እንደምን ከረማችሁ ውድ አንባቢዎች፣ ባለፈው ሳምንት “ኢትዮጵያዊነት- ከየት ወዴት?” በሚል ርዕስ አንድ ጽሑፍ አስነብቤአችሁ እንደነበረ ታስታውሳላችሁ። ይህ ጽንሰሃሳብ ሰፊ በመሆኑ ከፊሉን ለዛሬ በይደር ማሳደራችን ይታወሳል። እነሆ ዛሬ በቀጠሮዬ መሠረት ቀጣዩን ክፍል ይዤ ቀርቤያለሁ፤ መልካም ንባብ።
ማንነት የታሪክ ሂደት ውጤት ነው። ያለማቋረጥ የሚታነፅ እንጂ ላንዴና ለመጨረሻ ተጠርቦና ተቆርጦ የሚሰጥ አይደለም። ቋሚና ተለዋዋጭ የሆኑ ነገሮች በማንነት ውስጥ አሉ። ሰው የሚደክመው አሁን ያለውን ማንነት ለማቆየት ብቻ ሳይሆን በዚያው ማንነት የተሻለ ማንነት ለመቀዳጀትም ነው። በነበረበት ቦታና ባለበት ደረጃ መቅረት የሚፈልግ የለም። ሁሌም ለተሻለ ማንነት ይታገላል። ይህ ማንነት የብዙ ነገሮች ድምር ውጤት ነው። በእኔ ማንነት ውስጥ የተፈጥሮ ሕግ አለ፤ የሌሎች ሰዎችና የራሴ ሥራ ውጤቶችም አሉ። ከእነዚህ ውስጥ በነባር መልካቸው ወይም በሌላ መንገድ የሚቀጥሉ ይኖራሉ፤ አርጅተው የሚወድቁና በምትካቸው የሚፈጠሩ አዳዲስ ገጽታዎች አሉ። በዚህ መልክ የግለሰብ የማንነት ግንባታ እስከ ሕይወት ማብቂያ ድረስ ይቀጥላል። ሰዎች የግል ወይም የቡድን ማንነት አላቸው። በዚህ ማንነት ተደራጅተውና ተቀናጅተው የሚተጋገዙ ወይም የሚገፋፉ ሊሆን ይችላሉ። የኢትዮጵያውያን የዜግነት ማንነት የሆነው ኢትዮጵያዊነትም በዚሁ መልክ የሚታይ ነው።
ጠንካራና የማይደፈር ማንነት አለ። ሊደፈር የሚችል ማንነትም ሊኖር ይችላል። ኢትዮጵያዊነት ባንድ በኩል የማይደፈርና የሚያኮራ ማንነት ነው፤ በሌላ በኩል ግን የተደፈረ ማንነትም ነው። ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ክብርና ነፃነት፤ ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር ያላስደፈሩ ሕዝቦች ናቸው። በሩቅም ሆነ በቅርብ ኃይሎች የተቃጣባቸውን ተደጋጋሚ ወረራና ጥቃት በጀግንነት አመክነዋል። ቅኝ ገዢዎች ዓለምን እንደ ቅርጫ በተቀራመቱበት ዘመን በአልደፈርባይነት በራሱ ንጹህ ተጋዳይነትና ቀናኢነት ያልተንበረከከው ብቸኛ ጥቁር አፍሪካዊ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። የኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያዊነት በዚህ ገድል ይንፀባረቃል። በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያውያን በድህነትና በረሃብ፤ በማይምነትና በተለያዩ ችግሮች ተገርፈዋል። ዛሬም ቢሆን እየተጻፈ ያለው ይኸው ታሪክ ነው። መደፈር በማይገባቸው እኩይ ነገሮች ተደፍረዋል። ኢትዮጵያዊነት በዚህም ይገለፃል።
