በ1955 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተመሰረተው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቀመጫ እንዲሆን ታስቦ የተገነባው የአፍሪካ አዳራሽ የተመረቀው ከ59 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 29 ቀን 1953 ዓ.ም ነበር፡፡
የአፍሪካ አዳራሽ ሕንጻ ግንባታ የተጠናቀቀው በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ነበር፡፡ 75 ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የተገነባው ግዙፉና ዘመናዊው የአፍሪካ አዳራሽ ሕንጻ ሶስት ሺ 600 ካሬ ሜትር ላይ ያረፉ የስብሰባ አዳራሾች ፣ አምስት ሺ 500 ካሬ ሜትር ላይ የተገነቡ ጽህፈት ቤቶች እንዲሁም አራት ሺ 700 ካሬ ሜትር ቦታ የሚሸፍኑ ጠቅላላ አገልግሎት የሚሰጡ ልዩ ልዩ ሕንጻዎችን ያካተተ ነው፡፡
የመጀመሪያውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የምስረታ ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ያስተናገደው የአፍሪካ አዳራሽ ከ10 ዓመታት በኋላ ተጨማሪ ጽሕፈት ቤቶችን ያካተተ ባለ ስድስት ፎቅ ሕንፃ አክሏል፡፡ በቅርቡም በግቢው ተጨማሪ ሕንፃ አስገንብቶ ለአገልግሎት አበቅቷል፡፡
እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በሳሉት ቶታል ሊበሬሽን ኦፍ አፍሪካ” የተሰኘ 150 ካሬ ሜትር ስፋት ባለው የመስታወት ላይ ሥዕል ያጌጠው የአፍሪካ አዳራሽ አሁን በአፍሪካ ተጠቃሽ ከሆኑት ሰው ሰራሽ ቅርሶች አንዱ ለመሆን በቅቷል፡፡
በምርቃት ስነስርዓቱ ወቅት ለእይታ የበቃውና ባማረ መንገድ ምርቃቱን ለማብሰር የተቀረጸው የንጉሡ መልእክት “ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ንጉሰ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን ሕዝብ የወደፊት እድገት መታሰቢያ ይሆነ ዘንድ ከአሳባቸው አንቅተው መርቀው የመሰረቱትን ይህን ህንጻ ጥር 29 ቀን 1953 ዓ.ም የአፍሪካ አዳራሽ ብለው ሰየሙት” ይላል፡፡
አሁን ለዕድሳት ዝግ የተደረገው ይህ ህንጻ ዘመናዊ ቴክሎጂዎች ተካተውበትና ሕዝብ እንዲጎበኘው ለማድረግ የሚያስችሉ ተጨማሪ ግንባታዎች ተካሂደውበት ከሁለት ዓመታት በኋላ ተጠናቆ ዋነኛ የጎብኚዎች መዳረሻ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ለእድሳቱም 56 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር በጀት ተመድቦለታል፡፡
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 27/2012
የትናየት ፈሩ