ከአለማችን አምስት ህፃናት ውስጥ አንዱ ግጭትና ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች እንደሚኖር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እ.አ.አ. በ2018 ያወጣው መረጃ ያመለክታል። አፍሪካ ውስጥ ደግሞ ጉዳዩ ከዚህም በላይ አስከፊ ደረጃ የደረሰባቸው እና በየቀኑ የስቃይ ህይወት የሚያልፍባቸው አካባቢዎች አሉ።
በአልማዝ ሀብቷ የምትታወቀው ዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ደቡብ ሱዳን በየጊዜው የሰው ህይወት የሚቀጥፉ ግጭቶች ይነሳሉ። በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራትም የመንግስት ጦር እና የአማጽያን ጦር በተለያየ ወገን ተመድበው ሰላማዊ ዜጎች ላይ ሞት እና ስደት የሚያስከትል ችግር የማድረሳቸውን ጉዳይ የአለም መገናኛ ብዙሃን መዘገባቸው የእለት ተዕለት ትዕይንት ሆኗል።
በሊቢያ እንኳን የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነት ታክሎበት የመሳሪያ ድጋፍ ባልተለየው ጦርነት ሊቢያውያን አሰቃቂ ህይወት የሚገፉባቸው በርካታ ገጠራማ አካባቢዎች ዛሬም ደም ይፈስባቸዋል። የአፍሪካ ህብረትም ለዚህ ጉዳይ ትኩረት በመስጠት ምንም አይነት ግጭት የማይታይባት እና ሰላማዊ አፍሪካ እንዲሁም የጦር መሳሪያ ህገወጥ እንቅስቃሴ የማይታይባት አህጉር በ2020 ማየት የሚል አጀንዳ ይዞ የመሪዎቹን ስብሰባ በአዲስ አበባ ለማድረግ ተሰናድቷል።
የህብረቱ የ2020 እ.አ.አ. ውጥን መልካም ቢሆንም በቀሪዎቹ የዓመቱ አስር ወራት አፍሪካን ሙሉ ለሙሉ ሰላም ያላት እና ከግጭት የራቀች አህጉር ማድረግ ልዩ አምላካዊ ኃይል ካልመጣ በቀር የሚታሰብ አይሆንም። ምክንያቱም በየሀገሩ እና ቀጣናው ያሉ ችግሮች የተወሳሰቡ እና የጥቅም፣ የመሬት እና ስልጣን ጥያቄ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን ያቀፈ በመሆኑ ረዘም ያለ ሂደት እና ስራ የሚጠይቅ ነው።
ያም ሆነ ይህ ግን አፍሪካን በመጪው ጊዜ አንጻራዊ ሰላም የሚታይባት እና ግጭቶች ማጥፋት እንኳን ባይቻል መቀነስ የሚቻልባቸው እድሎች መኖራቸውን ማሰብ ግን ጤነኛነት ነው። ለዚህ ደግሞ አንዱ እርምጃ መሆን ያለበት የህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ላይ ጠበቅ ያለ ቁጥጥር ማድረግ ነው። በዘፈቀደ ከአንዱ ሀገር ወደሌላው ሀገር የሚዘዋወሩ የጦር መሳሪያዎች ንጹሃን ዜጎች ላይ መዓት እንዳያወርዱ ጠንካራ ህጎችን ማውጣትና መተግበር ይገባል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ህብረት አጀንዳ ጋር የሚያያዝ ስራ ቀድማ በማከናወን አንድ ርምጃ ወደፊት ትገኛለች። በተለይ የኢትዮጵያ መንግሥት የዜጎችን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ እንዲሁም የሕዝብን መብትና ደህንነት ለማስከበር ሲባል የጦር መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥርን በተመለከተ አዲስ ሕግ አውጥቷል። የጦር መሳሪያ ረቂቅ አዋጁም ታህሣሥ 28 ቀን 2012 ዓ.ም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ መጽደቁ ይታወሳል።
ህጉም ለግለሰብ ከሚፈቀድ የጦር መሳሪያ ብዛት እና አይነት ጀምሮ ምን አይነት ቦታዎች ላይ መያዝ አይቻልም እስከሚለው ድረስ ዝርዝር ጉዳዮችን ይዟል። በተለይም ሰላማዊ ሰልፍ ወይም አድማ በሚደረግባቸው ሥፍራዎች፤ በምርጫ አካባቢዎች፣ በሆቴልና ሲኒማ ቤቶች፣ ሙዚየሞች እና ተመሳሳይ በሆኑ የሕዝብ መዝናኛ ሥፍራዎች፣ ትምህርት ቤቶች እና የሐይማኖት ተቋማት ግቢ ውስጥ አለፍ ሲልም በሆስፒታሎች እና የህዝብ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ሥፍራዎች ግለሰቦች የጦር መሳሪያ ይዘው መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ህጉ በግልጽ አስቀምጧል። የእንደዚህ አይነቱ ህግ መውጣት እንደ በጎ እርምጃ የሚታይ ከመሆኑ በተጨማሪ ጠንካራ ቁጥጥር ማድረግ እና ህጉን በተገቢው መንገድ ማስፈጸም ደግሞ ዋናው ጉዳይ መሆኑ መዘንጋት የለበትም።
አፍሪካውያን መሪዎችም በአዲስ አበባ በህብረቱ አዳራሽ ሲሰበሰቡ በአህጉሪቷ ግጭት እንዳይባባስ እና ዜጎች በሰላማዊ መንገድ ወጥተው ወደየቤታቸው እንዲገቡ የሚረዱ ህጎች ስለሚወጡበት መንገድ፤ ስለሚወጡበት ብቻ ሳይሆን በአግባቡ ተግባራዊ ስለሚደረጉበት ስራ አጽንኦት ሰጥተው ሊመክሩ ይገባል።
ህግ ሳያወጡ እና ተግባራዊ እርምጃ ሳይወስዱ የአፍሪካን ሰላም እናረጋግጣለን ማለት ብቻ ከሆነ ግን ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ይሆናል። ለይስሙላ ተሰብስቦ ወደ የቤታቸው ለመመለስ ካልሆነና ነገሩን አጥብቀው ከያዙት ደግሞ እያንዳንዱ ለግጭት የሚረዳ መሳሪያ የሚያስገቡ ሀገራት እና ቡድኖች ላይ ጠንከር ያለ ውሳኔ ማስተላለፍ ይጠበቅባቸዋል።
አፍሪካውያን ህጻናት፣ ሴቶች እና አረጋውያን እንደሌሎች አህጉራት በተለይም እንደአውሮፓ እና ሰሜን አሜሪካ ሀገራት በሃገራቸው የሰላም አየር ተንፍሰው በሃገራቸው እንዲኖሩ ከተፈለገ ለስልጣንና ለገንዘብ የሚሮጡ መሪዎች ሳይሆን ሰላሟና ጸጥታዋ የተረጋገጠች አህጉር እውን እንድትሆን አበክረው የሚሰሩበት ወቅት አሁን ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 30/2012