ከራስ ጋር ንግግር በወንጪ….

የከተማው ግርግር እና ጫጫታ ለማሰብ ፋታ አይሰጥም። የመኪናው ጋጋታ እና ጥሩምባ አትኩሮትን ይወስዳሉ፣ የማኅበራዊ ሚዲያው የመረጃ ጎርፍ ለሰከንድ አይቆምም፤ ጊዜ የለም። ሁሉም ሩጫ ላይ ነው። ምክንያቱም አንዱ ሲሞላ ሌላው ይጎድላል፣ አንዱ ሲደፈን ሌላው ያፈሳል። መቼ፣ የት እንዴት እናስብ? በግራ እና በቀኝ ተወጥረን በየት በኩል ትንፋሽ አግኝተን ከራሳችን ጋር ቁጭ ብለን እንነጋገር፤ ይሄ እኔ የምኖርባት ከተማ ወግ ነው፡፡

እንደ እኔ በምክንያት እግር ጥሎህ እንደ ወንጪ አይነቶቹ የምድር ላይ ገነቶች ላይ ስትደርስ ግን፤ ከራስ ጋር ለመነጋገር፣ ለማሰብ እና እራስን ለማዳመጥ ትክክለኛ ቦታዎች ናቸው። ወንጪ ስንደርስ ንጹህ አየር፣ ጥቅጥቅ ባለው ደን መካከል አጮልቃ ድብብቆሽ የምትጫወት ፀሐይ ትቀበለናለች። ጆሯችን ከወፎች ዝማሬ እና ከጅረት ውኃ ድምጽ ውጭ የሚሰማው የለም።

ወንጪ ሰዎች ከራሳቸው ጋር ለመገናኘት፣ ከተፈጥሮ ጋር ለመወያየት፣ ከውስጣቸው ጋር ለመተዋወቅ ዕድል የሚሰጥ ቦታ ነው። ምክንያቱም፣ እዚህ የታክሲ ሰልፍ የለም፤ የትራፊክ ጭንቅንቅም የለም። አለፍ ብለህ ስልክንም፣ ቴሌዥንም ለምኔ ካልክ በአከባቢው ያለውን ጥቅጥቅ ያለ ደን እና የረጋውን የወንጪ ሀይቅ እያህ በጥሞና ማሰብ ብቻ። ወንጪ የረጋች የተመስጦ ቦታ፤ የምድር ገነት ናት።

የመጣንበትንና ያለፍንበትን መለስ ብሎ ለማየት፤ እምነታችንን እና እውነታችንን ለመፈተሽ፤ ህይወታችንን እና ትዝታችንን እያሰናሰልን ለማሰብ፤ ነጋችንን እና ህልማችንን ለመፈተሽ እድል የሚሰጥ ቦታ ነው፤ -ወንጪ።

የሆነ ጊዜ አንድ የቢቢሲ ጋዜጠኛ በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ሲጎበኝ ሳነቴ ተራራ ላይ ወጥቶ “an iceland on earth” ብሎ የሰራው ፕሮግራም ነበር። ወንጪ ላይ ሆኜ ይሄን ባስታወስኩ ጊዜ ይሄ ጋዜጠኛ ወንጪን ቢያይ ደግሞ “the heaven on earth” ብሎ ይዘግበው ነበር ስል አሰብኩ።

ከአዲስ አበባ በ140 ኪሎ ሜትር ርቀት እንዲህ አይነት የተፈጥሮ ጸጋ፣ እንዲህ አይነት መታደል አለ ብሎ ለመገመት ይቸግራል። ሀይቁ እስር ነው ያለው እኛ ደግሞ ከአፋፉ ላይ። ሀይቁ ግርጌ እኛ እራስጌ እንደማለት። እንዲህ ሲመለከቱት አንዳች ልባዊ ሐሴትን ይፈጥራል፡፡

በሀይቁ መሀል ጥቅጥቅ ባለ ጫካ የተሞላ አነስተኛ ደሴት ትታያለች። በደሴቷ ላይም በ14ኛው ክፍለ ዘመን የተገነባ ቤተክርስቲያን (ጨርቆስ ቤተክርስቲያን) አለ። ይሄ ደግሞ ሌላ ገጽታ፣ ሌላ ውበት፣ ሌላ ታሪክና ጥበብ ነው።

