
ዜና ሐተታ
ከታዳጊ ሀገራት ተርታ በምትመደበው ኢትዮጵያ ቀደም ባሉት ዓመታት በርካታ ሚሊዮን ዜጎች ለጤናቸው ዋስትና አልነበራቸውም። አንድ ሰው የጤና እክል ቢገጥመው እንደልቡ ከኪሱ ገንዘብ አውጥቶ ለመታከም ፈተና ነው። ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ የሚመሩ ዜጎች ወደ ሕክምና ተቋም ለመሄድ የሚያስችል ወረት የላቸውም። መንግሥት ይህንን ውስብስብ ችግር ለመፍታት የጤናውን ዘርፍ ከማሻሻል አንስቶ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርግ የመድኅን ሥርዓት ዘርግቷል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይህ ሥርዓት ውጤት እየታየበት መሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ። እነዚህ መረጃዎች የሚያረጋግጡልን የኢትዮጵያ መድኅን የቅርንጫፍ አስተባባሪዎች ናቸው።
አቶ ስማቸው ካሤ በኢትዮጵያ የጤና መድኅን አገልግሎት በአማራ ክልል የደብረ ማርቆስ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት፤ ከፍለው መታከም የማይችሉና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግና እያደረገ የሚገኝ ነው።
‹‹የደብረ ማርቆስ ቅርንጫፍ በስሩ የሚያስተዳድራቸው 31 ወረዳዎች አሉ›› የሚሉት አቶ ስማቸው፤ ምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ ምዕራብ ጎጃም ዞን እና ደብረ ማርቆስ ሪጂኦፖሊታንት ከተማ በማካተት ለማኅበረሰቡ የጤና መድኅን አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ይገልፃሉ። በዚህም ከ700 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን አገልግሎት አባል ማድረግ መቻሉን እና አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ይናገራሉ።
አቶ ስማቸው እንደሚገልፁት፤ በተያዘው በጀት ዓመት በተለይ የመክፈል አቅምን መሠረት ያደረገ መካከለኛ፣ ከፍተኛና፣ ዝቅተኛ የማኅበረሰብ ክፍል እንደየአቅሙ ወጥ የሆነ ዓመታዊ የክፍያ ሥርዓት በመዘርጋት 811 ሚሊዮን ብር (የወረዳና የክልል ድጎማን ጨምሮ)፣ ገንዘብ መሰብሰቡን ይገልፃሉ። ቅርንጫፉ በሚገኝበት ከ150 በላይ የጤና ተቋማት ጋር ውል በመያዝ ማኅበረሰቡ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ እየሆነ እንደሚገኝ ያስረዳሉ።
‹‹በክልሉ ባለው ወቅታዊ የፀጥታ ስጋት እንደ ልብ ተንቀሳቅሶ አገልግሎት ለማሳለጥ አስቸጋሪ ነው›› የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ከተግዳሮቶቹ መካከል አንዱ መሆኑን ያነሳሉ። የመድኃኒት አቅራቢ ድርጅት በሚፈለገው ልክ መድኃኒት አለማቅረብ፣ የግዢ ሥርዓቱ መድኃኒት በሚጠፋበት ሰዓት ከግል ድርጅቶች በጨረታ ለመግዛት ሂደቱ ውስብስብ መሆን የግብዓት አቅርቦት ውስንነቶች መኖራቸውን ይናገራሉ።
‹‹የመድኃኒት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት የማኅበረሰብ አቀፍ ፋርማሲዎች በየአካባቢው ለማቋቋም እየተሠራ ነው›› የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ዜጎች በተሟላ የጤና ደኅንነት ውስጥ እንዲሆኑ አገልግሎቱን ለማላቅ እንደሚሠሩ ይገልፃሉ። አገልግሎቱ በሚሰጥበት ቅርንጫፍ ያሉ ያልተመዘገቡ ቀሪ ነዋሪዎች በዚህ ሥርዓት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይሠራል ሲሉም ነው የገለጹት።
አቶ አብዱልናስር አሕመድኑር የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት የጅግጅጋ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን አገልግሎት አሰጣጥ ከጊዜ ወደጊዜ መሻሻል እያሳየ ነው። በክልላቸው ዜጎች በዚህ ሥርዓት ተጠቃሚ እየሆኑ ነው። በክልሉ በ68 ወረዳዎች ውስጥ 360 ሺህ 294 ዜጎች የጤና መድኅን አገልግሎት ተጠቃሚ ናቸው።
በበጀት ዓመቱ 9 ወራት ውስጥ በ37 ወረዳዎች 264 ሺህ 205 የጤና መድኅን አባላት ማፍራት መቻሉን የሚገልፁት ሥራ አስኪያጁ፤ በዚህም 230 ሚሊዮን 931 ሺህ ብር ተሰብስቧል። ይህ ገንዘብ ባለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ ማኅበረሰቡን ከጤና ተቋማት ጋር ውል በማሰር አገልግሎት እንዲያገኝ እያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል።
‹‹በክልሉ በሚገኙ 50 ወረዳዎች አቅምን መሠረት ያደረገ የጤና መድኅን አገልግሎት ክፍያ እየተደረገ ነው›› የሚሉት አቶ አብዱልናስር፤ የጤና መድኅን አገልግሎቱ ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን እና አገልግሎቱ አቅምን መሠረት አድርጎ እንዲሰጥ ሰፊ የትግበራ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት ከሰሞኑ አድርጎት በነበረው የዘጠኝ ወር አፈጻጸም ግምገማው ላይ በቀረበው ሪፖርት ላይ የተመለከተው መረጃ እንደሚጠቁመው፤ በዘንድሮው ዓመት ከተናጠል የክልሎች ድጎማና ከአባላት መዋጮ 14 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ የተሰበሰበ ሲሆን 5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ክፍያ መፈፀሙን ያመለክታል። እንደ ሀገር በጤና መድኅን ሥርዓት ውስጥ 60 ሚሊዮን ዜጎች ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለም ያመለክታል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም