
ሰኔ ሳይንሳዊ፣ ባህላዊ፣ ታሪካዊ፣ ተረታዊ… ብያኔዎች አሉት። የሰኔን ተረታዊነት እናስቀድም። ሰኔ መቃጠሪያ ህዳር መገናኛ፣ ሰኔ ነግበኔ፣ ለሞኝ ሰኔ በጋው መስከረም ክረምቱ፣ ሰነፍ ገበሬ በሰኔ ይሞታል፤ በሰኔ ገመሻ በበጋ ጤፍ እርሻ… የሚሉ ምሳሌያዊ አነጋገሮች አሉ። ‹‹ሰኔና ሰኞ›› የሚለው ፈሊጣዊ አነጋገርም ይታወቃል።
የሰኔ ሳይንሳዊ ባህሪ ደግሞ የክረምት መግቢያ ነው። ለዚህም ነው ተረትና ምሳሌዎች ከታታሪነት ጋር የተያያዙት። ሰነፍ ገበሬ በሰኔ ይሞታል የተባለው ገበሬ ጠንካራ መሆን ያለበት በሰኔ ስለሆነ ነው። ለሞኝ ሰኔ በጋው መስከረም ክረምቱ የተባለውም ሰኔ የክረምት ወር መጀመሪያ ስለሆነ በወቅቱ መሠራት አለበት ለማለት ነው።
የሰኔ ወር ባህላዊና ማህበራዊ አንደምታም አለው። የኢትዮጵያ የበጀት ዓመት የሚዘጋጀው በሰኔ ወር መጨረሻ ነው። አዲሱ በጀት ዓመት የሚጀምረው ከሐምሌ አንድ ነው። ይህ መንግሥታዊ አሠራር ቢሆንም እንደ ማህበራዊ ልማድ ተወስዶ ክረምት ሲመጣ በቤት ውስጥ ብዙ ዝግጅቶች ይደረጋሉ።
ልክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚያጸድቀው በጀት፤ በገበሬዎች ቤት የክረምት መውጫ በጀት ይፀድቃል። የቤት ውስጥ ፓርላማ በሉት! የሚበጀተው በጀትም ሽሮ፣ በርበሬ እና ሌሎች አስፈላጊ ምርቶች ናቸው። በሰኔ የሚበጀቱበት ምክንያት መጪው ክረምት በሥራ የሚወጠሩበት ስለሆነ፤ ወፍጮ ቤት ለመሄድ የሚያስችል ጊዜ ስለሌለ፤ ድሮ በድንጋይ ወፍጮ በእጅ ይፈጭ በነበረበት ዘመንም ጊዜ ስለማይኖር፤ ቀድሞ ለመዘጋጀት የሚደረግ ነው። ስለዚህ የገበሬ ቤት በሰኔ ወር መጨረሻ በጀት ይያዛል ማለት ነው።
በገጠር አካባቢ የሰኔ ወር የተለየ ቦታ አለው። የክረምት ወር መጀመሪያ ስለሆነ ሁሉ ነገር መዘጋጀት አለበት። ምክንያቱም ዋናው ክረምት ከገባ ሁሉም የቤተሰብ አባላት በሥራ የሚዋክቡበት ነው። ከዱር ያለው የግብርና ሥራ ላይ እንጂ ሽሮና በርበሬ ማዘጋጀት ላይ ሥራ መፍታት አይፈልጉም። ምክንያቱም ሽሮና በርበሬው ቀድሞ መዘጋጀት ይችላል፤ የእርሻ ሥራ ግን ወቅታዊ ነው፤ የዝናቡን መኖር ተከትሎ ብቻ የሚታረስ ነው። በተለይ የጤፍ እርሻ ደግሞ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ነው። እንግዲህ በዚህ ወቅት ማንም ወለም ዘለም ማለት አይችልም።
የሰኔ ወር የክረምት መጀመሪያ መሆን አካባቢያዊ ብቻ ሳይሆን ፌዴራላዊ አንደምታም አለው። ለምሳሌ በሰኔ ወር ብዙ ነገሮች ይዘጋሉ። ትምህርት ቤቶች ይዘጋሉ፣ አንዳንድ ተቋማት ይዘጋሉ (በተለይ በገጠር አካባቢ)፣ የመንግሥት ዓመታዊ በጀት እንኳን የሚጸድቀው በሰኔ ወር ነው። ለምሳሌ የዘንድሮው የ2018 ዓ.ም በጀት ጸድቋል።
የሰኔ ወር የክረምት መጀመሪያ መሆኑ እንደ ልማድ ባይሆን ኖሮ የ2018 ዓ.ም በጀት የሚጸድቀው መስከረም ወር ላይ መሆን ነበረበት። ምክንያቱም ሰኔ ማለት ገና 2017 ነው፤ 2018 የሚጀምረው መስከረም ላይ ነው። ዳሩ ግን አሠራራዊ ልማድ ሆኗል። ምርጫ ሲደረግም ግንቦት ወይም ሰኔ ወር ላይ ይደረግና፤ አዲስ መንግሥት የሚመሠረተው ግን መስከረም ላይ ነው። ይህ የእነ አሜሪካም አሠራር ነው። ህዳር ላይ(በእኛ ሰኔ እንደማለት ነው) ምርጫ አድርገው ጥር (በእኛ መስከረም ማለት ነው) አዲስ መንግሥት ይመሰርታሉ።
የሰኔ ወር በኢትዮጵያ ሳይንሳዊ፣ ባህላዊና ማህበራዊ ሁኔታው ብዙ ትዝታዎች አሉት። ለሠራተኛ ትዝታ አለው፣ ለተማሪ ትዝታ አለው፤ ለእረኛ ትዝታ አለው።
