ኢትዮጵያዊ ኬሚስትሪ የለም?

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ብርቱ ወግ ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለሀገር በቀል ሥርዓተ ትምህርት ተጠይቀዋል:: ጋዜጠኛው ሥርዓተ ትምህርታችን ሀገር በቀል አይደለም ብሎ ሲሞግታቸው ‹‹ኬሚስትሪ የትም ሀገር ቢሆን ያው ኬሚስትሪ ነው›› የሚል ይዘት ያለው መልስ ሰጥተዋል:: እንደ ኬሚስትሪ፣ ፊዚክስ እና ባዮሎጂ ያሉ መሠረታዊ የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶች ዓለም አቀፍ አሃድ (unit) ያላቸው ዓለም አቀፍ ትምህርቶች ናቸው:: የኅብረተሰብ ትምህርት ማኅበራዊ ሳይንስ ነውና እንደየሀገራቱ ሁኔታ ይለያያል:: የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶች ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ የሚያደርጋቸው ነገር አለ:: ያም ሆኖ ግን የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶችስ ቢሆን እንደየሀገራቱ ተፈጥሯዊ ሁኔታ አይለያዩም ወይ?

በግሌ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ለመሟገት እና ተከራክሮ ለማሸነፍ ብለው የተናገሩት ይመስለኛል:: ሀገር በቀል ሥርዓተ ትምህርት ሲባል የግድ ዓለም አቀፍ የሆኑ አሃዶችን መቀየር ማለት አይደለም:: ወይም ወጥ የሆነውን ሳይንሳዊ ልኬታ እና የኬሚስትሪ ባሕሪያት መቀየር ማለት አይደለም:: ዳሩ ግን የኬሚስትሪ ትምህርት የሚሰጥበት መንገድ በሁሉም ሀገራት ወጥ እና ተመሳሳይ ነው ማለት አይሆንም:: ለምሳሌ፤ ኢትዮጵያዊ ኬሚስትሪ ይኑር ቢባል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ እናቶቻችን የሚጠቀሟቸውን ባህላዊ የማብላላት እና የማዋሐድ ሥራዎች በኬሚስትሪ ማጥናት ማለት አይደለም:: ለምሳሌ፤ የአረቄ አወጣጥ ሂደት የኬሚስትሪ ውጤት ነው:: ኢትዮጵያዊው የአረቄ አወጣጥ ሂደት ግን አውሮፓና ሩሲያ ከሚመረት ቮድካ ጋር ተመሳሳይ አይሆንም:: ወይስ የኢትዮጵያ ባህላዊና ልማዳዊ ስለሆነና እንደ ኋላቀር ስለሚታይ በኬሚስትሪ ሳይንስ ውስጥ አይካተትም?

እዚህ ላይ የትምህርት ሚኒስትሩ የተናገሩትን አንድ ነገር ልጨምር:: የባህል መድኃኒት የመሳሰሉትን ባህላዊ ነገሮች ወደ ሳይንስ ምርምር ለማምጣት ‹‹አለኝ የሚል ሰው ይዞ ይምጣ!›› ብለዋል:: ሚኒስትሩ እዚህ ላይም ለመከራከር ብለው የተናገሩት ይመስለኛል:: የምንኖረው እኮ ብዙ ያልነቃ ማኅበረሰብ ባለበት ሀገር ውስጥ ነው:: ብዙ ነገሮች የሚደረጉት በልማድ ብቻ ነው:: አንድ የባህል መድኃኒት አዋቂ ይህን መድኃኒት መርምሩልኝና በዘመናዊ መንገድ ተሠርቶ በፋርማሲ ይሸጥ ሊል አይችልም:: ይህን ሥራ መሥራት ያለባቸው የትምህርት ተቋማት ናቸው:: የባህል መድኃኒት አዋቂዎችን ያሉበት ሄደው የሚጠቀሙትን ነገር መጠየቅ:: ከምን ቅጠልና ሥራሥር እንደሚያገኙት፣ እንዴት ሲያደርጉት ያድን እንደነበር፣ ምን ያህል ሰው አድኖላቸው እንደነበር… ከጠየቁ በኋላ ያድናል የተባለውን መድኃኒት በተባለበት መንገድ ሙከራውን ማድረግ ነው:: ይህ ምርምር ለመድኃኒትነት የሚሆን ከሆነ ባለቤቶቹን ዕውቅና መስጠትና መሸለም፣ የማያድን ከሆነ አደገኛነቱን መንገር እና ድጋሚ እንዳይጠቀሙት ማስጠንቀቂያ መስጠት፣ እንዲያውም በወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑን አስረግጦ መንገር ነው::

