
የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት እና ሩዋንዳ በዋሺንግተን ዲሲ የሰላም ስምምነት ተፈራርመዋል። ስምምነቱ የአሜሪካ፣ የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክና የሩዋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር እንዲሁም ዲፕሎማቶች በተገኙበት በዋሺንግተን ዲሲ፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢሮ ተፈርሟል። ስምምነቱን ያመቻቹት የትራምፕ ልጅ የቲፋኒ ትራምፕ ባለቤት አባት የሆኑት ማሳድ ቡሎስ የተባሉ ሊባኖሳዊ-አሜሪካዊ ባለሀብት ሲሆኑ፣ ትራምፕ ሰውየውን የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪያቸው አድርገው ሾመዋቸዋል።
በአሜሪካና በኳታር አሸማጋይነት የተፈረመው ስምምነት፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ለዓመታት ለዘለቀው አለመግባባትና በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በ‹‹ኤም23›› (M23) ታጣቂ ቡድን መካከል ለሚካሄደው ውጊያ እልባት እንደሚያስገኝ ተስፋ ተጥሎበታል።
በስምምነቱ መሠረት ኪንሻና ኪጋሊ በዘጠና ቀናት ውስጥ ቀጣናዊ የምጣኔ ሀብት ትስስር ማዕቀፍ ይፋ ያደርጋሉ፤ የሩዋንዳ ወታደሮች ከኮንጎ ግዛት ውስጥ ይወጣሉ። በ30 ቀናት ውስጥ ደግሞ የጋራ የፀጥታ ቅንጅት ሥርዓት ይዘረጋሉ። የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ አካባቢያቸው ይመለሳሉ።
ስምምነቱ ለረጅም ጊዜያት ሲጠበቅ እንደነበር የገለፁት የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴሬስ ካዪክዋምባ ቫግነር፣ ‹‹ስምምነቱ በጦርነቱ የደረሰውን ጉዳትና ሕመም ባያስረሳም የተጎጂዎችን መፃኢ ዕጣ ፈንታ ለማሻሻል የመጀመሪያ ርምጃ መሆን ይችላል። የችግሩ ዋና ሰለባዎች ከእኛ ብዙ እየጠበቁ ነው፤ ስምምነቱ እንዲከበር ይጠብቃሉ፤ ስምምነቱን ማክበር ያስፈልጋል፤ ልናሳፍራቸው አይገባም›› ብለዋል።
የሩዋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦሊቪዬ ንዱሁንጊሬ፣ ስምምነቱ ለግጭቱ መቆም ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል። ኮንጎ ‹‹የዲሞክራሲ ኃይሎች ለሩዋንዳ ነፃነት›› (FDLR) ለተባለው ታጣቂ ኃይል የምታደርገውን ድጋፍ እንድታቆም በአፅንዖት ጠይቀዋል። ሩዋንዳ ይህ ቡድን በ1994 የሩዋንዳ የዘር ፍጅት ወቅት ቱትሲዎችን በጨፈጨፉ ሁቶዎች የተመሠረተ እንደሆነ ታምናለች። ስምምነቱም ይህ ቡድን እንዲበተን ይጠይቃል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በበኩላቸው፣ ስምምነቱ ለ30 ዓመታት የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም ጠቃሚ ርምጃ እንደሆነ ገልፀዋል። ‹‹ስምምነቱ ሰዎች በሕይወት እንዲኖሩ እንዲሁም ለተሻለ ሕይወት፣ ለብልፅግና፣ ለኢኮኖሚ ዕድል፣ ለቤተሰብ ውሕደት፣ በአጠቃላይ ሕይወት የተሻለ ዋጋና ትርጉም እንዲኖሯት ለሚያደርጉ ነገሮች ሁሉ ሕልም እንዲሰንቁ የማድረግ ጉዳይ ነው። ጦርነትና ግጭት ካለ ግን እነዚህ ሕልሞች የማይታሰቡ ናቸው›› ብለዋል።
