መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በዓለም አቀፍ ደረጃ እናቶች በእርግዝናና በወሊድ ወቅት ከማህፀን ደም መፍሰስ፣ኢንፌክሽን፣ከፍተኛ የደም ግፊትና የጠና ምጥ ጋር በተያያዘ ለሞት ይዳረጋሉ፡፡በኢትዮጵያ 70 በመቶ የሚሆኑት እናቶች የሚሞቱት ከወሊድ በኋላ በሚያጋጥም መድማት መሆኑም ይጠቆማል፡፡ እናቶች በቤት ውስጥና ጤና ተቋማት እስከሚደርሱ በሚፈጠረው መዘግየትም ሞት ይይከሰታ፡፡
ኢትዮጵያ ይህን የእናቶች ሞት ለመቀነስ የሚያስችሉ በርካታ ዘርፈ ብዙ ተግባሮችን አከናውናለች፡፡ በእነዚህም ሥራዎች የእናቶችና ሕፃናት ሞትን መቀነስ ችላለች፡፡ ከወሊድ ጋር በተያያዘ ከአንድ ሺ እናቶች ስድስት መቶዎቹ ለሞት ይዳረጉ የነበረበትን ሁኔታ ወደ 410 ዝቅ ማድረግ መቻሉም ማሳያ ይሆናል፡፡ በምእተ ዓመቱ የልማት ግቦች በጤናው ዘርፍ ከተቀመጡ ግቦች ስኬታማ የሆነችው አንድም በዚሁ የእናቶችና ሕፃናትን ሞት በመቀነስ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ሀገሪቱ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ አሁንም ርብርቧን አጠናክራ ቀጥላለች፡፡ እናቶች በጤና ተቋማት ክትትል እንዲያደርጉና እንዲወልዱ የሚያስችሉ ተግባሮች እየተከናወኑ ናቸው፡፡ የጤና ተቋማት እየተስፋፉ እንዲሁም በእናቶችና ሕፃናት ላይ የሚሠሩ የጤና ባለሙያዎች ቁጥር እንዲጨምር እየተደረገ ነው፡፡ የአምቡላንስ አገልግሎት እየተስፋፋ በመምጣቱ እናቶች በአስቸኳይ ወደ ጤና ተቋማት እንዲደርሱ የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ጉልህ ስፍራ ካላቸው ተግባሮች መካከል በሀገሪቱ በየዓመቱ እየተከበረ የሚገኘው የጤናማ እናትነት ወር ይገኝበታል፡፡ ዘንድሮም ወሩ ከነገ አንስቶ ‹‹በደም መፍሰስ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን በጋራ እንታደግ›› በሚል መሪ ሃሳብ ለአንድ ወር የተለያዩ ትምህርታዊ ቅስቀሳዎች በማድረግ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ13ኛ፣ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ደረጃ ደግሞ ለአምስተኛ ጊዜ ይከበራል፡፡
ወሩ መከበሩ እናቶች በጤና ተቋማት ቅድመና ድህረ ወሊድ ክትትል በማድረግ ራሳቸውም ሆኑ ሕፃናት ለከፋ ችግር እንዳይጋለጡ ለማድረግ ያስችላል፡፡ በወሊድ ምክንያት እናትም ልጅም እንዳይሞቱ ለተያዘው አቅድ መሳካት ጉልህ ስፍራ ይኖረዋል፡፡
ወሩ በአዲስ አበባ ከሚከበርባቸው መንገዶች መካከል ጥር 8 ቀን 2011ዓ.ም በጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ውስጥ የሚካሄደው የደም ልገሳ መርሐ ግብር ይገኝበታል፡፡ እናቶች በወሊድ ወቅት ደም እንደሚያስፈልጋቸው የሚታወቅ እንደመሆኑ ደም በመለገስ መርሀ ግብሩ ውጤታማ እንዲሆን በማድረግ ኃላፊነትን መወጣት ያስፈልጋል፡፡ ህብረተሰቡ ይህን ኃላፊነቱን እንዲወጣ ለማድረግ የሚመለከታቸው አካላት ቅስቀሳ በማድረግና ደም ለጋሾች ሲቀርቡም በማስተናገድ ኃላፊነታቸውን መውጣት ይኖርባቸዋል፡፡
የጤናማ እናትነት ወር የዛሬ ወጣት ሴቶች የወደፊት እናቶችን ጭምር በማሳተፍ ለማክበር መታቀዱ ያልተለመደ እና ለውጤታማነት የሚያበቃ መሳሪያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ወጣቶች በእናትነት ወቅት ለችግር እንዳይደረጉ ከወዲሁ ማከናወን ባለባቸው ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የሚያስችል ሁነኛ ማስተማሪያ እንደመሆኑም በቀጣይም ተጠናክሮ ሊሠራበት ይገባል፡፡
