የመልካም ምኞትና የበረከት ቃል ለኢትዮጵያ በሚል መሪ ቃል የተቋቋመው ክብሬ ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ማህበር አዲስ መጽሐፍ “መጽሐፈ ኢትዮጵያ” በሚል አዘጋጅቷል። ማህበሩ በኢትዮጵያ እና በምስራቅ አፍሪካ ሰላምን ፍቅርን አንድነትን ማጎልበት ዓላማው አድርጎ የተመሰረተ ሲሆን በዋነኝነት ደግሞ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ለተጀመረው የፍቅር እና የትንሳኤ ጉዞ አጋዥ ለመሆን ነው።
መፅሀፈ ኢትዮጵያ በማለት የተሰየመው ልዩ መዝገብ ኢትዮጵያዊያን ለሀገራቸውና ለህዝቦቻቸው ያላቸውን ፍቅር የሚገልጹበት እና በፅሁፍ ለትውልድ የሚያስተላልፉበት የክብር መዝገብ ነው። መጽሐፉ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሳተፍበት ዘመን ተሻጋሪ መዝገብ (መጽሐፍ) በስነ-ፅሁፍ ዓለም አዲስ የፈጠራ ስራ ሲሆን በኢትዮጵያዊያን የተጀመረ የዚህ ዘመን አስደናቂ ክስተት ከመሆኑ በላይ የስልጣኔና የጥበብ መገኛ ለሆነው ህዝብ ኩራት ነው፤ በፍቅር እና በይቅርታ የኢትዮጵያን ትንሳኤ ለሚጠባበቀው ይህ ትውልድ ደግሞ ተስፋ ፈንጣቂ ፀሀፊ በመሆን ታሪክ ሰሪ ያደርገዋል ።
የባለራዕዩ ትግል
የማህበሩ ሰብሳቢ እና የዚህ ሀሳብ አመንጪ ወጣት አዲስ አበባየሁ ራዕዩን ሲነግራቸው ቀልድ የሚመስላቸው ብዙ ናቸውና ቁም ነገረኞቹን ለማግኘት ከተማዋን በእግሩ ሲያስስ ያመሻል። መውጣት፣ መውረድ ያደቀቀው አካሉ፣ ፀሐይ የጎዳው ገጹ ልፋቱን ይመሰክራሉ። ከጥቂት ጊዜያት በፊት የነበረ ደም ግባቱ ከድቶታል። በፎቶ የሚወጣው መልኩ፣ በመስታወት የሚያየው ገጹ የተጎዳና እሱን የማይወክል እንደሆነ ያውቃል። ጠዋት ወጥቶ መንገድ ላይ ሲንከራተት ለሚውል ወጣት ዘንጦ መዋል ከባድ ነው። ብዙ የማይመቹ ነገሮች ቢኖሩም፣ ከመጽሐፉ አይበልጥበትምና ማልዶ ተነስቶ ይወጣል።በመንገዱ የሚያገኛቸውን አቁሞ ያናግራቸዋል። የመንግሥት ቢሮዎችን ያንኳኳል። ትምህርት ቤቶች ይገባል። የሕዝብ መገልገያ ቦታዎች ያዘወትራል። የአዲስ ሕይወት አሰልቺ ድግግሞሽ ይመስል እንጂ ነግቶ እስኪመሽ በገጠመኞች የተሞላ ነው። የ
በአንፃሩ ደግሞ ቀበል አድርገው ለአገራቸው ያላቸውን ስሜት በደስታ የሚገልጹ ብዙ ናቸው። ከማይረሳቸው ሰዎች መካከል ወመዘክር ግቢ ውስጥ ያገኛቸው የሕክምና ባለሙያ ስለአገራቸው ሳግ እየተናነቃቸው የጻፉት አንዱ ናቸው። ጫማ መጥረጉን ገታ አድርጎ ስለአገሩ የተሰማውን የጻፈ ሊስትሮም ሁኔታው ትዝ ይለዋል። ለጉብኝት የመጡ የውጭ ዜጎችም በየቋንቋቸው ስለኢትዮጵያ የሚሰማቸውን ይጽፋሉ። የመቶሺዎች ማስታወሻ የሚሆነው መጽሐፍ የዓለም ቋንቋ የሚንፀባረቅበትም ነው። በአውሮፓ፣ በእስያና በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የሚነገሩ ቋንቋዎች መልዕክታቸውን የጻፉ አሉ። በየብሔረሰቦች ቋንቋ የተጻፉት ማስታወሻዎች ደግሞ በዛ ይላሉ። ስለኢትዮጵያ መልካም የሚያስቡ በየቋንቋቸው ሐሳባቸውን የሚገልጹበት ይህ መጽሐፍ በቅጽ ተከፋፍሎ የሚወጣ ይሆናል። ለማኅበረሰቡ ተደራሽ በሆኑ ላይብረሪዎች ተባዝቶ እንዲቀመጥ እንደሚደረግ አዲስ ይናገራል።
በየትምህርት ቤቶቹ ተንቀሳቅሶም አዲሱ ትውልድ ስለአገሩ ያለውን መልካም ምኞት መግለጽ እንዲችል ዕድሉ ይሰጣል። የእያንዳንዱ ተማሪ ጽሑፍም ቅጂው ተጠርዞ በየላይብረሪው እንዲቀመጥ ይደረጋል።በራሱ ተነሳሽነት የጀመረውን ይህንን ፕሮጀክት የሚደግፈው ሌላ አካል የለም። ወረቀት፣ እስኪርቢቶ፣ ይቸገራል። እስካሁን የቀጠለውም ያገኘውን ነገር እየሠራ በሚያገኘው ገንዘብ የሚጎድለውን እያሟላ ነው።
የግድግዳ ጌጥ፣ የአበባ ማስቀመጫና የመሳሰሉትን ሠርቶ አንዱን እስከ 100 ብር ይሸጣል። ‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ባላ እንዲሉ› እየዞረ ጽሑፍ ይሰበስባል፣ ጌጦቹን የሚገዛው ካገኘ ይሸጣል። ባገኘው ወረቀትና እስኪርቢቶ ያሟላል። ‹‹300 ብር መሥራት ከቻልኩ በቃ ሀብታም ነኝ፤›› ይላል። ያለበትን የገንዘብ ችግር ሲገልጽ። ያገኘውን ሁሉ የሚያውለው በወረቀትና እስኪርቢቶ ግዥ ነው። ይህንን ወጪ የሚጋራው አካል ቢኖር ደስተኛ ነው። ታዲያ በዚህ ሁሉ ድካም የቆመው ራዕይ መስመር የያዘ ይመስላል፤ ፕሮጀክቱ ከኢምሳ ጋር በመተባበር የራሱ የሆነ ድረ ገጽ ኖሮታል። ዜጎች ባሉበት ሆነው ኦንላይን የሚጽፉበት ዕድል እንደሚፈጥር ባለራዕዩ ወጣት ይናገራል።
100 ሺሕ ደራሲያን
ይህ መጽሐፍ ባለራዕዩ ወጣት አዲስና ጓደኞቹ ለኢትዮጵያ የሚያቀርቡት ገፀ በረከት ነው። በጣት የሚቆጠሩ ደራሲያን ባሉበት አገር ዕልፍ ደራሲያን ማለትም ማህበሩ በእቅዱ ላይ እንዳስቀመጠው 100 ሺሕ ደራሲያን የሚሳተፉበት ከወዴት ይገኛሉ ካሉም ትክክለኛ ጥያቄ ነው። ነገር ግን ወጣቱ የራሱ መንገድ አለው። ስለኢትዮጵያ መልካም መልካሙን ማሰብ የቻለ፣ ለአገሩ የሚቆረቆር፣ ለወገኑ የሚያዝን አገሩን የሚወድና ፊደል የቆጠረ ሁሉ ለዚህ ታሪካዊ ጥራዝ ደራሲ ይሆናል። የሚያውቃትን፣ የሚወዳትን፣ የሚመኛትን ኢትዮጵያ ምጡቅ የሥነ ጽሑፍ ችሎታ የለህም ተብሎ ሳይገለል ከሦስት ገጽ ባልበለጠ ወረቀት ላይ ይጽፋታል። ትልቅ ትንሽ ሳይል በሚሳተፉበት በዚህ መጽሐፍ ያልተደመጡ ሐሳቦች ይታተማሉ። ከሊስትሮና ከጎዳና ተዳዳሪ ጀምሮ ያሉ ሁሉም ዜጎች እኩል፣ ‹‹ኢትዮጵያዬ›› ይሉበታል።
በመጽሐፉ ማን ይሳተፋል
ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ባለስልጣኖች፣ የህዝብ ተወካዮች ፣ የሀይማኖት መሪዎች ፣ታዋቂ ሰዎች እንዲሁም ለአፍሪካዊያን መልካም አስተዋፅኦ ያበረከቱ የውጪ ሀገር ዜጎች ጭምር ነው የሚሳተፉበት። መጽሐፉ የሁሉም ኢትዮጵያውያን እንደመሆኑ መጠን አካል ጉዳተዮችንም የሚያካትትበት የተለየ የመረጃ ቋት ተዘጋጅቷል።ይህም ማለት መስማት የተሳናቸው በቪዲዮ በምልክት ቋንቋ ስለ አገራቸው የበረከት ቃላቸውን የሚናገሩበት ምልክቱም ወደ ጽሑፍ የሚቀየርበት አዲስ አሰራር ተዘርግቷል።ይህ ብቻ አይደለም ማየት የተሳናቸው ደግሞ የተለየ የብሬል ሶፍትዌር በማዘጋጀት ሀሳባቸውን እንዲያሰፍሩ ማድረግ አሊያም በመቅረጸ ድምጽ በመቀረጽ ሃሳባቸውን መግለጽ አንደሚችሉም ሁኔታው ተመቻችቷል።
መዳረሻ ቦታዎች
ስለ መዳረሻ ቦታዎች የማህበሩ መስራች እና ባለዕራዩ ወጣት ሲናገር በተመረጡ የአፍሪካ ሀገራት ማለትም ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ ፣ ጂቡቲ፣ ሱዳን ፣ ኬንያ…… ውስጥ በሚገኙ ቤተ-መጻህፍቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመንግስትና የግል መስሪያ ቤቶች ፣ መስኪዶች ፣ ቤተ-ክርስቲያኖች፣ መናፈሻ እና መዝናኛ ቦታዎች ወ.ዘ.ተ ይሆናሉ ብለዋል።
መጽሐፈ ኢትዮጵያ ማህበር በአይነቱ ልዩ የሆነው የስነ ፅሁፍ ስራ የሀይማኖት ነፃነት የብሔር ብሔረሰቦችን አንድነት እና መቻቻል ማዕከል በማድረግ በጥንቃቄ የሚሰራ ስራ በመሆኑ ከመንግሥት ዘንድ ሙሉ ተቀባይነት ማግኘቱን ወጣቱ ይናገራል።
ከላይ እንደገለፅነው የዜጎችን የአንደበት መልካም ፍሬ ቃል በማፃፍ እና በመሰብሰብ ለዘመናት በቤተ‐ መፃህፍትና በሙዚየም ውስጥ የሚቀመጠው ይህ ልዩ መጽሐፍ ያልተለመደ እና ልዩ በመሆኑ አሁንም በስነ ፅሁፉ ዓለም ኢትዮጵያን ቀዳሚ ያደርጋታል። ስለዚህ ማህበራችን ክብረ ኢትዮጵያ ሀገርህን ዕወቅ ማህበር ለህዝብ ያቀረበው ልዩ የስነ-ፅሁፍ ፈጠራ ስራ ለሀገራችን ሰላምና አንድነት፣ ለሀገራችን የስነ-ፅሁፍ ዕድገት፣ ለቋንቋዎቻችን ዕደገት ታላቅ አስተዋፅኦ የሚያበረክት ስለሆነ የእናንተ ተቋም ድጋፍ እና ትብብር እንዲያደርግልን በትህትና እንጠይቃለን ።
በዚህ መጽሐፍ መዝገብ ላይ እስካሁን ካሰፈሩት የፅሁፍ መልዕክቶች መካከል ለኢትዮጰያ ህዝብ የተፃፈ የፍቅር ደብዳቤዎች ፣ የመልካም ምኞት መልዕክቶች ፣ የበረከት ቃሎች (ቡራኬና ምርቃት በሀገር ሽማግሌዎች) ፀሎትና ልመና እንዲሁም በጎና የሚያንፅ ሀሳብ ያላቸው የፅሁፍ መልዕክቶች የተካተቱ ሲሆን መልዕክቶቹ ወይም ፅሁፎቹ የተፃፉት በሀገር ውስጥና በውጪ ቋንቋዎች ነው ።
