እንደመንደርደሪያ፤
አክሰስ ሪል እስቴት አክሲዮን ማህበር ቤት ሰርቶ ለቤት ገዢዎች ለማስረከብ ውል ይገባል። ከ 2ሺ500 ደንበኞችም አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ይሰበስባል። ደንበኞቹ በውላቸው መሰረት ቤታቸውን ለመረከብ ቢጠባበቁም ሳይሆን ይቀራል። “ቤት ለምቦሳን” ይጠባበቁ የነበሩት ደንበኞቹም የአክሰስ ሪል እስቴት አክሲዮን ማህበር ቀውስ ውስጥ መግባቱን ያረጋግጣሉ። ቤት ገዢዎቹ መንግስትን ህግ ያስከብርልን ወይ ከቤታችን አልያም ከገንዘባችን እንሁን እያሉ ሲጠይቁም ዓመታት ተቆጥረዋል። ጉዳዩን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ይዘውት የነበረ ከመሆኑም በላይ ኮሚቴ አዋቅረው ለችግሩ መፍትሄ ይሆናሉ ተብለው የቀረቡ ምክረ ሃሳቦችም ተግባራዊ እንዲሆኑና ፈጣን ፍትህ እንዲሰጣቸው እየተሰራ የነበረ ቢሆንም ውጤቱ ግን አልታየም።
የቀደመ ታሪክ
ቅሬታ አቅራቢው የአክሰስ ሪል እስቴት አክሲዮን ማህበር ቤት ገዢዎች የአብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አክሎግ ስዩም ድርጅቱ የተቋቋመበት መንገድ ለችግሩ መንስኤ ነው ብለው ያምናሉ። ድርጅቱ በ50 ሺ ብር ካፒታል በአምስት ግለሰቦች የተቋቋመ መሆኑን እንደመንስኤ ያነሳሉ። መስራቾቹም ዋና ስራ አስኪያጅና የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ይሰሩ የነበሩት አቶ ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ የቦርድ ሰብሳቢና ዋና ስራ አስኪያጅ (በሜቴክ ኢምፔሪያል ሆቴል ግዢ ተጠርጥረው በማረፊያ ቤት የሚገኙ)፣ አቶ ሃይለልዑል ታምሩ፣ አቶ አለምነህ ተክሌ፣ አቶ ሃምሳሉ ባዬና ወይዘሮ ትዕግስት ነገዴ በ2000 ዓ.ም ስራው መጀመሩን ያስታውሳሉ።
ወዲያው ሼር መሸጥ እንደጀመሩ፣ ለ652 ሰዎች የአንድ ሺ ብር ካፒታል መጠን ያለው 34 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር አካባቢ የተሰበሰበ እንዲሁም 41 ሚሊዮን ብር አካባቢ ደግሞ የተፈረመ ሼር ሽያጭ ይደረግና ስራው ይጀመራል። ይህ ከሆነ በኃላ ገንዘቡን ለታለመለት ዓላማና ለታሰበው ጉዳይ ሳይውል ከመቅረቱም በላይ ለቤት ገዢዎች ቤት ገንብቶ የመሸጥ ዓላማና ከግንባታ ጋር የሚገናኙ መሰረተ ልማቶች የማምረትና የመግዛት ፣ የማስመጣት ዓላማዎቹን ወደ ጎን ይተዋል። በዋናነትም ቤት ገንብቶ የመሸጥ ዓላማውን ተግባራዊ ባለማድረጉም ችግሩ ሊከሰት ችሏል ሲሉ ተወካዩ ይናገራሉ።
እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ ችግሩ የተከሰተው ድርጅቱ ሕግና ስርዓትን ተከትሎ ፋይናንሱን መጠቀም ባለመቻሉ ሲሆን ምንም አይነት ስርዓት ሳይዘረጋ፣ ከባለአክሲዮኖች የተሰበሰበውን ገንዘብ በንግድ ሚኒስቴር ሳያስመዘግብ፣ በሼር ካፒታልነትም ሳይታወቅ ገንዘቡን ሲጠቀምበት ነበር ሲሉ ይወቅሳሉ። በተጨማሪም ምንም ስርዓት ሳይዘረጋ ለቤት ገዢዎች ሽያጭ መጀመሩ ችግሩን እንዳባባሰውም ያክላሉ፡፡
ሁለት ሺ 500 ያህል ቤት ገዢዎች በአገር ውስጥና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ናቸው ይላሉ።
ድርጅቱ ውጭ አገር የመሸጥ ፍቃድ ሳይኖረው ከኢትዮጵያ ውጭ ቢሮ ከፍቶ በውጭ ምንዛሬ ሽያጭ ሲያከናውን ነበር ያሉት ተወካዩ ገንዘቡም ወደ ኢትዮጵያ ሳይገባ አየር ላይ ቀርቷል። ይህም ድርጅቱ የሰራው ሌላው ስህተት ነው ። በህጋዊ መንገድ በደረሰኝ የተሸጡትም ቢሆኑ የሚገባው ተግባር ሳይፈጸምባቸው ለሌሎች አላማዎች ውለዋል፡፡