ከባለጫካዋ ደሴት ነጠል ብሎ ሌላ ውኃ ገብ መሬት አለ፤ ይሄን “ፔኒንሱላ” በሉት። ዛኒጋባ የቆርቆሮ ቤቶች እና የሳር ጎጆዎች አለፍ አለፍ ብለው ይታያሉ። ውኃ ገቡ መሬት እንደ “ኦክቶፖስ” አይነት ቅርጽ ይዞ ተዘርግቷል። ውኃው ደግሞ በተለያየ አቅጣጫ እስከ ቤታቸው ተዘርግቷል።

ወደ ሐይቁ ለመውረድ ባሰብን ጊዜም ዳገቱን እየቆረጠ ዚግዛግ እየሠራ በሚሄደው ውብ አስፓልት መንገድ ተፈጥሮን እያደነቅን ተጓዝን። የተራራው ወገብ ጋ ስንደርስ ሀይቁን በቀኝ በሩቁ እያየነው አለፍነው። ጠመዝማዛውን መንገድ ጨርሰንም ወደ ሐይቁ ዳር ተቃርበናል። አስገራሚውን ነገር በአከባቢው ያሉ አርሶአደሮች ወደ ከተማ ለመውጣት በየአጥራቸው ስር ያቆሟትን የራሳቸውን ታንኳ ይጠቀማሉ።

እዚህ ሁሉም የራሱ ጀልባ አለው። ገበያ ለመሄድ፤ ዘመድ ለመጠየቅ ወይም ለመንግሥት ጉዳይ ሲወጡም፣ ሲገቡም የግል ጀልባቸውን እየቀዘፉ ሐይቁን ተሻግረው ወደ መዳረሻቸው ይሄዳሉ። እኛም በሐይቁ አካባቢ ባለ ሎጅ ቅጥር ግቢ ገባን፡፡

በሎጁ የታቀፉ በግራና በቀኝ አለፍ አለፍ እያሉ የሚታዩ የገጠር ቤቶችም አሉ። በዚህ ውስጥ የሚገለጠው የአካባቢው ማኅበረሰብ አኗኗር፣ ባህል፣ የቤት አሠራር፣ አመጋገብ እና ሁሉም ማህበረሰባዊና ስነልቦናዊ ውቅር የጉብኝቱ አካል ነው። በዚህ ያለው የሚያምር ተፈጥሮ፣ ላንድስኬፕ፣ መልክዓምድር(ጂኦግራፊ እና ቶፖግራፊ) ሰው ሲጨምርበት ህይወትን ሙሉ አድርጎታል።

ከላይ ከአፋፉ እስከ ውሃው ግርጌ ጥቅጥቅ ባለ ደን ውስጥ ባህርዛፍ ፈልጋችሁ አታገኙም። በአንጻሩ በጥቅጥቅ ጫካ ውስጥ ወርቃማ ቀለም ያለው የተንዠረገጉ ቀጫጭን ቅጠሎች ዘርግቶ በብዛት የሚታየው የኮሶ ዛፍ ነው። ቅጠሉ ሲታይ ይመር እንጂ ቀርባችሁ ስትነኩት ግን ጥንካሬ እና ከርዳዳ ሆኖ ታገኙታላችሁ። ውበቱ ለአይን እንጂ ሲነኩት እጅ ያሰበስባል፣ እንደ ስሙ ይኮሰኩሳል። ግራር፣ ጽድ እና ሌሎች የማላውቃቸው ትልልቅ ዛፎች የቁልቁለቱን ጉዞ አሳማሪዎች ናቸው።

ሐይቁ ስር ደርሰን ከመኪናችን ወረድን። ያመጣንን መንገድ፣ የወረድነውን አቀበት ሽቅብ ቀና ብዬ ተመለከትኩት። 360 ዲግሪ የሰማይን አድማስ የሚታከክ፣ ጥቅጥቅ ባለ ደን የተሸፈነ ተራራ ተቀበለኝ። ወንጪ ትበርዳለች፤ ደንበኛ ደጋ ነች። በስፍራው ስትደርሱ በሚገርም ተፈጥሮ፣ በሚገርም መልክአምድር መካከል እራሳችሁን ታገኙታላችሁ።