የዜጎች ማንነት የሚታነፀነው በወላጅ፤ በጎረቤት፤ በኅብረተሰብ፤ በመንግሥት፤ በርዕዮተዓለም፤ በተቋማትና በመሳሰሉት ነው። ብዙ እኩይ ነገሮች ባነቀዙት ሀገርና ኅብረተሰብ ውስጥ ጠንካራና መልካም ማንነትን መገንባት አስቸጋሪ ነው። ዛሬ ያለንበት የእድገት ደረጃ ሲገመገም የኢትዮጵያዊነት እኩይ ገጽታ ከሰናይ ገጽታው በላይ መሆኑን ይጠቁማል። ዓለም ለእነዚህ መጥፎ ነገሮች በምሳሌነት የምትጠቀመው እኛ ኢትዮጵያውያንንና ኢትዮጵያን ነው። በዚህ ምክንያት አንፀባራቂው የነፃነትና የቀናኢነት ታሪካችን በሚፈለገው መጠንና ዓይነት አልደመቀም፤ እኛም አንገታችንን በልበ-ሙሉነት ማቅናት አልቻልንም። ለምንና እንዴት ሆኖ የዜግነት ማንነታችን የተዳከመው የሚል ጥያቄ ማንሳት ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያ የብሔር-ብሔረሰብና ሕዝቦች ሀገር ናት። በዚህ ምክንያት ዜጎች ሁለትና ከዚያ በላይ ማንነት ለመያዝ የሚገደዱበት ሁኔታ ነበረ፤ አለ። አንድ ሰው በሀገራዊ ማንነቱ ኢትዮጵያዊ ነው፤ በብሔር-ብሔረሰባዊ ማንነቱ ኦሮሞ፤ አማራ፤ ሱማሌ፤ ሲዳማ፤ ሀዲያ፤ ኮንሶ፤ ትግሬ፤ ጋሞ፤ ወላይታ ወዘተ ሊሆን ይችላል። ለሁለቱ ማንነት እኩል ክብርና አሴት መስጠት አንድ መንገድ ነው፤ አንዱን ከሌላ ማስበልጥ ደግሞ ሌላው ነው። የኢትዮጵያ ገዢዎችና ሥርዓቶቻቸው ምርጫ ሆኖ የቆየው ሁለተኛው ነው።
እንደ አንዳንድ አክራሪ ወገኖች እምነት ኢትዮጵያዊነትና ሌላነት ማለትም ብሔር-ብሔረሰባዊ ማንነት (ኦሮሞነት፤ ሲዳማነት፤ አማራነት፤ ሱማሌነት፤ ትግሬነት፤ ሀዲያነት፤ ኮንሶነት፤ ወላይታነት ወዘተ.) አይደለም እኩል መሆን አብረው መሄድ አይችሉም። እንዲህ ዓይነት አቋም ያላቸው ወገኖች #እኛ ብቻ ኢትዮጵያውያን ነን$ ማለት የሚከጅሉ ናቸው። በኢትዮጵያዊነት ሌላነትን (ማለትም ሀዲያነትን፤ ኦሮሞነትን፤ አማራነትን፤ ትግሬነትን፤ ሱማሌነትን፤ ኮንሶነትንና ሌሎችን) አሳነሱ። በማወቅ ወይም ባለማወቅ በየጊዜው የነበሩ የፖለቲካ ሥርዓቶችና ገዢዎች ኢትዮጵያዊነትን አግላይና ገፊ አድርገው ተጠቅመውበታል። በኢትዮጵያዊ ማንነት የብሔር-ብሔረሰባዊ ማንነትን (በሌላ አገላለጽ ኢትዮጵዊነትን) ሲገፉ የነበሩ ወገኖች ባንድ በኩል፤ በብሔር-ብሔረሰባዊ ማንነታቸው ኢትዮጵያዊነትን ሲሸሹ የነበሩ ዜጎች በሌላ በኩል ተሰልፈው ቆይተዋል። ሥርዓቶችና ገዢዎች የተወሰኑ ዜጎችን አቅፈው ሌሎች ዜጎችን ወደ ዳር ገፍተዋል። ኢትዮጵያዊነት በይበልጥ እንዲወደድ ወይም እንዲታቀፍ በማሰብ፤ ወይም የራሳቸውን ኢትዮጵያዊ ማንነትና ማዕከልነት አጉልቶ ለማሳየት በመፈለግ ራሳቸውን ኢትዮጵያዊ የመሆኛ ፍቃድ ሰጭና ከልካይ አደረጉ። ኢትዮጵያዊ መሆን የሚቻለው የራስን የብሔር-ብሔረሰባዊ ማንነት በመተውና የሌላን የብሔር-ብሔረሰብ ማንነት በመቀበል ብቻ እንዲሆን መታሰቡ በብዙኃኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም። የማይታሰብና የማይሞከር ሆነ።
