አዲስ አበባን የቆረቆሯትና ከአድዋ ድል መሪ ተዋንያን መካከል ዋነኛዋ የነበሩት እቴጌ ጣይቱ ብጡል ህይወታቸው ያለፈው ከ102 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት የካቲት አራት ቀን 1910 ዓ.ም ነበር።
እቴጌ ጣይቱ ነሐሴ 12 ቀን 1832 ዓ.ም ጐንደር ደብረታቦር ከተማ ተወለዱ። ገና ልጅ ሳሉ አባታቸውን በጦርነት ስላጡ ወደ ጐጃም ተጉዘው በደብረ መዊዕ ገዳም በዘመኑ ይሰጥ የነበረውን ትምህርት ተከታትለው ፅህፈትን፣ ንባብን፣ ግዕዝና አማርኛ ቅኔን፣ ታሪክንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በሚገባ ተምረው አጠናቀዋል።
እቴጌ ጣይቱ የዘር ሐረጋቸው የሚመዘዘው ከኢትዮጵያ ነገስታት ተዋዕረድ ውስጥ በመሆኑ በስርዓትና በእንክብካቤ ያደጉ ናቸው። አጤ ቴዎድሮስ ወደ ሸዋ ዘምተው አጤ ምኒልክን ማርከው ወደ ጐንደር ወስደዋቸው በሚያሳድጓቸው ወቅት፣ ምኒልክ በተለያዩ ሰዎች አማካይነት ጣይቱ ስለምትባል ሴት ብልህነትና አርቆ አሳቢነት ወሬ በተደጋጋሚ ይሰሙ ነበር። ጣይቱ ማን ናት? ምን አይነት ሰው ናት እያሉ ልባቸው መንጠልጠል ጀመረ።
“ጣይቱ የምትባል ብልህ ሴት ትወለዳለች” እየተባለ በወቅቱ የሚነገር ንግርት እንደነበር ፀሐፊያን ይገልፃሉ። ጣይቱ ከብልህነቷ የተነሳ ኢትዮጵያን ትመራለች እየተባለ ለረጅም ጊዜ ሲነገር ቆይቷል። ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደስላሴ “ጣይቱ በምትባል ሴት የኢትዮጵያ መንግስት ታላቅ ይሆናል እየተባለ ሲነገር ይኖር ነበርና ከአፄ ምኒልክ አስቀድሞ የነበሩ አንዳንድ ነገሥታት ስሟ ጣይቱ የምትባል ሴት እየፈለጉ ማግባት ጀምረው ነበር። ነገር ግን ጊዜው አልደረሰም ነበርና አልሆነላቸውም። ዘመኑ በደረሰ ጊዜ ግን አፄ ምኒልክ እቴጌ ጣይቱን አገቡ። እቴጌ ጣይቱም የብሩህ አዕምሮ ባለቤት ስለነበሩ በመንግሥቱ ስራ ሁሉ አፄ ምኒልክን ይረዱ ነበር። እንደ ንግርቱም ቃል ኢትዮጵያ በእቴጌ ጣይቱ ዘመን ታላቅ ሆነች” ብለዋል ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ስላሴ በ1915 ዓ.ም ባሳተሙት የህይወት ታሪክ በተሰኘው መፅሐፋቸው።
ፋንታሁን እንግዳ ታሪካዊ መዝገበ ሰብ በተሰኘው መፅሐፋቸው “ይህን ሁሉ አጥንተው የሚያወቁት ንጉሥ ምኒልክ ሚያዝያ 25 ቀን 1875 ዓ.ም በአንኮበር መድኃኒያለም ቤተ ክርስቲያን ከእቴጌ ጣይቱ ብጡል ጋር በቁርባን ጋብቻውን ፈፀሙ። አምስት ዓመታት ቆይቶም ጥቅምት 27 ቀን 1882 ዓ.ም ጣይቱ ብጡል እቴጌ ተብለው ተሰየሙ” በማለት ፅፈዋል።
አፈወርቅ ገብረእየሱስ ዳግማዊ አጤ ምኒልክ በተሰኘው መፅሐፋቸው ስለ ጣይቱ ሲገልጹ “የሸዋ ቤተ-መንግሥት ዓለሙ የዚህን ቀን ተጀመረ። የሸዋ ቆሌ፣ የሸዋ ደስታ የዚህን ቀን ተጀመረ። የሸዋ መንግሥት ከጣይቱ በኋላ ውቃቢ ገባው፣ ግርማና ውበት ተጫነው፣ ጥላው ከበደ፣ የእውነተኛው አዱኛ፣ የእውነተኛው ደስታ ከጣይቱ ብጡል ጋር ገባ” ብለዋል።
