ኢትዮጵያ በቅኝ የተገዙ የአፍሪካ አገራት ለነጻነት እንዲነሱ፤ እንዲታገሉም ያደረገች፤ ከነጻነትም በኋላ ለአፍሪካ ህብረት (ለወቅቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት) መመስረት ዋናውን ሚና የተጫወተች አገር ናት፡፡ ከቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዘመን ለአፍሪካ ህብረት ምስረታ ከተጫወተችው ሚና በተጨማሪ የአፍሪካ ሃገራት ነጻነታቸው እንዲጎናጸፉ ከፍተኛ ድጋፍ አድርጋለች፡፡
በዘመነ ደርግም የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ ፕሬዝዳንት መንግስቱ ኃይለማርያም የተለያዩ አገራት የነጻነት ታጋዮች ስልጠናና ድጋፍ በመስጠት፤ በዓለም አቀፍ መድረክም ለአፍሪካ ጉዳይ ጥብቅና በመቆም ለአህጉሪቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡
በኢፌዴሪ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊም የኢትዮጵያ ለአፍሪካ ጉዳይ ቋሚ ጠበቃ የመሆን ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ መድረክ በአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ አፍሪካን በመወከል ለአህጉሪቱ ጥቅሞች ሰርታለች፡፡ የሩዋንዳ፣ የቡርንዲ፣ የላይበሪያ፣ የዳርፉር፣ የአብየ እንዲሁም የሶማሊያ ህዝቦች ሰላም እንዲያገኙ መስዋእትነት በመክፈል አሁንም ለአፍሪካ ጉዳይና ጥቅም ያላትን ጠንካራ አቋም አሳይታለች፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የስልጣን ዘመንም ይኸው አቋም ቀጥሏል፡፡
ከለውጥ በኋላ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር በሆኑት ዶክተር አብይ አህመድም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላምና ደህንነት ያላትን የማይለዋወጥ አቋም ቀጥሏል፡፡ በሶማሊያ፣ ዳፉርና አብየ የኢትዮጵያ መከላከያ ስራዊት ለሰላም ከሚሰራቸው ስራዎች በተጨማሪ በሱዳን ተፈጥሮ የነበረው አለመረጋጋት ወደ ሰላም እንዲመጣ፤ የደቡብ ሱዳን ኃይሎች ተቀራርበው ስለሰላም እንዲመክሩ፣ በተለይ ደግሞ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ከኤርትራ ጋር የነበረውን ችግር ለመፍታት የሰላም ስምምነት በማድረግ፤ በጅቡቲና ኤርትራ መካከልም ሰላም እንዲሰፍን ኢትዮጵያ ከፍተኛ ስራ ሰርታለች፡፡
ኢትዮጵያ በተለያዩ ስርዓተ መንግስታትና መሪዎች በአፍሪካ ጉዳይ የነበራት አቋም የማይቀየር ነው፡፡ ይህ አቋም አሁንም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ህብረቱም ኢትዮጵያና መሪዎቿ ለአበረከቱት አስተዋጽኦ ተገቢውን ቦታና ክብር እየሰጠ ነው፡፡ ይህም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡
ህብረቱ የኢትዮጵያ መሪዎችም ላደረጉት አስተዋጽኦም ማስታወሻ ይሆን ዘንድ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ ከውሳኔዎቹም መካከል ለህብረቱ መመስረት ግንባር ቀድም ሚና ለተጫወቱት ቀዳዋሚ ኃይለ ሥላሴ በህብረቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ሃውልት እንዲቆምላቸው ተወስኖ በአፍሪካ ህብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ ተግባራዊ ተደርጓል፤ ሌላኛው የአፍሪካ ህብረት ዋናው ህንጻ “መለስ ዜናዊ አፍሪካ ህብረት ሰርቪስ ሴንተር” በሚል በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ስም እንዲሰየም ተደርጓል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ኢትዮጵያ ለህብረቱና ከአህጉሪቱ ጥቅሞች የማይለዋወጥ ጽኑ አቋም ስላላት ነው፡፡
ኢትዮጵያ በየትኛውም ዘመን በነበሩት መሪዎቿ በአፍሪካ ህብረትና በአፍሪካውያን ጉዳይ ላይ ያሳየችው አቋም የጸና እና ያልተቀያየረ ነው፡፡ ይህ አቋም አሁን ተጠናክሮ ይቀጥል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በመደመር ፍልስፍና የበለጸገች ኢትዮጵያ ብሎም አፍሪካን ለመገንባት እያከናወኑ ያለው ተግባር ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ‹‹ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነት ተምሳሌት፣ ለአፍሪካ ነጻነት ግንባር ቀደም ሚና የተጫወተች፣ አፍሪካውያን አንድ ሆነው ጠንካራ ኅብረት እንዲመሠርቱ የማዕዘን ድንጋዩን ያስቀመጠች በመሆኗ አፍሪካውያን እኅቶቻችንና ወንድሞቻችን ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ወደ ሌላ ሀገር እንደሚመጡ አይሰማቸውም፤ የሚመጡት ወደ ሀገራቸው ነውና ነው›› ሲሉ ለስብሰባው ለመጡት እንግዶች ‹‹እንኳን ደህና መጣችሁ›› በሚለው መልዕክታቸው መግለጻቸው አሁንም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ለአፍሪካ ህብረትና ለአፍሪካ ጉዳይ ያላቸው ቀና አቋም ቀጣይ መሆኑ ማሳያ ነው፡፡
በየትኛው ዘመንም ሆነ በየዘመኑ ኢትዮጵያን በመሯት መሪዎች ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት አላማዎች ያላትን የማይቀያየር አቋም እንዲሁም ለአህጉሪቱ ሰላምና ጸጥታ የምትተጋ አገር መሆኗን አሁንም ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 1/2012