አረንጓዴ ዐሻራ ኢትዮጵያ እንድታንሰራራḷ

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር 2011 ዓ.ም ሲጀመር ኢትዮጵያ በስምንት ዓመታት ውስጥ 50 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል አቅዳ ወደ ሥራ ገብታለች። ባለፉት ስድስት ዓመታትም 40 ቢሊዮን ችግኝ ተክላለች። ሰባተኛ ዓመቱን በሚይዘው የዘንድሮ የችግኝ መርሃ ግብርም 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን በመትከል የተተከሉት ችግኞች ከ47 ቢሊዮን በላይ ታደርሳለች።

ከሀገር ውስጥ አልፎ ከፍተኛ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነትን ያገኘው የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በየዓመቱ እስከ 30 ሚሊዮን ሕዝብ የሚሳተፍበት ግዙፍ ፕሮጀከት ነው። በሰፊ የሕዝብ ተሳትፎ የሚከናወነው ይኸው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በሚተከሉት ችግኞች ብዛት በየዓመቱም የተለያዩ ክብረ ወሰኖችን እየሰበረ የዘንድሮ መርሃ ግብር ላይ ደርሷል። ዘንድሮም “በመትከል ማንሰራራት” በሚል መርህ ለሰባተኛ ጊዜ በሰፊ የሕዝብ ተሳትፎ ይከናወናል።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር እውን ከሆነበት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በተተከሉት ችግኞች እንደ ሀገር ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶች ተገኝተዋል። የሀገሪቱ ደን ሽፋን 23 በመቶ ከመድረሱም ባሻገር የአየር ንብረቱ የተረጋጋ እና ለግብርና ሥራም አመቺ ሆኗል።

አረንጓዴ ዐሻራ ኢኮኖሚ ነው። የተለያዩ ምርቶችን ምርታማነት በመጨመር በምግብ ራስን ከመቻል ባሻገር ሀገሪቱ የምታገኘው ዶላር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጓል። ኢትዮጵያ እያከናወነችው ያለው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ሀገሪቱን በአረንጓዴ ከማልበስ በሻገር የችግኝ ተከላን ከግብርና ጋር በማቀናጀት ማካሄድ እና አቮካዶን እንዲሁም ፓፓያን የመሳሰሉ ፍራፍሬዎችን ጨምሮ የተለያዩ ችግኞች እንዲተከሉ ያስቻለና በጥቂት ዓመታት ውስጥም ለምግብነት የሚውሉ ናቸው። ይህም ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን እንድትችል እና ከተረጂነት እንድትላቀቅ በማድረግ ረገድ ፋይዳው የጎላ ነው።

የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ከ35-40 በመቶ የሚሸፍነው ቡናም ምርታማነቱ ጨምሯል። ከጥቂት ዓመታት በፊት 700 ሚሊዮን ዶላር የነበረው የውጭ ገቢ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ሊደርስ ችሏል። በአረንጓዴ ዐሻራ ከተተከሉት ችግኞች ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የቡና ችግኞች በመሆናቸውም ኢትዮጵያ በቡና ምርት መጠኗ ከብራዚል እና ከቬትናም ቀጥላ የሦስተኛ ደረጃ እንድትቆናጠጥ አስችሏታል።

የሻይና ቅመማ ቅመም ዘርፍን ምርታማነት ማሳደግ በመቻሉ ለሀገሪቱ እስከ 20 ሚሊዮን ዶላር የማምጣት አቅም ላይ ደርሷል። የአረንጓዴ ዐሻራ ትሩፋት ለዘመናት እየታጠበ ወደ ጎረቤት ሀገራት የሚሄደውን አፈር መቀነስ መቻሉ ነው። በየዓመቱ 1ነጥብ 9 ቶን አፈር ወደ ጎረቤት ሀገራት ሲሄድ ቆይቷል። ሆኖም የአረንጓዴ ዐሻራ እንደ ሀገር መተግበር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በዓባይ ተፋሰስ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ችግኝ እየተተከሉ በመሆኑ ለዘመናት ለጎረቤት ሀገራት ሲሳይ ሲሆን የኖረውን የአፈር ሀብታችንን ለመጠበቅ ያስችለናል። በየዓመቱ ከአንድ ሄክታር መሬት ላይ በመሸርሸር ይባክን የነበረውን 130 ቶን አፈር ወደ 42 ቶን ዝቅ እንዲል ማድረግም ተችሏል።

በአጠቃላይ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የአፈር መሸርሸር፣ የብዝሀ ሕይወት መመናመንና የጎርፍ አደጋ እየፈተናት ላለችው ሀገራችን ሁነኛ መፍትሔ መሆኑን በተጨባጭ እየተረጋገጠ መጥቷል።

አረንጓዴ ዐሻራ ከኢኮኖሚ ፋይዳውም ባሻገር ማህበራዊ ግንኙነት እና አብሮነትን ያጠናክራል። አረንጓዴ ዐሻራ በመላው ሕዝብ ተሳትፎ የሚከናወን ነው። ተማሪው፣ አርሶ አደሩ፣ የከተማው ነዋሪ፣ የመንግሥት ሠራተኛ፣ የጸጥታ አካላት ወዘተ የሚሳተፉበት እና በጋራ ተሳትፎ ሀገራቸውን የሚያበለጽጉበት ተናፋቂ ወቅት ነው። ይህ ደግሞ አንድነትን የሚያጸና እና በጋራ ለሀገር ዕድገት መቆምን የሚያጠናክር ነው።

እነዚህ ሁሉ የአረንጓዴ ዐሻራ ትሩፋቶች ሲደማመሩ ኢትዮጵያ እንድታንሰራራ የሚያደርጉ እና የብልፅግና መሠረቷን የሚጥሉ ናቸው። ለመጪው ትውልድም የተሻለች ሀገር ለማውረስ የሚያስችል በመሆኑ ሁሉም ዜጋ በዘንድሮው አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ላይ በነቂስ ሊሳተፍ ይገባል!

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You