በወሩ የሚፈጸሙ ተግባሮች በጤናው ዘርፍ እየተከናወኑ ለሚገኙ ሥራዎች የራሳቸውን ሚና ያበረክታሉ፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን አቅድ ላይ በ2007 እንደተደረሰበት ከተገመተው ከ10ሺ እናቶች 420 ከነበረው የሞት መጠን በ2012 ዓ.ም ወደ 199 ዝቅ ለማድረግ የተጣለውን ግብ እንዲሁም በሰለጠኑ ባለሙያዎች በመታገዝ የወሊድ አገልግሎት ያገኙ እናቶች ሽፋንን በ2007 ከነበረበት 60 ነጥብ 7 በመቶ በ2012 ወደ 90 በመቶ ለማሳደግ የተያዘውን እቅድ ለማሳካትም የራሳቸውን ሚና ይጫወታሉና ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል፡፡
የጤናማ እናትነት ወርን ለመንግሥት መስሪያ ቤት ሠራተኞች የካንሰር ምርመራ በማድረግ የሚከበርበት ሁኔታም እንዳለ ከቅዱስ ጳውሎስ ሜዲካል ኮሌጅ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡ ይህም ለእናቶች የጤና ችግርና ሞት እየሆነ የሚገኘውን የማህጸን በር እና የጡት ካንስርን ለመከላከል ሀገሪቱ የተያያዘችውን ጥረት ለማሳካት ይረዳል፡፡ ሴት የመንግሥት ሠራተኞች ይህን ደጃቸው ድረስ የሚመጣ መልካም አጋጣሚ መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡
እናቶች በጤና ተቋማት እንዲወልዱ ለማድረግ እየተከናወነ ያለው ተግባር አልጋ በአልጋ እንዳልሆነ ይታመናል፡፡ የመሰረተ ልማት ችግር ፣ የጤና ባለሙያዎች ሩህሩህነት ማነስ አሁንም ተግዳሮት መሆናቸውን የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ፡፡
አምቡላንስ በታሰበው ፍጥነት አገልግሎት መስጠት እንዲችል መንገዶች ምቹ ሊሆኑ ይገባል፡፡ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ከተያዘው እቅድ በመነሳት አምቡላንስ ገጠር ድረስ የሚዘልቅ እንደመሆኑ መንገዶችን ምቹ በማድረግ በኩል የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡
የህሙማን ባህሪ በራሱ አስቸጋሪ መሆኑ ፣ ሀገሪቱ ለጤና ባለሙያዎች የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ማድረግ የማትችል መሆኗ ባለሙያው ለሥራው ያለውን ተነሳሽነት ሊያጎድለው ይችላል፡፡ ይሁንና ባለሙያው ስለእናቶች ብሎ ርህራሄ ተላብሶ ሊሠራ ይገባል፡፡ ይህ ርህራሄ በገንዘብ ሊተመን አይችልም፡፡ ከጥሩነት ብቻ የሚመነጭ ነውና ለእናቶች ለሚደረግ ርህሩህነት ሰፊ ቦታ መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡
የጤና ባለሙያዎች ርህራሄ የተሞላበት አገልግሎት ለመስጠት በመንግሥት ደረጃ የተያዙት ተግባሮችም ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል፡፡ የጤና ባለሙያዎችም በግልም ይሁን በማህበር የእነዚህን የባልደረቦቻቸውን ክፍተት ለመሙላት ሥራ ይኖርባቸዋል፡፡ የጥር ወር የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ብዙ የሚሠራበት ወቅት ይሁን እንጂ ምንጊዜም ቢሆን እናቶችን ከሞት የመታደግ ተግባርን በቸልታ የምናልፈው ሊሆን አይገባም፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2011