ጋዜጠኝነት እንደ ምንኩስና

በኦርቶዶክስ አማኞች ዘንድ ምንኩስና የሚባል ሃይማኖታዊ ሥርዓት አለ:: ይሄውም አማኙ ዓለም በቃኝ ብለው ገዳም የሚገቡበት ማለት ነው:: በሃይማኖታዊ ስነ ሥርዓቱ የሚከወን ነገር አለው:: እሱን እንተወውና ዋና ነገሩ ግን ከምንም ነገር ገለልተኛ የሚሆኑበት ማለት ነው:: የመነኮሰ ሰው በዚህ ዓለም በሕይወት እንደሌለ ነው የሚቆጠረው:: በሕይወት እንዳለ ሰው ሆኖ በምንም ጉዳይ ላይ አስታየት አይሰጥም:: ለምሳሌ በወገኑ ላይ በደል ቢደርስ ተበደለብኝ ብሎ ተቆርቋሪ አይሆንም:: ባደግኩበት አካባቢ እንደማውቀው መነኩሴ ለሽምግልና አይመረጡም፤ ምክንያቱም የማግባባት፣ የመዋሸት እና ሰዎችን የማታለል ሥራ ስለማይሠሩ! ሽምግልና ማታለል ነው ማለቴ አይደለም፤ ዳሩ ግን ሰዎችን የመቆጣት እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም የመዋሸት ብልጠት ይኖረዋል:: ይህ ደግሞ ለመነኮሰ ሰው አይሆንም::

ይሄን ምሳሌ ያነሳሁት ጋዜጠኝነት ይህን ያህል ገለልተኛ ይሆናል ብዬ አይደለም:: እንዲህ አይነት ጋዜጠኝነት በየትኛውም ዓለም አይኖርም! የሙያው ሳይንስ የሚለው ግን ልክ እንደዚህ እንደምንኩስናው ነው:: ከየትኛውም ነገር ገለልተኛ ነው መሆን ያለበት:: ልክ እንደመነኩሴ ሁሉ በወገኑ ላይ በደል ቢደርስ ተቆርቋሪ ሊሆን አይገባውም፤ ወይም በተቻለ መጠን ሰዋዊ ስሜቱን ተቆጣጥሮ የራሴ ወገን ሳይል ጉዳዩን ብቻውን ማየት አለበት::

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶክተር ተሻገር ሽፈራው በአንድ ወቅት ‹‹የመብት ተሟጋችነትና ጋዜጠኝነት የተለያዩ ነገሮች ብቻ ሳይሆኑ ተፃራሪም ናቸው›› ብለው ነበር:: በማብራሪያቸውም፤ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንም ሆኑ የግል መገናኛ ብዙኃን ገለልተኛ እንዳልሆኑ ገልጸው ነበር::

በነገራችን ላይ የጋዜጠኝነት ሳይንሱ የሚለው ነገር የትኛውም የዓለም ሀገር የማይተገበር መሆኑ ግልጽ ነው:: ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪዎቹ እነ ቢ ቢ ሲ፣ ሲ ኤን ኤን፣ አልጄዚራ… ወዴት እንደሚያዘነብሉ እናውቃለን:: የዴሞክራሲ ቁንጮ ናቸው የሚባሉት የምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን የሚያነጣጥሩት በምሥራቁ ዓለምና በአፍሪካ ሀገሮች ችግር ላይ ነው:: በአንፃሩ የምሥራቁ ዓለም መገናኛ ብዙኃን የሚያስጨንቃቸው የምሥራቁ ዓለም ደህንነት ነው:: የዓለም አጀንዳ የሆነውን የእስራኤል እና የኢራን ጉዳይ ማየት በቂ ምስክር ነው:: ጉዳዩ አንድ ሆኖ ሳለ፤ አዘጋገባቸው ግን የተለያየ ነው:: የተበዳዮች ጉዳይ ለምዕራባውያን ሚዲያዎች እና ለምሥራቁ ዓለም ሚዲያዎች የተለያየ ነው::

የራሳችንን ጉድ ትቼ የውጭውን የጠቀስኩት፤ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያ ብቻ ተደጋጋሚ ውግዘት ስለሚደርስበት ነው:: ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ ሌላው ዓለም ሳይንሱ እንደሚለው የሚሠራ የለም:: የጋዜጠኝነት ሙያ ሞቷል ከተባለ እንደ አጠቃላይ ነው የሞተው::

ጋዜጠኝነት ማህበራዊ ሳይንስ ነው:: ይሄ ማለት እንደ ፊዚክስና ኬሚስትሪ ተፈጥሯዊ ሳይንስ አይደለም ማለት ነው:: ከሀገር ሀገር ሊለያይ ይችላል:: ሀገራት በሚከተሉት ሥርዓት ላይ ይወሰናል:: እንኳን በሀገር ደረጃ በአንድ ሀገር ውስጥ ራሱ የተለያየ መገናኛ ብዙኃን የተለያየ አሠራር ሊኖራቸው ይችላል:: የየራሳቸው ዓላማ ይኖራቸዋል:: ለዚህም ነው የመረጃ መምታታት የሚያጋጥመው:: አንዱ የዘገበውን ሌላው ካልፈለገው ‹‹ውሸት ነው›› ሊል ይችላል::

ስለጋዜጠኝነት ሙያ ተደጋግሞ የሚነገረው ነገር ‹‹ወገንተኝነቱ ለሕዝብ ነው›› የሚለው ነው:: አንዳንዶች ግን ይሄ ራሱ ትክክል አይደለም የሚሉ አሉ:: ጋዜጠኝነት ወገንተኝነቱ ለማንም ሳይሆን በቃ ለእውነት ብቻ ነው:: ያ እውነት ሕዝብ የሚጎዳ ቢሆን ራሱ መዘገብ አለበት እንደማለት ነው::

