አሜሪካዊቷ ሞዴልና የቴሌቪዥን ፕሮግራም አስተዋዋቂ አሽሊ ግርሃም ለልጇ ‹‹ምኒልክ›› የሚል ስም አወጣች። ምክንያት ስትባል ደግሞ በኢትዮጵያ ጥበባዊ ሥራዎች ስለተገረመች። ምኒልክ የጠቢቡ ሰለሞን ልጅ ስለሆነ እና የዚች ጥበበኛ አገር ንጉሥ ስለሆነ።
እንግዲህ የእኛዎቹ ጉደኞች ማፈሪያ ክርክር የተጀመረው እዚህ ላይ ነው። እናንተ ምን አገባችሁ እሷ ያለችው የኛን ምኒልክ ነው፤ አይ! እናንተ ናችሁ የማያገባችሁ እሷ ያለችው ይሄኛውን ምኒልክ ነው የሚሉ ንትርኮች ተጀመሩ። ክርክሩ ቀዳማዊ ምኒልክን ነው ያለችው አይ ዳግማዊ ምኒልክን ነው ያለችው በሚል ነው።
ቅጡን ያጣው የብሄር ፖለቲካ ነው ለዚህ ያበቃን። በእነዚህ ተከራካሪዎች እሳቤ ቀዳማዊ ምኒልክ የትግራይ ተደረገ፤ ዳግማዊ ምኒልክ ደግሞ የአማራ ተደረገ። በቀዳማዊ ምኒልክ አማራ አያገባውም፤ የትግራይ ብቻ ነው፤ በዳግማዊ ምኒልክ ትግራይ አያገባውም፤ የአማራ ብቻ ነው። ለዚህም ነው ‹‹እናንተ ምን አገባችሁ፤ እናንተ ምን አገባችሁ›› መባባል የተጀመረው። አሁን ይሄን አሳፋሪ ክርክር ሴትየዋ ብትሰማ እንዴት ይገርማት?እንዴትስ አድርጋ ትታዘበን?
አያችሁ! ኢትዮጵያን ዓለም ‹‹ኃያል አገር!›› ብሎ ቢመዘግብልንም እንኳ እኛ አንስማማም ማለት ነው። ኃያል የተባለችው በአክሱም ነው፤ አይ አይደለም በላሊበላ ነው፤ በዳሽን ተራራ ነው፤ ኧረ ዳሎል ነው፤ በኮንሶ እርከን ነው፤ በሶፍ ዑመር ዋሻ ነው…. በእገሌ ጥቅጥቅ ደን ነው… እያልን ልንጨቃጨቅ ነው ማለት ነው። እውነታው ግን ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ ያደረጋት የእነዚህ ሁሉ ድምር ነው። የአክሱም ሀውልት ብቻውን ምንም ነው፤ ኬንያ ወይም አሜሪካ ካለ አንድ ቅርስ አይለይም። የሶፍ ዑመር ዋሻም ብቻውን ምንም ነው፤ የባሌ ጥቅጥቅ ደን ብቻውን ምንም ነው። ኢትዮጵያን ውብ ያደረጋት የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት መሆኗ ነው። በአንድ ጊዜ ብዙ ዓይነት ነገር የሚታይባት መሆኗ ነው። በብርድ አንዘፍዛፊውን የዳሽን ተራራ እና እንደ እሳት የሚጋረፍ የኤርታሌ እሳተ ገሞራን በአንድነት ስለያዘች ነው ድንቅ ሀገር የሆነችው።