ይህንን ልዩ ሀገር አቀፋዊ እና አህጉራዊ የፅሁፍ ስራ በሁሉም የሀገራችንና የአፍሪካ ቋንቋዎች በማፃፍና በመሰብሰብ በአይነቱ ልዩ የሆነ መዝገብ የማዘጋጀቱን ስራ በ2009 ዓ.ም መጀመሩ የሚታወስ ነው። በአራት ኤግዚብሽኖች ላይ እና በብሔራዊ ቤተ መጻህፍት ለአንድ ወር ያህል ለንባብ የሚመጡ አንባቢዎችን በማሳተፍ በርካታ ፅሁፎችን ሰብሰቧል በተጨማሪም ከህዳር 4 ቀን 2011 እስከ ህዳር 14 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ስራውን በብሔራዊ ሙዚየም አቅርቦ በርካታ ኢትዮጵያዊያንና የውጪ ሀገር ዜጎችን ተሳትፈዋል።
ወጣት አዲስ ይናገራል “ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በኤግዚብሽን ማዕከልና በአፍሪካ አንድነት ድርጅት በተካሄዱት የንባብ አውደ ርዕይ ላይ በርካታ ኢትዮጵያዊያንን አፅፈናል። እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አዘጋጅቶት በነበረው ባህላችን ለሰላም እና አንድነታችን በሚል መሪ ቃል በተሰየመው ኤግዚብሽን ላይ ከጥር 25 እስከ 27 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ በመሳተፍ በርካታ ዜጎችን አፅፈናል በማህበራችን ቤተ-መፃህፍት የፍቅር ቃል ተንቀሳቃሽ ቤተ መፃህፍት በኩል የተሳትፎና የምስጋና ሰርተፊኬት አግኝተናል ።”
ከህዳር 4 ጀምሮ እስከ ህዳር 14 ቀን 2011 ዓ.ም በብሔራዊ ሙዚየም በርካታ የሀገር ውስጥና የውጪ ሀገር ጎብኚዎች የፅሁፍ ስራው ተሳታፊ ማድረጋቸውን ያስታወሰው ወጣቱ በዕቅዳቸው መሰረት ሁሉንም ፅሁፎች ሰብስበው ሲጨርሱ ዜጎች የተሳተፉበት ልዩ መጽሐፍ በህትመት ለአንባቢያን እንደሚበቃ እንዲሁም በትምርት ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሚገኙ ቤተ- መፃህፍቶች በማኖር ለጥናትና ምርምር ግብአትነትና በቅርስነት በክብር ለትውልድ እንዲተላለፍ እንደሚያደርጉ ወጣት አዲስ ከደስታ ጋር ገልጿል።
በዋነኝነት ደግሞ ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር በመቀናጀት ግጭቶችን ለመፍታት ለሚደረገው በጎ እና ሰላማዊ እንቅስቃሴ መሳካት ጥቅም ላይ እንዲውል እናደርጋለን ያው ዋት አዲስ በተጨማሪም ሀገሪቱ እና ህዝቦቿን ተጠቃሚ ሊያደርግ በሚያስችል መልኩ ማህበራቸው በህትመት ለሚያወጣው መፅሔትቶች እና መፅሐፍቶች ምንጭ ሆኖ እንዲያገለግል እንደሚጠቀሙበት ገልተዋል። እንደ ወጣቱ ባለራዕዩ ገለጻ ይህን መሰል ስራ በአለማችን ላይ ተሰርቶ ስለማያውቅ በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ እና በዩኔስኮ መዝገብ ላይ ሰፍሮ ኢትዮጵያ እንዲያስጠራ የተቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ገልጿል።እኛም ውጥኑ ከግብ እንዲደርስ ልባዊ ምኞታችንን እንገልጻለን። መልካም ሰንበት!
አዲስ ዘመን ጥር 24/2012
አብርሃም ተወልደ