ለብዙዎቻችን አዲስ ያልሆነና የባቢሎን ሰዎችን በተመለከተ ያነበብነው ወይም ደግሞ የሰማነው አስተማሪና ዘመን ተሻጋሪ መልዕክት አለ። ይህ ታሪክ በጥንት ዘመን የነበሩ ባቢሎናውያን በተባበረ ክንዳቸው ከፈጣሪያቸው ጋር ለመድረስ ሊገነቡ የጀመሩት ግንብ ከቋንቋ መደበላለቅ የተነሳ መናዱና ጅምራቸው በእንጭጩ መቋጨቱን የሚያመለክት ነው። እውነት ነው! ምንም ያህል ወርቅ የሆነ አጀንዳና ዓላማ ቢኖርና ሚሊዮንና ቢሊዮን ህዝቦችን ማሰለፍ ቢቻል ለተመሳሳይ ዓላማ የተሰለፈ ኃይል ቋንቋው ከተደበላለቀ ጋት እንኳን መራመድ አይችልም። ይሁንና እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ የቋንቋ መደበላለቅ የሚወገደው ሁሉም ሰው አንድ ዓይነት ቋንቋ ስለተናገረ ሳይሆን ለተሰማራበት ዓላማ የሚያስተላልፈውን መልዕክት ወጥነት ባለው መልኩ መረጃ መስጠት ሲችል ነው።
ቋንቋ ተደበላለቀ የሚባለው በአንድ ሥርዓት ውስጥ የሚሰሩ ክፍሎች በአንድ ተመሳሳይ ጉዳይ ላይ መልዕክታቸው አራምባና ቆቦ ሲሆን ነው። የኮሙኒኬሽን አስተምህሮ በተለይም ከመንግስት አካላት የሚተላለፍ መልዕክት ቁጥብ፣ አውነተኛ፣ ግልጽና ወጥ መሆን እንዳለበት ያሰረዳል። በቀውስ ወቅት የሚተላለፉ መልዕክቶች ደግሞ እጅግ ጥንቃቄ የተሞሉና ወጥነታቸው የተረጋገጠ ሊሆን ይገባል። ፌዴራላዊው ሥርዓት እንደተጠበቀ ሆኖ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትን ተሳትፎ ያረጋገጠ፣ መረጃዎቹ የጠሩ፣ ለውዥንብር በር የማይከፍቱና የተማከሉ ሊሆን ይገባል።
ከዚህ ውጪ ግን ለአንድ ዓላማ የሚሰሩ ተቋማት በአንድ ጉዳይ ላይ እንደጥንታውያኑ ባቢሎናውያን በተደበላለቀ ቋንቋ የሚያወሩ ከሆነ በአገርም ሆነ በህዝብ ላይ የሚደርሰው ጉዳት እጅግ ከፍተኛ መሆኑ አይቀሬ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ኅብረተሰቡ እንዲህ ዓይነት ግራ የሚያጋቡ መልዕክቶችን ሲሰማ እውን መንግስት አንድ ሆኖ በአንድ ልቡ እየሰራ ነውን የሚል ጥርጣሬን ያጭርበታል። አንደኛው ሌላ ተናግሮ ሌላኛው የዚያን ተቃራኒ ሲያወራ ደግሞ በተአማኒነቱ ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ ያሳድራል። ከመንግስት አካላት የሚተላለፉ መልዕክቶችን አምኖ ለመቀበልም ይቸገራል። ከዚህ የከፋው ደግሞ የመረጃ ክፍተቱን እየተጠቀሙ መረጃዎችን በማዛባት ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት ለሚጥሩ ኃይሎች ትልቅ ቀዳዳ ይከፍታል።
ከመረጃ አሳጣጥና ከሙኒኬሽን ጽንሰ ሃሳብ ጋር ተያይዞ ይህን ጉዳይ ዛሬ ያነሳነው ከደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መጥፋት ጋር ተያይዞ የታየው የመንግስት መረጃ አሰጣጥ ኅብረተሰቡ ላይ ጥያቄ እየፈጠረ መሆኑ አሳስቦን ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ መረጃ ለመስጠት መዘግየት የታየ ሲሆን ይህንን መሰረት በማድረግም መረጃ የሚያዛቡ ኃይሎች አሉባልታና የተሳሳቱ መረጃዎችን በመልቀቅ በህዝቡ ውስጥ ውዥንበር እንዲፈጥሩ ዕድል ሰጥቷቸዋል።
በዚህ ጉዳይ ዙሪያ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት፣ በፌዴራል ፖሊስ፣ በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልል ጸጥታና ደህንነት ቢሮና ደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ወዘተ የተሰጡ መግለጫዎች የሃሳብ ልዩነቶች የተስተዋሉባቸው መሆናቸውም እንዲሁ ህዝቡንና መገናኛ ብዙሃንን ግራ ሲያጋቡ ተስተውሏል። ለማናችንም ግልጽ እንደሆነው በንጹሃን ተማሪዎች ላይ የተፈጸመው የዚህ ወንጀል ዋነኛ ዓላማ ለዘመናት ተዋደውና ተፋቅረው በኖሩ ብሄሮች መካከል ግጭት መፍጠር ነው። በዚህ እኩይ ተግባር ላይ መረጃን ወጥ በሆነ ሁኔታና በጥንቃቄ አለማስተላለፍ ደግሞ በቤንዚን ላይ እሳት እንደመጨመር ይቆጠራል።
ስለሆነም መንግስት ይህን እንደ ትልቅ ትምህርት ወስዶና የኮሙኒኬሽንና መረጃ አሰጣጥ ስርዓቱን ፈትሾ የማስተካከያ እርምጃዎችን በፍጥነት መውሰድ ይኖርበታል። አንድ ዓላማን ሰንቆ እንደመስራቱም ቋንቋው እንደባቢሎናውያኑ ተደበላልቆ ከቆመለት ዓላማ ከማደናቀፉ በፊት አስቀድሞ መላ ሊያበጅለትም ይገባል እንላለን!
አዲስ ዘመን ጥር 23/2012