ሞኑን አዲስ አበባ እንግዶችን ለመቀበል ሽር ጉድ ስትል ከርማለች። እንግዶች ከማለት ይልቅ ቤተኞች ማለቱ ይቀላል። የአፍሪካ መሪዎችና ዲፕሎማቶች ለ33ኛ መደበኛ አህጉራዊ ጉባዔያቸው የተሰባሰቡት በጋራ አጀንዳዎች ላይ ለመምከር ስለመሆኑ በሚሊዮን ለምንቆጠረው የአህጉሪቱ ተወላጆችና የዓለም ማሕበረሰብ አባላት አስቀድሞ ዜናው እንዲደርሰን ተደርጓል። የመሪዎቹ ጉባዔ ያተኮረበት መሪ ሃሳብ የጠብመንጃ ላንቃዎች በአፍሪካ ምድር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለሚዘጉበት ሁኔታ (Silencing the Guns) ለመመካከርና ሌሎች በርካታ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ በመምከር የተስማሙባቸውን ውሳኔዎች በአሜንታ ለማጽደቅ ነው።
የአፍሪካዊያንና የጠብመንጃ ወዳጅነት ዘመናት ያስቆጠረ ስለመሆኑ መናገሩ ጉንጭ አልፋነት ይመስለኛል። ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ልክ እንደኛ ባህል በቋንቋቸው፣ በኪነጥባባቸውና በሥነ ቃሎቻቸው ጠብመንጃን በፍቅር እሹሩሩ እያሉ ሲያሞካሹ ስለመኖራቸው የሚካድ እውነታ አይደለም። ለምሳሌ፤ በሀገራችን አነጋገር “ጠመንጃ ያለ ጥይት ዱላ፤ ወንድ ያለ ሴት ቀወላላ” የሚባል የቆየ አባባል አለ።
“ሃይማኖት ጋሻው፤ እግዜር ቀን እጁ፣
እርሳስ (የጠብመንጃ ቀለህ) ብታፏጭ እርሱ ምን ግዱ።”
እየተባለም በእንጉርጉሮ ይገለጻል። የአፍሪካዊያን ወንድሞቻችን ብቻ ሳይሆኑ እኛ ኢትዮጵያዊያንም ለጠብመንጃ ያለን ፍቅር ከ-እስከ የሚባል እንዳልሆነ ልባችንም ሌሎችም በሚገባ ይመሰክራሉ። ለማንኛውም ምኞት አይከፋምና የአፍሪካ አለቆቻችን የተወያዩበትና የወሰኑት አጀንዳ እንደ መሪዎቹ ልብ ሳይሆን እንዳፋቸው እንዲሆንልን ፈጣሪ ለውሳኔያቸው ተፈጻሚነት ያስጨክንልን ከማለት በስተቀር ምን ማለት ይቻላል።
ዛሬ ዛሬ ነገርና ጊዜ ተገለባብጦ የአፍሪካን አህጉር መልክና ውበት ሲያጠለሹና ሲያንቋሽሹ የኖሩት ቅኝ ገዢ ሀገራት የተቃባነው ደም ስለደረቀ “እባካችሁ ለልማት እንተባበር” በማለት የአህጉራቱን መንግሥታት መማጸናቸውን ብዙ ትምህርት ይሰጠናል።
እውነት ነው አፍሪካ ከቅኝ ገዢዎች መዳፍ ሥር በ1955 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ተላቃ በልጆቿ መዳፍ ውስጥ ከገባች ገና የአንድ ጎልማሳ ሰው ዕድሜ ያህል ቢሆን ነው። ባለፉት የአፍሪካ የቅኝ አገዛዝ ዘመናት ሀገራችን ኢትዮጵያ ግን በጨለማ ውስጥ የነጻነት ቀንዲልና ተምሳሌት ሆና መኖሯ ለእኛ ትርጉሙ ቢቀልም ለሌሎች ሀገራት የሚሰጠው ትምህርት ቀላል አይደለም።
ብዙ የአፍሪካ ሀገራት በየዓመቱ ከቅኝ ገዢዎቻቸው የተላቀቁባቸውን ዕለት የሚያከብሩት “የነጻነት ቀን” እያሉ ነው። ኢትዮጵያ ግን የካቲት 23ን እና ሚያዝያ 27ን ስትዘክር የኖረችውና የምትኖረው “የአድዋ እና የፋሽስት ወራሪዎች ድል የተመቱበት ዕለታት” መሆኑን ለጀግኖች ልጆቿና ለዓለም ማሕበረሰብ እያስታወሰች ጭምር ነው።
