በታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ላይ የኢትዮጵያ እና የግብፅ (ምስር) ድርድር የዘወትር ጸሎት ከሆነ ውሎ አድሯል ። በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ እና ግብፅ ወቅታዊ ድርድር ከመሄዴ በፊት የኢትዮጵያ እና የግብፅን የጎሪጥ እየተያዩ ጥርስ መነካከሳቸውን የተመለከተ ትንሽ እንድል ይፈቀድልኝ ፤ ምንም እንኳን ብዙ የተባለለት ቢሆንም ። የኢትዮጵያ እና የግብፅ ነገር “ላዩ ዳባ ውስጡ ደባ “ ስለሆነ ሁኔታውን ደጋግመን ብንመለከተው የሚከፋ አይመስለኝም ። ጥንታዊቷ ግብፅ ጳጳሶቿን ተጠቅማ ቀጥሎም ደግሞ“ ወርቅ የተሸከመች አህያ የማትገባበት ቤት የለም “ እንዲሉ የስዊዝ ቦይ በ1869 እ.ኤ.አ መከፈት እና በኋላም የካምፕ ደቪድ ስምምነት ግብፅን ከኢትዮጵያ እጅጉን በተሻለ ደረጃ ከባድ ወይም ዘመደ ብዙ እንድትሆን አስችሏታል ። የግብፅ ዘመደ ብዙ መሆኗን እንደ ምሳሌ ሁለት አብይ ማስረጃዎችን መመልከት ይቻላል። አንደኛ፦ በ1870ቹ መጀመሪያ ላይ ከዲቭ እስማኤል ፓሻ ኢትዮጵያን መውረር ሲጀምር የወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉስ ነገስት አፄ ዮሀንስ አራተኛ እርዳታን በመሻት የአውሮፓ ሃገራት ማለትም ለታላቋ ብሪታኒያ ፣ ፈረንሳይ ፣ ሩሲያ እና ለሌሎች ደብዳቤ ፅፈው ነበር ። ነገር ግን“ የክረምት መሻገሪያህን በበጋ ተመልከት“ እንዲሉ ግብፅን የሆነ ነገር ቢሉ በስዊዝ ቦይ ላይ የሚኖራቸው ጥቅም ጥያቄ ውስጥ እንዳይገባባቸው በማሰብ አውሮፓዊ ሀገር ለአፄ ዮሀንስ ደብዳቤ ምላሽ የሰጠ አልነበረም። ሁለተኛ ፡- ኢትዮጵያ ግድብ ለመገንባት የሚሆን ገንዘብ ብድር ፈልጋ የተለያዩ ሀገራትን በሮች ብታንኳኳም ምላሽ የሰጣትም ሀገር እንዳልነበር የሚታወቅ ሃቅ ነው ። ነገር ግን“ እልህ ሚስማር ያስውጣል“ እንዲሉ ኢትዮጵያ ግድቡን በራሷ ለመስራት ቆርጣ ተነሳች ። ትንሹ የአስዋን ግድብ የተባለውን እንግሊዝ በ1899 እ.ኤ.አ ጀምራ በ1902 አ.ኤ.አ ጨርሳ ለግብፅ ያስረከበች ሲሆን የአስዋን ትልቁ ግድብ የሚባለውን ደግሞ ሩሲያ ሙሉ ወጪዋን በሚባል ሁኔታ የግድቡን ወጪ በመሸፈን በ1960 እ.ኤ.አ ጀምራ በ1970 እ.ኤ.አ ጨርሳ ለግብፅ አስረከበች። ለዚህ ነው ግብፅ ከኢትዮጵያ የተሻለች ቂጠ ከባድ ናት ማለቴ ።
በወርልድ ዋተር ካውንስል ገለፃ እና የተለያዩ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በአለማችን 40 % በመቶ የሚሆኑት ህዝቦች ሁለት መቶ ሀምሳ( 250 ) ወንዞችን በጋራ ይጠቀማሉ ። ከነዚህም መካከል ሀያ ስድስት (26 ) የሚሆኑ ሀገራት በውሃ እጥረት እና በአጠቃለይ ውሃን ምክንያት ባደረገ ፍጥጫ ውስጥ መግባታቸው ይሰማል ። በመሆኑም እነኝህ በውሃ አጥረት ምክንያት ፍጥጫ ውስጥ የገቡ ሀገራት በሚጋሯቸው ወንዞች ላይ የሚኖራቸውን የተጠቃሚነት መብት ለማሳደግ የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስዱ ይታያል ። ለምሳሌ ባንድ ወቅት ግብፅ ከአመታዊ በጀቷ ሰላሳ ሶስት (33 ) % የሚሆነውን ለመከላከያ ሃይሏ ወጪ ማድረጓ ዓለምን ሳይሆን ግብፃዊያንንም ያስገረመ እና ትኩረትን የሳበ ነበር።
ወደተነሳንበት ርዕስ እንመለስ እና ሰሞኑን በሚካሄድ ላይ ባለው የኢትዮጵያ እና የግብፅ ድርድር ማን ድርድሩን ባሸናፊነት እየመራ ነው ? ከድርድሩስ ኢትዮጵያ ምን ትጠብቅ ? በኢትዮጵያ እና በግብፅ እየታየ ያለው በአባይ ወንዝ ላይ ለመንገስ የሚታየውን መራኮት ላይ ከብዙ ነገር ጋር ሊያመሳስለው ይችላል ። እንደኔ ግን የሁለቱን ሀገራት ግብግብ በተወሰነው መልኩ የካፒታሊዝምን የኢኮኖሚዊ ገፅታ ሲይዝ ይታያል ። እንዴት ? ብሎ ለሚለው የሚከተለውን አመክንዮ እንመልከት። በካፒታሊስቶች አለም አንድ የቢዝነስ ድርጅት ቢታመም ሌላ የቢዝነስ ድርጅት አስታሞ ለማዳን ጥረት አያደርግም ። ለምን? ምክንያቱም በካፒታሊስቶች ስርአት የአንዱ ድርጅት መታመም እና መሞት ለሌላው ድርጅት ህይወት እና እድገት ነው ። ይህን እንድል ያስቻለኝ ምንድን ነው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ድክመቷ ለግብፅ ሰርግ እና ምላሽ ነው። ምክንያቱም በኢትዮጵያ ድክመት ለመጠቀም በተደጋጋሚ ግብፅ (ምስር) ስትታትር መታየቷን በምሳሌ አስደግፎ መግለፅ ስለሚቻል ። ለምሳሌ ጀብሀን ማን ነው ግብፅ ላይ ቢሮ ከፍቶ ያደራጀው ፤ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ ጦርነት ግብፅ ለማን ረዳች ፤ አሁንስ ቢሆን ግብፅ ኢትዮጵያ ላይ ችግር ለመፍጠር ላይ ታች እያለች አይደለም ወይ? ባንፃሩም አትዮጵያም የግብፅን ድክመት አትጠላውም ። ለዚህ ነው የኢትዮጵያን እና የግብፅን ግንኙነት ከካፒታሊስቶች የኢኮኖሚ ስርአት ጋር ያገናኘሁት ።
በድርድሩ ኢትዮጵያ በእውቀታቸው እና በሙያቸው አንቱ የተባሉ እንደነ ዶክተር ስለሺ በቀለ ያሉ ተደራዳሪዎቿን ማሰለፏ ድርድሩን በበላይነት እየመሩት እንዳለ እያየን ነው። የግድቡ ሙሌት ሃያ ዓመት ይፍጅ ቢባልም እንኳን ኢትዮጵያ አሸናፊ ናት ። እደግመዋለሁ? የግድቡ ሙሌት ሃያ አመት ይፍጂ ቢባልም እኳን አትዮጵያ አሸናፊ ናት። ለምን? አባይ ስንት ሺህ አመት እንዲሁ ሲፈስ ኖሮ የለም እንዴ? ነገር ግን አንዳንድ ፖለቲከኞች እና አክቲቪስቶች መንግስት የሚያብጠለጥሉበት አጀንዳ ያገኘን መስሎአቸው የሆነ ያልሆነውን ሲሉ ስሰማ የምትሰሩት እና የምትናገሩት ነገር የሀገርን ጥቅም ወደ ኋላ ጎትቶ የራሳችሁን የፖለቲካ ፍላጎት ለመጫን እንደፈለጋችሁ ያሳብቅባችኋል ። ሆኖም ግን ይህን ያልነው ለሀገራችን ነው ብትሉን “ የሽንኩርት ሌባ ሞኝነቱ ልሸተት ማለቱ “ እንደሆነ አትርሱት።
በአጠቃላይ በድርድሩ የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች “ለብልህ አይነግሩም ፣ለአንበሳ አይመትሩም“ የሆኑ አስተዋዮች ናቸው የሚል የፀና ሃሳብ አለኝ ። በምንም አይነት ስሌት የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፈው ሊሰጡ እንደማይችሉም እርግጠኛ ነኝ። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያዊ መሆናቸው ብቻ በቂ ነው። የኢትዮጵያንም ጥቅም አሳልፎ ለመስጠት ለድርድር የሚቀመጥ ካለ ተደራዳሪው እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል ፤ ግብፃዊ ነው የሚሆነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 23/2012
በአሸብር ሀይሉ