አራት መስቀልያ መንገዶች ተጋጥመው ስያሜውን ያገኘው አራት ኪሎ ለብዙ ሀገራዊ፣ ታሪካዊና ማሕበራዊ ጉዳዮች እምብርት ነው። የፖለቲካ፣ የትምህርት፣ የሃይማኖት፣ የታሪክ ዕሴቶች የተሰባሰቡበት አራት ኪሎ ከስሙ በላይ ይዘቱ ከፍ ብሎ ከመግዘፉ የተነሳ የአካባቢዎች ሁሉ ቁንጮ ለመሆን በቅቷል ብንል ገለጻችንን ያሳጥር ይመስለናል። በአራት ኪሎ መሃል ላይ የቆመውን የሚያዝያ 27ን የድል ሐውልት ብቻ መዘን ታሪካዊ ፋይዳውን ብንመረምር ብዙ ማለት ይቻላል።
የሐውልቱ ጉዳይ ከዛሬው ርዕሰ ነገር ጋር እጅግም ስላልተቆራኘ ጊዜና ዐውዱ ሲፈቅድ እንደገና እንመለስበታለን።ቢሆንም ግን ከታሪካዊው ቋሚ መዘክር ጋር የሚጣቀሰው የትምህርት ሚኒስቴር ህንጻ፣ ከፍ ብለው የሚገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክህነትና መንበረ ፓትርያርክ፣ የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤትና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሳይንስ ፋኩልቲ ከሀገሪቱ ነባርና ዘመናዊ የትምህርት ታሪክ ጋር ያላቸውን መስተጋብርና ትርጉም ጠቅሼ የማልፈው አንኳር ጥቁምታ በመስጠት ብቻ ይሆናል። አራት ኪሎ ማለት ይሄም ነው። ከሐውልቱ በቅርብ ርቀት በስተ ምእራብ በኩል ያሉት የሀገሪቱ አንጋፋ ማተሚያ ቤትና የፕሬስ ድርጅትም የአራት ኪሎን ድባብ ያገዝፉታል።
ከሐውልቱ ዝቅ ብለው የሚገኙት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት፣ የምኒልክና የኢዮቤልዩ ሁለት ታላላቅ አብያተ መንግሥታት የያዟቸው የታሪክና የፖለቲካ ቅርሶች እንደሚገባ ይፋ ስላልሆኑ ውበታቸውና ፋይዳቸው እጅግም ጎልቶ አይታወቅም። በአዲሱ የሪፎርም ሥርዓት ማግሥት ብልጭ ማለት የጀመሩት አንድነት ፓርክን የመሳሰሉ እንቅስቃሴዎች እንደታቀደላቸው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቀው ለድምድማት ሲበቁ ብዕሬ በዝርዝር ስለሚዳስሳቸው እስከዚያው በቀጠሮ ይደር ማስተላለፉን መርጫለሁ። ለእስካሁኑ መንግሥታዊ ጥረት ግን አመስግኖ ማበረታታቱ ተገቢ እንደሆነ አምናለሁ። አራት ኪሎ የሠፈር ስም ብቻ አይደለም የሚባለውም ስለዚሁ ነው።
በዋነኛነት በዚህ ጽሑፍ ለመዳሰስ የሚሞከረው ከላይ በተዘረዘሩት ታላላቅ ተቋማት መካከል ከፍ ብሎና ሞገስ ተላብሶ በተምሳሌትነት ስለቆመውና ወደ አንድ ክፍለ ዘመን ዕድሜ እየተንደረደረ ስላለው የአራት ኪሎው ፓርላማችን አንድ ክፍል ይሆናል። በትልቅ ማማ ላይ ስለተሰቀለውና ካሸለበ ዓመታት ስላስቆጠረው ታሪካዊ ሰዓት (Clock Tower)።
