ከዓለም ምርጥ የማራቶን ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው የቦስተን ማራቶን ከዚህ ቀደም ማሸነፍ የቻሉና የዓለም ቻምፒዮን የሆኑ አትሌቶች ዘንድሮ የሚፋለሙበት በመሆኑ በጉጉት እየተጠበቀ ይገኛል። የዓለም አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ የሰጠው ይህ ውድድር በተለይ በሴቶች ምድብ ባለ ክብረወሰኗን ኢትዮጵያዊት አትሌት ወርቅነሽ ደገፋን ጨምሮ ከዓለም ዙሪያ የተሰባሰቡ አምስት ከ2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ እንዲሁም አስራ ሁለት 2 ሰዓት ከ23 ደቂቃ በታች ማራቶንን ማጠናቀቅ የቻሉ አትሌቶች ተሳታፊ መሆናቸው ውድድሩን ተጠባቂ አድርጎታል።
የአሸናፊነት ቅድመ ግምቱ ለቦታው ባለ ክብረወሰን ለሆነችው አትሌት ወርቅሽ የሚሰጥ ቢሆንም፤ ከባድ ፉክክር የሚገጥማት መሆኑ ውድድሩን ይበልጥ አጓጊ አድርጎታል። እአአ በ2018 የውድድሩ አሸናፊ የነበረችው አሜሪካዊቷ ዴስሬ ሊንደን፣ የሁለት ጊዜ በየዓለም ቻምፒዮናዋ ኬንያዊት ኤድና ኪፕላጋት፣ እአአ በ2015 የቦታው ባለ ድል ካሮላይን ሮቲች እንዲሁም እአአ በ2014 የቦታውን ክብረ ወሰን የሰበረችው ኢትዮጵያዊቷ ብዙነሽ ዳባ የቦስተን ከተማ በምታስተናግደው ታላቁ የጎዳና ላይ ሩጫዋ ድምቀት የሚሆኑና ከ2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ በታች መሮጥ የቻሉ አትሌቶች መሆናቸውን አዘጋጆቹ አረጋግጠዋል።
እአአ በ2015 የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ነሃስ ሜዳሊያ ባለቤቷ ማሬ ዲባባ እንዲሁም በዚያው ቻምፒዮና የ10 ሺ ሜትር የብር ሜዳሊያ ያገኘችው ገለቴ ቡርቃ፣ መስከረም አሰፋ፣ የብርጓል መለሰ፣ በሱ ሳዶ እንዲሁም ሃፍታምነሽ ተስፋይ ደግሞ ሌላኛዎቹ በውድድሩ ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ የሚጠበቁ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው።
የ2017ቱ የዓለም ቻምፒዮን ባህሬናዊቷ ሮዝ ቺሊሞ፤ ያለፈው ዓመት የቶሮንቶ ማራቶን አሸናፊዋ ማግዳላይኔ ማሳይ፣ በሮም ማራቶን የሶስት ጊዜ ባለድል ራህማ ቱሳ፣ በ2018 ቦስተን ማራቶንን በሶስተኝነት ያጠናቀቀችው ክሪስታ ዱቼኔ እንዲሁም የሁለት ጊዜ የዓለም ግማሽ ማራቶን ቻምፒዮናዋ ሜሪ ንጉጊም በዚህ ማራቶን ላይ ተሳታፊ የሚሆኑና ለአሸናፊነቱ ቀላል ግምት የማይሰጣቸው አትሌቶች ናቸው።
በወንዶች በኩልም ብርቱ ፉክክር እንደሚኖር ማሳያ የሆኑ አትሌቶች እንደሚካፈሉ የታወቀ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከል አስር የሚሆኑት ማራቶንን 2 ሰዓት ከ07 እና ከዚያ በታች የሆነ ሰዓት ማጠናቀቅ የቻሉ አትሌቶች ናቸው። ያለፈው ዓመት የቦስተንና የቺካጎ ማራቶን አሸናፊው ኬንያዊ አትሌት ላውረንስ ቼሮኖ ክብሩን እንደያዘ ለመቆየት፤ ከዚህ ቀደም የነበሩ የቦስተን ማራቶን አሸናፊ አትሌቶችን መጋፈጥ የግድ ይለዋል። የሁለት ጊዜ የቦስተን ማራቶን አሸናፊውና የዶሃው የዓለም ቻምፒዮና ባለድሉ ሌሊሳ ዴሲሳ ዘንድሮም ሌላ ድል ለማስመዝገብ በቦስተን የሚገኝ መሆኑን አስታውቋል። እአአ የ2017 አሸናፊው ጃፓናዊ ዩኪ ካዋቺ እና የ2018ቱ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤቱ ጂኦፈሪ ኪሩይም በቦታው ድላቸውን ለመድገም ተዘጋጅተዋል።
ኡጋንዳዊው የኦሊምፒክና የዓለም ቻምፒዮን ስቴፈን ኪፕሮቲች፣ አልበርት ኮሪር፣ ኤርትራዊው አብራር ኦስማን፣ ኢትዮጵያውያኑ ደጀኔ ደበላ፣ ፍቅሬ በቀለ፣ ጀማል ይመር እንዲሁም ከሌሎች አገራት የተውጣጡ በርካታ አትሌቶችም በአሜሪካው ግዙፍ የጎዳና ላይ ሩጫ ተሳታፊ መሆናቸውን አዘጋጆቹ አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 23/2012
ብርሃን ፈይሳ