ምንም እንኳን ብዙ ጊዜ ያጋጠመኝ ቢሆንም የዛሬውን ጽሁፌን በቅርቡ ካጋጠመኝ አንድ ክስተት ብጀምር ጉዳዩን ግልጽ ያደርግልኛል ብዬ አምናለሁ። ባለፈው ሳምንት ለአንድ የመስክ ሥራ ወደ ደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ገጠራማ አካባቢ ሄደን ነበር። ከተማዋ የወረዳ ከተማ ናት። የገባነው አምሽተን ነበር። የዝግጅቱ አስተባባሪዎች ቀድመው ማረፊያ ይዘውልናል። ራት ከበላን በኋላ ወደተያዙልን ማረፊያዎች እየሄድን ነው። እንግዳ ናቸው ተብለን በከተማዋ ውስጥ የተሻሉ የሚባሉ ማረፊያዎች ናቸው የተያዙልን።
የተያዙልን ማረፊያዎች የተለያዩ ቦታዎች ስለነበሩ ሾፌሩ በየቦታችን እያደረሰን ነው። እንደ አጋጣሚ ሆኖ እኔ የመጨረሻው ነበርኩ። ሁሉንም ካደረሰ በኋላ እኔ ያለሁበት ቦታ ያለነው ጋዜጠኞች የመጨረሻዎቹ ነን። የመጀመሪያዎቹን እስከሚያደርስ ድረስ አብረን እየሄድን ነበር። እናም ይሄን የምነግራችሁን ገጠመኝ የማየት ዕድሉን አገኘሁ።
አንዲት ጋዜጠኛ ሁሉንም ቦታዎች እየሄደች ታያለች። የተሻለ ምቾት ያለው እየፈለገች ነው። ማንም ምቾት ስለማይጠላ አልገረመኝም። ሁላችንም ቢሆን አጥተን እንጂ ከዚያ የተሻለ ብናገኝ አንጠላም ነበር። ጋዜጠኛዋን በሥራ አጋጣሚ ከአንዴም ሁለቴ ተገናኝተን ስለምናውቅ ሰላም እንባባላለን። እናም ከአንደኛው ግቢ እንደወጣን በር ላይ አገኘኋትና ስሟን ጠርቼ ላወራት ስል አኩርፋለች። ያኮረፈችው እሷ የምትፈልገው አይነት ደረጃ ያለው ሆቴል ባለመኖሩ ነው። እንግዲህ በከተማዋ ውስጥ ያለው ይሄው ነው! በነገራችን ላይ አስተባባሪዎች ለሴቶች ሲባል የተሻለ የሚባለውን መርጠው ነበር የሰጧቸው፤ ያም ስላልመጠናት ነው ያኮረፈችው።
ጠዋት ስሰማ እንደምንም ተፈልጎ ከከተማው ወጣ ያለ የእንግዳ ማረፊያ ተሰጣት። ከዚያም በሞተር የሚያመላልሳት ሰው ተመደበ (እየተከፈለው ይሁን በራሱ ፈቃድ እንግዲህ አላረጋገጥኩም)። የምንበላውን አትበላም፣ የምናርፍበት አታርፍም። ይቺው ‘ጋዜጠኛ’ ጠዋት ስናገኛት የሆነ ስሙን የማላውቀው (የህመምተኛ ግሎኮስ የመሰለ) የሚጠጣ ይሁን የሚመጠጥ ነገር ይዛ ነው የምትንቀሳቀስ። ‹‹ያቺ በግሉኮስ የምትንቀሳቀሰዋ›› እያሉ ሲሳለቁባት ነበር።