እኛ ጉደኞቹ ቀዳማዊ ምኒልክ እና ዳግማዊ ምኒልክን የተለያዩ አገራት መሪዎች አደረግናቸው። አሜሪካዊቷ ሞዴል አሽሊ ያስቀመጠቻቸው ማብራሪያዎችና የሰጠቻቸው ቃለ መጠይቆች እንደሚያሳዩት የልጇን ስም ያወጣችው በቀዳማዊ ምኒልክ ነው። ምክንያቱም የንግሥት ሳባ እና የጠቢቡ ሰለሞን ልጅ ይላል። የንግሥት ሳባ እና የጠቢቡ ሰለሞን ልጅ ደግሞ ቀዳማዊ ምኒልክ ነው። በሌላ በኩል የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ንጉሥ ስለሆነ ብላለች። ያም ሆነ ይህ ቀዳማዊ ምኒልክን መሆኑ እርግጥ ነው፤ ግን ቀዳማዊ ምኒልክ የየት አገር ንጉሥ ነበር? ዳግማዊ ምኒልክስ የየት አገር ንጉሥ ነበር? ከቀዳማዊ ምኒልክ ጀምሮ ንጉሣዊ ሥርዓት እስከተወገደበት የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ድረስ የሰለሞን ሥርወ መንግሥት የሚባል ነው። ያ ማለት ነገሥታቱ የሰለሞን ዘር ነን ይሉ ነበር። እንኳን የተለያየ አገር ንጉሥ አድርገን ልንስላቸው አንድ ቤተሰብ ነን የሚሉ ናቸው።
እዚህ ላይ እንዲንደርስ ያደረገን የብሽሽቅ ፖለቲካ ነው። መጋቢ ሐዲስ እሸቱ እንዳሉት ነው ነገሩ። በበላይ ዘለቀ የሚፎክር ሰው ከበላይ ዘለቀ ፍቅር ይልቅ በዚያ የሚበሳጩ ሰዎች ያሉ እየመሰለው ነው። ለምኒልክ ካለው ፍቅር ይልቅ ምኒልክን የሚጠሉ ሰዎችን ያበሳጨሁ እየመሰለው ነው። አቶ መለስ ዜናዊን ለማድነቅ ዶክተር አብይን ማጣጣል የግዴታ የሚመስለው አለ፤ ዶክተር አብይን ማመስገን የሚቻለው አቶ መለስ ዜናዊን በመውቀስ ብቻ የሚመስለው አለ። ይሄ የቀዳማዊ ምኒልክ ነው፤ የዳግማዊ ምኒልክ ነው ክርክር መጋቢ ሐዲስ እሸቱ ያሉትን ያረጋግጣል።
በሁለቱም ወገን ያሉት የአሽሊን ፎቶ እየለጠፉ ሲናገሩ የነበረው አገራዊ ኩራትን መሰረት አድርገው አይደለም። ያኛውን ወገን ለማበሳጨት ነው። ‹‹የምኒልክ ጥላቻ ያለብህ ተቃጠል እንግዲህ! ቻለው እንግዲህ!›› ሲሉ ነበር። በዚያኛው ወገንም ‹‹ያንተን ምኒልክ መስሎህ! የኛ ምኒልክ ነው፤ ያንተ ምንድንትስ እንዳይመስልህ!›› ሲባባሉ ነበር። በሁለቱም በኩል የአገሬ ንጉሥ ያለ የለም።
እንግዲህ በአገራችን ባለውለታዎች በጋራ መኩራት አልቻልንም ማለት ነው። ራስ አሉላ አባነጋ የትግራይ፣ አብዲሳ አጋ የኦሮሞ፣ ፊት አውራሪ ገበየሁ የአማራ አድርገን ተከፋፍለናል፤ አቤት ቢሰሙ እንዴት ያፍሩ! (ኧረ እንኳን ይሄን ሳይሰሙ አረፉ!)