እቴጌ ዛሬ የአፍሪካ መዲና ተብላ የምትጠራውን አዲስ አበባን መስርተዋል። ከእንጦጦ እየወረዱ ፍልውሃ አጠገብ ድንኳን እያስተከሉ ሳምንትም ሁለት ሳምንትም ይነከሩ ነበር። ፍል ውሃ ለመነከር በተደጋጋሚ ከእንጦጦ በመውረዳቸው ምክንያት በኅዳር 1878 ዐፄ ምኒልክ ወደ ሐረርጌ በዘመቱበት አጋጣሚ አሁን ታላቁ ቤተ መንግሥት በሚገኝበት ቦታ ቤት እንዲሠራና አዲስ ከተማ እንዲቆረቆር ትእዛዝ ሰጡ። በዚህ መሠረት አዲስ አበባ ብለው ራሳቸው የሰየሙት ከተማ ከእንጦጦ ግርጌ ተመሠረተ። ምኒልክም ከሐረርጌ ዘመቻ ሲመለሱ የእቴጌን ሐሳብ ተቀብለው የቤተ መንግሥት ሥራው እንዲፋጠን አደረጉ አድባራትንም ተከሉ።
ጣይቱ ያልተሳተፉበት ልማት አልነበረም። ስልኩ፣ ባቡሩ፣ ኤሌክትሪኩ፣ ፊልሙ፣ ውሃው፣ መኪናው፣ ትምህርት ቤቱ፣ ሆስፒታሉ፣ ሆቴሉ፣ መንገዱ ወዘተ… መገንባትና መተዋወቅ ሲጀምር ጣይቱ የባልተቤታቸው የአፄ ምኒልክ ቀኝ እጅ ነበሩ። እቴጌ ጣይቱ ኢትዮጵያውያን መሳፍንትን ባላባቶችንና ተራውን ሕዝብ በግብራቸውና በድግሳቸው ሁልጊዜም ያስደስቱ ነበር። ነገር ግን የአውሮፓውያን እንግዶች ብዛት እየጨመረ ሲመጣ ለእነሱ የሚሆን የግብር ምግብ ማዘጋጀት አስቸጋሪ መሆኑን ተረዱ። በዚህ ጊዜ ለፈረንጆች እንደ ባሕላቸው ምግብና መጠጥ የሚቀርብበት ቤት እንዲሠራ ሐሳብ አቀርበው በስማቸው የሚጠራው ጣይቱ ሆቴል ተከፈተ።
እቴጌ ጣይቱ የጣሊያን አጭበርባሪዎች ኢትዮጵያን አሳስተው ውጫሌ ላይ የተደረገውን የሁለቱን ሀገሮች ውል ቅኝ ግዛት መያዣ ለማድረግ ማሴራቸውን ከተረዱ በኋላ በልበሙሉነት ከኢጣሊያ መንግስት ጋር ጦርነት ለመግጠም ተነሱ። የኢጣሊያውን ዲፕሎማት አንቶኔሊን ጣይቱ እንዲህ አሉት፡- “ያንተ ፍላጐት ኢትዮጵያ በሌላ መንግስት ፊት የኢጣሊያ ጥገኛ መሆኗን ለማሳወቅ ነው። ነገር ግን ይህን የመሰለው የምኞት ሃሳብ አይሞከርም! እኔ ራሴ ሴት ነኝ። ጦርነት አልፈልግም። ነገር ግን ይህን ውል ብሎ ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ!” ሲሉ ተናግረዋል።በሀገራቸው ሉዐላዊነት ላይ ምንም ዓይነት ድርድር እንደማያደርጉ በትንታግ ንግግራቸው አሳውቀዋል። ከዚያም ሦስት ሺ እግረኛ ወታደርና ስድስት ሺ ፈረሰኛ ጦር እየመሩ ከአጤ ምኒልክ ጐንና ከሌሎችም የአድዋ ጀግኖች ጋር ሆነው ዘምተዋል።
በዐድዋ ዘመቻ ወቅት የእቴጌ ጣይቱ ዋና የሥራ ድርሻ የሠራዊቱን ስንቅ ማሰናዳት ነበር። ወቅቱ በአብዛኛው የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ርሃብና ድርቅ የነበረበት በመሆኑ እንዲሁም በሽታ የቀንድ ከብቱን ስለፈጀው ለሚዘምተው ሠራዊት ስንቅ ማደራጀት ከባድ ነበር። እቴጌ ጣይቱ በየአካባቢው ያሉ የሥጋ ዘመዶቻቸውን በመጠቀም ለሠራዊቱ ስንቅ የሚሆን እህል መጀመሪያ ወረ ኢሉ እንዲከማች አደረጉ።
ቀጥሎም ይህ ስንቅ የሚጓጓዝበትን መንገድ አመቻችተው እስከ አድዋ ድረስ በልክና በሚበቃ መልኩ ለሠራዊቱ እንዲደረስ ያደርጉ ነበር። ስንቅ ባነሰ ጊዜም ሰሜን ጎንደር ያሉ ዘመዶቻቸው ይዘው እንዲመጡ ያደርጉ ነበር።
የመቀሌው ከበባ በድል እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉትም እቴጌ ጣይቱ ናቸው። የጣሊያን ወታደሮች መቀሌ እንዳየሱስ ላይ ፎርቶ ዲ. ጋሊያኖ የሚባለው ቦታ መሽገው ለሁለት ሳምንት የኢትዮጵያን ጦር አላስጠጉም ነበር። እቴጌ ጣይቱ ባመጡት ብልሐትና በራሳቸው ከሚመራው እና ከሚታዘዘው ጦር ምርጥ ተዋጊዎችን በሌሊት ልከው ጣሊያኖች የሚጠቀሙበትን ከምሽጋቸው በስተደቡብ ያለውን ማይንሽቲ የተባለውን ምንጭ በኢትዮጵያውያን እጅ እንዲገባ አድርገዋል። ይህ ወታደራዊ እርምጃ በጣሊያኖች ዘንድ ከፍተኛ የውሃ ችግር በመፍጠሩ ጣሊያኖች ምሽጋቸውን ለቅቀው እንዲሄዱ አስገድዷቸዋል።
በዋናው የዐድዋ ጦርነት ቀን እቴጌ ጣይቱ የሚመሩት ጦር በውጊያ ከመሳተፉ ባሻገር የሚቆጣጠሯቸው የሥራ ቤት ሴቶች ውሃ በማቅረብ፣ ቁስለኛ በማንሣትና በማከም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ጦርነቱ በብዙ ቦታዎች በመደረጉ አንዱን ክፍል የጣሊያን ጦር አሸንፎ የሚመጣውን ጦር እንዲሁም የደከመውን “አይዞህ በርታ ውጊያው አላለቀም ንጉሡም አልተመለሱም” እያሉ ሲያበረታቱ ውለዋል።
እቴጌ ጣይቱ በዘመናቸው እጅግ ገናና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴት ነበሩ። በእስራኤል ውስጥ በተለይም በእየሩሳሌም ውስጥ ያለውን የዴር ሱልጣን ገዳምን በመርዳትና የኢትዮጵያ መሆኑን አስረግጠው ያስመሰከሩ ሃይማኖተኛ እና ፖለቲከኛ ነበሩ። ኢትዮጵያ በጦርነቱም፣ በስልጣኔውም፣ በፖለቲካውም፣ በመንፈሳዊውም ዓለም ጠንክራ እንድትወጣ ብዙ ጥረዋል።ተሳክቶላቸዋልም።
ታህሳስ ሦስት ቀን 1906 ዓ.ም አጤ ምኒልክ ሲያርፉ የቤተ-መንግስት ሹማምንቶች እቴጌ ጣይቱን ስልጣን ከሸዋ እጅ ወጥቶ ወደ ጐንደር ሊሄድ ነው በሚል ፈሩዋቸው። ስለዚህ ጣይቱ እንጦጦ ማርያም ሄደው በግዞት እንዲቀመጡ ተደረጉ። በጣሙን አዘኑ። በዚያው የሐዘን ስሜታቸው አፍሪካዊቷ ጀግና እቴጌ ጣይቱ የካቲት አራት ቀን 1910 ዓ.ም ሌሊት ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
እቴጌ ጣይቱ ከማረፋቸው አስቀድመው ለንግሥት ዘውዲቱ “ልጄ ማሚቴ ሆይ አደራዬን ሰጥቼሻለሁ” ብለው መናዘዛቸው በታሪክ ይወሳል። በዚሁ መሠረት ንግሥት ዘውዲቱ በታኅሣሥ ወር 1920 ዓ.ም የአፄ ምኒልክን አፅም ከቤተ መንግሥቱ አስወጥተው ለማረፊያው በታዕካ ነገሥት በአታ ቤተ ክርስቲያን አሳንፀው በነበረ ጊዜ የእቴጌንም አጽም እዚሁ እንዲያርፍ ቢፈልጉም የእንጦጦ ማርያም ካህናት እቴጌ ጣይቱ ለኛም እናታችን ናቸውና መታሰቢያነታቸውን እንሻለን በማለት የተቃውሞ ድምፅ አሰሙ። ቢሆንም የኑዛዜውን ቃል አብራርተው በማስረዳታቸው ፈቅደውላቸዋል። በመጨረሻም የእቴጌ ጣይቱ፣ የአፄ ምኒልክና የንግሥት ዘውዲቱ መካነ መቃብር በታዕካ ነገሥት በዓታ ቤተ ክርስቲያን ምድር ቤት ውስጥ በመንበሩ ትይዩ ተፈልፍለው በተሰሩ እብነ በረድ ሳጥኖች ታሽገው እንደቆዩ በወለሉ ላይ ጎን ለጎን ተቀምጠው ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 4/2012
የትናየት ፈሩ