የአክሰስ ሪል እስቴት በሂሳብ ምርመራ አገልግሎት ኮርፖሬሽን ልዩ ኦዲት ተደርጎ የተገኘውን ሪፖርት መሰረት በማድረግም መረጃው እንደሚያመለክተው፤ ለቤት ግንባታ ሊውል ይገባ የነበረው አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ለተለያዩ የጥቅም ግንኙነት ላላቸው ድርጅቶች በብድር፣ ለግለሰቦችና ደንበኞች በተፈጸመ ክፍያ፣ ለቋሚ ንብረት ግዢ፣ ለስራ ተቋራጮች ቅድመ ክፍያ ፣ ለእርዳታና ስጦታ፣ ለአበልና ጉዞ በኮሚሽንና በመሳሰሉት ጉዳዮች ገንዘቡ ወጪ በመደረጉ ለታለመለት ዓላማ ሳይውል መቅረቱን ያመለክታል።
ቤት ሳይገነባ ሌሎች ድርጅቶችን እንዲያቋቁም መደረጉን አቤቱታ አቅራቢው ይጠቅሳሉ። አሁን በስራ ላይ የሌሉ ወይም በንግድ ሚኒስቴርና በከተማ አስተዳደሩ ሕጋዊ እውቅና የሌላቸው ድርጅቶችን በማቋቋምና ብድር በመስጠት በርካታ ገንዘብ ባክኗል ትልቁ የችግሩ መነሻም ሆኗል ይላሉ።
በሌላ በኩልም ችግሩን ለመፍጠር መንስኤው ትግበራው ዓላማውን ያለመከተሉ ነው። ቤት ለመገንባት የተፈጠረ ድርጅት ዓላማውን ወደ ጎን በመተው ሌሎች ድርጅቶችን በማቋቋም ስራ ላይ አሳልፏል። ከሌሎች ሰዎች ጋር በመሆን ላቋቋማቸው ድርጅቶች የባንክ ስራ የሆነውን ብድር በወለድ ጭምር የማበደርና ብድሮቹ ያለመመለሳቸውም በመጥቀስ እነዚህ ድርጊቶችም የተፈጸሙት ከ2000 ዓ.ም እስከ 2003 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ነው።
ቤት ገዢዎች ገንዘባቸውን በከፈሉ ከ 12 እስከ 24 ወራት ቤታቸውን ይረከባሉ ቢባልም በተገባው ውል መሰረት ርክክቡ ሊፈጸም አልቻለም። ይህን መፈጸም ባለመቻሉም የአክሰስ ሪል እስቴት አክሲዮን ማህበር መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ አገር ጥለው ሲወጡ ማኔጅመንቱም እንዲበተን ሆኗል።
ጠቅላላ ጉባኤ ተጠራ
የአቶ ኤርሚያስ ከአገር መውጣትን መረጃ የሰሙት ጥቂት ቤት ገዢዎች ተሰብስበው ወደቢሮ በመሄድ ካገኟቸው የማኔጅመንት አባላት ጋር በመነጋገር መፍትሄ እንዲሰጧቸው ወይም ከዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ጋር እንዲያገናኟቸው ጠይቀው የቦርድ አባላት ችግሩ በሰላማዊ መንገድ የሚፈታበትን መስመር እንዲዘረጋ ተስማሙ።
አቶ ሃምሳሉ፣ ወይዘሮ ትዕግስት፣ ኢንጂነር ታምራትና አቶ ተስፋዬ ለገሰ የተባሉትን የአክሰስ ሪል እስቴት የዳይሬክተሮች ቦርድን በፍቃደኝነት ከተሰባሰበው የቤት ገዢዎች ኮሚቴ ጋር በመገናኘት ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚጠሩ ቃል በመግባት የጋራ መፍትሄ ለመፈለግ ስምምነት ላይ ይደርሳሉ። ለሶስት ወራት ይህንን ሲሰሩ ቆይተው ሰኔ 09 ቀን 2005 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ ችግሩን ይፋ አደረጉ።
ችግሩ ቢፈጠርም አክሰስ ሪል እስቴት አክሲዮን ማህበር በቤት ገዢዎች ገንዘብ በርካታ ይዞታዎች እንዳሉት አስታውቀው ወደ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ቢሰበስብም አንድም ቤት እንዳልተገነባ ይፋ አደረጉ። ችግሩን መፍታት የሚቻለው ለመንግስት አቤቱታ በማቅረብ ድርጅቱ ሕጋዊ ማንነቱን ሳይለቅ መብታቸውን የሚያስከብሩበትን ጥያቄ በጋራ የማቅረብ ስራ ለመስራት ለቤት ገዢዎቹና ለጠቅላላ ጉባኤው ሃሳብ ቀረበ።
ሃሳቡ በሁለቱ ጠቅላላ ጉባኤዎች ተቀባይነት በማግኘቱ በቤት ገዢዎቹ እና በባለአክሲዮኖቹ እያንዳንዳቸው የስራ ማስኬጃ አምስት ሺ ብር እንዲያዋጡ ስምምነት ላይ ተደረሰ። በዚህም ስድስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ገደማ ተዋጣ። ሽያጭ ለተደረገለት 19 ሳይቶች ለእያንዳንዳቸው ኮሚቴ እንዲዋቀር እንዲሁም ለቤት ገዢው ተጠሪ የሚሆን አንድ አብይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራ እንዲጀመር ተወስኖ ተግባራዊ ሆነ።
ተግባራዊ እንቅስቃሴ
‹‹መንግስት ከአደጋ እንዲታደገን ስለመጠየቅ›› በሚል የመጀመሪያውን አቤቱታ ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በማቅረብ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ላሏቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ለመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት (አሁን የፈረሰ)፣ ለከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዳያስፖራ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት፣ በቀድሞ ስሙ በፍትህ ሚኒስቴር የዜጎች መብት ስነምግባር ክትትል ቡድን ለኦሮሚያ ክልል መንግስት ጽህፈት ቤት (ሁለት ይዞታዎችን ስለሚመለከት) ጣልቃ በመግባት ትብብርና ድጋፍ በማድረግ ከችግራቸው እንዲታደጓቸው ሚያዝያ 21 ቀን 2005 ዓ.ም አቤቱታ አቀረቡ።
በእዚህ ሂደት ምላሽ ባለማግኘታቸው ሰኔ 06 ቀን 2005 ዓ.ም ‹‹ላቀረብነው ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጥ ስለመማጸን›› በሚል ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ደብዳቤ አስገቡ። ህጋዊ ውክልና ተቀብሎ ስራ የጀመረው 19 አባላትን ያካተተው አብይ ኮሚቴ አቤቱታውን ማቅረብ ቀጠለ። ከኮሚቴው ጋር ለመስራት ፍቃደኛ የሆኑት የድርጅቱ የቦርድ አባላት ሁለት አዳዲስ የቦርድ አባላት አካተው ቢሮውን አጠናከሩ።
ያኔ በአክሰስ ሪል እስቴት አካውንት ውስጥ 129 (አንድ መቶ ሃያ ዘጠኝ) ብር ብቻ በመገኘቱ ለስድስት ወራት ደመወዝ ላላገኙት ሰራተኞችና የማኔጅመንት አባላት አዲስ ከተቋቋመው የዳይሬክተሮች ቦርድ በብድር መልክ ገንዘብ በመውሰድ ድርጅቱ ፈርሶ እንዳይቀርና ምላሽ የሚሰጥ አካል እንዳይጠፋ በማድረግ ቀዳሚውን ተግባር አከናወኑ።
በቤት ገዢው በኩል ያለው አቤቱታ ተጠናክሮ ቀጠለ ። በአክሲዮን ማህበራትና በሪል እስቴቱ የቀደመው ማኔጅመንት በፈጠረው የገንዘብ ብክነት የገጠመውን ችግር ምክንያት በማድረግ አቤቱታውን ለመንግስት ማቅረብ ጀመረ። ተከታትሎ የቀረበው አቤቱታ ጫና በመፍጠሩ ሰኔ 25 ቀን 2006 ዓ.ም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የከተማ ልማትና ቤቶች ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የሚመራ ዘጠኝ አባላት ያሉት አብይ ኮሚቴ አቋቁመው ስራው እንደተጀመረ ያመለክታሉ።
የመንግስት ጣልቃ ገብነትና የቀረቡ መፍትሄዎች
በአክሰስ ሪል እስቴት አክሲዮን ማህበርና በቤት ገዢዎቹ መካከል የተፈጠረውን ችግር አስመልክቶ የሁሉንም ወገኖች ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መንገድ የመፍትሄ ሃሳብ የሚያቀርብ አብይ ኮሚቴ እንዲቋቋም ይወሰናል። ጉዳዩ ተጣርቶ በሕግ አግባብ መወሰድ ያለባቸው እርምጃዎች እንዲወሰዱ፣ ተጠያቂ መሆን የሚገባቸው አካላት እንዲጠየቁ፣ ከሕግ አግባብ ውጭ የተወሰዱ እንቅስቃሴዎች ሁሉንም ወገን ባማከለ ሁኔታ እንዲስተካከሉና እርምት እንዲወሰድ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ይታዘዛል።