ያለመታደል ሆኖ ለታሪክ አጠባበቅና እንክብካቤ ያለን ዝቅ ያለ ሀገራዊ ክብርና በእጃችን ያሉትን የታሪክ ቅርሶች ለማካፈል የምናሳየው ንፍገት ብዙውን ጊዜ ለቅርሶቻችን ክብር እንዳንሰጥና እንድንታወር ምክንያት ሆኖናል። ከአናታቸው በላይ አንቀላፍቶ ስላሸለበው የፓርላማው ሰዓት ጉዳይ በተመለከተ “የሕዝብ ተወካዮቹ” ለምን እንደቆመ ምክንያቱን ጠይቀውና አስጠይቀው ስለመሆኑ በግሌ እጠራጠራለሁ። ከእኛ ወጥተው እንደኛው ስለመሆናቸው ግን አልፈርድባቸውም።
የእግረ መንገድ ትዝብቴን ወርውሬ ልለፍ። ከጥቂት ዓመታት በፊት መለስተኛ ጥናት ለማድረግ ፈልጌ የፓርላማውን ቤተ መጻህፍት ለተወሰኑ ሰዓታት ንባብ እንዲፈቅዱልኝ የጠየቅኋቸው አንድ ሹም እንደምን እንደገላመጡኝና እንዳበሻቀጡኝ ሳስበው ለእኔ ሳይሆን ለእርሳቸው ሥነ ምግባር አፍርላቸዋለሁ። ለነገሩ እንዴት የፓርላማችን ቤተ መጻሕፍት በአንድ ተራ ዜጋ ለንባብ ጥያቄ ሊቀርብ ቻለ በሚል ስሜት እንዳበሻቀጡኝ ገብቶኛል። ለምን አይፈቀድልኝም ብዬ ክርክር ብገጥም ዱላና እስር ሊከተል እንደሚችል ከምክንያት አልባ ቁጣቸው ስለተረዳሁ የተለየኋቸው አንድ የግል ተሞክሮዬ ትዝ እያለኝ ነበር። “ምነው ለእኒህ ሹም መንግሥት ፈቃድ ሰጥቷቸው የታላቋን አሜሪካ ኮንግረስ ቤተ መጻሕፍት የእንግዶች መስተንግዶ አይተው እንዲማሩ በላኳቸው” የሚል። ይህንን ውሎ ያደረ የግል ቅሬታዬን በቅርቡ ለክብርት የጽሕፈት ቤት ኃላፊዋ እንደ ቀልድ ጣል አድርጌላቸው ስለተፈጸመው ስህተት ማዘናቸውን ከገጽታቸውም ከንግግራቸውም ተረድቻለሁ።
ርዕሰ ነገሬን በግል ተሞክሮ ላዋዛው። ምናልባትም ብዕሬ በቁጭት እየተብከነከነ ይህንን ጉዳይ ጫን አድርጎ ለመዳሰስ የፈለገው የትዝታው አደራ ክብደት ተጭኖት ስለመሆኑ ጥሩ ማሳያ ሊሆን ይችላል። ጸሐፊው ነፍስ ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬው የጉልምስና ዕድሜው ከአራት ኪሎ አካባቢ ተለይቶ አያውቅም። አራት ኪሎና ማንነቱ በሚገባ የተሸረበው በፍቅር ነው። በታዳጊነት የልጅነት ዕድሜው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው ፓርላማውን ተጎራብቶ ይገኝ በነበረው የቀድሞው ወወክማ (ወጣቶች ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር) ይባል በነበረው ዝነኛ የስፖርትና የትምህርት ማዕከል ውስጥ ነበር።
