ይቺ ‹‹ደንበኛ ንጉሥ ነው›› የምትባል ነገር የስንቱ ማጭበርበሪያ ሆነች! ቆይ ግን ደንበኛ ንጉሥ ነው ማለት ምን ማለት ነው? ‹‹ሰማይ አይታረስ ንጉሥ አይከሰስ›› እንደሚባለው የማይጠየቅ ማለት ይሆን? ወይስ እንደ ንጉሥ የተከበረ ነው የሚለውን ለመግለጽ ነው? የማይጠየቅ የማይከሰስ ለማለት ከሆነ ደንበኛ ንጉሥ መሆን የለበትም፡፡ የተከበረ ነው የሚለውን ለመግለጽ ከሆነ ይሁን!
እርግጥ ነው ማለት የተፈለገው የተ ከበረ ነው ለማለት ነው፡፡ ደንበኛ ንጉሥ የሚሆነው ግን ለባለሆቴሉ ብቻ ነው እንዴ? ደንበኛ ንጉሥ ሲሆን እኮ ራሱም የተከበረ መሆን አለበት፡፡
ከአንድ ጓደኛዬ ጋር በተደጋጋሚ እንጨቃጨቃለን፡፡ በገባንበት ካፌና ሆቴል ሁሉ በትንሽ ትልቁ ‹‹ባለቤቱን ጥሪልኝ›› ይላል፡፡ ባለቤቱ ሲመጣ እኔ ከባለቤቱ ወገን ሆኜ ነው ከጓደኛዬ ጋር የምጨቃጨቀው፡፡ ብዙ ጊዜ በባለቤቶች ትዕግስት እገረማለሁ:: አንዳንዴ በባለቤቶች ቦታ ብሆን ብዬ ራሴን እጠይቀዋለሁ፡፡ ‹‹ሂድ ውጣ ከዚህ!›› የምል ሁሉ ይመስለኛል፡፡ እርግጥ ነው እንዲህ ማለት በጣም ነውር ነው፤ ግን ራሱ ደንበኛው ሥርዓት ካልያዘስ? አንዳንዱ እኮ ጭራሽ ሲለማመጡት ይብስበታል!
ከዚህ ጓደኛዬ ጋር የምንጨቃጨቀው ባለቤቱን ሊያስጠራ በማይችል ቀላል ነገር ጥሩልኝ ሲል ነው፡፡ እርግጥ ነው ባለቤቱን መጥራትና አስተያየት መስጠት ገንቢ ነው፤ ግን ደግሞ በቁጣ መሆን የለበትም፤ አስተናጋጆችን የሚያሳጣና የሚያስቆጣ መሆን የለበትም፡፡ ባለቤት የሚጠራው ከበድ ያለ ነገር ሲሆን ነው፡፡ ለምሳሌ ምግቡ ውስጥ ባዕድ ነገር ከተገኘ፣ መጸዳጃ ቤት አይከፈትም ከተባለ፣ መሰረታዊ ነገሮች የሉም ከተባለ… ባለቤቱን ጥሩልኝ ብሎ አስተያየት መስጠት ተገቢ ነው፡፡
ሁሌም የሚያሳዝኑኝ ደግሞ ምስኪን አስተናጋጆች ናቸው፡፡ ምግቡ ዘገየ ብሎ የሚደነፋው አስተናጋጇ ላይ ነው፤ አስተናጋጇ እኮ ተቀብሎ ማምጣት እንጂ እሷ አይደለችም የምታበስለው፡፡ መቼም ያን ያህል ያቆያት ከኪችን ጠረጴዛው ጋ ማድረሱ አይደለም፤ እሷም እኮ ቶሎ ቢመጣ አትጠላም፤ ችግሩ ግን ያለው ከአዘጋጆች ነው፡፡ የምግቡን ይዘትና ጣዕም በተመለከተም የሚደነፋው አስተናጋጇ ላይ ነው፡፡ አስተናጋጇ እኮ ጤፍ አቅራቢ አይደለችም፤ የእሷ ሥራ የታዘዘውን መናገርና የተዘጋጀውን ምግብ ለደንበኛው መስጠት ነው፡፡ እንዲህ እንዲህ አይነቱ አስተያየት ነው ለባለቤቱ መነገር ያለበት፡፡