በተጨማሪም በሪል እስቴት አሰራርና በአክሲዮን ማህበራት አደረጃጀት ላይም የሚያጋጥሙ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት መወሰድ ስለሚገባቸው ሁኔታዎች የመፍትሄ አቅጣጫዎች እንዲቀርቡ ይወሰናል። ትእዛዙን እንዲተገብሩት በአባልነት ያካተታቸው የንግድ ሚኒስትር የነበሩትን አቶ ከበደ ጫኔን፣ የፍትህ ሚኒስትር የነበሩትን አቶ ጌታቸው አምባዬን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደዋኖ ከድርን፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል የነበሩትን አቶ አሰፋ አብዩ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ የነበሩትን አቶ አባተ ስጦታውን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትህ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ምትኩ ማዳ፣ ከአክሰስ ሪል እስቴት አክሲዮን ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ መኩሪያ ደጉን፣ ከቤት ገዢዎች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አክሎግ ስዩምንና በንግድ ሚኒስትር የሚኒስትር ዴኤታ አማካሪና የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኑረዲን መሀመድን ነበር።
ኮሚቴው ከድርጅቱ ጋር በተገናኘ የችግሩ መነሻና መንስኤውን ባጣራው መሰረት ስርዓት ያለመበጀቱ፣ በድርጅቱ ውስጥ የፋይናንስ የወጪና የገቢ ሂደቶች በአግባቡ አለመተግበራቸው፣ የተሰበሰበው ገንዘብ ዓላማውን ለሳቱ ጉዳዮች መዋሉ የችግሩ መነሻና መንስኤ መሆናቸውን ከሁለት ዓመታት ምርመራ በኋላ ሰኔ 08 ቀን 2008 ዓ.ም የአፈጻጸም ሪፖርት ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አቀረበ።
ያልተተገበሩት የቴክኒክ ኮሚቴው ዋና ዋና የውሳኔ ሀሳቦች
ችግሩ መፈጸሙ እና መንስኤውን የአፈጻጸም ሪፖርቱ ያረጋግጣል። የመፍትሄ አማራጮችን በመለየትም ለቀጣይ ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች ያስቀምጣል። በዋናነትም በሪል እስቴቱ ቤት ገዢዎች ህጋዊ ሆነው በማህበር እንዲደራጁ ይወሰናል። አክሲዮን ማህበሩ በሕግ አግባብ የሚፈርስበት መንገድ እንዲፈለግ እና መብቶቹ ለቤት ገዢዎቹ እንዲተላለፉ፣ የኩባንያውን የመሬት ይዞታዎች በሚመለከት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኩል በፍጥነት ወደ መሬት ባንክ እንዲገቡ፣ ግንባታ የተጀመረባቸው የመሬት ይዞታዎች ለግንባታው የወጣው ወጪ በመሀንዲሶች ተገምቶና የስራ ተቋራጮች ወጪ ተቀንሶ ወደፊት ለቤት ገዢዎቹ እንዲተላለፉ እንዲደረግና ለቀጣይ እርምጃ ወሳኝ የሆነው የኦዲት ስራ በተቻለ መጠን በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ውሳኔ ይቀርባል።
የችግሩ መነሻ መንስኤ የሆኑ ግለሰቦች የሂሳብ ምርመራ አገልግሎት ኮርፖሬሽን፣ በስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንና ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት ጋር በመቀናጀት የምርመራና የማጣራት ስራን አጠናቅቀው ተጠያቂ አካላትን
በዐቃቤ ህግ በኩል እንዲጠየቁ እንዲደረግ ይወሰናል። ቤት ሰሪዎችን በተመለከተም ለጊዜው ሁሉም በአንድ ማህበር ተደራጅተው መንቀሳቀሱ ተመራጭ መሆኑ ተሰምሮበታል። ግን በገቡት ውል መሰረት ገንዘብ ለከፈሉት ብቻ የከተማው አስተዳደር ከለሙትም ይሁን ካለሙት መሬቶች ወደፊት በሚደረጉ ቅንጅቶች መሰረት የቤት መስሪያ ቦታዎች የሚሰጥበት ሁኔታ እንዲመቻች የሚሉ የውሳኔ ሃሳቦች ቀርበዋል።
ሪል እስቴቱ በአክሲዮን ማህበራትና በዘርፍ ላይ የፈጠረው ችግር ታውቆ አስፈላጊው የእርምት እርምጃ ተወስዶበት መቀጠል ከቻለ እንዲቀጥል ካልቻለ ደግሞ ሕግና ስርዓቱን ተከትሎ የሚፈርስበት መንገድ እንዲፈጠርም ተወሰነ ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም በቀረበው የመፍትሔ አቅጣጫ መሰረት እያንዳንዱ ተቋም እንዲፈጽም መመሪያ ማስተላለፋቸውን ተከትሎ ሐምሌ 03 ቀን 2003 ዓ.ም ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ በልዩ ሁኔታ እንዲደራጁ ደብዳቤ ተጻፈ። ጥቅምት 03 ቀን 2009 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማት ማኔጅመንት የአክሰስ ሪል እስቴት የመሬት ይዞታዎችን በሚመለከት ለአስሩም ክፍለ ከተሞች ውሳኔው እንዲፈጸም ትእዛዝ ሰጠ።
ጉዳዮቹን የማስፈጸም ስራም ተጀመረ። ለከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር የአክሰስ ሪል እስቴትን በሚመለከት በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት እንዲተገበር ተጻፈ። የሽግግርን አገልግሎት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤትም ለአስሩ ክፍለ ከተሞች ከላይ በወረደው ትእዛዝ መሰረት እንዲያስፈጽሙ እና እንዲያስተገብሩ ጻፈ። ይሁን እንጂ ወደ ተግባር የሚቀይር አካል አልተገኘም ሲሉ በምሬት ይናገራሉ።
ከ2008 ዓ.ም ሰኔ ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶክተር) የሚመራው የለውጥ አመራር ወደ ሃላፊነት እስኪመጡ ድረስ አንዲትም ወደመሬት ጠብ ያለ ተግባር እንዳላዩም ቅሬታ አቅራቢዎቹ ያመለክታሉ። የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ ስለምንረዳ፣ ከእኛ በላይ የአገሪቱ ችግር ይበልጣል የሚል እምነት ስላለን ነገሮችን እየተመለከትን ቆየን። ስርዓትን በተከተለ መንገድ እንዲያልቅ ጥያቄያችን እንዲፈጸም የጠበቅነው ሳይሳካ አብይ አህመድ (ዶክተር) ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ ሲሉ ያስታውሳሉ።
ሚያዝያ 17 ቀን 2010 ዓ.ም ‹‹ውሳኔ ያጣው የአክሰስ ሪል እስቴት አክሲዮን ማህበር ቤት ገዢዎች በደልን መፍትሄ እንዲሰጡን ስለመጠየቅ›› በሚል የመጀመሪያ ጥያቄያቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ማቅረባቸውን ይጠቁማሉ። ምላሽ ሳያገኙ ሲዘገይባቸውም ድጋሚ የሚመለከታቸውን ተቋማት እየተመላለሱ የሚጠይቁት አቤቱታ አቅራቢዎቹ አዳዲስ ኃላፊዎች ወደ ኃላፊነት መምጣታቸውን ተከትሎ ለጉዳዩ አዲስ በመሆናቸው ጉዳያቸውን ለመገንዘብ ጊዜ እንዲሰጧቸው ይጠይቋቸዋል። ይህ ያሳሰባቸው ቤት ገዢዎች ወደጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በማምራት ጉዳዩን ሲያጣሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅጣጫ የሰጡበት የውሳኔ ደብዳቤ ግንቦት 13 ቀን 2010 ዓ.ም ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ወይዘሮ ደሚቱ ሃምቢሳ ለከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ መላኩን መረጃ ያገኛሉ።
ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት
ግንቦት 13 ቀን 2010 ዓ.ም ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተላከው ደብዳቤ የት ጠፋ?
