በአማራ ክልል ሰላምን የሚደግፉ ሕዝባዊ ሰልፎች ተካሄዱ

አዲስ አበባ፡- በአማራ ክልል በሚገኙ በተለያዩ ከተሞችና የገጠር ወረዳዎች መንግሥት ሰላምን ለማጽናት እየወሰደ ያለውን ርምጃ የሚደግፍና ጥያቄዎችን በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላምን ማጽናት እንደሚገባ የሚያሳስብ ሕዝባዊ ሰልፍ ተካሂዷል፡፡

በባህርዳር፣ በጎንደር፣ ደሴ፣ ደብረብርሃን፣ ደብረማርቆስና ሌሎች ከተሞችና ወረዳዎች መንግሥት ሰላምን ለማጽናት እየወሰደ ያለውን ርምጃ የሚደግፍና ጥያቄዎችን በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላምን ማጽናት እንደሚገባ መልዕክት ያለው ሕዝባዊ ሰልፍ መካሄዱን አሚኮ ዘግቧል፡፡

መንግሥት በተደጋጋሚ የሚያደርገውን የሰላም ጥሪ እንደግፋለን፤ የሀገራችንን ሰላም ለማወክ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር የተሰለፉ ኃይሎችን በፅኑ እንቃወማለን፤ ሰላሜን እጠብቃለሁ፣ ሁለንተናዊ ብልፅግናዬን አረጋግጣለሁ፤ የልማት ማዕከል የነበረውን ክልላችንን የጦርነት ቀጣና ለማድረግ የሚሠራው ሥራ የባንዳነት እና የፅንፈኝነት ጥግ ነው የሚሉ መፈክሮች በሕዝባዊ ድጋፍ ሰልፉ ላይ አስተጋብተዋል።

አሚኮ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ተቀስቅሶ በነበረው ጦርነት ከተማቸው ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት መድረሱን አስታውሰው፤ አሁን አካባቢያቸው ወደ ሰላም በተመለሰበት ወቅት ዳግም የጦርነት ነጋሪት የሚጎስሙ አካላትን እንደሚቃወሙ ገልጸዋል።

መንግሥት የሚያቀርበውን የሰላም ጥሪ እንደግፋለን ያሉት ነዋሪዎቹ፤ ጥያቄ አለን የሚሉ አካላት ነፍጥ በማንሳት ሳይሆን ለውይይት ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

የልማት እና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ሰላም ወሳኝነት አለው ያሉት የሀርቡ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መሐመድ ሹመት፤ ማኅበረሰቡ ለሰላም መጠበቅ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

ፅንፈኛው ኃይል አርሶ አደሮች እንዳያርሱ፣ ነጋዴዎች ነግደው እንዳያተርፉ፣ ተማሪዎችም እንዳይማሩ ትምህርት ቤቶችን በመዝጋት የአማራ ሕዝብ ጠላት መሆኑን በግልጽ አሳይቷል። ይህንን ኃይል በጋራ ማውገዝ ያስፈልጋል ብለዋል ከንቲባው።

በሕዝባዊ ሰልፉ ላይ ሰላምን እንሻለን፣ ክልላችንን የሰላም እና የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ለሰላም ዘብ እንቆማለን፣ ጽንፈኝነትን እናወግዛለን፣ ከመንግሥት ጎን እንቆማለን፣ መንግሥት ሕግን በማስከበር የዜጎችን ሰላም ሊያስጠብቅ ይገባል የሚሉ እና ሌሎች መልዕክቶች ተላልፈዋል።

በአማራ ክልል ለሁለት ዓመታት በቀጠለው የእርስ በርስ ግጭት በርካታ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ደርሷል ያሉት የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ ቢምረው ካሣ፤ ችግሮችን በውይይት መፍታት እየተቻለ የሚደረግ የግጭት እንቅስቃሴ ተቀባይነት የለውም ብለዋል። መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ ሰላም መምጣት እና ሀገራዊ ተሳትፎን ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት።

ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን በውይይት መፍታት እና ዘላቂ ሰላምን ማጽናት ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

በድጋፍ ሰልፉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ በግጭቱ ምክንያት የትምህርት፣ የግብርና እና ሌሎችም ተግባራት ተስተጓጉለዋል ነው ያሉት። በተለይ በቅርቡ ይጠናቀቃል የተባለለት የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ እንዲስተጓጎል መደረጉ ታሪክ ይቅር የማይለው ስህተት እንደሆነ ገልጸዋል።

ችግሮች ሁሉ በውይይት እና ምክክር እንዲፈቱ እንሠራለን ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው፤ የመንግሥት የሰላም እጆች ሁሌም አይታጠፉምና ታጥቀው በጫካ የሚታገሉ ወገኖች የሰላምን አማራጭ እንዲቀበሉ አጽንዖት ሰጥተዋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ በበኩላቸው ጥምር የፀጥታ ኃይሉ በከፈለው መስዋዕትነት የዞኑ እና የከተማ አስተዳደሩ ሰላም መሻሻል እያሳየ ስለመምጣቱ አንስተዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት፤ ሰላምን ለማስፈን እና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ መንግሥት በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል። “ሕዝባችን የሰላም አምባሳደርነቱን በተግባር አሳይቷል”፤ ይሄው ተግባሩ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፤ “ሰላም እንፈልጋለን” ብለዋል።

በጫካ ለሚገኙ የታጠቁ ኃይሎችም በጦርነት የሚገኝ ውጤት ስለሌለ ዛሬም የሰላም በሮች ክፍት መሆናቸውን በመገንዘብ የሕዝቡን እና የመንግሥትን የሰላም ጥሪ እንዲቀበሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You