ደንበኛ ሁሉ ንጉስ አይደለም፡፡ አንዳንዱ ደንበኛ ‹‹ምነው ባልመጣብኝ›› የሚባል ነው፤ ‹‹ከእሱ የሚገኝ ገንዘብ በአፍንጫዬ ይውጣ›› የሚያሰኝ ነው፡፡ እንዲህ አይነቱን አመለቢስ ደንበኛ ንጉሥ ነው ማለት አያስኬድም፡፡ መጠቀም ያለበትን ነገር በሥነ ሥርዓት መጠቀም የማይችል ከሆነ ችግር ነው፡፡ ፀባዩ አስቸጋሪ ከሆነ ንጉሥ ሊሆን አይችልም:: ለምሳሌ ከተዘጋጀ በኋላ ያየዙትን የሚቀይሩ አሉ፤ ተሰርቷል ሲባሉ ‹‹እሪ›› ብለው ይደነፋሉ፤ ይሳደባሉ፡፡ የዚህን ጊዜ አስተናጋጇ ትሳቀቃለች፡፡
በተለይም በቡድን ሆነው የሚደረግ ነገር ደግሞ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ጭቅጭቅ የሚያጋጥመውም ከሁለት በላይ ሆነው ሲስተናገዱ ነው፡፡ ለሚያዝዙት ነገር የጋራ ውሳኔ ላይ አይደርሱም፡፡ አንዱ ይሄ ነው ሲል ሌላው አይ ይሄ መሆን አለበት ይላል፤ እነርሱ ሲጨቃጨቁ አስተናጋጇ ሥራ ፈታ ነው የምትቆመው፡፡ ይህኔ ደግሞ ሌላኛው ደንበኛ ዘገየሽ ብሎ ይደነፋል፡፡ እስከምትወስኑ ብላ ስትሄድ ደግሞ ራሳቸው ሲጨቃጨቁ የነበሩትም ይቆጧታል፡፡
እዚህ የቡድን መስተንግዶ ላይ ሌላው የሚገርመኝ ነገር አንድ ጊዜ አያዝዙም:: መጀመሪያ ይህን ያህል ይበቃናል ይባልና ይታዘዛል፤ እሱን ከታዘዘ በኋላ ሌላ ይጨመር ይባልና ይጨመራል፡፡ ያ ዘግይቶ የተጨመረው ከመጀመሪያው ትዕዛዝ እኩል እንዲመጣ ይጠበቃል፡፡ በመሃል ደግሞ የሌላ ደንበኛ ትዕዛዝ ይኖራል፡፡ ደንበኞች ግን ይሄን እንኳን አይረዱም፡፡
በሁለቱም ወገን ችግር ይኖራል፤ ይሄ ያለና የሚያጋጥም ነው፡፡ ዋናው ችግር ግን በሀሳብ መግባባት እየተቻለ ስድብና ዛቻው ነው፡፡ ደንበኛ ንጉሥ ነው ማለት እንደፈለገው መሳደብና ማመናጨቅ አለበት ማለት አይደለም፡፡ በቃ አግባብ ካልሆነ አግባብ ያልሆነበትን ምክንያት አስረድቶ አሳማኝ ከሆነ አ ለመ ክፈልም እኮ ይችላል፡፡ እንዲያውም ባለቤቶችን ይሉኝታ የሚያሲዝ በፀባይ የተነገረ ነገር ነው እንጂ እልህ መጋባት አይደለም፡፡
ችግሩ የአንዳንድ ሰዎች ባህሪ ክብር አይወድም፡፡ ሁለት ገጠመኞችን ልንገራችሁ:: በአንድ ወቅት አዋሽ ባንክ አራት ኪሎ ቅርንጫፍ ለመገልገል ገባሁ:: በባንኩ አሰራር ትኬት ይሰጥና ቁጥር ሲጠራ ወደተጠራበት መስኮት በመሄድ ነው ደንበኞች የሚገለገሉት:: የያዝኩት ትኬት ቁጥር ወደተጠራበት መስኮት ሄድኩ፡፡ አገልግሎት ከሚሰጠው ሰራተኛ ጎን ያለው መስኮት ባዶ ነው (እየሰራ አይደለም):: አንድ ደንበኛ መጣና ባዶ መስኮቱ ላይ ቆመ፡፡ ሰራተኛ እንደሌለው ያወቀው እኛን እያስተናገደ ያለው ሰራተኛ ግን ‹‹ና›› የሚል ምልክት ሰጠው፡፡ ሰውየው መጣና ብር ለማስገባት የሞላውን ቅጽ ሰጠ፡፡ ሰራተኛው ጉዳዩ ይሄ መሆኑን ሲያው ቅ ‹‹አይ ወረፋ ይዘህ ነው የምትስተናገድ›› አለው፡፡ ያ ደንበኛ ቆጣ ብሎ ‹‹ታዲያ ለምን ጠራኸኝ?