በቻይና ውሃን ከተማ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ (የኖቭል ኮሮና ቫይረስ – Novel Coronavirus ) እስካለፈው ዕረቡ ዕለት ድረስ ብቻ 170 ሰዎችን ቀጥፏል። የቻይና ጤና ሚኒስቴር ይፋ እንዳደረገው 7 ሺ 711 ሰዎች በቻይና ብቻ በበሽታው ከመያዛቸው በተጨማሪ በቻይና ውሃን (Wuhan) ግዛት የተከሰተው ቫይረስ በአስደናቂ ፍጥነት ወደ 16 አገራት መዛመቱን ቢቢሲ ዘግቧል። እነኒውዮርክ ታይምስ እስከ ሐሙስ (ጥር 21 ቀን 2012 ዓ.ም) ዕለት ጠዋት ድረስ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 7ሺ 700፣ የአገራቱን ቁጥር ወደ 18 ከፍ ማለቱን ዘግበዋል። የሁሉም አገራት ሰዎች በበሽታው የተያዙት ወደቻይና ለተለያዩ ጉዳዮች በመጓዛቸው ነው። በቫይረሱ ከተያዙት የውጭ ዜጎች መካከል ካናዳ (3)፣ ዩናይትድ ስቴትስ (5)፣ ፈረንሳይ (5)፣ጀርመን (4)፣ሲንጋፖር (10)፣ አውስትራሊያ (6)… ይገኙበታል።
ኒውዮርክ ታይምስ እንደዘገበው የቫይረሱ ምልክት ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው፤ በውሃን (Wuhan) ከተማ አንድ የባህር ምግቦችና የዶሮ ውጤቶች መሸጫ ሱፐርማርኬት መሆኑን ይፋ አድርጓል። ውሃን የቻይናዋ ሁቤ ግዛት መናገሻ ከተማ ናት። ወደ 11 ሚሊዮን ሕዝብ በመያዝ ከቻይና ከተሞች በሕዝብ ብዛት 7ኛ ረድፍ ላይ ተቀምጣለች። የዓለም ጤና ድርጅት የኖቭል ኮሮና ቫይረስ በሽታ ከታህሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በቻይና ውሃን ክልል መከሰቱን ማረጋገጡ የሚታወስ ነው።
በኢትዮጵያዊው ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የሚመራው የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ባለፈው ማክሰኞ ዕለት በሽታውን በፍጥነት መመከት ስለሚቻልበት ሁኔታ ዓለም አቀፍ ምክክር አካሂዷል። ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ብቻ በሽታው በፍጥነት ከሰዎች ወደ ሰዎች እየተዛመተ መሆኑን ለተሰብሳቢው አረጋግጠዋል።
ሳይንቲስቶች ለቫይረሱ ክትባት ለማግኘት ደፋ ቀና እያሉ ቢሆንም የቫይረሱ የመዛመት ፍጥነት ትንፋሽ የሚሰጥ አልሆነም። የክትባት ተስፋ ስለመኖሩም ይኸ ጹሑፍ እስከተጠናቀረበት ሐሙስ ዕለት ድረስ የተጨበጠ ነገር የለም።
የበሽታው መከሰት በቻይና ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ቀላል የማይባል መደናገጥን ፈጥሯል። የቻይናን ጠንካራ ኢኮኖሚ መነቅነቅም ጀምሯል። ቻይና ግን ችግሩ እንደተከሰተ ፊትዋን በፍጥነት ወደ አደጋ መከላከል መልሳለች። በውሃን ግዛት በስድስት ቀናት የሚጠናቀቅ ትልቅ ሆስፒታል ለመገንባት ተነስታ በ48 ሰዓታት ጊዜ ውስጥ 1000 አልጋ ያለው ዘመናዊ ሆስፒታል ገንብታ ለአገልግሎት በማብቃት ዓለምን በአግራሞት አፍ አስከፍታለች። ሆስፒታሉ የኢንተርኔት አገልግሎት ጭምር ያነገተ፣ እጅግ ዘመናዊ ሲሆን ሕሙማንን ተቀብሎ ማ ስተናገድ ጀምሯል።
በቀላሉ ከሰዎች ወደ ሰዎች የሚተላለፈው ይኸው ወረርሽኝ መሰል አደጋ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ እንደጠበል ማዳረስ ይዟል። ከችግሩ ጋር ተያይዞ በርካታ አየር መንገዶች ወደቻይና በተለይ ውሃን ከተማ የሚያደርጉትን በረራዎች የሰረዙ ሲሆን እንደዩናይትድ ስቴትስ፣ ብሪታኒያ፣ ደቡብ ኮርያ፣ ካናዳ፣ ፍሊፒንስ፣ማሌዥያ እና የመሳሰሉ አገራት ዜጎቻቸውን ከውሃን ከተማ በፍጥነት በማውጣት ሥራ ላይ ተጠምደው ከርመዋል። በተጨማሪም ራስዋ ቻይና በወሰደችው የጥንቃቄ እርምጃ መሠረት የአውሮፕላን፣ የባቡር፣ የአውቶቡስ እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ሆኗል። የቻይና እግርኳስ ፌዴሬሽን “ስፖርት ለጤንነት” የሚለውን መርህ ተከትሎ የ2020 ውድድሮችን በሙሉ ለመሰረዝ ተገዷል። በቻይና የሚገኙ ግዙፎቹ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጎግል፣ ስታርባክስ እና ቴስላ ሥራ ለማቋረጥ ተገደዋል። ውርጅብኙ ቻይናን እያራዳት ይገኛል። ለወትሮ በመኪና ጢም የሚሉት የውሃን አውራ ጎዳናዎች ባልተለመደ መልክ ጭር ብለው ለተመለከተ አጃኢብ መሰኘቱ አይቀርም።
የኖቭል ኮሮና ቫይረስ (Novel Coronavirus ምንድነው?
የኖቭል ኮሮና ቫይረስ (Novel Coronavirus) በቫይረሱ የተያዘ ሰው ወደ ጤነኛ ሰው በቀላሉ ሊተላለፍ የሚችል የህመም አይነት ስለመሆኑ በዶ/ር ሆነሊያት ኤፍሬም ቱፈር በሶሻል ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ልክ እንደጉንፋን በበሽታው የተያዘ ሰው በሚያስል እና በሚያስነጥስ ጊዜ፣ ማንኛውም አይነት የንክኪ ወቅት እና በቫይረሱ የተበከሉ ቁሳቁሶችን በመንካት ይተላለፋል።
የኮሮና ቫይረስ የተያዘ ሰው የሚያሳያቸው ምልክቶች ከላይኛው የመተንፈሻ አካል ኢንፌክሽን
(Upper respiratory tract infection) ምልክቶች ጋር ተመሳሳይ ናቸው። እነዚህም፡- የራስ ምታት ህመም፣ ትኩሳት፣ ሳል፣ የአፍንጫ ፈሳሽ፣ የጉሮሮ ህመም፣ የድካም ስሜት፣ ትንፋሽ ማጠር ናቸው።
ለኮሮና ቫይረስ እስካሁን ምንም አይነት ህክምና ወይም ክትባት ያልተገኘለት ሲሆን ለኢንፌክሽኑ ተጋላጭነትን ለመከላከል የእጅዎን ንፅህና በሚገባ በውሃ እና በሳሙና በመታጠብ መጠበቅ፣ በተጨናነቀ እና አየር እንደልብ በማይዘዋወርበት ቦታ አለመገኘት፣ አፍዎን፣ አፍንጫዎንና አይንዎን ፅዱ ባልሆነ እጅዎ አለመንካት፣ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጋር ያለዎትን ቅርርብ መቀነስ ናቸው።
የኢትዮጵያ ዝግጅት
ከጤና ሚኒስቴር በተገኘ መረጃ መሠረት ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል ከሁሉም ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ መንገደኞች የሙቀት ልየታ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ በቻይና የተከሰተው እና አሁን ላይ በተለያዩ 10 የዓለም ሀገራት የታየው የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ የመከላከል ስራዎች ተጠናከረው እየተሰሩ መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም የመንገደኞች የሙቀት መለኪያ መሳሪያዎች በሁሉም ስፍራዎች መተከላቸውን እና ይህም ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኞች በመሳሪያው እያለፉ የሰውነታቸው የሙቀት መጠን እንዲለካ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ከቻይና እና ሌሎች ቫይረሱ ከታየባቸው 10 በላይ ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሰዎችን ደግሞ እያንዳንዳቸው በየግል የሰውነት ሙቀት ልኬት እና ስለ ራሳቸው መረጃ እና ስለሚሰማቸው ስሜት ቅፅ እንዲሞሉ እየተደረገ ስለመሆኑም ገልፀዋል።
ቅፅ የሞሉ ሰዎችም ምንም እንኳ ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ የትኩሳት እና የሳል ምልክት ባይታይባቸውም በሞሉት ቅፅ መሰረት በሚኖሩበት አድራሻ ድረስ በመሄድ በየቀኑ የህክምና ክትትል እየተደረገባቸው ስለመሆኑም ነው የተናገሩት።
ዶክተር ሊያ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ፋና 90 ጋር በነበራቸው ቆይታም፥ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል በዓለም አቀፉም በሀገር ውስጥ መንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል በኩል የሚገቡ ሁሉም መንገደኞች የሙቀት መጠናቸው እየተለካ እንዲያልፉ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