ከንቲባ ጽህፈት ቤት ያመሩት የቤት ገዢዎቹ ለመዝገብ ቤት ደብዳቤያቸው ግንቦት 15 ቀን 2010 ዓ.ም መድረሱን ግንቦት 17 ቀን 2010 ዓ.ም ደግሞ ለከንቲባው መድረሱ ይነገራቸዋል። ወደ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ያመሩት አቤቱታ አቅራቢዎቹ ደብዳቤው እንዳልደረሰ ግን ቀጥታ ለከተማ ከንቲባው ገብቶ ሊሆን ስለሚችል እንዲያጣሩ ይነገሯቸዋል። ይህንኑ ሲያጣሩም እነርሱን የሚመለከት ምንም አይነት ደብዳቤ እንዳልደረሰ ይነገራቸዋል። (በእዚህ ጊዜ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አምባሳደር ድሪባ ኩማ ነበሩ) ። ከንቲባ ጽህፈት ቤት ሲያጣሩም የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ እንዲታገሱ ይነግሯቸዋል። ግን በሂደቱ አምባሳደር ድሪባ ኩማ የሹመት ጊዜያቸው በመጠናቀቁ ለምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ኃላፊነቱን ያስረክባሉ፤ ጉዳዩን ያውቁት የነበሩት የጽህፈት ቤት ኃላፊውም አቶ ይመኑ ተነስተው በአቶ ዘመዴነህ ይተካሉ ጉዳዩም ለተተኪዎቹ አመራሮች አዲስ ይሆናል።
ጉዳዩን አዲስ ለተተኩት ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) እንድናቀርብ ታዘዝን ይላሉ አቤት ባዮቹ። የካቲት 2011 ዓ.ም በደብዳቤ እንዳቀረቡም በመጥቀስ፤ የከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊና ምክትል ኃላፊ እንዳነጋገሯቸውም ነው የሚጠቅሱት። ደብዳቤው ሊገኝ እንዳልቻለ፣ እየተጓተተ ረጅም ጊዜ መቆየቱን ይህም በመንግስት ጭምር እንደሚታወቅ ይነግሯቸዋል። በቢሮ እድሳት ምክንያት ሊጠፋ እንደሚችል በመግለጽም ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የደብዳቤውን ኮፒ ዳግም እንዲልክላቸው አቤት እንዲሉ ይገልጹላቸዋል። እነርሱም ለምክትል ከንቲባው ጉዳዩን እንደሚያቀርቡም ያረጋግጡላቸዋል።
ቤት ገዢዎቹም ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ቢሮ የተላከው ደብዳቤ መጥፋቱን በመግለጽ ድጋሚ ቅሬታ ያሰማሉ። ቤት ገዢዎቹ እየተንገላቱ መሆኑን በመግለጽም እንግልቱንና ምላሽ መነፈጉን ከግምት በማስገባት አስቸጋሪ ቢሆንም የደብዳቤው ቅጂ በድጋሚ እንዲላክ ሲሉ ጥቅምት 10 ቀን 2012 ዓ.ም ዳግመኛ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ቢያመለክቱም ምላሽ አላገኙም።
ቤት ገዢዎቹ በራሳቸው ሂደት ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለን ቀጠሮ አስይዘው ገብተው አነጋገሩ። ለምክትል ከንቲባው ጉዳዩን በዝርዝር አስረዱ። ኢንጂነር ታከለ ጉዳዩን በእዚህ ደረጃ እንደማያውቁት ገልጸው፤ ግን በአገር አቀፍ ደረጃ የነበሩ የሪል እስቴል ችግሮችን ኮሚቴ አዋቅረው መፍታታቸውን ይነግሯቸዋል። ጉዳዩ በእርሳቸው ሳይሆን በፌዴራል ደረጃ ሊፈታ የሚገባው መሆኑን ተገንዝበው እንደነበር ይገልጹላቸዋል። ሆኖም በውይይታቸው ጉዳዩ ከማህበራት ማደራጀት፣ የመሬት ጥያቄን የመወሰንና የሪል እስቴቱን ጉዳይ የመጠየቅ የከተማው መሆኑን እየገለጻችሁ ነው። ይህንን አሁን መመለስ አልችልም። ከሚመለከታቸው የቢሮ ኃላፊዎች ጋር ተነጋግሬ ጥቅምት ወር 2012 ዓ.ም መጨረሻ አሳውቃለሁ አሉ።