›› አለ፡፡ ሰራተኛውም በትህትና ‹‹አይ ምን እንደምትፈልግና ወዴት መሄድ እንዳለብህ ልነግርህ ነው›› አለው:: ደንበኛው ግን ቁጣው እየባሰበት ሄደ፡፡ ‹‹ጠርተኸኛል ታስተናግደኛለህ!›› አለ ቆጣ ብሎ፡፡ ባንኩ ውስጥ የነበረው ተገልጋይ ሁሉ በዚያ ደንበኛ ተገረመ፡፡ ምንም እንኳን እያወቀው ቢሆንም ለትህትና ሲባል ‹‹ወረፋ ተይዞ ነው›› እያሉ አስረዱት፡፡ ሰውየው ግን ጠርቶኛልና ማስተናገድ አለበት ብሎ ድርቅ አለ፡፡ ከዚህ በኋላ የባንኩ ሰራተኛም ትዕግስቱ አለቀ መሰለኝ መኮሳተርና የእልህ ቃላት መናገር ጀመረ፡፡ ወደ መሰዳደብ ገቡ:: ይህኔ እንደምንም ብለው ደንበኛውን ወደሌላ መስኮት ወሰዱት፡፡
እንግዲህ ልብ በሉ! ሰውየው የቆመው ባዶ መስኮት ላይ ነው፡፡ የባንኩ ሰራተኛ ‹‹ና‹‹ ባይለው ኖሮ ባዶ መስኮት ላይ ምን ሊሰራ ነበር? እውነት ያ ሰውየ የባንክ አሰራር ጠፍቶት ነው? እሺ ጠፍቶት ነው እንበል፤ ታዲያ ከተነገረው በኋላ ለምን ወረፋ አልያዘም? ሰውየው በአለባበሱም ሆነ በአካላዊ ገጽታው የተማረ የሚባል አይነት ነው፡፡ ለነገሩ ለጭቅጭቅና ለህገወጥ አሰራር የተማረ የሚባለው ነው የባሰበት፤ ያልተማሩ የሚባሉት የነገሯቸውን ሁሉ ይሰማሉ፡፡
ሌላኛው ገጠመኝ የመንግስት ሰራተኞች ማመላለሻ አውቶብስ (ፐብሊክ ሰርቪስ) ውስጥ ያስተዋልኩት ነው፡፡ በአውቶብሱ ውስጥ የሚበላ ነገር መያዝ የተከለከለ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ያም ሆኖ ግን አንዳንድ ጊዜ ደረቅ ምግቦችና በእሸት ወቅት እንደ በቆሎ ያሉ ነገሮች አልፎ አልፎ ይታያሉ:: የዚያ አውቶብስ ሾፌር ማንም ሰው ቆሎ፣ ብርቱካንና በቆሎ ሊሸጡ ከሚገቡ ልጆች እንዳይገዛ ከልክሏል መሰለኝ (እኔም በዚያ አውቶብስ ብዙ ቀን ስላልሄድኩ አላወቅኩም)፡፡ እናም የዚያን ቀን አውቶብሱ ሲቆም የሆነች ልጅ በቆሎ ይሁን ቆሎ ልትሸጥ ጠጋ ስትል አንደኛው ሰራተኛ ሊገዛ ይሁን ሊጠይቅ እጁን ሰደድ ሲያደርግ ሾፌሩ ተቆጣ፡፡ ሰራተኛውም ይቅርታ ብሎ ተወዉ:: እንደተወው እያወቀ ሾፌሩ ግን ቁጣውን ቀጠለ፡፡ ማንም ሰው እንዳይገዛ ብየ ተናግሬ ለምንድነው ለመግዛት የምትሞክረው ሲል ተቆጣ፡፡ ሰራተኛውም አላወቅኩም ነበር፤ በዚህ አውቶብስ የመጣሁት ዛሬ ነው ሲል መለሰ፡፡ አውቶብሱ ውስጥ ያሉ ሌሎች ሰራተኞችም እሱ ገና ዛሬ ነው የመጣው ስላላወ ነው እያሉ ለሾፌሩ መናገር ጀመሩ፡፡