ለየት ያለ የሙቀት ልኬት የተገኘባቸው መንገደኞች ከተገኙም ለብቻቸው የሚቆዩበት በቦሌ ጨፋ እስከ 30 ሰው የሚይዝ ኳራንቲን ማእከል መዘጋጀቱን እና ሌላ ተጨማሪ ቦታ የማዘጋጀት ስራ እየተሰራ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በኮሮና ቫይረስ በመያዝ የተጠረጠሩ እና በሀገር ውስጥ ምርመራ ነፃ መሆናቸው የተረጋገጠ አራት ኢትዮጵያውያን አሁንም ለብቻቸው ተለይተው ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑንም አስታውቀዋል።
ከእነዚህም ውስጥ የሳል እና የትኩሳት ምልክት የታየባቸው ሁለት ሰዎች ብቻ ናቸው፤ ሁለቱ አብረው ስለመጡ ብቻ አብረው እንዲለዩ ተደርጓል ያሉት ዶክተር ሊያ፥ ምልክት የታየባቸው ሁለቱ ኢትዮጵያውያንም አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ እየጠፋላቸው መሆኑን ገልፀዋል። ለተጨማሪ ምርመራ ናሙናቸው ወደ ደቡብ አፍሪካ መላኩን በማስታወስ፥ የማረጋገጫ ምርመራው በሁለት ቀናት ውስጥ ይደርሳልም ነው ያሉት።
ምርመራውን በሀገር ውስጥ በቀጣይ ሳምንት ለማስጀመር በሂደት ላይ እያለም ነው ዶክተር ሊያ አክለው የገለፁት።
ለባለሙያዎችም ከቅድመ ጥንቃቄ ጀምሮ ሽታውን መከላከል እና ማከም ዙሪያ ግንዛቤ የመፍጠር እና ስልጠናዎች እየተሰጡ ነው ያሉት ዶክተር ሊያ፥ ሌሎች ግብአት የማሟላት ስራ እየተሰራ ስለመሆኑን አስታውቀዋል።
ኖቬል ኮሮና ቫይረስ አስቀድሞ መከላከልን አስመልክቶ እየተሰራ ያለው የቅድመ መከላከልና ጥንቃቄ እንዲሁም የድንገተኛ አደጋ ምላሽ ሥራዎች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ።
- በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከ ቻይና እና አጎራባች አገሮች ለሚመጡ መንገደኞች የሙቀት ልየታ (thermal screening) እና ፎርም የማስሞላት ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል። የልየታ ስራውን ለማጠናከር በቂ የሰው ኃይል ተመድቧል።
- በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ጊዜያዊ የለይቶ መከታተያ ክፍልና የሰው ሃይልን ጨምሮ አስፈላጊው ግብአት ተዘጋጅቷል።
- በበሽታው ለተጠረጠሩ መንገደኞች የጊዜያዊ ማቆያ ማዕከል በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ውስጥ ተዘጋጅቷል፤
- የከፋ ሁኔታ ላልታየባቸው 30 ለሚሆኑ በበሽታው የሚጠረጠሩ ታካሚዎችን የሚይዝ የለይቶ ማከሚያ የህክምና ማእከል በቦሌ ጨፋ ተዘጋጅቶ አስፈላጊው የህክምና እና ልዩ ልዩ ግብአቶች የተሟሉ ሲሆን በዚህ ማእከል በሽታው የተረጋገጠባቸው፣ የተጠረጠሩ እና ተለይቶ ክትትል ለሚደረግላቸው ክፍሎች ተለይተው ተዘጋጅቷል።
- በጽኑ ለታመሙና ከፍተኛ የህክምና ክትትል ለሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል የተለየ ክፍል ተዘጋጅቷል።
- በጤና ሚኒስቴር የሚመራ የኖቭል ኮሮና ቫይረስ የወረርሽ ቅድመ ዝግጅት የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን በማካተት ብሄራዊ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ወደ ወደ ስራ ገብቷል።
በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚመራ የቴክኒካል ቡድን ተ ቋቁሞ ሥራውን ጀምራል።
በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ጋር በመሆን ለኖቭል ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ቅድመ ዝግጅት የአደጋ ማስተባበሪያ ማእከል (Emergency Operation Center ) ወደ ተግባር ገብቷል።