ህዳር 01 ቀን 2012 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ዐቃቤ ህግ ለሆኑት አቶ ሞሊቶ አባይነህ ጉዳዩ እንደተመራላቸው የሚገልጹት አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ በአካል ቀርበው ጉዳዩን በዝርዝር ያስረዷቸዋል። ጉዳዩ በጣም አጽንኦት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑንና ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) በአግባቡ ሊያውቁት የሚገባ መሆኑን ይገልጹና ማስረጃዎቻቸውን አደራጅተው እንዲሰጧቸው በመግባባት ይለያያሉ። ግን ምላሽ ሊያገኙ አልቻሉም። ሰነዱን ወደጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ቢልኩትም፤ ጉዳዩን ወደ አዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ይመልሰዋል። የከተማው የከንቲባ ጽህፈት ቤትም በአጀንዳነት እንዲታይ አቅጣጫ መሰጠቱን ምክትል ዐቃቤ ህግ አቶ ሞሊቶ መረጃውን እንደነገሯቸው ይገልጻሉ።
የቤት ገዢዎቹ የተፈጠረባቸው ስጋትና ጫና
እንደ አቶ አክሎግ አብዛኞቹ ቤት ገዢዎች ስጋት ገብቷቸዋል። አሁን ምርጫም እየደረሰ በመሆኑ ጉዳያችንን የሚያይልን አይኖርም እስከመቼ እንታገሳለን ? በማለት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እናሳውቅ በማለት የስጋትና የተስፋ መቁረጥ ደረጃ ላይ የደረሱ አሉ ሲሉ ያብራራሉ።
በእዚሁ መሃል ፍርድ ቤቶች በእኛ ገንዘብ የተገዙ መሬቶችን በሃራጅ እንዲሸጡ፣ አጥሩ እየተገነጠለ ችግኝ እየተተከለበትና ለተለያየ ዓላማ እየዋለ ነው። ካርታ ያለው በአክሰስ ሪል እስቴት ስም የተመዘገበ 89 ሰዎች ወደ 220 ሚሊዮን ብር የከፈሉበትና ጉዳዩ ወደመሬት ባንክ በአደራ ገብቶ የተቀመጠ ይዞታ ሌላ ተግባር ላይ መዋሉ ትክክል እንዳልሆነ በመቃወም ለወረዳው፣ ለክፍለ ከተማው መሬትና ማኔጅመንት ጽህፈት ቤትና ለዋና ስራ አስፈጻሚው በደረጃ ቅሬታ አቀረብን ይላሉ አቶ አክሎግ። ሆኖም ምላሽ ሊሰጣቸው እንዳልቻለም ይናገራሉ።
ለከንቲባ አስተዳደር ጽህፈት ቤት አቤት አሉ። ምላሽ ጠፋ። በአደራ የተያዙ ይዞታዎች በመሆናቸው በፍርድ ቤት እንዲታገዱ ማድረጋቸውን ይጠቅሳሉ። እግድ መኖሩን ያረጋገጠው የከተማ አስተዳደሩም አስተዳደራዊ መፍትሄ እስኪሰጠው እንደሚታገስ ይገልጻል። ሆኖም በሌላ ገጽታው ደግሞ በቤት ገዢዎቹ ላይ ስጋት አዘለ። ተስፋ መቁረጥም አሳደረ።
በመሆኑም ቤት ገዢዎቹ ጥር 20 ቀን 2012 ዓ.ም ‹‹የቅሬታና የአቤቱታ መርሀ ግብር›› አዘጋጅተው ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አቀረቡ። በእለቱም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቅሬታና አቤቱታ ዳይሬክቶሬት ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች የቤት ገዢዎቹን ተወካዮች አስገብተው ያነጋግሯቸዋል። ጉዳያቸው ባግባቡ እንደሚታወቅ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ (ዶክተር) አቅጣጫ እንደሰጡበት አስታወሷቸው። መፍትሄ ማግኘት እንደነበረባቸው መዘግየቱ ተገቢ እንዳልሆነም አስረዷቸው። ስጋት እንዲያድርባቸው ያደረገውን ይዞታዎቹን ለሌላ ዓላማ እንዲውሉ መደረግና ተያያዥ አቤቱታቸውን አቀረቡ።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያገኙት ምላሽ
