በመጪው የፈረንጆቹ ወር የመጀመሪያው ዕለት በሚካሄደው የቶኪዮ ማራቶን የአምናዎቹ አሸናፊዎች በድጋሚ ተሳታፊ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። በዓለም ላይ ስመጥር ከሆኑትና የዓለም አትሌቲክስም የፕላቲኒየም ደረጃ ከሰጣቸው የጎዳና ላይ ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነውን የቶኪዮ ማራቶንን ኢትዮጵ ያዊያኑ አትሌቶች እንደሚያደምቁትም ይጠበቃል። የአትሌቶቹ የግል ፈጣን ሰዓትም በሁለቱም ጾታ ቀዳሚ መሆኑ ደግሞ ፉክክሩ በአንድ ሃገር አትሌቶች መካከል ስለሚያደርገው፤ ውድድሩን ይበልጥ አጓጊም ያደርገዋል።
አትሌት ብርሃኑ ለገሰ በወንዶች ምድብ የሚመራ ኢትዮጵያዊ ሲሆን ቀዳሚው ፈጣን ሰዓትም የግሉ ነው። የአምናው የዚህ ውድድር ባለ ድል ርቀቱን ለማጠናቀቅ የፈጀበት 2:04:48 የሆነ ሰዓት ቢሆንም፤ከስምንት ወራት በፊት በተካፈለበት የበርሊን ማራቶን 2:02:48 በመግባት የራሱን ሰዓት አሻሽሏል። ይህም ከባዱንና ረጅሙን የማራቶን ውድድር ከ2 ሰዓት ከ05 በታች የሆነ ሰዓት ካስመዘገቡ ስምንት ምርጥ አትሌቶች ተርታ የሚያሰልፈው ነው። ብርሃኑ በፈጣን ሰዓቱ እንዲሁም በቦታው ባለው ልምድ ታግዞ ዘንድሮም አሸናፊ የመሆን ከፍተኛ ቅድመ ግምትን ያግኝ እንጂ፤ ፈተና ሊሆኑበት የሚችሉ አትሌቶችም በውድድሩ ተካተዋል።
ውድድሩን ሊያከብዱት አሊያም በአሸናፊነት ሊያጠናቅቁ ይችላሉ በሚል ከሚጠበቁት አትሌቶች መካከል አንዱ የሃገሩ ልጅ ጌታነህ ሞላ ነው። 2:03:34 ደግሞ አምና የዱባይ ማራቶንን በቀዳሚነት ያጠናቀቀበት እንዲሁም በቶኪዮ ማራቶን ተሳታፊዎች መካከል ሁለተኛው ፈጣን ነው። አትሌት ሲሳይ ለማም ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ሲሆን፣ በበርሊን ማራቶን ብርሃኑ ለገሰን ተከትሎ የገባበት ሰዓት 2:03:36 የግሉ ፈጣን ነው። በአንድ ደቂቃ ልዩነት የሚከተሉት አሰፋ መንግስቱ እና ሃይሌ ለሚም በተመሳሳይ በውድድሩ መሳተፋቸውን ያረጋገጡ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ናቸው። ኬንያዊያኑ ዲክሰን ቹምባ፣ ቱቲስ ኢክሩይ፣ አሞስ ኪፕሩቶ እንዲሁም ባህሬናዊው አል ሃሰን አል አባስም ቀላል ግምት የማይሰጣቸው አትሌቶች ናቸው።
እንደ ወንዶቹ ምድብ ሁሉ የሴቶቹን ምድብ የምትመራውም የአምናዋ የዚህ ውድድር አሸናፊ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሩቲ አጋ ናት። ሩቲ የርቀቱን የመጨረሻ መስመር የረገጠችው 2:20:40 በሆነ ሰዓት ሲሆን፤ የግሏን ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበችው ግን እአአ በ2018ቱ የበርሊን ማራቶን (2:18:34) ነው። ይህም በውድድሩ ከሚካፈሉት አትሌቶች ቀዳሚዋ ያደርጋታል። ከአትሌቷ ጋር በውድድሩ የሚሰለፉት የሃገሯ ልጆችም እአአ በ2015 እና 2018 የቶኪዮ ማራቶን አሸናፊ የነበረችው ብርሃኔ ዲባባ እንዲሁም እአአ የ2014 ባለ ድሏ ትርፌ ጸጋዬም ከቀዳሚዎቹ የአሸናፊነት ተገማች ይጠቀሳሉ። በማራቶን ሰፊ ልምድና አቅም ያላቸው፤ ትእግስት ግርማ፣ አዝመራ ገብሩ፣ ሹሬ ደምሴ፣ ማርታ ለማ፣ ሱቱሜ አሰፋ እና ሰንበሬ ተፈሪም በኢትዮጵያ በኩል ተሳታፊ የሚሆኑ አትሌቶች ናቸው።
የቶኪዮ ማራቶንን በዳይሬክተርነት የሚመሩት ታዳኪ ሃያኖ ውድድሩ በሁለት መልክ የሚካሄድ መሆኑን ይጠቁማሉ። የመጀመሪያው ምድብ 2ሰዓት ከ03 ደቂቃና ከዚያ በታች በሆነ ሰዓት ለመግባት ፍላጎት ላላቸው አትሌቶች ነው። ሁለተኛው ደግሞ ከ2:04:40-2:05:30 በሆነ ሰዓት ሩጫቸውን በሚያጠናቅቁ አትሌቶች መካከል የሚካሄድ ነው። በዚህ ውድድር ውጤታማ የሚሆኑ አትሌቶችም ከወራት በኋላ በሚካሄደው የቶኪዮው ኦሊምፒክ ቲኬት ለመቁረጥ የሚያስችላቸው ነው። በመሆኑም በርካታ ጃፓናዊያን አትሌቶች በእድሉ የሚጠቀሙ ይሆናል ሲሉም ዳይሬክተሩ ያብራራሉ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 30/2012
ብርሃን ፈይሳ