ጋዜጠኝነት ልክ እንደ መነኩሴ ነው ካልን (ሳይንሱም ገለልተኛ ነው እንደሚለው) ጋዜጠኝነት ለሕዝብ ወገንተኛ መሆን የለበትም እንደማለት ነው:: ሕዝብ ራሱ ሊሳሳት ይችላል:: የአንድ አካባቢ ሕዝብ የሌላን አካባቢ ሕዝብ ቢሳደብ መዘገብ አለበት ማለት ነው:: ገለልተኛ ነው ከተባለ ስለምንም ነገር ሊያገባው አይገባም:: በዚህ ሎጂክ ከሄድን ለሀገር ጥፋት ይሆናል ማለት ነው::

እንደ እውነቱ ከሆነ ይሄኛው አይነት ገለልተኝነት በፍጹም ሊጠቅም አይችልም:: መገናኛ ብዙኃን ማለት ለአንድ ሀገር እድገትና ብልፅግና፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መስፈን የሚሠራ መሆን አለበት:: አራተኛው የመንግሥት አካል ከተባለ ደግሞ ሀገር የሚያጠፋ መንግሥት ስለሌለ ከዚህኛው ትርጉም ጋር አይሄድም ማለት ነው::

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የጋዜጠኝነት ሙያ ካየነው ዝብርቅርቁ የወጣ ነው:: ለየትኛውም አልሆነም:: ለሕዝብም ወገንተኛ ያልሆነ፤ ለእውነትም ወገንተኛ ያልሆነ ነው:: የዚህ ደግሞ አንዱ ችግር የህብረተሰቡ የመገናኛ ብዙኃን ግንዛቤ (Media Litracy የሚባለው ማለት ነው) አለመኖር ነው:: በአየር ሞገድ የሚሰራጭ ሬዲዮ ሁሉ ትክክል ይመስለዋል፤ ታትሞ የወጣ ጋዜጣና መጽሔት ሁሉ ትክክል ይመስለዋል:: ይሄ ችግር አልተማረም በምንለው የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ ብቻ ያለ አይደለም፤ ይባስ ብሎ የተማረ በሚባለው ውስጥ ነው:: የተማረ የሚባለው ደግሞ ችግሩ አላምጦ አይውጥም:: ለመንግሥት አካላት የግል መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ሁሉ ውሸት ነው፤ ለግል መገናኛ ብዙኃን ተከታዮችም የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ሁሉ ውሸት ነው:: ገለልተኛ የሆነ ሰው ግን ዘውግ አይፈጥርም:: ሁሉንም ያያል፤ የተጠራጠረውን ያጣራል::

ዶክተር ተሻገር ሽፈራው በአንድ ወቅት ከአንድ ጋዜጣ ጋር ባደሩት ቃለ መጠይቅ ጋዜጠኝነትና የመብት ተሟጋችነት ተቃራኒ መሆናቸውን የገለጹት የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ያሳያል:: በተለይም የክልል መገናኛ ብዙኃን እየሠሩ ያሉት የሰብዓዊ መብት ተሟጋችነትና የመብት ማስከበር ሥራ ነው:: ይሄ ሥራ ቀላል ነው ማለት አይደለም፤ ትልቅ ሥራ ነው:: ዳሩ ግን ይሄ የጋዜጠኛ ሥራ ሳይሆን የመብት ተሟጋቾች ነው:: ጋዜጠኛ የሆነውን ሁነት ብቻ ነው ሳያዛባ መዘገብ ያለበት:: የራሱ ወገን ተበድሎ ሊሆን ይችላል፤ በሙያው ውስጥ ግን ተቆርቋሪነቱ ለእውነት ብቻ ነው:: ጋዜጠኝነት ዓለም አቀፍ ሙያ ነው፤ እንኳን በብሄር በሀገር ራሱ የሚታጠር አይደለም::

ወደዚህ ሙያ የሚገባ ሰው ልክ እንደመነኩሴዎች መሆን አለበት:: የራሱን ጥቅም የሚጎዳ እውነት ሊደብቅ አይገባውም:: ህሊናው ይሄን ለማድረግ ማመን አለበት::

በነገራችን ላይ የጋዜጠኝነት ሙያ እንደመነኩሴ ነው ያልኩት የህሊና ሥራ ስለሆነ ነው እንጂ የትኛውም ሙያ ከወገንተኝነት የጸዳ መሆን እንዳለበት ግልጽ ነው:: ከሌሎች ጋር ሲነጻጸር ግን የበለጠ ህሊናዊ ነው:: ለምሳሌ የህግ ባለሙያ የሚመራው በተደነገጉ ህጎች በአንቀጽ እየተመራ ነው:: የህክምና ባለሙያ ወጥ በሆነ ሳይንስ እየተመራ ነው:: ለየትኛው በሽታ ምን አይነት ህክምና ወይም መድሃኒት እንደሚያስፈልግ ያውቀዋል:: በዚያ መሰረት ይፈጽማል:: እርግጥ ነው በዚህም ውስጥ የፈለጉትን መጥቀምና ያልፈለጉትን መጉዳት ይቻላል:: ህግ ማዛባት ይቻላል፤ በሽታው የማይፈቅደውን መድሃኒት ማዘዝ ይቻላል:: ቢሆንም ግን የጋዜጠኝነት ሙያ ደግሞ ከእነዚህ ሁሉ በላይ የህሊና ሥራ ነው!

ምንኩስናው እንኳን ባይቻል፤ ቢያንስ ሕዝብ ከሕዝብ የሚያጋጭ ውሸት መዘገቡ ይቅር!

በዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 9 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You