ትልቁ ትዝታ ግን የተማሪዎች ነው። ተማሪ ከአንደኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ የሰኔ ትዝታ አለበት። ከአንደኛ እስከ መሰናዶ ትምህርት ቤት እያለ ከክፍል ጓደኞቹ ጋር ስለሚላመድ የሰኔ ወር መለያየትን ይዞ ሲመጣ ቅር ይላል። በልጅነት አዕምሮ እኮ የሞት ፍርድ እንደመጠባበቅ በሉት። ለደረጃ የሚፎካከሩ ተማሪዎች ደግሞ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ የሚባባሉበትና የሰኔ ወር ቁርጣቸውን የሚነግራቸው ነው።
ስለ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ትዝታ አለው። ይሄ ነገር በተለይም ለመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎችና ለተመራቂዎች የተለየ ቦታ ይኖረዋል። የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ለጀመሪያ ጊዜ ከቤተሰብ የሚለይበት ነው። እነዚህን ቤተሰቦቹን የሚያገኛቸው በሰኔ ወር ነው። እዚህ ጋ የቤተሰብ ናፍቆት አለ፤ እዚህ ጋ ደግሞ ከተለያየ የሀገሪቱ ክፍል ከተውጣጡ ጓደኞቹ ጋር ሌላ ሕይወት ጀምሮ ሌላ ትዝታ ፈጥሯል፤ ሰኔ ላይ እነዚህን ልጆች ይለያቸዋል። የሰኔ ወር ለዚህ ተማሪ የትዝታ ምስቅልቅሎሽ ያለው ነው።
የሰኔ ወር ለተመራቂ ተማሪዎች ከማንም በላይ የተለየ ትዝታ አለው ብንል ትክክል ነን። ከልጅነቱ ጀምሮ ሲመኘው የነበረውን ሙያ የሚያረጋግጠው በዚህ ወር ነው። እንደገና መወለድ ልንለው እንችላለን። ያ ‹‹እንኳን ደስ ያላችሁ›› የሚለው መዝሙር ሆድን የሚያላውሰው በዚህ ወር ነው። ይሄ ትዝታ ለተመረቅንበት ዓመት ብቻ ሳይሆን የሰኔ ወር በመጣ ቁጥር የቴሌቭዥን ዜና ላይ ስናየው በትዝታ ወደተመረቅንበት ዩኒቨርሲቲ የሚወስደን ነው።
የሰኔ ወር መጨረሻ ለመንግሥት ሠራተኛውም ልዩ ወር ነው። የበጀት መዝጊያ ላይ ብር ላለመመለስ ተቋማት ያልሠሩትን ሥራ ሁሉ የሠሩ ለመምሰልና ለሪፖርት ይሯሯጣሉ። በዚህ አጋጣሚ ብሩ ላልታሰበለት ዓላማ ይውላል ማለት ነው። ኧረ እንዲያውም አሸሼ ገዳሜ ሁሉ ይኖራል። ይህን ሁሉ ሁነት የያዘው የሰኔ ወር ግን እንደሌሎቹ ወሮች 30 ቀን ብቻ ነው? ያሰኛል!
ሰኔ 30 የሚለው ቃል ታዋቂ ቃል ሆኗል፤ በስሙ ብዙ ነገሮች ተሰይመውበታል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቢቀዛቀዝም የንባብ ቀን እየተባለም ይጠራ ነበር። ምንም እንኳን ሁሉም ትምህርት ቤቶች የሚዘጉት ሰኔ 30 ቀን ባይሆንም፤ ዳሩ ግን ሰኔ 30 ተብሎ ይጠራል። ፕሮግራሞች እንደዬ አደራሩ ከሰኔ 30 ቀን በፊትም በኋላም ሊሆኑ ይችላሉ፤ ዳሩ ግን የሰኔ ወር መጨረሻ በሆነው ቀን ይሰየማሉ። በዚህም ምክንያት ሰኔ 30 በተማሪዎች፣ በተመራቂዎች፣ በመንግሥት ሠራተኞች፣ አንዳንዴም በግለሰብ ደረጃ በጉጉት የሚጠበቅ ቀን ይሆናል።
በነገራችን ላይ ሰኔ 30 ከብዙ ዓመታት በፊት የተለያዩ ሰዎች በተማሩበት ትምህርት ቤት ለመገናኘት ቀጠሮ የሚይዙበትም ነበር። ሲለያዩ፤ ከዚህ ዓመት በኋላ እንገናኛለን ብለው ይቀጣጠራሉ፤ ቃላቸውን ያከበሩ ከሆነ ይገናኛሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ ፊልሞች ሁሉ ተሠርተዋል።
በአጠቃላይ ሰኔ 30 በብዙ ማህበራዊ ጉዳዮቻችን ላይ ትዝታ ያለው ነውና እንኳን አደረሰን ቢባል አያንስበትም!
ለተማሪዎችም ለሠራተኞችም መልካም የክረምት ወቅት!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም