የዛሬ አስር ዓመት በ2002 ዓ.ም ከቻይና የተነሳው ‹‹ሳርስ›› የተባለው ቫይረስ ለሳንባ ምች በሽታ አጋላጭ በመሆን በመላው እስያ ተስፋፍቶ ለ800 ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኖ ነበር፡፡ ያኔ ቫይረሱ ከእንስሳት ወደ ሰው በንክኪ የሚተላለፍ የቫይረስ ዓይነት እንደሆነ በመገለፁ በተለይ ዶሮዎችን ለማስወገድ በዘመቻ መልክ የማጥፋት ሥራዎች ተሰርተው ነበር፡፡
የመተንፈሻ አካል ክፍሎች ላይ ከባድ ችግርን ሊያደርስ እንደሚችልና ለሳምባ ምች እንደ ሚያጋልጥ የተነገረለት ይህ የቫይረስ ዓይነት ከአስር ዓመት በኋላ ግብሩን አንድ አድርጎ ስሙን ግን ቀይሮ ኮሮናቫይረስ ተብሎ ከዚያው ከቻይና መከሰቱን ሰምተን ሳናበቃ በቻይና ከዉሃን፣ ከቤጂንግ፣ ከጉዋንግዶንግ፣ ከዩናን፣ ከሻንጋይ፣ ከሲሹዋን፣ ከሻንዶንግ ግዛቶችና ከግዋንግዢ ዥዋንግ ራስ ገዝ አስተዳደር 15 የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ የተጠቁ ሲሆን ከ100 በላይ ቻይናውያን ለህልፈት የመዳረጋቸውን ዜና አደመጥን፡፡
መቼም ቢሆን ኢትዮጵያ የዓለም አካል እንደመሆኗ ዜጎቻችን ወደልዩ ልዩ ዓለማት መጓዛቸው፤ የውጭ ዜጎችንም ማስተናገዳችን ስለማይቀር በድንገተኛ ሁኔታ በዚህ ቫይረስ የተጠቁ ወገኖች ቢኖሩን እንደምን መከላከልና ወረርሽኙ ሳይዛመት በቁጥጥር ሥር ማዋል እንደምንችል ቀድመ ጥንቃቄ ማድረግ በማስፈለጉ የጤና ሚኒስቴራችን ሰሞኑን የሰጠው መግለጫ ለጉዳዩ ትኩረት መሰጠቱን የሚያመለክት ነው፡፡
በ2002 ዓ.ም. ከቻይና በተነሳው የሳርስ ቫይረስ ኢትዮጵያውያን ዜጎች እንዳይጠቁ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የመንገደኞች መውጫና መግቢያ የምርመራ ቡድን ተቋቁሞ፤ በየጤና ተቋማቱ ዝግጅት ተደርጎ ያንን አስከፊ ጊዜ ካለችግር ማለፋችን የሚታወስ ሲሆን፤በአሁኑ ወቅትም ከዚያን ጊዜ በበለጠ ዝግጅት ተደርጎ ምናልባት በቫይረሱ የተጠቁ ቢኖሩ የቫይረሱ ስርጭት ከመስፋፋቱ በፊት በቁጥጥር ስር የሚውልበት ሁኔታ መፈጠሩ ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን ያመለክታል፡፡
የጤና ሚኒስቴር በኮሮና ቫይረስ ሳይያዙ አይቀሩም ተብለው የተጠረጠሩ አራት ሰዎች በኢትዮጵያ መገኘታቸውን፤ ሦስቱ ቫይረሱ በተከሰተበት ዉሃን ግዛት ተማሪዎች እንደነበሩና በማከሚያ ማዕከል ተለይተው ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነ ታውቋል። ከተለዩት ተጠርጣሪዎች በሁለቱ ላይ የሳል እና የሙቀት ምልክት መታየቱ፤ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ደግሞ ምንም ዓይነት የህመም ምልክት ባያሳዩም ወረርሽኙ ከተከሰተበት ስፍራ የመጡ በመሆናቸውና ምልክቱ ከታየባቸው ሰዎች ጋር ግንኙነት ስለነበራቸው ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን አስታውቋል።
የኮሮና ቫይረስ ከቀላል እስከ ከባድ የመተንፈሻ አካል ሕመም የሚያስከትል የቫይረስ ዝርያ ሲሆን፤ ሞትን ሊያስከትል የሚችል ህመም እንደሆነ፤ በሽታው ያለበት ሰው ሲያስነጥስ ወይም ሲያስል፣ ባልበሰሉ ምግቦችና ከታማሚው ሰው ጋር በሚደረግ የቅርብ ንክኪ ሊተላለፍ እንደሚችል፤ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ትኩሳት፣ ሳል፣ የትንፋሽ መቆራረጥና የመተንፈስ ችግር ምልክቶች እንደሚታዩባቸው፤ በሽታው የጠናባቸው ሰዎች ላይ ደግሞ እንደ የሳምባ ምችና ከባድ የመተንፈሻ አካላት ህመም እንደሚታይ፤ ይህንን መሰሉ ምልክት ሲታይም ወዲያውኑ በአቅራቢያ ወደሚገኝ የጤና ተቋም መሄድ እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጠቃሚ መረጃዎችንና ማሳሰቢያዎችን ለኅብረተሰቡ መስጠቱ የትኩረቱ አካል በመሆኑ ተቋማቱ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡
በቻይናዋ ዉሃን ግዛት ተከስቶ ከቻይና ውጪ ወደ በርካታ አገራት እየተዛመተ የሚገኘው ኮሮና ቫይረስ በአሜሪካ፣ በፈረንሳይ፣ በጃፓን፣ በደቡብ ኮሪያ፣ በታይዋንና በአውስትራሊያ በሽታው መታየቱን ለማወቅ ተችሏል።
መንግሥት ይህንን ያህል የቅድመ ጥንቃቄ ዝግጅት ካደረገ ኅብረተሰቡ ስለበሽታው የተጠቀሱት ምልክቶች ሲያጋጥሙት በአቅራቢያ ወደሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ ማሳወቅ፤ በሚያስልና በሚያስነጥስበት ጊዜ በሽታው ወደ ጤነኛ ሰው እንዳይተላለፍ አፍና አፍንጫን በክንድ፣ በመሃረብ ወይም በለስላሳ ወረቀት በመሸፈን፤ አፍና አፍንጫን ለመሸፈን የተጠቀሙበትን ወረቀትም በአግባቡ በቆሻሻ መጣያ ውስጥ ማስወገድና እጅን በውሃና በሳሙና በመታጠብ የበኩሉን የመከላከልና የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ ይገባዋል። ለመከላከሉ ሥራ አጋዥ በመሆንም ሊከሰት ከሚችል ወረርሽኝ አገርንም ሕዝብንም መታደግ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 22/2012