ልጅቷ መብቷ ነው። ምናልባትም እኮ ለእሷ ሌሎች ጋዜጠኞች ምቾት ስለማያውቁ መስሏት ይሆናል። ደረጃቸው ይሄው ብቻ ነው ብላ ሊሆን ይችላል። ውድ ምግብና ውድ ሆቴል ስላለመዱ ነው ብላ ይሆናል። ስለዚህ እሷ ከምቾት ውጪ ያለመደች ከሆነ ትክክል ናት፤ መጎሳቆል የለባትም! የልጅቷ ስህተት አንድ ብቻ ነው፤ ጋዜጠኛ መሆን አልነበረባትም! ጋዜጠኝነት የቅንጦት ኑሮ ብቻ የሚዘገብበት አይደለም። ተጎሳቁሎ የሚኖረውን ማህበረሰብ ሕይወት ማየት ነው። ይሄ ማለት የግድ እነርሱ የሚመገቡትን መመገብ ማለት አይደለም፤ የጤናም ሆነ የስነ ልቦና ችግር የሚያስከትል ከሆነ መተው ይቻላል፤ ዳሩ ግን ለምን እንዲህ አይነት ቦታ መጣሁ ማለት ከጋዜጠኝነት ሙያ ጋር ፈጽሞ አይሄድም። እንዲያውም በእሷ ምክንያት ጠዋት ስለጋዜጠኝነት ሥራ እየተወራ ነበር። ጋዜጠኝነት ማለት ከላይ ያለውንም ከታች ያለውንም የኑሮ ደረጃ የሚያውቅ ነው። አንደኛው ጋዜጠኛ የሰጠው አስተያየት አሳምኖኛል። ያቺ ልጅ እንደዚያ ስትሆን የነበረችው ‹‹እንዲህ አይነት ሆቴል አደርኩ፣ የማይረባ ሆቴል ግቢ ብለውኝ ዞር በሉ! አልኳቸው›› ለማለት ነው እያለ ነበር። ይሄን ነገር ደግሞ ብዙ ጋዜጠኞች ሲሉ ሰምቼ አውቃለሁ። እንዲህ አይነት ቤት አልገባም፣ እንዲህ አይነት አልጋ ላይ አላድርም… እያሉ ከአስተባባሪ ጋር የሚጣሉ ብዙ ጊዜ አጋጥመውኛል።
አሁንም ለምን ያማርጣሉ እያልኩ አይደለም፤ ዳሩ ግን ማማረጥ እንኳን ያለብን ቢያንስ አማራጭ ባለበት ቦታ ነው። ባህርዳር፣ ሐዋሳ፣ መቀሌ…. ከሆነ ልናማርጥ እንችላለን፤ እልም ያለ ገጠር ውስጥ ሄዶ ሳውና ባዝ፣ ስቲም ከየት ይገኛል? ለሁለትና ሦስት ቀን ከእነዚህ ውጪ ቢታደር ይሞታል እንዴ? የሆነውስ ሆነና ግን እነዚህ ጋዜጠኞች ሁሌም በእንዲህ አይነት ምቾት ውስጥ የሚኖሩ ናቸው? ወይስ በእንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ምቾትን ለማየት ነው?
