በመላው አገሪቱ 21 ሚሊዮን አባላት ያሏቸው 90 ሺህ የህብረት ሥራ ማህበራት አሉ። ማህበራቱ 26 ቢሊዮን ብር በማስመዝገብ በአሥር የሚቆጠሩ ዓመታትን አሳልፈዋል። የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ማህበራት መመስረት መልካም ቢሆንም፤ ዕድገታቸው ግን ከነጠላ ማህበርነት ወደ ህብረት (ዩኒየንነት) ከማደግ የዘለለ አይደለም። በገጠር የሚገኙት ማህበራት የአርሶ አደሩን ምርት በመሰብሰብ ለገበያ በማቅረብ ላይ፤ በከተማ የሚገኙት የሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት ደግሞ ለሸማቹ ህብረተሰብ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ከማቅረብ የዘለለ ሥራ ሲሰሩ አይስተዋሉም።
የገጠር ህብረት ስራ ማህበራት በእርግጥ ለአርሶ አደሩ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በማቅረብ ላይ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ የሚያቀርቡትን ምርጥ ዘር በማባዛት ስራ ላይ የተሰማሩ አሉ። እነርሱም ቢሆኑ በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ብዙሃኑ ያገኙትን ምርት በመሸጥ ላይ ብቻ ያተኮሩ ናቸው። በአርሶ አደሩ ምርት ላይ እሴት በመጨመር በሚፈለገው መጠን በአግሮ ፕሮሰስ ላይ የተሰማራ እና ወደ ኢንቨስትመንት የገባ የህብረት ሥራ ማህበር ማግኘት ግን እጅግ አዳጋች ነው።
የማህበሩን አባላትም ሆነ ማህበሩን የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግ ትልልቅ ዕቅዶችን በማዘጋጀት ያንን አላማ ለማሳካት መንቀሳቀስ ላይ ከፍተኛ ክፍተት በመኖሩ ብዙሃኑ ማህበራት በተለመደ ሥራ ላይ ተሰማርተው ዕድገታቸውን ተገትቷል። በከተማ ያሉትም ቢሆኑ ዘይት፣ ዱቄት እና ስኳር ከመሸጥና ምናልባትም ትንሽ ሸቀጦችን ከማቅረብ በዘለለ ወደ ኢንቨስትመንት ሲያመሩ አይስተዋሉም።
የሌሎች የአውሮፓም ሆነ የኤዢያ አገራት የህብረት ሥራ ማህበራት ከአገራቱ ኢኮኖሚ ጋር የጠበቀ ቁርኝት ያላቸው ናቸው። ማህበራቱ ከአገር አልፈው አለም አቀፋዊ እስከመሆን ደርሰዋል። “የህብረት ስራ ማህበር አባት” የሚል ስያሜ ያተረፈው የስኮትላንድ ነዋሪው ሮበርት ኦን በጥጥ ንግድ ላይ ተሰማርቶ የመንደሩን ነዋሪዎች በማነሳሳቱ እና የተነቃቃ ተሳትፎ በማድረጋቸው ሁሉም ከድህነት መላቀቅ ችለዋል። የሮበርት መንደር ነዋሪዎች የህብረት ሥራ ማህበሩ ሥራዬ ብለው በመንቀሳቀሳቸው እርሱም በዕውቀት ታግዞ በመምራቱ ስኬታማ ሆነዋል።
የኢትዮጵያ የህብረት ሥራ ማህበራት ከተለመደው የሽያጭ ተግባር ወጥተው ከፍተኛ ለውጥ ለማምጣት በሚያስችል የኢንቨስትመንት ሥራ ላይ መሰማራት አለባቸው። ለምሳሌ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ አርሶ አደሩ የሚያመርተውን ማንጎ፣ ሙዝና ብርቱካን በጥሬው ለገበያ ከማቅረብ ይልቅ በጁስ መልክ አዘጋጅተው በአገር ውስጥም ሆነ በአለም አቀፍ ገበያ ላይ በመሰማራት ራሳቸውን ማሳደግ ካልቻሉ የአባላቶቻቸውን ህይወት መቀየር ያዳግታቸዋል። ለአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት የሚጠበቅባቸውንም መወጣት አይችሉም። በበቂ ደረጃ መንግስትን መደገፍም ሆነ አገርን ማሳደግ እንዲሁም ህዝብን ተጠቃሚ ማድረግ ይሳናቸዋል።
ከሽያጭ የምትገኘዋን ጥቂት ትርፍ በመዝረፍ ላይ የተሰማሩ የማህበራት ስራ አስኪያጆችንም ሆኑ የማህበራት የቦርድ አመራሮችን ድርጊቱን የሚፈፅሙ ከሆነ ማጋለጥ፤ በአግባቡ አቅደው ማህበራቱን ማሳደግ ካልቻሉ ደግሞ እንዲቀየሩ ማድረግ ከማህበራት አባላት ይጠበቃል። እንዲያደራጁ፣ ድጋፍና ክትትል እንዲያደርጉ በወረዳም ሆነ በዞን፤ በፌዴራልም ሆነ በክልል በየደረጃው የተቀመጡ የመንግስት አካላትም ማህበራቱን እንዲመሩ ከተመረጡ አካላት ጋር ተመሳጥሮ ከመመዝበር ይልቅ ሁሉንም በሚጠቅም እና አገርን በሚያሳድግ መልኩ እንዲሰሩ መደገፍ እና መከታተል አለባቸው።
የአባላትን ቁጥር መጨመር እና ገንዘብ እንዲያዋጡ መገፋፋት ብቻ ሳይሆን ሃሳብ እንዲያፈልቁ መጋበዝ፤ ማበረታታት፤ ሰራተኞቹም የሚሰሩት ስራ ለመስራት ያህል ሳይሆን ትልቅ ለውጥና እድገት ታሳቢ አድርገው እንዲንቀሳቀሱ መገፋፋት፤ የነገ ተስፋቸውን በማመላከት የእነርሱንም ሆነ የአባላቱን ህይወት መቀየር ላይ ማተኮር ይገባቸዋል።
የህብረት ስራ ማህበራት ባሉበት ቆመው በነበሩበት አዙሪት ውስጥ ከመሽከርከር ይልቅ ትልቅ ራዕይ ሰንቀው ነገን ለትልቅ ጉዳይ ማጨት፤ ያገኙትን ከመሸጥ በተጨማሪ እሴት ጨምሮ ምርትን ማብዛት፤ ብሎም፤ በአለም ገበያ ውስጥ በመሳተፍ ከራስ አልፎ የአገርን ኢኮኖሚ ለመደገፍ ሚናቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል። ይህንም ለማድረግም የማህበራት መሪዎች በዕውቀት ታግዘው መንቀሳቀስ አለባቸው።
ዕቅዳቸውን ከመገደብ ይልቅ ከራስ አልፈው ለሌሎችና ለአገር በሚበጅ ኢንቨስትመንት ላይ ለመሰማራት አስፍተው ማሰብና መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል። የህብረት ሥራ ማህበራት ደጋፊ የመንግስት አደረጃጀቶችም መደገፍና ዘመናዊውን መንገድ ማሳየት አለባቸው። አባላቱም የጋራ ግፊት በመፍጠር ሩቅ ያስቡ፤ በህብረታቸው ከመንደር ወጥተው በአለም ገበያ መሳተፍን ዓላማ ያድርጉ፤
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2012