ሾፌሩ ግን ባሰበት፡፡ ‹‹ና ውረድ!›› አለው:: ሰራተኛውም ደጋግሞ ይቅርታ ጠየቀ (ልብ በሉ ምንም ነገር ሳይገዛ ነው)፡፡ ሾፌሩን ቢያባብሉ ቢያባብሉ እየባሰበት መጣ፡፡ እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ችግር የተፈጠረው:: ይቅርታ ሲል የቆየው ሰራተኛም እልህ ተጋባና ይቅርታውን ወደ ስድብ ቀየረው፡፡ ሾፌሩና ሰራተኛው የከረረ ስድድብ ውስጥ ገቡ፡፡ ሾፌሩ ሊደባደብ መስኮት በርግዶ ወረደ፤ ሰራተኛውም ሊደባደብ ዘሎ ሲወርድ (በሩ ክፍት ነበር) ከፊት የነበሩ ሰዎች ተረባርበው ያዙት፡፡ ሁለቱም ተይዘው ‹‹ያዙኝ ልቀቁኝ ሆነ!›› ሾፌሩ ጥፋቱን አምኖ ይሁን ባህሪው ሆኖ ባላውቅም መታገሉን ትቶ ወደ መኪናው ገባ፡፡ ሰራተኛው ግን ማን ይቻለው፡፡ ገድየው ካልሞትኩ አለ:: እንደምንም በትግልም በሽምግልናም ሰራተኛው በሌላ ትራንስፖርት እንዲሄድ ተደረገ፡፡
ሁሉም ሰው የፈረደው በሾፌሩ ነበር፡፡ አዎ! ጥፋተኛ ሾፌሩ ነው፡፡ አንደኛ ሰራተኛው ምንም ጥፋት የለበትም፤ የሰራተኛው ጥፋት በኋላ ካልተደባደብኩ ማለቱ ነው፤ ይሄ ደግሞ የሰው ልጅ ባህሪ ነውና ያን ሁሉ ሲሰድበው መበሳጨቱ አይቀርም:: እንኳን ሊገዛ በእጁ እንኳን አልነካውም:: ሁለተኛ፤ ሰራተኛው በተደጋጋሚ ነው ይቅርታ የጠየቀው፡፡ ጥፋት እንኳን ያጠፋ ሰው ይቅርታ ሲጠይቅ ይቅር ይባል ነበር በባህላችን፡፡
በነገራችን ላይ ብዙ ሾፌሮችና ረዳቶች ላይ የታዘብኩት ነገር የሚለማመጥ ሰው አይወዱም፤ መሰዳደብን ነው ልማድ ያደረጉት፡፡ ታክሲ ውስጥ እንኳን ልብ ብላችሁ ከሆነ ቆጣ ብሎ ለሚናገር ሰው ነው ሲሽቆጠቆጡ የሚታዩት፡፡ በትህትና ካናገርካቸው ፌዝና ስላቃቸው ዕልህ ነው የሚያስገባው፡፡ በእነርሱ ቤት ‹‹ሙድ›› መያዛቸው ነው፡፡ ልብ ብላችሁ ከሆነ ታክሲ ውስጥ ተሳፋሪውም በቁጣ ነው የሚናገረው:: በትህትና ‹‹ተሻግሮ ወራጅ አለ›› ካልክ ‹‹አደባባዩ ላይ አይሻልህም›› ይልሃል ረዳቱ:: ተሳድቦና ገላምጦ ለሚናገራቸው ግን ተሽቆጥቁጠው ነው የሚታዘዙ፡፡ የአንዳንድ ሰዎች ባህሪ እንዲህ ነው፡፡
የየትኛውም መገልገያ ቦታ ደንበኛም ባለቤትም ንጉሥ መሆን አለበት፡፡ይህ ሲሆን ነው ተግባብቶና ተመካክሮ ህይወትን ቀና ማድረግ የሚቻለው፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 30/2012
ዋለልኝ አየለ