የዓለምን እግር ኳስ የሚመራውና 211 አባላት ያሉት ፊፋ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን ከአራት ወራት በኋላ ያደርጋል። ለአዘጋጅነቱ ደግሞ አፍሪካ የተመረጠች ሲሆን፤ የአህጉሪቱ መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባም ኃላፊነቱን ተረክባ ወደ ዝግጅቱ በመንደርደር ላይ ትገኛለች። ከሁለት ዓመታት በፊት የካፍን 60ኛ ዓመት ምስረታ ተከትሎ ጠቅላላ ጉባኤውን በስኬት ያጠናቀቀችው አዲስ አበባ ፤ 69ኛውን ጉባኤ ባሰናዳችውና ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖን ዳግም ለመሪነት በተመረጡበት የፓሪሱ ጉባኤ ላይ 70ኛውን መድረክ እንድታዘጋጅ መመረጧ ይታወቃል።
ለዚህ የሚሆነውን ዝግጅት አስቀድማ የጀመረችው ኢትዮጵያ ለጉባኤው አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ከሰሞኑ ምክክር ያደረጉ መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በድረ ገጹ አስነብቧል። ዝግጅቱን ለማድረግም ከስፖርት ኮሚሽን፣ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት፣ የኢሚግሬሽን ጉዳዮች፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት፣ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ አየር መንገድ፣ ገቢዎችና ጉምሩክ፣ የወጣቶች ስፖርት አካዳሚ፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር፣ የብሮድካስት ባለስልጣን፣ ብሄራዊ መረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የተውጣጡ አካላት ጥምረት ፈጥረዋል።
ለጉባኤው ዝግጅት የሚያደርግ ብሄራዊ አብይ ኮሚቴም የተዋቀረ ሲሆን፤ የኮሚቴው የበላይ ጠባቂም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ናቸው። ሰብሳቢዎቹ ደግሞ ኮሚሽነሩ አቶ ኤሊያስ ሽኩርና የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያሥ ጂራ መሆናቸው ታውቋል። በመጠናቀቅ ላይ ባለው ሳምንትም ኮሚቴው በዕቅድ ዝግጅቱ ላይ ውይይት ያደረገ ሲሆን፤ የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዱቤ ጂሎ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያሥ ጂራ፣ የካፍ ተወካይ ወይዘሪት መስከረም ታደሰ እንዲሁም ሌሎች ተገኝተዋል። ጉባኤው ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ የሚያስችል መነሻ ሰነድ ቀርቦም ምክክር ተደርጎበታል።
በፊፋ ኮርፖሬት ኢቨንት ማናጀር ካትሪን አስተርበርገር በበኩላቸው ለጉባኤው ዝግጅት በቀዳሚነት መከናወን ያለባቸው ጉዳዮች ላይ ገለጻ አድርገዋል። ከተማዋ ትልልቅ ስብሰባዎችን ለማስተናገድ አዲስ ባትሆንም ወሳኝ የሚባሉ ጉዳዮች ላይ ግን በተለየ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል። የመጀመሪያውም ከፊፋ አባላት ባሻገር ቁጥራቸው በዛ የሚል ሌሎች አካላትም በጉባኤው ወቅት የሚገኙ መሆኑን ነው ማናጀሯ የጠቆሙት። 1 ሺ400 ከሚሆኑት የጉባኤው ተሳታፊዎች ባሻገር 600 ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚና አፍሪካ ህብረት የሚሰሩ እንዲሁም ጉባኤውን ውጤታማ ለማድረግ የሚረዱ 300 ባለሙያዎች ከጉባኤው ሁለት ሳምንት አስቀድመው አዲስ አበባ የሚገኙ ይሆናል።
በጉባኤው ተሳታፊ ለሚሆኑ አባል አገራት ተወካዮች ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት የትኛውን የቪዛ ዓይነት መጠቀም እንደሚገባቸው መለየት እንዲሁም የህክምና አገልግሎት በምን መልክ ማግኘት አለባቸው በሚል ቅድመ ዝግጅት ማድረግም ሌላኛው ነው። ጉባኤው ሲካሄድ በመንገዶች የትራፊክ መጨናነቅ እናዳይፈጠር፣ የመጓጓዣ አማራጮች እንዲሁም መጓጓዣዎች የአቅጣጫ አመልካች መሳሪያ መግጠም እንደሚያስፈልግም ማናጀሯ አሳስበዋል። ለጉባኤው አስፈላጊ የሆኑ መሳሪያዎች ወደ አገሪቷ ሲገቡ በገቢዎችና ጉምሩክ እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ትብብር እንዲያደርጉ፣ ጉባኤውን ለመዘገብ የሚገኙ የመገናኛ ብዙሃን የሚገቡበት ቪዛ ምን መሆን አለበትና የተሳታፊነት ማረጋገጫ ወረቀት በምን መልኩ ማግኘት አለባቸው በሚለው ጉዳይ ላይም ምላሽ መስጠት ይጠበቃል።
ለቴሌኮም አገልግሎት የሚውሉ 400 ሲም ካርዶች፣ 4ጂ ኢንተርኔት እና የሬዲዮ መገናኛ ዘዴዎችን ማዘጋጀትም እንደሚያስፈልግና ለጉባኤው ተሳታፊዎች የደህንነት ዋስትና መስጠት እንደሚገባ ተጠቁሟል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 23/2012
ብርሃን ፈይሳ