አንድነት አንድ ዓይነትነት አለመሆኑ ይሰመርበትና ጥቅሙ ብዙ እንደሆነ ግን ማንም አይክደውም። “ዘጠና ሚሊዮን ህዝቦች አንድ ላይ ብናጨበጭብ ድምጻችን በጣም ይሰማል” ከሚለው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አባባል ጀምሮ “ብንደመር እንጠነክራለን” እስከሚለው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ መልዕክት የአንድነትን አስፈላጊነትና ጠቀሜታ አጉልተው ያሳያሉ። ‘ድር ቢያብር አንበሳ ያስር’ እንደሚለው ብሂል አንድነት የማሸነፍና የድል ሚስጥር ነው!
ለማናችንም ግልጽ እንደሆነው ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አገራት በብዙ ነገሮች ተምሳሌት ናት። ለማሳያም ያህል የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ምልክት በሆነው አድዋ ኢትዮጵያውያን በመራር ትግልና በአኩሪ መስዋዕትነት ያስመዘገቡት ድል ለአፍሪካ ህዝቦች ትልቅ አቅም ሆኖ በአፍሪካውያን ምድር ወራሪ ኃይል እንደፈለገ መፈንጨት እንደማይችል አስተምረውበት አልፏል። በቅርብ ጊዜ ትወስታችን እንኳን ኢትዮጵያ ከዓለም ታላላቅ የኃይል ማመንጫ ግድቦች አንዱ የሆነውን ታላቁን የህዳሴ ግድብ በራሷ አቅም በመገንባት እንደነጻነት ትግሉ ሁሉ በልማትም ለአፍሪካውያን ጥሩ ተምሳሌት ሆናለች።
በተደጋጋሚ በአፍሪካውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንደሚገለጸው አፍሪካውያን በብዙ ነገር ኢትዮጵያን መከተል ይፈልጋሉ። ስለሆነም እኛ ኢትዮጵያውያን በምናቅደውም ሆነ በምንተገብረው ነገር ሁሉ በአገር ደረጃ ሳንታጠር ለአፍሪካ የሚመጥን መሆኑን አረጋግጠን መወሰን አለብን። አፍሪካውያን በምርጥ ተግባሮቻችን የሚኮሩብንን ያህል በማይመጥኑን ተግባራት እንደሚያፍሩብንም ሊዘነጋ አይገባውም።
አፍሪካውያን በአንድ መድረክ የሚሰባሰቡበትን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ፣ የፓን አፍሪካኒዝምና የአፍሪካውያን የነጻነት ትግሎችን በመደገፍ ብሎም ለአፍሪካ ኅብረት ምስረታ ኢትዮጵያ ጉልህ ሚና መጫወቷ በታሪክ መዛግብት የተሰነደ አኩሪ ታሪካችን ነው። አገራችንን በተለያየ ዘመናት የመሩ
መሪዎች ምንም እንኳን በአገር ወስጥ ብዙ ችግር ቢፈጥሩም በአፍሪካ አንድነትና ነጻነት ላይ የነበራቸው አቋም ግን ወጥና የማያወላውል እንደነበረም ግልጽ ነው። አፍሪካውያን ወንድሞቻችን የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ በሚገቡበትም ወቅት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አኩሪ መስዋዕትነት በመክፈል በወርቅ ቀለም የተጻፈ አኩሪ ገድል ደጋግሞ ፈጽሟል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ልዩነትን በውይይት መፍታት ተስኖን አንዳንድ ጊዜ የሚፈጸሙ ድርጊቶች እንደ ተምሳሌት የሚቆጥሩንን አፍሪካውያንን አንገት ያስደፋል። ከኢትዮጰያዊነት አልፈን አፍሪካኒዝምን ማቀንቀን በሚገባን በዚህ ወቅት ጥቃቅን ልዩነቶችን እየቆጠርን ስንገፋፋ መታየቱ እጅግ አሳዛኝ ነው።
በተለይም የአገሪቱ ምርጥ አዕምሮዎች መሰባሰቢያ በሆኑትና የአገሪቱን የነገ ተስፋዎች ያፈራሉ ተብለው በሚጠበቁ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ሰባራ ሰንጣራ ምክንያቶችን እየፈለጉ ብሄር ለይቶ ወደ ግጭት ሲገባና በዚህም ክቡር የሆነ የሰው ልጅ ህይወት ሲያልፍ መመልከቱ እጅግ ያንገበግባል።
በተለይም በህዝቦች መስዋዕትነት በአገራችን እውን የሆነው የለውጥ አመራር አገሪቱን ማስተዳደር ከጀመረ ወዲህ የሃሳብ ልዩነቶች በነጻነት የሚስተናገዱበት መድረክ ወለል ብሎ ተከፍቷል። አገሪቱ በብዝሃነት የደመቀች መሆኗን ይህንን ልዩነት በሚገባ ማስተናገድ የምርጫ ጉዳይ አለመሆኑ ከግንዛቤ ተወስዶ ይህንኑ አብዝሃነት የሚቀበልና የሚያስተናግድ ፌዴራላዊ ስርዓትም እውን ሆኗል።
ስለሆነም በአሁኑ ወቅት ወደ ግጭትና ብጥብጥ እንድናመራ የሚያደርግ ምንም ዓይነት ተጨባጭ ምክንያት የለም። ይልቁኑ በተከፈተው ዴሞክራሲዊ ስርዓት በአግባቡና በኃላፊነት በመጠቀምና ዴሞክራሲያዊ፣ ተዓማኒና ፍትሃዊ ምርጫ በማድረግ ለአፍሪካውያን ተምሳሌት ልንሆን ይገባናል።
ዛሬ የአፍሪካውያን አንድ መሆን እጅግ አስፈላጊ መሆኑ የታመነበትና ለዚህ በሚሰራበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ኢትዮጵያ ዴሞክራሲን አስፍናና የህዝቦቿን ፍላጎት አጣጥሞ የሚሄድ ሥርዓት ዘርግታ አንድነቷን ሳታረጋግጥ የአፍሪካ አንድ መሆን ማሰብ ያዳግታል። ስለሆንም ልዩነትን የተቀበለና ያከበረ ጠንካራ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ዕውን በማድረግ አፍሪካዊ አንድነትን ልናጠናክር ይገባል እንላለን!
አዲስ ዘመን የካቲት 3/2012