ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 2/2011