የጋዜጠኝነት ሙያ የግድ በመቸገርና በመጎሳቆልም አይገለጽም። አንድ ጋዜጠኛ ደሳሳ ጎጆ ፈልጎ ስለተኛ፣ ድሃው የህብረተሰብ ክፍል የሚመገበውን ስ ለተመገበ፣ በጠጠር መንገድ ስለሄደ… ጎበዝ ጋዜጠኛ ነው ማለት አይደለም። እያልኩ ያለሁት እንደሥራውና እንደቦታው ሁኔታ አውዳዊ መሆን አለበት ነው። ለህዝብ ማድረስ ያለበት እኮ በብዙኃኑ ያልታዩ ነገሮችን ነው። ባለኮከብ ሆቴል ውስጥ ያለውን ኑሮ እኮ በፊልምና በድራማ ያዩታል። የአስፋልት መንገድ ያለበትን አካባቢ እኮ በብዙ አጋጣሚ የመታየት ዕድሉ ሰፊ ነው። አንድ ጋዜጠኛ ማሳየት ያለበት የመታየት ዕድል ያጡትን ነው። ያልታወቁ ነገሮችን ነው ማስተዋወቅ ያለበት። የሚገርመው ግን የአገራችን ጋዜጠኞች ሲያወሩ የሚሰማው ስለከተማዋ የጭፈራ ቤት አቅርቦት ነው። ስላደሩበት ሆቴል ምቾት ነው። ችግርን ተጋፍጠው የሚሰሩ የሉም ማለት አይደለም፤ እያወራሁ ያለሁት ምቾት ምቾቱን ብቻ የሚመርጡትን ስለሆነ ነው።
የጋዜጠኝነት ሥራ እውቀት ብቻ ሳይሆን ፍላጎትና ፍቅር ነው። ስለታዘዘ ሳይሆን ያንን ሥራ ሲሰራ ትልቅ እርካታ ይሰጠኛል ብሎ መሆን አለበት። ብዙ ጊዜ የምንታዘበው ግን ያለፍላጎት በትዕዛዝ ሲሆን ነው። በተለይም የመስክ ሥራዎች ላይ ትልቅ ችግር አለ። እንዲያውም ጋዜጠኞች ሲመደቡ ለዚያ ጉዳይ ምን ያህል ቅርብ ናቸው በሚል መሆን አለበት። ተረኛ ስለሆነ ብቻ ባይመደብ ጥሩ ነው። አንድ ጥሩ ገጠመኝ ልንገራችሁ።123ኛውን የዓድዋ ድል በዓል ለማክበር የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የጋዜጠኞች ጉዞ አዘጋጀ። ጉዞው የጉብኝት ስለሆነ ከዕለቱ አንድ ሳምንት ቀድመን ነው የተነሳነው። የጉዞው አስተባባሪዎች የሚጎበኙ ቦታዎችን ዝርዝር አውጥተዋል። ዝርዝሩም ለጋዜጠኞች ተሰጥቶናል። እነዚህ የሚጎበኙ ቦታዎች በዓድዋ ድል ከፍተኛ ሚና ያላቸው ናቸው። ከአንኮበር ቤተ መንግስት ጀምሮ እነ ውጫሌ፣ ወረኢሉ፣ ማይጨው… ይጎበኛሉ።
ከሚጎበኙ ቦታዎች አንዱ ወደሆነው ውጫሌ እየሄድን ከፍተኛ ክርክር ተፈጠረ። ክርክሩ ማየት አለብን የለብንም የሚል ነው። ልብ በሉ! ውጫሌ ማለት ለዓድዋ ድል ምክንያት የሆነው የውጫሌ ውል የተፈረመበት ቦታ ነው። ጥቁር ነጭን ያሸነፈበት አሻራ ያረፈበት ነው። ይሄን ቦታ ‹‹ምን ሊያደርግልን ነው የምንጎበኝ?›› የሚሉ ጋዜጠኞች ተፈጠሩ። ቦታው ከዋናው መንገድ አሥር ኪሎ ሜትር ያህል ያስኬዳል። መንገዱም ምቹ አይደለም። አንዳንድ ጋዜጠኞች ‹‹መቼም አሁን እየተፈራረሙ አይደለም! ምኑን ነው የምናየው?›› እያሉ ተከራከሩ፤ ምክንያታቸው በዚያ አስቸጋሪ መንገድ ላለመሄድ ነው። አስተባባሪው ግራ ተጋባ። ‹‹በቃ እንተወው!›› እንዳይል ደግሞ እዚህ ጋ ሌላ የከረረ ቁጣ መጣበት። በተለይም ሁለት የቴሌቪዥን ጋዜጠኞች መረር ብለው ተቆጡ። ከፈለጋችሁ ሂዱ እንጂ ሥራችንን ሳንሰራ አንመለስም አሉ።