ዛሬ የጥንቱ ወወክማ ስሙን በማይመጥን ተግባር አዘቅዝቆ ሕጻናትና ወጣቶች ቴያትር በሚል መታወቂያ መጠራቱ ታሪኩን ለሚያውቅ እኔን መሰል ሰው ያሸማቅቃል። “ዕድሜ ለደርግ መንግሥት” እልፍ አእላፍት ዝነኛ ስፖርተኞችና የቀለም ተማሪዎች መፍለቂያ የነበረው ያንን ታላቅ ምንጭ በአንድ ገጽ ቀላጤ አዳፍኖ መሄዱ በታሪክ ፊት እንዳስወገዘውና እንዳስነቀፈው ይኖራል። ሥልጣን የጨበጠው የዛሬው መንግሥት ታሪኩን መርምሮ ዘር፣ ቋንቋና ሃይማኖት ሳይለይ ታላላቅ ስፖርተኞችንና ምሁራንን ያፈራውን ይህንን ተቋም ለባለቤቶቹ ቢመልስ በእጅጉ ያስከብረዋል፤ ያስመሰግነዋልም።
የጸሐፊው የመለስተኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የነበረውም እንዲሁ የአራት ኪሎው ዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት፣ ለሦስተኛ ደረጃ ትምህርቱ የተቀበለውም የአራት ኪሎ ተጎራባቹ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ከምረቃ በኋላ የመጀመሪያ የእንጀራው መስሪያ ቤት አራት ኪሎ የሚገኘው አንጋፋው ማተሚያ ቤት ሲሆን ከዓመታት በኋላም ዛሬም ድረስ የጸሐፊው የዕለት እንጀራ ቢሮው አድራሻ በፓርላማው ትይዩ በሚገኘው ታሪካዊ ሕንጻ ውስጥ ነው። ከዚህ የበለጠ ፍቅር ከየት ይገኛል።
በዚህ ረጂም የአራት ኪሎ ቤተኛነቱ ከጸሐፊው ትዝታ በፍጹም ሊደበዝዝ ያልቻለው በየሩብ ሰዓቱ ይደወል የነበረው የፓርላማው የሰዓት ማንቂያ ነው። ከልጅነት እስከ እውቀት እንደ ጥዑም ሙዚቃ ሲያዳምጥ የኖረው የዚያ የፓርላማ የሰዓት ድምጽ ዛሬ ደቂቃና ሰዓት ቆጣሪዎቹ አሸልበው ካንቀላፉ ዓመታት ተቆጥረዋል። በየሩብ ሰዓቱ የሚደመጠው የድምጹ ልሳን ከአራት ኪሎ አየር ላይ ከጠፋም ሰነባብቷል። በቅርብ ወራት ውስጥ ለጥቂት ቀናት ያህል ድምጹን ሰምተን መደሰት እንደጀመርን ውሎ ሳያድር እንደገና ድርግም ብሎ ጠፍቶ ወደ ቀድሞው እንቅልፉ መመለሱን እናስታውሳለን።
የፓርላማው ሰዓት ለአድማጩና ለተመልካቹ ብዙ ፋይዳ ነበረው። የአካባቢው ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶችና ነዋሪዎች በሰዓቱ ድምጽ መቀስቀስ ብቻ ሳይሆን ንቁ አእምሮ እንዲኖራቸው፣ ለሰዓት አከባበር ያላቸው ከበሬታም ከፍ እንዲል አስተዋጽኦው ቀላል አልነበረም። ብዙዎች ከእጃቸው ሰዓትና በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ላይ ከሚገኘው ሰዓት ቆጣሪ ይልቅ በእጅጉ የሚታመነው የፓርላማው ሰዓት ነበር። ለሕዝብ ተወካዮቹም ሳይቀር በስብሰባ ላይ ድካምና መጫጫን ሲያጋጥማቸው ለማንቃትና የኃላፊነታቸው ማሳሰቢያ የኅሊና ተምሳሌትም ነበር ብንል ማጋነን አይሆንም። እኒህ የተዘረዘሩት ገር ሃሳቦች ሲሆኑ መረር የሚል ትርጉሙን በተመለከተ ግን እንመለስበታለን።