አጠቃላይ የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ እሳት የማጥፋት ስራ ለመስራት እንዳስገደዳቸው በመግለጽ ችግራቸውን በቶሎ አለመፈታቱ ስህተት መሆኑን በማመን መንግስት ጉዳዩን ለመፍታት ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑ ተገልጾላቸዋል። አቤቱታው ምላሽ አለማግኘቱ እንዳሳሰባችሁ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሚመለከታቸው ኃላፊዎች በጽሁፍ በማቅረብ በአንድ ሳምንት ውስጥ ምላሹን እንደሚያሳውቋቸው ይነግሯቸዋል።
የሚጠይቁት ፍትህ
የአክሰስ ሪል እስቴት ቤት ገዢዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያቀረቡት አቤቱታ እንዲተገበር ይጠይቃሉ። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የቴክኒክ ኮሚቴ በማቋቋም ጉዳዩ ተጣርቶ ለችግሩ መፍትሄ ይሆናሉ ተብለው የቀረቡ ምክረ ሃሳቦቹ ፍሬ አፍርተው ወደሚመለከታቸው ቢሮዎች ተልኮ በአፈጻጸም ሪፖርት የተወሰኑ ውሳኔዎች እንዲፈጸሙም ይጠይቃሉ።
‹‹የዘገየ ፍትህ እንደተነፈገ ይቆጠራል›› እንደሚባለው ከዛሬ ዘጠኝ ዓመት በፊት የገዛነው ቤት ተሰርቶ ቢሆን፣ ዛሬ ከፍተኛ ዋጋ ይኖረው ነበረ ሲሉ በቁጭት ይናገራሉ። መንግስት ትኩረት በሰጠው ልክ ሊፈታ ባለመቻሉ ቤቱን ብንገነባ ከእዛን ጊዜው የበለጠ በአራትና በአምስት መቶ በመቶ እጥፍ ማውጣት ይጠበቅብናል ይላሉ። ከ900 መቶ ሺ ብር እስከ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር አውጥተው እንደነበረ አስታውሰው፤ ወደፊት ለመገንባት እንኳን ከኪሳችን ገንዘብ ለማውጣት እንገደዳለን ይላሉ። አሁንም ጉዳዩ ከእዚህ በላይ ከዘገየ ቤት ገዢው መገንባት የማይችልበት ደረጃ ላይ ይደርሳል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ። ጉዳዩ በመንግስት በተሰጠው ትኩረት ልክ ፈጣን እልባት እንዲሰጠው ፍላጎት አለን ባይ ናቸው።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ፈጣን ፍትህ እንዲሰጥ የምንፈልግበት ምክንያት አንዳንድ ቤት ገዢዎች ከዚህ አለም በሞት እየተለዩ ብዙዎች የውርስ ወረቀት እያስገቡ ነው ። ትናንት አብረውን የነበሩ ዛሬ በሕይወት የሉም በማለት ይማጸናሉ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቅሬታና አቤቱታ ዳይሬክቶሬት
አክሰስ ሪል እስቴት አክሲዮን ማህበር ቤት ገዢዎች የተወከሉት አባላት ቅሬታቸውን ለሚመለከታቸው ኃላፊዎች አቅርበው መነጋገራቸውን ሰምተናል። ጉዳዩ በቅሬታና አቤቱታ ዳይሬክተር ደረጃ የሚወሰን ባለመሆኑ የበላይ አካል የወሰነው ለቅሬታና አቤቱታ ዳይሬክቶሬት ሊወርድ ይችላል አለበለዛ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንደሚነጋገር ይጠበቃል።
የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል የቴክኒክ ኮሚቴው ሁለት ዓመታት ፈጅቶ ባቀረበው የውሳኔ ሃሳብ መሰረት ፖለቲካዊ፣ ህጋዊና አስተዳደራዊ ውሳኔ በመወሰን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጉዳዩን መቋጨት ያስፈልጋል እንላለን።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 27/2012
ዘላለም ግዛው