- በመደበኛነት የዓለማችንን ወቅታዊ ሁኔታ ክትትል በማድረግ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ወቅታዊ መረጃ እና ምክረ ሃሳብ እየተሰጠ ነው።
- የክልል እና የከተማ ጤና ቢሮዎችን አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉ በኢሜል ፣ በደብዳቤና በተለያዩ የመገናኛ መንገዶች የዓለም የጤና ድርጅት ምክረ ሐሳቦችን መሰረት ያደረገ የማንቂያ መልዕክት አስተላለፈናል።
- የዝግጁነትና ምላሽ ለመስጠት የሚረዳ የትግበራ እቅድ ተዘጋጅቷል።
- ለባለሙያዎችና ለሚመለከታቸው አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠት ተ ጀምሯል።
- ህብረተሰቡን ስለ ቫይረሱ ወረርሽኝ ለማንቃና ግንዛቤ ለመፍጠር የሚያስችል ወቅታዊ መረጃዎችን በተከታታይ ለሁሉም መገናኛ ብዙሃን እየተሰጠ ይገኛል፤ ክትትልም ይደረጋል።
- ሕብረተሰቡን፣ መንገደኞችን እንዲሁም የጤና ባለሙያዎችን ለማንቃት፣ አስፈላጊ የጤና ተግባቦት መረጃዎችን የማዘጋጀት እና የማሰራጨት ተግባራት እየተከናወነ ይገኛል።
- ከአፍሪካ ሲዲሲ እና ከዓለም የጤና ድርጅት ጋር በምክር እና ሪኤጀንትን በመተለከተ በትብብር ለመስራት ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ኮሮና እና ኢቦላ ምንና ምን ናቸው?
የኢቦላ በሽታ በቫይረሱ የሰው አካል ውስጥ መባዛት የሚመጣ፣ በፍጥነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው። ኢቦላ ቫይረስ ሰውነት ውስጥ ከገባ በኋላ የማያቋርጥ ደም መፍሰስ የሚፈጥር ሲሆን ዋነኛ ምልክቶቹም ከፍተኛ ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ ተቅማጥ፣ ድካም፣ ሆድ ቁርጠት፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ትውከት፣ በሰውነት የተለያየ ቦታና ሰውነት ውስጥ ደም መፍሰስ ናቸው።
ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍባቸው ዋና ዋና መንገዶች ከታማሚው ወይም ከአንዳንድ እንስሳት ዝንጀሮ፣ የሌሊት ወፍ ወዘተ ከሚወጡ ፈሳሽ ነገሮች ማለትም (ደም፣ ላብ፣ ምራቅ፣ ንፍጥ፣ ሽንት) ጋር ቀጥታ ንክኪ በማድረግ (በመጨባበጥ፣ መሳሳም፣ መነካካት) ነው።
ቫይረሱ ሰው ሰውነት ከገባ በኋላ ከ2 – 21 ቀን ምንም ምልክት ሳያሳይ የመቆየት ባህሪ ያለው ሲሆን በአብዛኛው ሠው ግን ከ8 -10 ቀናት ውስጥ ምልክቶቹ መታየት ይጀምራል።
በቫይረሱ የተያዘ ሰው 90 በመቶ ለሞት የመዳረግ (በማያቋርጥ ደም መፍሰስ) ምክንያት ያለው ሲሆን ያም ሆኖ በሽተኛው በተገቢው ቁጥጥር ስር ከዋሉ በሽታው የመዛመት ዕድል በጣም አናሳ ነው።
ቫይረሱ በተለያያ ጊዜ የማገርሸት ባህሪ ያለው ሲሆን በቅርብ በተለየ ሁኔታ በምዕራብ አፍሪካ አገሮች (በላይቤሪያ፣ ሴራሲዮንና ጊኒ) አገርሽቶ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱም አይዘነጋም።
በምስራቅ አፍሪካ ቫይረሱ አንድ ወቅት ላይ በሱዳን የታየ ሲሆን በኢትዮጵያ ቫይረሱ አልገባም።
እንግዲህ ከቻይናው ኮሮና ቫይረስ ጋር ኢቦላ ሊያመሳስለው የሚችለው ከመተላለፊያ መንገዶች መካከል በቀላሉ ከሰዎች ወደሰዎች መተላለፉ አንዱ ሲሆን ሌሎች የመተላለፊያ መንገዶች እና በፍጥነት ለሞት የመዳረጉ ሁኔታ ሊጠቀስ ይችላል።
ይህ ዓምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ አስተያየታቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሑፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 23/2012
ፍሬው አበበ