
አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ለምግብ ዋስትና እና ብዝኃ ሕይወት የሚያግዝ ጠንካራ የንብ ማነብ ባህል ያላት ናት ሲሉ በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የግብርና ዘርፍና እንስሳት ክፍል መሪ ተመራማሪ ደሳለኝ ቤኛ (ዶ/ር) ገለጹ።
ደሳለኝ ቤኛ (ዶ/ር) በማር ምርት ላይ ያደረጉትን ጥናት አስመልክቶ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ለምግብ ዋስትና እና ብዝኃ ሕይወት የሚያግዝ ጠንካራ የንብ ማነብ ባህል አላት። ከአፍሪካ ቀዳሚ የማር ምርት አምራች ሀገር ነች ብለዋል።
ኢትዮጵያ ወደ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሚጠጉ ንብ አናቢዎች እንዲሁም በተፈጥሮ ብዙ ለንብ መቅሰም አገልግሎት የሚውሉ አበባዎች እንደሚገኙባትም አመልክተው፤ ከእምቅ ሀብቷ በየዓመቱ እስከ 500ሺህ ቶን ማር ማምረት እንደሚቻል ተናግረዋል።
ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ከእምቅ አቅሟ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው 10 በመቶ ያህል ብቻ እንደሆነ አመልክተው፤ ይህም የማር ዘርፉን ለማሻሻል በትኩረት የሚደረጉ ጥረቶች አስፈላጊ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ደሳለኝ (ዶ/ር) በጥናታቸው እንዳመላከቱት፤ ከ92 በመቶ በላይ የሚሆነውን የማር ምርት የሚይዘው ባህላዊ የንብ ማነብ ዘዴ ነው። ይህም ብዙ ጊዜ ዝቅተኛ የማር ምርት እና ጥራትን ያልጠበቀ ምርት እንዲኖር ያደርጋል። የኢትዮጵያ ማር የወጪ ንግድ ማሽቆልቆል የመነጨው ከዚህ ልማዳዊ አሠራር የተነሳ እንደሆነም ያስረዳሉ።
ጥራቱን ያልጠበቀ እና ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ያላከበረ የማር ምርት በዘርፉ የሚፈለገውን የውጭ ምንዛሪ ለማስገባት አዳጋች እንደሚያደርገው ተናግረዋል። ይህን ጠቃሚ ኢንዱስትሪ ለማነቃቃት የታለሙ ጣልቃ ገብነቶችን በአፋጣኝ ማከናወን እንደሚያስፈልግ በጥናቱ መመልከቱን አንስተዋል።
ጥናቱ ሦስት ዓመት የፈጀ ሲሆን፤ ለፖሊሲ ለውጥ በግብዓትነት በሚያገለግል መልኩ በባለሙያዎች አስተያየትና ምክረ ሀሳብ እንዲዳብር ተደርጓል። በውይይቱ፤ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከምርምር ማዕከላት እና ከክልል ተቋማት የመጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ለጥናቱ አጋዥ ይሆናል ያሉትን ሃሳብ የሰጡ ሲሆን ሀሳቦቹ ለጥናቱ በግብዓትነት የሚያገለግሉ መሆናቸውን ደሳለኝ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ስሜነህ ደስታ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም