የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በየዓመቱ በፌዴራል የመንግሥት ተቋማት በርካታ ገንዘብ ጉድለት እንዳለ በኦዲት ግኝትነት ያቀርባል። ማስተካከያም እንዲደረግ ምክረ ሃሳቡን ይለግሳል። ተቋማቱን የሚቆጣጠረው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ተቋማቱ እንዲያስተካክሉና በማያስተካከሉት ላይ ዕርምጃ እንዲወስድ በየዓመቱ ያሳስባል።
ምክር ቤቱም ተቋማቱ ማስተካከያ እንዲያደረጉ በየጊዜው ቢመክርም መስሪያ ቤቶቹ ግን በዓመቱ ለሚከሰቱት የኦዲት ግኝቶች ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት ማስተካከያ አላደረጉም። ማስተካከያ ባለማድረጋቸውም እስከአሁን ጠንከር ያለ ተጠያቂነት አልተደረገም። በየዓመቱ በችግር ላይ ችግር እየተደራረበ ነው። በዚህም በቢሊዮን የሚቆጠር የህዝብ ገንዘብ እየባከነ ነው።
ለምሳሌ ዋና ኦዲተር ከ2002 እስክ 2009 ዓ.ም ባደረገው ኦዲት አላግባብ ሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ተከፍሏል። ክፍያው የተፈጸመው በተለያየ ደረጃም ቢሆንም በ190 የፌዴራል ተቋማት ነው። ከዚህ ውስጥ ከፍተኛ ከፍያ የፈጸሙ 35 ተቋማት ናቸው። በአጠቃላይ በየዓመቱ በርካታ የኦዲት ግኝት የሚገኝ ሲሆን ማስተካከያ ግን እየተደረገ አይደለም።
ዋና ኦዲተር በየዓመቱ በሚያቀርበው ኦዲት በተለያዩ የኦዲት ዓይነቶች ከፍተኛ መጓደልን ያሳያል። የኦዲት ጉድለቱን መሰረት ተደርጎ ዕርምጃ ሳይወሰድ ቆይቷል። ይህ የተደራረበ ችግር ያስጨነቀው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ዓመት አላግባብ የተከፈለው ሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ለማስመለስ በዋና አፈጉባዔው ልዩ ኮሚቴ አቋቁሞ ነበር። ሆኖም አላግባብ የተከፈለውን ገንዘብ ማስመለስ አልቻለም።
የተቋቋመው ልዩ ኮሚቴም በግንቦት 2011 ዓ.ም ላይ ገንዘቡን ማስመለስ ባለመቻሉ በጠቅላይ አቃቢ ህግ በኩል በመክሰስ ገንዘቡን እንዲመልሱና ተጠያቂ እንዲሆኑ የውሳኔ ሃሳብ ለምክር ቤቱ አቅርቧል። ምክር ቤቱም የውሳኔ ሃሳቡን በማጽደቅ በጠቅላይ አቃቢ ህግ እንዲከሰሱ ኃላፊነት ሰጥቷል።
ውሳኔ ከተላለፈ ዘጠኝ ወራትን ቢያስቆጥርም እስከአሁን ገንዘብ አለመመለሱን የፌዴራል ዋና ኦዲተር አስታውቋል። ጠቅላይ አቃቢ ህግ በ14 ተቋማት አላግባብ ገንዘቡን የከፈሉ ኃላፊዎች፣ ሠራተኞችና ተባባሪዎቻቸው ላይ በቅርብ ክስ እመሰርታለሁ ቢልም እስከአሁን ገንዘቡን ከሶ አላስመለሰም። ምክር ቤቱ ለጠቅላይ አቃቢ ህግ ክስ መስርቶ ገንዘብ እንዲያስመልስ ውሳኔ ቢያሳልፍም ገንዘቡን በማስመለስ ረገድ ምንም ውጤት አልመጣም።
ምክር ቤቱና ጠቅላይ አቃቢ ህግ የፌዴራል ዋና ኦዲተር በየዓመቱ የሚያቀርበውን የኦዲት ግኝት መሰረት በማድረግ ተቋማቱ እንዲስተካከሉና ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባቸው ነበር። ነገር ግን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህን ኃላፊነቱን ለበርካታ ዓመታት አልተወጣም። ጠቅላይ አቃቢ ህግም በቢሊዮን የሚቆጠር የህዝብ ገንዘብ በህገ ወጥ መንገድ ሲባክን ህጋዊ ዕርምጃ ከመውስድ ይልቅ ከዳር ቆሞ ተመልካች መሆን የለበትም። ስለሆነም ሁሉም ኃላፊነታቸውን በሚገባ መወጣት አለባቸው፡፡
አገሪቱ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እየተበደረችና ከድሃው ህዝብ አፍ ተፍልቅቆ የሚሰበሰብ ግብር አላግባብ ማባከን በአገር መቀልድ ነው። በመንግሥት ኃላፊነት ላይ ሆኖ ይህን እያዩ ለበርካታ ዓመታት የማስተካከያ ዕርምጃ አለመውስድ ደግሞ አገርን መካድ በህዝብም መቀለድ ነው። አገሪቱ በብዙ ቢሊዮኖች ዶላር እዳ ውስጥ ናት። ይህ እዳ አገሪቱን ወደ አጣብቂኝ እየወሰዳት ነው። በዚህ በኩል ደግሞ የህዘብ ገንዘብ ያለተጠያቂነት እየባከነ ነው። ይህን ችግር በአስቸኳይ አለመፍታትና ዝም ብሎ መመልከትም በአገርና በህዝብ መቀልድ ነው። ስለሆነም የኦዲት ግኝቶች በየጊዜው ይታረሙ። ያለፈውም ስህተት ሳይውል ሳያደር ተጠያቂነት በሚያሰፍን መልኩ መፍትሔ ይሰጠው፡፡ የህግ የበላይነት በማስፈን የህዝብ ገንዘብ ለህዝብ ይዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 24/2012