የሚገርመውን ነገር ደግሞ ልንገራችሁ። በቦታው ላይ ሙዚየም እየተገነባ ነው። ሙዚየም እየተገነባ እንደሆነም አስተባባሪው ተናግሯል። ይህን እያወቁ ነው ‹‹ምኑን ነው የምንጎበኘው?›› ያሉት። በብዙ ጭቅጭቅ መሄድ አለብን የሚለው ቡድን አሸነፈና ሄድን። እንደተባለውም ሙዚየም እየተገነባ ነበር። ይሄንን ነው እንግዲህ ማየት የለብንም የተባለ።
አሁንም እነዚህ ጋዜጠኞች መብታቸው ነው። በዓድዋ ታሪክ የመኩራት ግዴታ የለባቸውም፤ ሲቀጥል ደግሞ በዓድዋ ታሪክ መኩራት የግድ ሁሉንም ቦታዎች በማየት ላይሆን ይችላል። ዳሩ ግን እነዚህ ጋዜጠኞች ለሚሊዮን ህዝብ ሊያደርሱ ነው የተላኩት። የውጫሌ ውል የተፈረመበትን ቦታ ሄጄ መመልከት አልፈልግም ያለው ጋዜጠኛ ሚሊዮን ህዝብ እንዳያይ አድርጓል። እየተገነባ ያለውን ሙዚየም ህዝብ እንዳያውቅ አድርጓል።
ለዚህ ነው በእንዲህ አይነት የመስክ ሥራዎች ጋዜጠኛ መመረጥ አለበት ያልኩት። ዳሩ ግን ከጥቅም ጋር ስለሚያያዝ የሚመደቡት በተራ ነው። አንድም ሥራ ይዞ ባይመጣ ተረኛ ከሆነ ይመደባል። ሄዶ ግን ለህዝብ መድረስ የሚገባውን መረጃ አዳፍኖት ይመጣል። በሌላ በኩል፤ በጋዜጠኞች ዝንባሌም መሆን አለበት። ለምሳሌ ለታሪክና ባህል፣ ለፖለቲካና ኢኮኖሚ፣ ለስፖርትና መዝናኛ… እንደየ ጉዳዩ ባላቸው ቅርበት ቢመደቡ ሥራው በአግባቡ ይሰራል። እርግጥ ነው ከሁሉም ያልሆነም አለ፤ በሁሉም የማይሞቀው፤ የማይበርደው አለ፤ እንዲህ አይነቱ በስህተት ነው ጋዜጠኛ የሆነው።
ሌላ አንድ የመጨረሻ ገጠመኝ ልንገራችሁ። ይሄኛው ገጠመኝ ራሴ ያየሁት ሳይሆን 2008 ዓ.ም ራሱ ጋዜጠኛው ባለበት ሲጫወቱ ነው የሰማሁት ነው።
ለአንድ የሁነት ዘገባ ወደ ደሴ ይመደባል። ጉዳዩ ጥናቶችና የመድረክ ውይይቶችም ያሉበት ስለሆነ ለቀናት የሚደረግ ነው። አጅሬው የፕሮግራሙ ዝርዝር ላይ አይቶ መቼ እንደሚያልቅ አውቋል። ወጣ ገባ ሲል ቆይቶ አንድ ቀን ለካ ያደረበት ጭፈራ ቤት ሞቆታል። ቀንም ሌሊትም እያለ ሲዝናና ቆይቶ የመዝጊያ ፕሮግራሙን ሊከታተል በመጨረሻዋ ቀን ሄደ። ወደ አዳራሹ መግቢያ በር ላይ ሲደርስ ጥበቃው ‹‹ምን ፈልገህ ነው?›› ይለዋል። ይሄ ጋዜጠኛም አፉን ሞልቶ እውነቱን ሲናገር ‹‹የመቼህን ነው ጨርሰው ከሄዱ!›› አለው። ለካ ከተባለው ቀን ቀድመው ጨርሰው ሄደዋል። ጋዜጠኛው የአንድ ወር ደመወዝ እንደተቀጣ ነግሮናል። ታዲያ ይሄ ‹‹ድንቄም ጋዜጠኛ!›› አያሰኝም?
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 23/2012
ዋለልኝ አየለ