የአልጀዚራው አላይን ኡይካኒ ከሰሜን ኪቩ ግዛት ዋና ከተማ ጎማ ባሰራጨው ዘገባ፣ ስምምነቱ ትልቅ ርምጃ ቢሆንም የ‹ኤም-23› ታጣቂዎች ከአካባቢው መቼ እንደሚወጡ ግልጽ ስላልሆነ በአካባቢው ግራ መጋባት እንደሚስተዋል ገልጿል። ሩዋንዳ ‹ኤም-23› አካባቢውን እንዲለቅ የመጠየቅ ኃላፊነት እንደሌለባት ሁልጊዜም እንደምትገልጽ እና ቡድኑ ለአካባቢው አስተዳዳሪዎችን መሾሙንና አየር ማረፊያዎችን መቆጣጠሩንም የኡይካኒ ዘገባ ያመለክታል።
የሰላም ስምምነቱ የአሜሪካ መንግሥትና ኩባንያዎች እንደታንታለም፣ ወርቅ፣ ኮባልት፣ መዳብና ሊቲየም ያሉ ብርቅዬ ማዕድናትን እንዲያለሙ ያስችላቸዋል። እነዚህ ማዕድናት ለቴክኖሎጂ ምርቶች አስፈላጊ ግብዓቶች ናቸው። በተለይም አሜሪካና ቻይና የንግድ ጦርነት ውስጥ በገቡበት እና በአፍሪካ ውስጥ የበላይነትን ለመያዝ በሚፋለሙበት በዚህ ወቅት ይህ የስምምነቱ ክፍል ለአሜሪካ ትልቅ ብሥራት ሳይሆን አይቀርም ተብሏል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከስምምነቱ መፈረም ቀደም ብሎ ባሰሙት ንግግር ‹‹ብዙ የማዕድን መብቶችን ከኮንጎ ለአሜሪካ አስገኝተናል። እዚህ በመገኘታቸው ክብር ተሰምቷቸዋል›› ብለዋል። የኮንጎና የሩዋንዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን በዋይት ሐውስ በተቀበሉበት ወቅት ደግሞ ‹‹ግጭቱና ውድመቱ አብቅቷል፤ ቀጣናው አዲስ የተስፋና የዕድል ምዕራፍ ጀምሯል። ይህ ምርጥ ቀን ነው›› በማለት ተናግረዋል።
ኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 24 ትሪሊዮን ዶላር የሚገመት ያልተነካ እምቅ የማዕድን ሀብት ያላት ሲሆን፣ በጦርነቱ በፈጠረው ሕገ ወጥ ንግድ ምክንያት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ሚያወጣ ማዕድን እንዳጣች ገልፃለች።
የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት እና የ‹‹ኤም23›› (M23) ታጣቂ ቡድን ከሁለት ወራት በፊት በኳታር አሸማጋይነት ተኩስ ለማቆም ተስማምተው ነበር። ባለፈው መጋቢት ደግሞ የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንትና የ‹‹ኤም23›› ታጣቂዎችን ትደግፋለች የምትባለው የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ በዶሃ/ኳታር ተወያይተው፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረው እንደነበር ይታወሳል።
የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት እና የ‹‹ኤም23›› ታጣቂ ቡድን ግጭት ከአስከፊው የሩዋንዳ የዘር ፍጅት ጋር የተሳሰረ ታሪክ አለው። የቡድኑ አብዛኞቹ ታጣቂዎች በዘር ጭፍጨፋው ዋና ተጠቂ የነበረው የቱትሲ ጎሳ አባላት ናቸው። ቀደም ሲል የአማፂ ቡድኖች አባላት የነበሩት ብዙዎቹ የቡድኑ ታጣቂዎች፣ የኮንጎ ብሔራዊ ጦር አባል ለመሆን ተስማምተው የነበረ ቢሆንም ‹‹መገለል ደረሰብን፤ የተገባልንም ቃል አልተፈፀመልንም›› ብለው በድጋሚ ‹ጥራኝ ዱሩ› ብለው ወደ ጫካ የተመለሱ ተዋጊዎች መሆናቸው ተገልጿል።
ስሙን እ.አ.አ ማርች 23 ቀን 2009 (March 23) በተፈረመው የሰላም ስምምነት ምክንያት ‹‹ኤም23›› (የማርች 23 ንቅናቄ) ብሎ የሰየመው አማፂ ቡድን በዋናነት የሚንቀሳቀሰው በምሥራቃዊ ኮንጎ በምትገኘውና ኮንጎ ከዑጋንዳና ከሩዋንዳ ጋር በምትጎራበትባት ሰሜን ኪቩ ግዛት ውስጥ ነው።