አንድ የባህል መድኃኒት አዋቂም ሆነ ባህላዊ ዕቃዎችን የሚገጣጥም ሰው ለዘመናዊው ትምህርት እና ለሥርዓተ ትምህርት ቀረጻ ቅርብ አይሆንም:: አንዲት ጥጥ የምትፈትል እናት ይሄ ነገር በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ይካተትልኝ፤ በዩኒቨርሲቲዎችም ወደ ኢንዱስትሪ ይግባ ልትል አትችልም:: ስለዚህ መሆን ያለበት፤ በባለሙያዎች አስጠንቶ ወደ ሥርዓተ ትምህርት እንዲመጣ ማድረግ ነው:: ባህላዊ ነገሮችን ወደ ዘመናዊ ለማምጣት እና የሳይንስ ምርምርን ለማሳደግ መሥራት ያለበት ከላይ ያለው የተማረው ምሑር እንጂ ምንም የማያውቅ የባህል የዕደ ጥበብ ሠራተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሄዶ ‹‹ይሄን ነገር በቤተ ሙከራ አረጋግጡልኝማ!›› ሊል አይችልም::

ወደ ሀገር በቀል ሥርዓተ ትምህርት እንመለስ!

በዘመነ ኢሕአዴግ በብዙ ምሑራን ከፍተኛ ወቀሳ ይቀርብ የነበረው ሥርዓተ ትምህርታችን ሀገር በቀል አይደለም በሚል ነው:: ከለውጡ መንግሥት ወዲህ ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተደጋጋሚ የሚናገሩትን ጨምሮ ስለሀገር በቀል እውቀቶችና ሀብቶች ብዙ ተብሏል:: አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከወራት በፊት በሠራው ዘገባ፤ ራሱ ትምህርት ሚኒስቴር ሀገር በቀል እውቀቶችን ወደ ሥርዓተ ትምህርት ለማስገባት እያጠና እንደሆነ መረጃ ሰጥቶናል:: ሀገር በቀል እውቀት ይጠናል ሲባል በልማዳዊ መንገድ ከማሳ ላይ የተቀጠፈ የባህል መድኃኒት በቀጥታ በፋርማሲ ይሸጥልን ማለት አይደለም:: የፈጀውን ጊዜ እና ገንዘብ ፈጅቶ አስፈላጊውን ሂደት አልፎ ነው:: የሕክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት አንድ መድኃኒት ሙሉ የመድኃኒትነት ደረጃ ላይ ለመድረስ በትንሹ እስከ ሰባት ዓመታት ይወስዳል፤ በእርግጥ የአሠራሩ ሁኔታ ይወስነዋል::

ኢትዮጵያዊ ኬሚስትሪ ይኖራል:: ለምሳሌ፤ የመማሪያ መጽሐፉ ላይ ለኬሚስትሪ ጽንሰ ሀሳቦች እናቶቻችን የሚያዘጋጁትን ነገር ምሳሌ ማድረግ ማለት ነው:: ኬሚስትሪ ማለት የግድ በኒኩለር ማብላላት ደረጃ ብቻ አይደለም:: ወጥ መሥራትም ኬሚስትሪ ነው:: ልጆች ጽንሰ ሀሳቡ ግልጽ ይሆንላቸው ዘንድ በአካባቢያቸው በሚያውቁት ነገር መሆን አለበት:: አለበለዚያ ትምህርቱ የሽምደዳ ብቻ ይሆናል:: እስካሁን የመጣንበት መንገድ ውጤታማ ያላደረገን ሽምደዳ ብቻ ስለሆነ ነው:: ተመራቂዎችን ወደ ሥራ ፈጠራ መውሰድ ያልቻለው የውጭ ንድፈ ሀሳብ ሽምደዳ ስለሆነ ነው:: አንድ ተማሪ ጎበዝ የሚባለው ስክሪፕት አጥንቶ እንደሚተውን ተዋናይ የመጽሐፉን ጽሑፍ ሸምድዶ ሲናገር ነው:: አንድ ተማሪ እንደዚያ ሆነ ማለት ጭንቅላቱ የመረጃ መያዣ ፍላሽ ዲስክ ሆነ ማለት ነው:: ፍላሽ ዲስክ ግዑዝ የሆነ ቁስ አካል ነው:: ያዝልኝ ያሉትን መረጃ ይይዛል እንጂ አይተረጉምም:: የሽምደዳ ትምህርት ልክ እንደዚያ ነው::