በሌላ በኩል ደግሞ እውነተኛ ማንነት ያለው በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ሳይሆን #በኦሮሞነት፤ አማራነት፤ ሱማሌነት፤ ትግሬነት … ውስጥ ነው ብለው የሚከራከሩ አሉ። እነዚህ ደግሞ #እኛ ኦሮሞዎች፤ አማሮች፤ ሱማሌዎች፤ ትግሬዎች፤ ሲዳማዎች … ነን እንጂ ኢትዮጵያውያን አይደለንም$ ማለት የሚቃጣቸው ናቸው። የሁለተኛው አቋም የመጀመሪያውን ያህል የሚያከር ባይሆንም አንዱ ሌላውን መፍቀድ እንደማይችል አድርጎ መውሰዱ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የሚያዳክም እንጂ የሚያጠናክር አልሆነም። ከኢትዮጵያዊነቱ የተገፋ ኢትዮጵያዊ በበኩሉ ኢትዮጵዊነትን እስከመግፋት ድረስ በመሄድ ጥፋትን በስሕተት ለማረም ማሰቡ ተጨማሪ ጉዳት ነው። ሀዲያ ሀዲያነቱን፤ ኦሮሞ ኦሮሞነቱን፤ ትግሬው ትግሬነቱን፤ አፋሩ አፋርነቱን፤ ሌሎችም እንዲሁ እነርሱነታቸውን ከኢትዮጵዊነታቸው በላይ አጥብቀው የሚይዙበት አዝማሚያ መፈጠሩ ችግር እንጂ ዕድገት አላመጣም።
ኢትዮጵያዊነት ሌላነትን (ማለትም ብሔር-ብሔሰባዊ ማንነትን) የሚጠላ ከሆነ ሌላነትም በተራው ኢትዮጵያዊነትን መቀበል አይገባውም ብለው የሚከራከሩ ወገኖች አሉ። የበለፀገ አስተሳሰብ ባለው ማሕበረሰብ ውስጥ በዚህ መንገድ ማሰብ ትክክል አይደለም። ትልቁ የኢትዮጵያውያን ስሕተት ስሕተትን በስሕተት የምናርም መሆናችን ነው። #እሾህን በእሾህ$ ማለት ጊዜ ያለፈበት ፈሊጥ ነው። ኢትዮጵያ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ናት። የማንኛችንም የግል ንብረት አይደለችም። የግለሰቦች፤ የትውልዶች፤ የብሔሮች፤ የብሔረሰቦችና ሕዝቦች እናት ናት። አንዱን ከፍ ሌላውን ዝቅ ያደረጉት ግለሰቦች፤ ቡድኖችና ሥርዓቶች እንጂ ኢትዮጵያ አይደለችም። ጥቂቶች በፈጸሙት በደል የኢትዮጵያን የእናትነት ፍቅርና ክብር ማሳነስ አይገባም። በእርግጥ እንዲህ ዓይነቱን እምነት ለመቀዳጀት ጊዜ ይፈጃል። ቢሆንም ዛሬ ካልተጀመረ ነገን የተሻለ ማድረግ ያስቸግራል።
ይህ የማግለልና የመገለል ሥርዓት የተዘረጋው ባብዛኛው የብሔር-ብሔረሰብና የሕዝቦች ማንነት መገለጫ የሆኑ እምነቶችን፤ ቋንቋዎችን፤ ባህሎችንና አስተሳሰቦችን መሠረት በማድረግ ነው። በዚህ ምክንያት በብዙ ወገኖች ዘንድ ኢትዮጵያዊነት አግላይ ነው የሚል እምነት ፈጠረ። በብሔር-ብሔረሰብ ማንነታቸው በተፈጠረው ጭቆናና ጫና ኢትዮጵያዊነትን የራሳቸው የዜግነት ማንነት አድርገው መቀበል የተሳናቸው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈጠሩ። በብሔር-ብሔረሰብ ማንነት፤ በቋንቋና በእምነት፤ በባሕልና አስተሳሰብ ልዩነት መግፋትና መገፋት ኢትዮጵያዊነትን ተፈታተነው። በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያዊነት የማያባራ ውዝግብ ፈጥሮ መቆየቱ ብቻ ሳይሆን ለራሱም በሁሉም ዜጎች ሕሊናና አዕምሮ ውስጥ የሚገባውን ክብርና ቦታ እንዳያገኝ ተደርጓል።
ለመሆኑ #ለኢትዮጵያዊነት ስንል አንገታችንን ለካራ እንሰጣለን$ ከሚሉ ዜጎች መካከል ስንቶች ናቸው ከአንጀት ኢትዮጵያዊ የሆኑት; ለኢትዮጵያዊነት በሚሰጡት እሴት ዜጎችን በሁለት መልክ ልንከፍላቸው እንችላለን – በልባዊ ኢትዮጵያዊነትና በአፋዊ ኢትዮጵያዊነት የሚንቀሳቀሱ በማለት። ልባዊ በሆነ ኢትዮጵያዊነት መንፈስ የሚኖሩና የሚንቀሳቀሱ ዜጎች ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ከራሳቸው በላይ የሚወዱና የሚያከብሩ ናቸው። ፍቅራቸው ባብዛኛው ከመሬት ሳይሆን ከሕዝቡ፤ ከባሕሉ፤ ከእሴቱ፤ ከአብሮነቱ፤ ከመቻቻሉና ከመሳሰሉት ነው። እነዚህ ዜጎች በቁጥር ትንሽ እንደሆኑ ይታሰባል። በአፋዊ ኢትዮጵያዊነት ስሜት የሚንቀሳቀሱ ወገኖች ደግሞ ከኢትዮጵያ በላይ ራሳቸውን ይወዳሉ። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጭንብላቸው ነው። ከምንም በላይ መሬትና ሀብቷ ሁሉ የራሳቸው እንዲሆን የሚመኙ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ የግል ንብረታቸው ቢሆን ፍቃዳቸው ነው። በዚህ እሳቤ የሚንቀሳቀሱ ወገኖች ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ ይገመታል።
ስለኢትዮጵያዊነት ያለው ችግር መታየት የሚኖርበት ከገፊዎች ብቻ ሳይሆን ከተገፊዎች አንጻርም ነው። ተገፋን የሚሉ ብዙ ዜጎች ለኢትዮጵያዊነት ቀዝቃዛ መንፈስ ነበራቸው። አንዳንዶቹ ጭራሽ #የሌሎች እንጂ የኛ አይደለም$ ብለው ያመኑ በሚመስል መልክ ራሳቸውን እስከ ማግለል ደርሰዋል። በኢትዮጵያ ምድር ለተፈጠረ ሰው (ከሕግ በስተቀር) ኢትዮጵያዊነትን የሚነፍግ አንዳችም ኃይል የለም። የሌሎች ስሜትና አመለካከት ሌላውን ሰው የሆነውን እንዳይሆን ሊያደርገው አይገባም። ማንም ሲገፋው ዜጋ ዝም ብሎ መገፋት የለበትም። መቀራረብና መነጋገር፤ መከራከርና መሟገት፤ ማመንና ማሳመን እያለ ለማንና ለምን ብሎ ነው የዜግነት ማንነቱን የሚያስደፍረው; ኢትዮጵያዊነት መኖር የጀመረው አንድ ሰው በኢትዮጵያ ምድር ላይ ከተፈጠረ ጊዜ አንስቶ ነው።አንድ ቡድን ወይም ሥርዓት የፈጠረው አይደለም። በኢትዮጵያ ምድር ላይ የተፈጠሩ ዜጎች ሁሉ የሰሩት፤ በቅብብሎሽ ከዚህ ያደረሱትና በቅብብሎሽ የሚያስቀጥሉት ነው – ኢትዮጵያዊነት።
ብዙዎቻችን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከውጭ ያጠለቅናቸው ጭንብሎች እንጂ ከውስጥ የታነፅንባቸው ደምና አጥንት ያደረግናቸው አይመስልም። እነዚህ እሴቶች በውጭያችን እንጂ በውስጣችን የሉም። ሀቁ ያ ቢሆን ኖሮ ከምንም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት መቅደም ባልተሳናቸው ነበር። ያ ቢሆን ኖሮ ሁላችንም ማዕከል የምናደርገው ራሳችንን ሳይሆን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ነበር። እውነቱ ያ ቢሆን ኖሮ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መግባባት አቅቶን ችግሮችን (እንደ መልካም ነገር) ከትውልድ ወደ ትውልድ ስናስተላልፍ አንኖርም ነበር። እውነቱ ያ ቢሆን ኖሮ ሀገርን መስረቅና መዝረፍ፤ በሀገር ጉዳይ ላይ ወገንን መጥላት፤ ማሰቃየት፤ ማሳደድና ሕይወቱን ማጥፋት ባልተገባ ነበር።
ገዢዎቻችን ኢትዮጵያን ሲገዙ ‹ኢትዮጵያ እናታችን፤ ክብራችን፤ ፍቅራችን› ይላሉ። በሚፈጽሙት ግፍ ምክንያት ከሥልጣን ሲወርዱ ግን ከምድረገጽ መጥፋት እንዳለባት የጠላት ሀገር ያዩአታል። ማየት ብቻ አይደለም ዕድገቷንና ለውጧን ለማጨናገፍ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። መቼም ቢሆን የኢትዮጵያንና የሕዝቧን ጉዳይ ከራሱ ጉዳይ በላይ አድርጎ የሰራ አመራር አልነበረም። የሌሎች ሀገር መንግሥታት ሀገሮቻቸውን ያሳደጉት በሕዝቦቻቸው ታግዘው ነው። በኢትዮጵያ ግን መሪዎች ሀገርን እናሳድጋለን የሚሉት የዜጎቿን አናት እየመቱ ነው። ሕዝቦችን እያሳነሱ መሬቷን ማሳደግ እንዴት ይቻላል; የሀገር እድገት ወይም ልማት ከምንም በላይ የሕዝብ እድገት ወይም ልማት ነው። ሀገርን የሚያለማና የሚያስከብር በአግባቡ የተያዘና የሚመራ ሕዝብ ነው። በሀገሩ የማይከበር ሕዝብና በዜግነቱ የማይተማመን ግለሰብ ሀገርን እንዴት ይገነባል;
ኢትዮጵያ የእናንተ፤ የእነርሱ፤ የኔ፤ የኛ፤ የሁላችንም ነች ለማለት ማንኛችንም አንቸገርም። ራሳችንን በእርሷ ውስጥ፤ እርሷን በራሳችን ውስጥ የምናደርግ እውነተኛ ዜጎች ግን ሁላችንም አይደለንም። የብዙዎቹ ኢትዮጵያዊነት የይስሙላ ነው። ሀገሪቱ ስትመቻቸው ከማንንም በላይ ኢትዮጵያውያን የሚሆኑ፤ ሳትመቻቸው ስትቀር ከመቅጽበት ወደ ኢ-ኢትዮጵያውያን የሚቀየሩ ወገኖች አሉ። እነርሱ ሲገዟት #እናታችን፤ ፍቅራችን፤ ክብራችን$ እያሉ ያንቆለጳጵሷታል። ሌላ ኢትዮጵያዊ ሲገዛት ግን መወረርና መጥፋት ያለባት የጠላት ሀገር ትደረጋለች። እኛ የማንገዛት ሀገር መኖር የለባትም እስከ ማለት ይደርሳሉ። #እኔ ከሌለሁ ሰርዶ አይብቀል$ እንዳለችው እንስሳ መሆን ይቃጣቸዋል።
ለማስረጃ ከቅርብ ታሪካችን አንድ እውነት መዝዘን እንይ። ጥንታዊ ታሪክና ሥልጣኔ አላቸው ከሚባሉት ሀገሮች ተርታ ነበረች በሚባልላት ኢትዮጵያ በደርግ ዘመነ-መንግሥት በሰሜኑ ሀገራችን ውስጥ በተፈጠሩ አማጺ ቡድኖች የመቶ ዓመት ታሪክና ዕድሜ ተሰፈረላት። የሀገሪቱ በትረ-ሥልጣን በእጃቸው ሲገባ ደግሞ እነዚሁ ወገኖች መልሰው የብዙ ሺህ ዘመናት ታሪክ ባለቤት ናት ብለው በራሳቸው መንገድ ሰፉላት። አንድ ሌላ ማስረጃ እንጨምር። ብዙ ጀግኖች የወደቁላትን ባንዲራ የኢህአዴግ መሪዎች የጨው መቋጠሪያ ጨርቅ ነች ብለው ክብሯን ዝቅ አደረጉ። በለስ ቀንቷቸው ሥልጣን በመያዝ ሀገሪቱን እንዳስፈለጋቸው አድርገው የመዘወር ዕድል ሲያገኙ ደግሞ #የባንዲራ ቀን$ ብለው በመወሰን ዘመሩላት። ይኸም ኢትዮጵያዊነት አይደል:: የኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግር ሀገርንና ሥርዓትን መለየት ባልቻሉ፤ ሀገርንና ሕዝብን በራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት በሚለኩ መሪዎችና ፖለቲከኞች መመራቷ ነው። የሀገር ክብርና ዋጋ በሰዎች የፖለቲካ አስተሳሰብና ፍላጎት ከፍና ዝቅ ማለት አይገባውም። ይህን ማንሳት የተፈለገው ኢትዮጵያዊነት በዚህም የሚገለጽ መሆኑን ለማሳየት ነው።
ዛሬ በኢትዮጵያ ምድር በሀገር ደረጃ ማሰብ ተዳክሟል። የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ባለ-ሀገር ወይም እንደ ዜጋ ማሰብ ያቆመ ይመስላል። ሀገራዊ ንቃቱና አመለካከቱ፤ ብሔራዊ ስሜትና ፍቅሩ ተዘበራርቆበታል። አስተሳሰቡ ከነበረበት ደረጃ ወርዶ ወርዶ ክልል ገባ። ከክልልም ወርዶ ወርዶ ከዞኖች ገባ፤ ከዞኖች ወደ ወረዳዎች፤ ከወረዳዎች ወደ መንደር ዘለቀ። ብዙ ወገኖች ዛሬ የሚያስቡት በመንደር ወይም በቀበሌ ደረጃ ነው። ብሔራዊ አቅማችንና አቋማችን ቁልቁል ተምዘግዝጎ ወረደ። ይህ መውረድ ብቻ ሳይሆን መዋረድም ነው። ዛሬ እየኖርንና እያሰብን ያለነው እንደ ሀገር ሳይሆን እንደ መንደር ነው። ጥቂት መሪዎች ለራሳቸው ጥቅም ብለው በፈጠሩትና በሚፈጥሩት ችግር ብሔራዊ ክብራችንና ማንነታችን ጥያቄ ውስጥ ገባ።
በአሁኑ ጊዜ ሀገራዊ ጉዳዮች ባለቤት ያላቸው አይመስሉም። ዜጎችን የሚፈታተኑ ሀገራዊ ችግሮች ሲፈጠሩ የሃይማኖት አባቶች፤ የሀገር ሽማግሌዎች፤ ታዋቂ ሰዎችና ምሁራን ለመፍትሔ ፍለጋ በፍጥነት መንቀሳቀስና መመካከር ይጠበቅባቸዋል። ዛሬ እንዲህ ዓይነት የኃላፊነት ስሜት በተሟላ መልኩ አይታይም። ቢኖርም የመደመጥ ዕድሉ ይህን ያህል ነው። ሁሉም ሁሉን ይፈራል። ማን ማንን ያምናል; መደማመጥ የሚኖረው መተማመን ሲኖር ብቻ ነው። የብዙ ሺህ ዘመናት ታሪክና ሀገር ባለቤት ነን ብንልም አስተሳሰባችን በዚያ ዕድሜ መጠን የበሰለና የሰላ አይደለም። ኢትዮጵያ ዛሬን እንጂ ነገን አሻግሮ ማየት የሚችሉ መሪዎችና ፖለቲከኞች ያፈራች አትመስልም። በውሸት ወይም በስርቆት፤ በክፋት ወይም በጥፋት፤ በመቀማት ወይም በመሰዋት ዛሬን መኖር እንጂ ነገ ለዛሬው ተግባራቸው የሚፋረዳቸው መሆኑን ማስተዋል የማይችሉ ወገኖች በዝተዋል። የኛ ትውልድ ከማልማት ይልቅ ማጥፋት የሚቀናው ስለሆነ ኢትዮጵያን የሚመጥናት አልሆነም።
ይቀጥላል
አዲስ ዘመን አርብ ጥር 22/2012
ጠና ደዎ (ፒኤችዲ)፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