አሉላ አባነጋ ከጣሊያን ወራሪ ጋር ሲጋፈጥ የነበረው ለኢትዮጵያ እንጂ ለትግራይ ብቻ አልነበረም። አጼ ዮሐንስ 4ኛ ከደርቡሽ ጋር ሲዋጋ አንገቱን የተሰዋ ‹‹ትግራይ ትግራይ›› እያለ ሳይሆን ‹‹ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ›› እያለ ነበር። እነ ጃጋማ ኬሎና አብዲሳ አጋ የተዋጉት ኢትዮጵያ ብለው እንጂ ኦሮሞን ብቻ ብለው አልነበረም። እነ ፊታውራሪ ገበየሁ በጠላት መድፍ አፍ ውስጥ የገቡት ኢትዮጵያን እንጂ አማራን ብቻ ነፃ ለማውጣት ሄደው አልነበረም።
እንዲህ ዓይነት ብሽሽቅ አገራዊ ኩራት ያሳጣል። ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ አይቀበለውም ነው። እኛ እንዲህ ስንባባል የሰማ የውጭ አገር ሰው ምን ይላል? ራሷ አሽሊ ብትሰማ እንዴት ይገርማት ይሆን? አሜሪካዊት የኮራችበትን እኛ አልኮራንበትም ማለት እኮ ነው። እሷ ኢትዮጵያን በጎበኘችበት ጊዜ በጣም ተደሰተች፤ በጥበብ ሥራዎች ተደመመች። ላሊበላንና ሌሎች አስገራሚ ታሪካዊ ቅርሶችን አየች። የኢትዮጵያ የእጅ ጥበብ የሆኑ ሥራዎችን አስተዋለች። ከጥበብ ሥራዎች አንዱ የሆነውን የሐበሻ ቀሚስ ለበሰች። ከዚያም ታሪክ እንደሚነግራት የመጀመሪያው ንጉሥ የንገሥት ሳባ እና የጠቢቡ ሰለሞን ልጅ መሆኑን አወቀች። ልጇንም ምኒልክ አለችው፤ ታዲያ ምን ነበር ሁላችንም የኛ ነው ብንል?
እግረ መንገድ አንድ ትዝብት ልጨምር። በቻይና በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና በሚያደርገው በረራ ቅሬታዎች ሲነሱ ነበር። የአየር መንገዱ ሰዎችም ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ምላሽ ወደ ቻይና የሚደረገውን በረራ ማቋረጥ መፍትሔ አይሆንም ሲሉ ነበር። እዚህ ላይ በወቃሾችም መፍረድ አይቻልም። በድሃ አገር ውስጥ ቢገባ ጉዳቱ የከፋ ነውና ለመፍራት ያስገድዳል።
እዚህ ላይ የምንታዘበው ነገር ግን ከዚህ ጉዞ ጋር የማይገናኝ ዳሩ ግን በዚህ አጋጣሚ የአየር መንገዱን ዝና ለማጥፋት ሲደረጉ የነበሩ ጥረቶች ናቸው። ይሄ አየር መንገድ እኮ የጠላት አገር ንበረት አይደለም፤ ከነ ገመናውም ቢሆን የራሳችን ነው። በዝናው የኮራነውን ያህል ጥፋት ከተገኘም ለሌሎች አገራት አሳልፎ መስጠት የራስን ነውር ማውጣት ነው። አየር መንገዱ ብዙ ተፎካካሪ አገራት አሉት፤ ይሄን የአገር ውስጥ አሉባልታ ተጠቅመው ዝናውን ማውረድ ይችላሉ። በዚያ ላይ ደግሞ የሚባሉት ነገሮች አሉባልታና ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር የማይገናኙ መሆናቸው። ወደ ቻይና የሚያደርገውን በረራ ባለማቋረጡ መውቀስ ይቻል ይሆናል፤ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ ሌላ ገመና መፈለግ ግን የሚያመለክተው ነገር ስሙ እንዲጠላ መፈለግን ነው። የራስ የሆነን ነገር እንደጠላት ንብረት ማየት የአገር ፍቅርና ተቆርቋሪነት ሊሆን አይችልም። የውጮችን እኮ የምናከብረው ባለቤቶች ሲያከብሩት ስላየን ነው።
አሽሊ ግርሃም የልጇብ ስም ምኒልክ አለች። ምኒልክ የሚል ስም አሜሪካ ውስጥ የተለመደ አይደለም። ይሄን ስም የሰማ ሁሉ ምን ማለት ነው ብለው ይጠይቋታል፤ እሷም ምክንያቷን ትናገራለች። በዚህ ሁሉ ውስጥ የኢትዮጵያ ስም ይጠራል ማለት ነው። አሽሊ ታዋቂ ናት፤ ስለዚህ የሚደጋገምበት አጋጣሚ ብዙ ነው ማለት ነው። ልጇ ምን እንደሚሆን አይታወቅም፤ የአሜሪካ ፕሬዚዳንትም ሊሆን ይችላል። በዚህ ሁሉ ውስጥ የኢትዮጵያ ስም ይጠራል ማለት ነው። አሽሊ ግርሃም እናመሰግናለን!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 7/2012
ዋለልኝ አየለ