ቆሻሻ በአግባቡ ካልተያዘ በሰው ልጆች፣ በአካባቢ እና በእንስሳት ደህንነት ላይ ከፍተኛ አደጋ ያስከትላል፡፡ አደጋውን ለመከላከል የሁላችንም ድርሻ ወሳኝ ቢሆንም፤ ስርዓት ለማክበር ደግሞ ህግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው። ለዚህም ሲባል በአገሪቷ የአካባቢ ተፈጥሮን ደህንነት ማስጠበቅ የሚችሉ ሕጎች፤ ደንቦች እና መመሪያዎች በየጊዜው ይፀድቃሉ። ይሁን እንጂ የተደነገጉ ህጎችንና መመሪያዎችን ተግባራዊ ሆነው ሥራ ላይ ካለመዋላቸው የተነሳ በተለያየ ጊዜ የቆሻሻ አወጋገድ ችግሮች ይስተዋላሉ።
እርግጥ ነው ከኢኮኖሚ ዕድገት እና ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በአገሪቷ በሚገኙ ክልሎች የሚመነጨው ቆሻሻ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል፡፡ በተለይም ፈጣን የከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ በከተሞች የሚመነጨው የቆሻሻ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል። ይህን ችግር ለመከላከል ህግን ተግባራዊ ማድረግ ወሳኝ ቢሆንም፤ ለህብረተሰቡ ግንዛቤን ማስጨበጥ ደግሞ ቀዳሚ ሥራ ሊሆን ይገባል።
ከሆስፒታሎች እና ከተለያዩ ፋብሪካዎች የሚወጡ ፍሳሾች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ለመጣው የአካባቢ ብክለት ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙ ሲሆን፤ በከተሞች የሚታየው የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ በአብዛኛው ወንዞችን መሰረት ያደረገ በመሆኑ በከተሞች አካባቢ የሚገኙ ወንዞችን ከጥቅም ውጪ ሲያደርጋቸው ህግ አስከባሪውም ሆነ ሌላው ማህበረሰብ ጆሮ ዳባ ልበስ በሚል ዝምታን ሲመርጥ ይታያል። በተመሳሳይ ህብረተሰቡ እነዚህኑ ወንዞች በመጠቀም የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን ሲያለማ ይታያል።
ከፋብሪካም ሆነ ከሆስፒታሎች አካባቢ የሚገኙ ወንዞች በፍሳሾች መበከላቸው፤ በየቦታው ፕላስቲክን ጨምሮ በአካባቢው ተፈጥሮ ላይ ከሚያደርሰው ብክለት በተጓዳኝ የጤና ጠንቅ መሆኑም ዕሙን ነው። በፍሳሽ አወጋገድ ሰበብ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የውኃ አካላት ለጤና አደገኛ በሆነበት ደረጃ ለብክለት መዳረጋቸውን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሳይቀሩ ትኩረት ሰጥተው ዘግበውታል። በአካባቢው የሚኖሩ ወገኖችም ጉዳታቸውን ሲናገሩ ተደምጧል።
ታድያ ይህ ለህብረተሰቡ የጤና ጠንቅ የሆነው ቆሻሻ በአንዳንድ አገራት የሀብት ምንጭ ሆኖ ሲያገለግል ይታያል። ይሁን እንጂ በአገራችን ኢትዮጵያ ቆሻሻን ወደ ሀብት ለመቀየር የተደረገው እንቅስቃሴ እጅግ ዘግይቶ ቢሆንም ጅምሩ የሚበረታታ ነው። ታድያ ይህን መልካም ጅምር በማበረታታት ቀጣይነት ያለውና ውጤታማ የቆሻሻ አወጋገድን ባህል ማድረግ ከሁሉም የማህበረሰብ ክፍል የሚጠበቅ ነው።
በተለይም ፋብሪካዎች፣ ሆስፒታሎችና የተለያዩ አምራች ድርጅቶች ከማምረቻቸው የሚወጣውን የተበከሉ ቆሻሻዎች የሚያስወግዱበት አግባብ አካባቢን ከመበከል ጋር እጅግ የተቆራኘ በመሆኑ ትልቅ ትኩረት ሰጥተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል። በተለይም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ከወትሮው በተለየ መልኩ ሊሠራበት እና በማህበረሰቡ ላይ እያስከተለ ያለውን የጤና ቀውስ ሊቀርፍ ይገባል።
እርግጥ ነው ችግሩ ለአንድ አካል ብቻ የሚተው አይደለምና መንግሥትን ጨምሮ ሌሎች ድርጅቶችንም በጋራ በማሳተፍ በቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ዙሪያ የሚሠሩ ማኅበራትን ከስልጠና ጀምሮ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ውጤት ያለው ሥራ መሥራት ይጠበቃል። ከዚህ ባለፈም ህብረተሰቡ በቆሻሻ አወጋገድ ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ በመሥራት ጤናማ ህብረተሰብ መፍጠር ይቻላል።
በአጠቃላይ ከሆስፒታሎችም ይሁን ከፋብሪካዎች የሚወጣ የፍሳሽ ቆሻሻ በተገቢው መንገድ ካልተወገደ በማህበረሰቡ ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል። በርካታ ሆስፒታሎች ዘመናዊ የቆሻሻ ማቃጠያ ማሽኖች የሌላቸው ከመሆኑም በላይ የፍሳሽ አወጋገዳቸውም ሆነ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገዳቸው የአየር ብክለትን እየፈጠረ መሆኑ ታውቋል። ስለሆነም “ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ” እንዲሉ መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም ዜጋ በየደረጃው ኃላፊነቱን በመወጣት ከተማዋን ፅዱና አረንጓዴ በማድረግ ጤናማና ደህንነቱ የተጠበቀ ዜጋን እንፍጠር። ለዚህ ደግሞ የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 25/2012