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ግብርና ነው ይባላል:: የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች የግብርና ትምህርት ክፍል አላቸው:: ዳሩ ግን በግብርና የተመረቁ ተማሪዎች የአካባቢያቸውን የሰብል፣ የተክል እና የእንስሳት ዓይነትና ባሕሪያት እንኳን ለይተው አያውቁም:: በልጅነታቸው ተማሪ ናቸው ተብለው ከግብርና ሥራ ውጪ ይሆናሉ፤ በልምድ እንኳን አያውቁትም ማለት ነው:: ትምህርቱ ደግሞ ሀገር በቀል አይደለም:: ስለዚህ እነዚህ ልጆች ከሁለቱም ያልሆኑ ሆነዋል ማለት ነው:: አንድ ከዩኒቨርሲቲ በግብርና የተመረቀ ባለዲግሪ የአንድ ገበሬ ያህል እንኳን የግብርና እውቀት የለውም ማለት ነው:: አንድ በኬሚስትሪ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቀች ተማሪ የእናቷን ያህል እንኳን የወጥ አሠራር የቅመማ ሂደት አትችልም ማለት ነው:: በተመረቀችበት ኬሚስትሪም እዚህ ግባ የሚባል ዘመናዊ እውቀት አይኖራትም፤ ምክንያቱም ሽምደዳ ነው ተምራ የወጣችው::

የኬሚስትሪ ትምህርቷ ሀገር በቀል ቢሆን ግን በአካባቢያዊ ነገሮች መለማመዷ ወደ ዘመናዊ ምርምሮች ይወስዳታል ማለት ነው:: ይህን ለማወቅ የሥልጣኔን ሂደት ልብ ማለት ነው::

የሰው ልጅ በዋሻ ውስጥ ይኖር ከነበረበት የድንጋይ ዘመን ተነስቶ ዛሬ ያለበት ረቂቅ ዓለም ላይ የደረሰው በሙከራ ነው:: በዘመናት ልምምድ ነው፤ እነዚህን ልምምዶች ያደረጋቸው ግን በአካባቢው በሚያከናውናቸው ነገሮች ነው:: ኤሌክትሪክ ላይ የደረሰው መጀመሪያ እሳትን በማየቱ ነው:: ከዘመናዊ የልብስ አሠራር ቴክኖሎጂ በፊት የሽመና ሥራ ነበር:: ልብስ ከዚያ ባይጀመር ኖሮ አሁን ያለው ዓይነት አይዝም ነበር:: አንድ ቁስ አካል ሲጀመር እና ብዙ ዓመት ሲቆይ ይለያያል:: ለምሳሌ፤ የእጅ ስልክ (ሞባይል) ሲመጣ ብዙዎች ተደንቀናል:: ድሮ የነበረው ግን አሁን የለም፤ እየተሻሻለ ሄዶ አሁን ያለበት ላይ ደርሷል:: ይህ የሆነው የመጀመሪያውን በማየት ለሌላ አዲስ ነገር በመነሳሳት ነው::

በአጠቃላይ ሥርዓተ ትምህርት ሀገር በቀል ቢሆን ውጤታማ ያደርጋልና ትኩረት ቢሰጠው አዋጪ ነው:

በዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሐምሌ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You