ከጥቂት ዓመታት በፊት አንዳንድ ነዋሪዎች ኢህአዴግ መቶ ፐርሰንት ያሸነፈበት ፓርላማ የእንቅልፍ አዚም ወድቆበት ሰዓታችንንም እንቅልፍ ላይ ጣሉብን እየተባለ በግልጽና በለሆሳስ ይታማ ነበር። ለክፋቱ ደግሞ በቴሌቪዥን መስኮታችን ብዙውን ጊዜ ኢቲቪ በሸለብታ የቀን ህልም ላይ የነበሩ በርካታ ወንበረተኞችን ደጋግሞ ያሳየን ስለነበር ሃሜታችን እውነትነት ነበረው። ሰዓቱ ቢቆም አይፈረድበትም እንባባልም ነበር። ዛሬም ቢሆን የዘመነ ኢህአዴጉ ፓርላማ ተልዕኮውን ሊያጠናቅቅ ዳር ዳር በሚልበት ወቅት ያሸለበውን ሰዓታችንን ቀስቅሶ ቢሰናበት ሊያስመሰግነው ይችላል ባይ ነን።
በመሠረቱ ያሸለበው የፓርላማ ሰዓታችን ከእንቅልፉ ይንቃ ብለን የምንሟገተው ትርጉሙ ብዙ ስለሆነ ነው። እርግጥ ነው የእጅ ሰዓት ዛሬ ዛሬ ለማንም ሰው ብርቅና ድንቅ አይደለም። ሴኮና ሮመር እንደ ትናንቱ የክብር መገለጫ መሆናቸው ቀርቷል። “ሰዓት ስንት ነው?” ብሎ አላፊ አግዳሚውን እያስቆሙ መጠየቅም ፋሽኑ አልፎበታል። እድሜ ለእጅ ስልካችን። የፓርላማውን ሰዓት አሰናክለው ያቆሙት ይህንን ምክንያት አስበው ከሆነ ትልቅና ታሪካዊ ስህተት ነው። “አካባቢውን በድምጹ ከሚረብሽ ብለን ነው” በማለት ተመካክረው ከሆነም “በሕግ አምላክ! የፓርላማችን ሰዓት ትርጉሙ ቀላል አይደለም!” እያልን በፀሐይ ፊት እንሞግታቸዋለን። በበርካታ ሀገራት የሚገኙ መሰል በፓርላማ አናት ላይ የቆሙ ሰዓቶች መኖራቸውን እያጣቀስን እንከራከራቸዋለን።
በላ ልበልሃችንን የሌሎች ሀገራት ምሳሌዎችን እያጣቀስን ሙግቱን እንጀምር። በቅጽል ስሙ “Big Ben” በመባል የሚታወቀው የታላቋ እንግሊዝ የዌስት ሚኒስቴር ፓርላማዋ አናት የተሸከመው አስራ ሦስት ቶን የሚመዝን የማማ ላይ ሰዓት ነው። ከመቶ ስልሳ ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ይሄ የፓርላማ ሰዓት ዛሬም ሕያው ነው። እንደ እኛ ሀገር አልተኛም አላንቀላፋም። በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚታዩት ሰዓቶች ለለንደንና ለአካባቢው ነዋሪዎች ትርጉማቸው ከፍ ያለ ስለሆነ በየሩብ ሰዓቱ ከሚያሰሙት ድምጽ ታቅበው አያውቁም። “ጌታ ሆይ! ቀዳማዊት ንግሥት ቪክቶሪያን በሰላም ጠብቅ!” የሚለው ጸሎት ከበስተ ግርጌው የተጻፈለት ኤልሳቤጣዊ የማማ ሰዓት ለእንግሊዝ ዜጎች የኩራታቸው አንዱ መገለጫ ስለሆነ ደውሉ የሚደመጠው በኩራት ነው።
በካናዳ ኦታዋ ፓርላማ ሕንጻ አናት ላይ በሚገኘው የ93 ዓመቱ የሰላም ማማ (Peace Tower) አናት ላይ የተሰቀለው ሰዓትም እንዲሁ ከሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ቀጥሎ ዜጎቹ የሚኮሩበት ትልቁ ቅርሳቸው ነው። ሰዓቱን ለካናዳ መንግሥት በስጦታ ያበረከተቸው ታላቋ እንግሊዝ መሆኗን የሚናገሩትም ጅንን እያሉ ነው። በየሩብ ሰዓት የሚደመጠውን ሰዓት ካናዳዊያን ሲያደምጡ በፈገግታ ነው እየተባለም ይነገራል።
በበርካታ ሀገራት የፓርላማ አናቶች ላይ ከቆሙት የማማ ሰዓቶች በተጨማሪም ብዙ ታላላቅ የዓለማችን ከተሞች ከፍ ባሉ ማማዎች ላይ የተሰቀሉ ሰዓቶች (Clock Towers) እንዳሏቸው ይታወቃል። ምክንያቱን በሚገባ ባልረዳውም የብዙዎቹ ሀገራት ሰዓቶች የማንቂያ ደውላቸው የሚሰማው በየሩብ ሰዓቱ ነው። ለአብነት ያህልም በሳውዲ አረቢያ ከተማ በመካ የቆመው የዓለማችን ትልቁ የማማ ሰዓት፣ የዱባዩ ዲያራ፣ የህንዱ ከተማ የሙምባይ ራጃባይ፣ የኢጣሊያ ከተማዋ የቬነስ ቅዱስ ማርቆስ፣ በቤልጅዬሙ ከተማ በሊር የቆመው ዚመር፣ የሙኒክ ጀርመኑ ኒው ታውን ሆል፣ የሜሪላንዱ ብሮም ሲልተዘር አርትስ ታወር ላይ የተሰቀሉትን ግዙፍ የማማ ላይ ሰዓቶች መዘርዘር ይቻላል።
በተለይ በፓርላማዎች አናት ላይ በሚገኙ ማማዎች ላይ ተሰቅለው ደውላቸውን የሚያሰሙ ሰዓቶች በየሀገራቱ የከበረ ትርጉም እንዳላቸው ደጋግመን አንስተናል። በብዙ ሀገራት ሰዓቶቹ የየሀገራቱን ነፃና ሉዓላዊ የመንግሥትነት ክብርና የነፃነታቸውን ዘላለማዊ ቀጣይነት ያመለክታል ብለው ስለሚያምኑ ለሰዓቶቹ ያላቸው ክብር ከፍ ያለ ነው። ሰዓቶቹ እድሳት አስፈልጓቸው ለተወሰኑ ሳምንታት እና ወራት ሥራቸውን ሲያቋርጡ እንኳ ዜጎችና ቱሪስቶች ይቅርታ እየተጠየቁ በቅድሚያ እንዲያውቁት ይደረጋል። የእድሳት ጊዜያቱም ምን ያህል ቀናት እንደሚፈጅ በግልጽ ይነገራል። እንዳመቻቸው ሰዓቶቹን አያቆሟቸውም። ለምን ቢሉ በሰዓቶቹ ደውል ውስጥ የሚተላለፉት መልዕክቶች ትርጉማቸው በቀላሉ “የሰዓት ጩኸት” ብቻ ተደርጎ ስለማይቆጠር።
ወደራሳችን ጉዳይ እናቅና። የእኛ የፓርላማ ሰዓት የቆመው በማን ትዕዛዝና ሥልጣን ነው? የቆመበት ምክንያቱስ ምንድን ነው? ሰዓቱ ድምጹን አጥፍቶ ሲያንቀላፋ “ለምን?” ብለው የጠየቁ ወንበረተኞች አልነበሩም ወይስ ግድ አልሰጣቸውም። የሚዲያ ተቋማትስ የፓርላማው ሰዓታችን ለምን አንቀላፍቶ እንደተኛ ጠይቀውና ሞግተው ያውቃሉ? የዘመነ ኢህአዴግ ፓርላማውን እንኳ ለጊዜው ትተነው በዘመነ ብልጽግና ፓርቲ የፓርላማው ሰዓት ተቀስቅሶ የሕዝብ ተወካዮቹንም ሆነ እኛን ተራ ዜጎች እንዲቀሰቅሰን እምነት አሳድረናልና የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ! መልዕክታችን ነው። ሰላም ይሁን!!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 27/2012
የትናየት ፈሩ