‹‹ … ስድስት ወር፣ አመትም ይሁን ሁለት አመት ከዚያ በኋላ የተሟላ ሰላም ይፈጠራል ብሎ መናገር የሚያስችል ምንም መሰረት የለም። ከችግር ነፃ የሆነ ጊዜም የለም። ምርጫው ዛሬም ሆነ ነገ ቢደረግ መልኩ ይለያያል እንጂ ችግር አለ፤ ያ ችግር እንዴት ይፈታ ለሚለው ምክር ቤት ምርጫ ቦርድን በማገዝ፣ ፓርቲዎች በፈረሙት ሰነድ ልክ በዲሲፕሊን ተገዝተው ተባባሪ በመሆን፣ ዜጎች ምርጫው ድምፅ ማሰሚያ እንጂ መገዳደያ እንዳይሆን ጥበቃ በማድረግ፣ መንግስት አስፈላጊውን ሎጀስቲክስ፣ ጥበቃና ድጋፍ በማድረግና ሁሉም ባለድርሻ ከተባበረ ምርጫው ፈታኝ ቢሆንም ሊሳካ ይችላል›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ ልዩ ስብሰባ ተገኝተው ምርጫን በተመለከተ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች የሰጡት ምላሽ ነበር።
በርግጥም ተስፋ እና ስጋት ባንዣበበበት በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ መፃዒ የዴሞክራሲ ሂደት እጣ-ፈንታ ላይ ከሚወስኑ ኹነቶች ቀዳሚው ከፊት ለፊታችን እየጠበቀን የሚገኘው ምርጫ ዋነኛው ነው።ምርጫ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ህዝብን በመወከል ውሳኔ የሚያሳልፉ ወኪሎችን የመምረጥ ሂደትን የሚመለከት ሲሆን፤ ሃሳብን በነፃነት መግለፅ የሚያስችል፣ በታቀደለት ጊዜ የሚከናወን፣ ነፃና ፍትሃዊነት የተላበሰ የዴሞክራሲ መገለጫ ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ የሚካተት ነው።
ከዚህ ቀደም በአገሪቱ በተከታታይ በተካሄዱ አምስት ምርጫዎች ‹‹የሕዝቡ ድምፅ ሲነጠቅና ለገዢው ፓርቲ ሲሰጥ ቆይቷል›› የሚሉ ክሶች በተደጋጋሚ ተደምጠዋል። በዘንድሮ ምርጫ የዚህ አይነት ክስ መከሰት የለበትም። የምርጫው ሂደት ሰላማዊ፣ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና ተአማኒ መሆን አለበት። የለውጥ አካል የሆነው ኢህአዴግ በአገሪቱ እውነተኛ የዴሞክራሲ ሥርአት እንዲሰፍን ባሳየው ቁርጠኛነት የነበረውን ስርዓት አኩርፈው ከአገር የተሰደዱ፣ ለትጥቅ ትግል በረሀ የገቡና ከፖለቲካ ተሳትፎ ውጭ የሆኑትን ሁሉ በአገራቸው የዴሞክራሲ ስርዓት ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሰላማዊ ጥሪ በማድረግ ምቹ ሁኔታን መፍጠሩ ይታወቃል።ይህ ምቹ ሁኔታ ዘንድሮ ለሚካሄደው ምርጫ እጅግ ጠቃሚ በመሆኑ ሁሉም ሊጠቀምበት ይገባል።
ይህንን የመንግሥት የሰላም ጥሪ በመቀበል በአገር ቤት የከተሙት አንዳንድ የፖለቲካ ሃይሎች ቀደም ሲል የነበረባቸውን እንግልትና መሳደድ ዘንግተው ይሁን አውቀው ለመጪው ምርጫ ለአገር ሠላምና ለሕዝብ ደህንነት በሚበጅ መልኩ እየተንቀሳቀሱ ስላልሆነ ብዙዎችን የሚያሳስብ ጉዳይ ሆኗል። ስለሆነም ምርጫውን ሰላማዊ በማድረግ ረገድ የሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች እና የመላው ህዝብ የጋራ ጥረት ይጠይቃል።ስለዚህ ሁሉም የተሳካ ምርጫ እንዲካሄድ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።
መንግሥት ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ተግባራዊ መሆን የገባውን ቃል በመጠበቅ የምርጫ ቦርድን እንደገና በማዋቀር፣ የተሻሻለ የምርጫ ሕግ በማውጣትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ሊካሄድ ይገባል የተባለው ምርጫ እንደሚከናወን ቁርጠኝነቱን አሳይቷል።ነገር ግን አንዳንድ ፓርቲዎች ምርጫውን ለማካሄድ የሚቻልበት ሁኔታ የለም ሲሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ምርጫው የግድ መካሄድ አለበት እያሉ ነው። ነገር ግን ምርጫው በተያዘለት ግዜ ማካሄድ ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ በመሆኑ ምርጫውን ለማካሄድ ምርጫ ቦርድ ጊዜያዊ የጊዜ ሰሌዳ አውጥቷል።ስለሆነም የምርጫ ተዋንያን ለሰላማዊ፣ዴሞክራሲያዊ፣ፍትሃዊና ተአማኒ ምርጫ መስራት አለባቸው።ይህ ስራ የምርጫ ቦርድና የመንግስት ብቻ አለመሆኑንም መታወቅ አለበት።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ‹‹ የምርጫ ስኬት በምርጫ ቦርድና መንግስት ላይ ብቻ የሚያርፍ ሳይሆን ተዋንያኑ በሙሉ ለሰላሙና ለስኬቱ በጋራ መስራት ይኖርባቸዋል፤ ያንን ካደረግን ውጤታማ ምርጫ ማድረግ እንችላለን›› እንዳሉት የምርጫ ስኬታማነትን ለማየት የሚፈልግ አካላት ሁሉ ለተግባራዊነቱ በቀና መንፈስ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። የሰላማዊ ምርጫ ጉዳይ የመንግስት ጉዳይ ብቻ አይደለምና።
አዲስ ዘመን ጥር 27/2012