ጠዋት 12 ሰዓት የጀመረው ተራራ የመውጣት ጉዟችን የተገታው ቀጥ ባለው ተራራ መካከል ያገኘነው ለጥ ያለ ሜዳ ላይ ስንደርስ ነው። አረንጓዴ ለብሶ የተዘረጋው መሬት (ፕላቶ) በጉያው ብዙ የከረሰምድር ውኃ እንደታቀፈ ወደ መሬት የሚተፋው ውኃ ያሳብቅበታል።

እውነተኛው የአምቦ ውኃ(አምቦ ጠበል) እዚህም እዚያም ይፈልቃል። ከምንጩ ጨልፌ ጠጣሁት። ጎሮሮዬ የሚያውቀው አምቦ ውኃ ፈሰሰበት። ትንሽ እንደሄድን ከተራራው አናት ተወርውሮ ከአለት ጋር እየተጋጨ የሙዚቃ ቢት የሚፈጥር ድምጽ የሚያወጣ ፍል ውኃ አገኘን።

ሌላ አንድ ምእራፍ እንደተጓዛችሁ ሌላ ተዓምር መሳይ ጉዳይ ታገኛላችሁ። ሁለት መንታ ትልልቅ ጉድጓዶች በአንድ በኩል ሙቅ ውኃ፤ በሌላ በኩል ቀዝቃዛ ውሃ ያፈልቃሉ። ባለ ሙቅ ውሃው ጉድጓድ ጃኩዚ በሉት። ስለ የጭቃ ሳውና ኢንተርኔት ላይ ብታስሱ እንዴት ጠቃሚ እንደሆነ ዝርዝሩን ታገኙታላችሁ። የሞቀ ጭቃ በህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ነካሁ።

የተራራው ወገብ ላይ ሆናችሁ በግራ አምቦን፣ በቀኝ በኩል አዘቅዝቃችሁ የነበራችሁበትን ወንጪ ሀይቅ በጫካ መካከል ታዩታላችሁ። አሁን ሁለት ኪሎሜትር የሚረዝም ቀጥ ቀጥ ያለ ዳገት ይጠብቃችኋል። ይሄን ለመውጣት የከተማው ቡና እና ዘይት ይታገለን ጀምሯል። በዛ ቅዝቃዜ የሰውነታችን ላብ እንደ ጎርፍ ይወርዳል፣ ቢሆንም ምግብ የሆነ ኦክስጅን እየተነፈስን ነው።

ሆኖም ከሌሎች ተቆርጠን ላለመቅረት እና የተፈጥሮውን ውበት ሳንመለከት ላለማለፍ እንታገላለን እንጂ እኛ ደክሞናል። አንዱን ምዕራፍ እንደ ጨረስን የተዘጋጀ ማረፊያ ቦታ አግኝተን ባናርፍ ኖሮ ዳገቱ ያለንን አስጨርሶናል።

በየተራራው ወገብ የተዘጋጁ ማረፊያዎች በታንኳ ቅርጽ የተሰሩ የድንኳን ማደሪያዎች በጫካው መካከል ይገኛሉ። እነዚህን ማደሪያዎች ደግሞ ውጭ ማደር ብርቁ የሆነው ፈረንጅ እጅጉን ይወዳቸዋል። የማያልፉት የለምና ዳገቱን ጨርሰን ቁልቁለቱን፤ ቁልቁለቱንም አገባድደን ወደ መነሻችንና ማረፊያችን ተመለስን። ማረፊያ ሎጁ ከአካባቢው ተፈጥሮ ጋር ስምም ሆኖ የተሰራበት ጥራት፣ የማኅበረሰቡ ፍቅር እና እንክብካቤ ይደንቃል።

ከዚህ ሁሉ በኋላ ወንጪን ወደ ኋላ ትታችሁ ወደ ግርግሩ ስትመለሱ ይሄ በህይወት አንዴ የሚያጋጥም ሳይሆን ደጋግማችሁ የምትመጡበት ቦታ እንደሚሆን ለራሳችሁ ቃል ትገባላችሁ። ምክንያቱም፣ ወንጪ ሀገሬውን ብቻ ሳይሆን የውጪ ጎብኚውንም የሚያማልል፤ ኢትዮጵያንም ከኬንያ የላቀ ቱሪዝም እንድትስብ ከሚያደርጉ ማግኔቶች ትልቁ ነው ብል ያየሁትን በማመኔ ነው።

ኤፍሬም ተክሌ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You