የቡና ዋጋ ጭማሪ እያሳየ መምጣቱን የቡናና ሻይ ባለስልጣን በተለይ ለአዲስ ዘመን አስታውቋል፡፡ ይህም ባለፉት ዓመታት ከቡና ዋጋ ማሽቆልቆል ጋር በተያያዘ አርሶ አደሩ በቡና ላይ ፊቱን በማዞር ቡናውን እየነቀለ በሌላ ሰብል ይተካል በሚል ይሰጋ የነበረበትን ሁኔታ እንደሚለውጠው ባለስልጣኑ ጠቁሟል፡፡
የባለስልጣኑ የገበያ መረጃና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ኸይሩ ኑሩ እንዳሉት፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት ዓለም አቀፉ የቡና ዋጋ በመቀነሱ የኢትዮጵያ ቡናም መቀነስ ግድ ሆኖበት ነበር፤ በዚህ ዓመት በተለይ ያለፉት ሁለት ወራት ግን ዋጋ በእጅጉ መሻሻል አሳይቷል፡፡ ዋጋው እንደየአካባቢው ቢለያይም እሸት ቡና ከ15 እስከ 25 በመቶ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ የሆነው የይርጋ ጨፌና የሐረር ቡናም እስከ 30 በመቶ ጭማሪ አሳይተዋል፡፡ የዘንድሮ ጭማሪም ከቀደመው በእጅጉ የላቀ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ቡና በእዚህ መልኩ እያንሰራራ መምጣቱ ለኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ ለቡና አርሶ አደሮች ትልቅ የምስራች ነው። በእርግጥም ባለፉት ዓመታት ስለቡና ዋጋ መውደቅ ብቻ ስንሰማ ለነበርን ሁሉም ታላቅ ዜና ነው፡፡
እንደሚታወቀው፤ የቡና ልማትና ግብይቱ ቀደም ሲል አደረጃጀቱ ፈርሶ ቡና እንደማንኛውም የግብርና ምርት ተወስዶ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ቡና በባለቤትነት የሚመራው አካልም አጥቶ ቆይቷል፡፡ በዚህ የተነሳም በአገርም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ የግብይት ስርአትን ባልተከተለ መልኩ ተሰርቷል። ይህም ከዋጋ ጀምሮ ምርቱ በሁሉም ረገድ እንዲያሽቆለቁል እንዲሁም አገሪቱ ከቡና ዘርፍ በሚፈለገው መጠን ተጠቃሚ እንዳትሆን አድርጓታል፡፡
ሀገሪቱ ልማቷን ለማሳለጥ የምትፈልገውን የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት አቅዳ የነበረው አንድም ከቡና የወጪ ንግድ ነበር፡፡ በቡና ዋጋ መውደቅ ሳቢያ ይህን ማሳካት ተስኗት ቆይታለች፡፡ አንደ አማራጭ ስትጠቀም የቆየችው ብዙ ቡና በመላክ የሚፈለገውን ግብ ማሳካት ነበር፡፡ ይህ ሲሆን ቆይቷል፡፡
መንግስት ባለፉት ዓመታት የቡና ልማትና ግብይት ተግዳሮቶች ለመፍታት ተንቀሳቅሷል፡፡ የቡናና ሻይ ባለስልጣንን ከዓመታት በኋላ እንደገና እውን እንዲሆን በማድረግ ቡና ባለቤቱን መልሶ እንዲያገኝ አድርጓል፡፡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱም ከዘርፉ ተዋናዮች በተለይ ከቡና ላኪዎች፣ አቅራቢዎችና አርሶ አደሩ ጋር በመሆን የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያውንም ስራ ላይ አውሏል፡፡ በቡና መላክ ስራ ውስጥ ሲስተዋል የቆየውን ህገወጥ የመላክ ስራ ለመቆጣጠር ላኪዎች አዲስ ውል እንዲገቡ የሚያደርግ እርምጃ ወስዷል፡፡ አሁን የታየው የቡና ዋጋ ማንሰራራት ዓለም አቀፍ ገበያ የራሱ ሚና ሊኖረው ቢችልም፣ የእነዚህና ሌሎች የመንግስት እርምጃዎች ውጤት ተደርጎ መወሰድም ይኖርበታል።
የቡና ልማቱ ተጠቃሚዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እንደሆኑ ይታመናል፡፡ አርሶ አደሩ፣ በተለያዩ የግብይት ሰንሰለቶች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ አካላት እንዲሁም የሀገር ውስጥ የቡና ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ የቡና ዋጋ መጨመር ሁሉንም ወገኖች ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡ አርሶ አደሩ ቡና ካልተከለ፣ ካልተንከባከበ የቡና ምርት በበቂ መልኩ ማግኘት አይቻልም፡፡ በየዓመቱ ይታይ ከነበረ የቡና ዋጋ መውድቅ ጋር በተያያዘ ቡና ማልማቱን እንደሚተው ስጋት አሳድሮ እንደነበር ይታወቃል፡፡ አሁን ዋጋ ጭማሪ መታየቱ አርሶ አደሩ በቀጣይም ተጠቃሚ እንደሚሆን አስቦ ለቡናው ትኩረት እንዲሰጥ አስችሎታል፡፡
የቡና ዋጋ ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር በእጅጉ ቁርኝት እንዳለው ይታወቃል። አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ የታየው የዋጋ ማንሰራራትን በሚገባ ለመጠቀም በትኩረት መስራት ይገባል፡፡ ይህን መጠቀም መቻል ላኪውንም አርሶ አደሩንም ሀገርንም ይጠቅማልና ቡና በብዛትና በፍጥነት በመላክ ተጠቃሚ ለመሆን መስራት ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም የቡና ዋጋ ጭማሪው ትልቅ ዜና ነው፤ ዜናውን ይዘን በጭማሪው ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት አሁንም በትኩረት እንስራ!!
አዲስ ዘመን ጥር 26/2012