“እሳት ካየው ምን ለየው” እንዲሉ በቅኝ ግዛት ስር ወድቀው የነበሩት የአፍሪካ ሀገራትም ሆኑ በነጻነት ኖራለች የምንላት የሀገራችን ሕዝቦች በጋራ ዛሬም ድረስ ከርሃብና ከጠኔ፣ ከእልቂትና ከጦርነት፣ ከመፈናቀልና ከስደት፣ ከአምባገነን አገዛዝና ከወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ደዌዎች ነጻ ወጥተው ዲሞክራሲን ተለማ ምደው እየኖሩበት ነው ማለት አይቻልም።
በሌሎች ሀገራት ጠብመንጃ በግልጽና በነጻ ገበያ የሚቸበቸበው በአብዛኛው በአፍሪካ ምድር መጥቶ እንዲራገፍ ታቅዶ እንደሆነ በብዙ ጥናቶች ይጠቆማል። የሩቁን እንኳ ብንተው ከቅርብ ወራት ወዲህ የሀገራችን የጉምሩክ መሥሪያ ቤት በቁጥጥር ሥር አዋልኳቸው እያለ ሪፖርት የሚያደርግልንን የኮንትሮባንድ የጦር መሣሪያዎች ብዛትና ዓይነት ስናሰላ “እግዚኦ!” ብለን እንድናማትብ እንገደዳለን።
አፍሪካ የእርሻ መሬት በረከት የተትረፈረፈላት ሆኖ እያለ ማሳዋን ጦም በማሳደር ለልጆቿ የእርዳታ እህል እጆቿን ዘርግታ የምተቀበለው ወይንም የምትሸምተው ትናንት ቅኝ ከገዟት፤ ወይንም በስራ ትጋት ወደ ብልጽግና ከደረሱ ሀገራት ነው። የከበሩ ማዕድናት በማህፀኗ ውስጥ ታቅፋ፣ በከንቱ የሚፈሱ ወንዞቿን መገደብ ተስኗት፣ አምባገነን መሪዎቿን መግራት አቅም አንሷት “የወላድ መካንነቷን” ዛሬም እንደ ትናንቱ ለዓለም ማወጇን ቀንሳ ካልሆነ በስተቀር ሙሉ ለሙሉ ችግሮቿ ተፈትተዋል ማለት አያስችልም። ልጆቿ ለስደት፣ ምሁራኗ ለፍልሰት፣ ሀብቷን ለንቅዘት እየተዳረገ የባዕዳንን እጆች ለምጽዋት መማጠኗ ዛሬም እንቆቅልሽ እንደሆነባት አለ። አፍሪካ በርግጥም ምሥጢሯ ተፈትቶ ያልተጠናቀቀ አህጉር ነች። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የአፍሪካን ጉስቁልና ደጋግሞ በመተረክ “ከሰደበኝ መልሶ የነገረኝ ገደለኝ!” ይሉትን አባባል ለመድገም አይደለም። ይልቅስ ተስፋን ለማሳየት እንጂ።
ለዚህ ጽሑፍ የሰጠኋቸው ሁለት ተደጋጋፊ ርዕሶች የአፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና መሪዎች ተከታታይ ስብሰባዎች በተካሄዱባቸው እለታት ጎን ለጎን የተከበሩ የአፍሪካ ምሁራንና ታላላቅ ልጆቿ ለአምስት ቀናት ያህል ከአራቱም የአህጉሪቱ ቀጣናዎች ተሰባስበው የመከሩባቸው መሠረታዊ ርዕሰ ጉዳዮች ነበሩ።
ከጥር 27 እስከ የካቲት 1 ቀን 2012 ዓ.ም የቆየውን ይህንን ታላቅ የአፍሪካዊያን ምሁራን ጉባዔ ለአስራ አንደኛ ጊዜ ያዘጋጀው ቤዛ ኢንተርናሽናል ሚኒስትሪስ የተባለ ተቋም ሲሆን፤ ባለ ራዕዩ ደግሞ ዶ/ር ቤተ መንግሥቱ ይባላሉ። ዶ/ር ቤተ መንግሥቱ ከሦስት ዐሠርት ዓመታት በላይ በበርካታ የአፍሪካና የዓለም ሀገራት በተለያዩ ኃላፊነቶች በማገልገል አንቱታንና ከበሬታን ያተረፉ ታላቅ ኢትዮጵያዊ አባት ናቸው። ኢትዮጵያዊ ብቻ ከማለት ይልቅ ኢትዮጵያን ራሷን በነፍስና በልባቸው አርግዘው ስለ ሰላሟና ስለ ብልፅግናዋ ሲመኙና ሲሰሩ የኖሩ በሀገራቸው ፍቅር የተነደፉ ብርቱ ሰው ናቸው ማለቱ ይቀላል። ጸሐፊው ከእኚህ ኢትዮጵያዊ ታላቅ አባት ጋር ያለው ዕውቂያ የአንድ ጎልማሳ ሰው ዕድሜ ያህል ስለሚሆን ምስክርነቱ እውነት ነው። በአሁኑ ወቅት እያገለገሉ ካሉበት ሚኒስትሪ በተጨማሪ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተቋቋመው የእርቅና የሰላም ኮሚሽን ውስጥ አባል በመሆንም የዜግነት ግዴታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።
አፍሪካ ተነሽ (Africa Arise)
ይህ ርዕስ ለአስራ አንድ ዓመታት ያህል ጉባዔው የተስተናገደበት መሪ ሃሳብ ሲሆን፤ በየዓመቱም በዋናው መሪ ርዕስ ሥር አንዳንድ ጭብጥ እየተመረጠ ጥናቶች ይካሄዱበታል። የ2012 ዓ.ም ጉባዔ ትኩረት ያደረገው አፍሪካዊያንን ለተግባር በሚያነሳሳና በሚያነቃ ድምፀት በተመረጠው “ተነስተን እንስራ” የሚለው ርዕስ መሪ ሃሳብ በማድረግ ነበር። የቀረቡት በርካታ የጥናት ወረቀቶች ተስፋን የሚያለመልሙ ብቻ ሳይሆኑ ለተግባራዊ ርምጃም የሚያነሳሱና የሚያስወስኑ ጭምር ነበሩ። ከጥናት አቅራቢ ምሁራኑ መካከል ዩጋንዳዊቷ ወ/ሮ ክሪስቲ ሙሲሲ በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት በማገልገል ላይ ያሉ፣ በሀገራቸው ኬኒያ በተፅእኖ ፈጣሪነታቸው ጎልተው የሚታዩትና የሚደመጡት ቢሾፕ ዴቪድ ኦዲንጌ፣ ጋናዊው ምሁር ዶ/ር ዲላ አዴዴቮህ፣ ዛምቢያዊው ቢሾፕ ጆሹዋ ባንዳ፣ ኬኒያዊው ካሊስቶ ኦዴዴ፣ ከኢትዮጵያዊያን ምሁራን መካከልም ዶ/ር ምህረት ደበበ፣ ዶ/ር ማሙሻ ፈንታ፣ ፓስተር ዘሩባቤል መንግሥቱና ሣህሌ ሽፈራው ይገኙበታል።
ምሁራኑ በሙሉ ባቀረቧቸው የተዋጣላቸው ጥናቶችና ገለጻዎች ለማመልከት የሞከሩት የአፍሪካን ጉስቁልና፣ ርሃብ፣ የጦርነት ትርምስና የስደት ታሪክ በመተንተን ክፉ ገመናዋን መግለጽ አልነበረም። ይልቅስ የአህጉሪቱን ውበት፣ ድምቀት፣ ተስፋና ብልጽግናዋን በማጉላት ከተገዳዳሪዎቿ ክስተቶችና ማነቆዎች ነጻ ስለምትወጣበት መንገዶች ምሁራዊ እይታዎችንና ተስፋዎችን በማመላከት ለተግባራዊ እርምጃ የሚያነሳሱ ነበሩ። ልጆቿ ቢተባበሩ አይደለም ለራሳቸው ለተቀረው የዓለም ማሕበረሰብም መፍትሔ መሆን እንደሚቻሉ በጥልቅ የጥናት ውጤቶቻቸው አመላክተዋል።
የአፍሪካ መሠረታዊ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት በተቀባቡ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ቋንቋዎችና ንግግሮች ብቻ ሳይሆን መሪዎችም ሆኑ ሕዝቦቿ ወደ ቀልባቸውና ወደ ኅሊናቸው በመመለስ ለሰላምና ለእርቅ ሲሸነፉ እንደሆነ አስረግጠው መክረዋል። የሀገሪቱ ምሁራን፣ የእምነት ቤተሰቦች፣ ፖለቲከኞችና በየደረጃው ያሉ የየሀገራቱ መሪዎች ከጠብመንጃ አፈሙዝ ይልቅ በመልካም የሰላም ቃል ተደማምጠው ቢነጋገሩ እንቆቅልሻቸው በቀላሉ ሊፈታና ብልጽግናና ሰላም የየሀገራቱ መለያ እንደሚሆን በበቂ ማስረጃ ለማሳየት ሞክረዋል።
የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በ1955 ዓ.ም የተቋቋመበት መርህ “በአባል ሀገራቱ መካከል የፖለቲካና የኢኮኖሚ ውህደት ለመፍጠርና ቅኝ አጋዛዝንና የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝን ከአፍሪካ ምድር ጨርሶ ለማስወገድ” በሚል መሠረታዊ ዓላማ ቢሆንም ስድስት ዐሠርት ዓመታት እያስቆጠረ ያለው ይህ ርዕይ ለምን ወደ ፍጻሜ ሊደርስ እንዳልቻለም ከፖለቲካ ወገንተኝነት በጸዳ ምልከታ በድፍረት ሄሰዋል። እ.ኤ.አ አፍሪካ በ2063 ዓ.ም እደርስበታለሁ ብላ ስላቀደቸው የሩቅ ህልምም ቅኝት አድርገዋል።
ጉባዔው የተጠናቀቀው እሁድ የካቲት 1 ቀን 2012 ዓ.ም በአፍሪካ ሕብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ በተከናወነ የቁርስ ላይ የጸሎት ሥነ ሥርዓት ነበር። በዚሁ በማለዳ መርሃ ግብር ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ተወካዮች፣ የኢስዋቲኒ (የቀድሞዋ ሲዋዚል) ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የቡርኪናፋሶ ካርዲናል፣ የዛምቢያ ፕሬዚዳንትን በመወከል በኢትዮጵያ የሀገሪቱ አምባሳደር፣ የተወሰኑ የአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ታድመው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይን ጨምሮ የተለያዩ መሪዎችና ከፍተኛ የሃይማኖት አባቶች በአፍሪካ ሰላምና ብልጽግና ጉዳዮች ላይ እጅግ የሚያነቃቃ ንግግርና ፀሎት አድርገዋል።
የመርሃ ግብሩ የበላይ ጠባቂ የሆኑትና አንጋፋው የአፍሪካ አባት በመባል የሚታወቁት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት የተከበሩ ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ እጅግ ጠቀሚ የሆነ አባታዊ ምክር በመስጠት ጉባዔው በሚያስደንቅ ስኬት ሊጠናቀቅ ችሏል። ቤዛ ኢንተርናሽናል ሚኒስትሪስ በአፍሪካ ደረጃ በትልቅነታቸው በግንባር ቀደምነት ከሚጠቀሱ ግዙፍ የጉባዔ አዳራሾች ተርታ ሊሰለፍ የሚችልና ስድስት ሺህ ተሰብሳቢዎችን ሊያስተናግድ የሚችል ሁለገብ የአፍሪካዊያን የጉባዔ አዳራሽ (Afirica Convention Center) በማስገንባት ላይ ሲሆን፤ ክቡር የናይጄሪያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኦባሳንጆ ግንባታውን ተመለክተው አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
በጉባዔዎቹ ላይ የቀረቡትን እጅግ ጠቃሚና ወቅታዊ የጥናት ወረቀቶች ይዘት በተመለከተ እንዳመቸ ዋና ዋና ሃሳቦች ላይ በማተኮር በተከታይ ጽሑፌ መጥኜ ለአንባቢያን ለማቅረብ እሞክራለሁ። ሰላም ይሁን!!
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 4/2012
በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