ቡድኑ በማዕድን ሀብት የበለፀገውን የኮንጎ ምስራቃዊ ክፍል ለመቆጣጠር በአካባቢው ከሚርመሰመሱት ከ100 በላይ ታጣቂ ቡድኖች መካከል የተሻለ ጥንካሬ ያለው ተዋጊ ኃይል እንደሆነም ይታመናል።
አካባቢው ከግጭት የተላቀቀ ባይሆንም የቅርቡ ደም አፋሳሽ ጦርነት የተስፋፋው የ‹‹ኤም23›› አማፂያን ጎማ እና ቡካቩ የተባሉ የምሥራቃዊ ኮንጎ ሁለቱን ትልልቅ ከተሞች ከተቆጣጠሩ በኋላ ነው። ከዚያ ወዲህ ቡድኑ ግስጋሴውን በማፍጠን ሌሎች ከተሞችን ተቆጣጥሯል። በኮንጎ ምዕራባዊ ጫፍ ወደምትገኘው እስከ ዋና ከተማዋ ኪንሻሳ ድረስ እዘልቃለሁ ብሎም ዝቷል።
ሩዋንዳ በዚህ የኮንጎ ግጭት ውስጥ ወሳኝ ሚና ያላት ሀገር ናት። ትደግፈዋለች የሚባለው የ‹‹ኤም23›› አማፂ ቡድን የቱትሲ ጎሳ አባላት ስብስብ ነው። የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ካጋሜም የቱትሲ ተወላጅ ናቸው። የ‹‹ኤም23›› አማፂ ቡድን ከኮንጎ መንግሥት ጋር የሚዋጋው ሁቱዎች የሚመሩት ‹‹የዲሞክራሲ ኃይሎች ለሩዋንዳ ነፃነት›› (FDLR) የሚባለው ታጣቂ ኃይል ከኮንጎ መንግሥት ጋር ተባብሮ በደል የሚያደርስባቸውን በኮንጎ የሚኖሩትን የባንያሙሌንጌ ቱትሲ ወገኖቼን ከጥቃት ለመጠበቅ ነው ይላል።
ሩዋንዳ ደግሞ ‹‹የዲሞክራሲ ኃይሎች ለሩዋንዳ ነፃነት›› የተባለው ታጣቂ ቡድን ‹‹በሩዋንዳን የዘር ጭፍጨፋ እጁ አለበትና ደመኛ ጠላቴ ነው፤ ለሉዓላዊነቴም ትልቅ ስጋት ነው›› ትላለች። ከዚህ በተጨማሪም ቡድኑን የሚያስታጥቀው የኮንጎ መንግሥት እንደሆነ ሩዋንዳ ደጋግማ ገልፃለች። ቡድኑ በኪጋሊም ሆነ በምሥራቅ ኮንጎ ቱትሲዎች ላይ የደቀነው ስጋት በዘላቂነት እንዲወገድ የቡድኑ መወገድ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነውና ቡድኑን ከምድረ ገጽ ሳላጠፋ እንቅልፍ አይወስደኝም ብላለች።
ኮንጎ በበኩሏ የጎን ውጋት ለሆነባት የ‹‹ኤም23›› አማፂ ቡድን ወታደራዊ ድጋፍ የምታደርገው ሩዋንዳ እንደሆነች ታምናለች። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሩዋንዳ አራት ሺህ ወታደሮቿን ከቡድኑ ጎን አሰልፋ እየተዋጋች እንደሆነ ይፋ አድርጓል። ፈረንሳይና እና አሜሪካም ሩዋንዳ ቡድኑን እንደምትደግፍ ቢገልጹም፣ ሩዋንዳ ግን እጄ የለበትም ባይ ናት። በጉዳዩ ላይ ያላትን ተሳትፎም አማፂ ቡድን የማስታጠቅ ሳይሆን ሉዓላዊነትን የማስከበር ብሔራዊ ተልዕኮ አድርጋ ትቆጥረዋለች።
ግጭቱ የሚካሄድበት አካባቢ የተትረፈረፈ የማዕድን ሀብት ባለቤት መሆኑ ደግሞ ግጭቱ ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ ምክንያትም እንዲኖረው አድርጎታል። እነዚህ ማዕድናት ደግሞ የሞባይል ስልክ፣ ካሜራና የመኪኖችን የውስጥ ክፍሎችን ለመሥራት የሚያገለግሉት እጅግ ውድና ተፈላጊ ሀብቶች ናቸው። ኮንጎ ሩዋንዳ እነዚህን ማዕድናት እየዘረፈችኝ ነው የሚል ተደጋጋሚ ክስም ታሰማለች። ሩዋንዳ ግን እንደተለመደው ‹‹የለሁበትም›› ትላለች።
ተፃራሪ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገውን ምሥራቃዊ ኮንጎን ሰላም የራቀው፣ ድህነት፣ ረሃብ፣ በሽታ፣ ሞት፣ ስደትና እንግልት የሚፈራረቁበት የምድር ሲዖል አድርገውታል። ተንታኞች እንደሚሉት የስምምነቱ መፈረም በጎ ርምጃ ቢሆንም እኤአ ከ1990ዎቹ ጀምሮ ሚሊዮኖችን የቀጠፈውን ግጭት ግን በፍጥነት ያስቆመዋል ተብሎ አይጠበቅም። ቀሪው ዓለምም ስምምነቱን በተስፋና በስጋት እየጠበቀው ነው።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም