መንግሥት በ2012 ዓ.ም የዜጐችን ኑሮ የሚያሻሽልና ለሦስት ሚሊዮን ወጣቶች በቂ የሥራ ዕድል የሚፈጥር፣ አስተማማኝ የኢኮኖሚ እድገት እውን እንደሚያደርግ ቃል ተገብቶ ሥራው በተቀናጀ መልኩ እየተከናወነ ይገኛል።
በዚህ የተቀናጀ ተግባር የሥራ ዕድል ከተፈጠረባቸው ዘርፎች መካከል የግብርና፤ የኢንዱስትሪ እንዲሁም የግል እና የመንግሥት አገልግሎት ዘርፎች ትልቁን ቦታ ይይዛሉ። የተፈጠረው ሥራ ግን ከተያዘው ዕቅድ ያነሰ መሆኑን የኢትዮጵያ ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን አስታውቋል። የወቅቱ የፖለቲካ አለመረጋጋት ለዜጎች በርካታ የሥራ ዕድል እንዳይፈጥር ዕንቅፋት ቢሆንም በዚህ ሁኔታ ውስጥ ተሆኖም የተፈጠሩ የሥራ ዕድሎች መኖራቸው ልብ ሊባል ይገባል።
በገጠር እየተፈጠረ ያለው የሥራ ዕድል በተለይ ወጣቱን ማዕከል ያደረገ ሆኖ በማህበር በመደራጀት በሚፈልጉት የሥራ መስክ እንዲሰማሩ ዕድሉን ፈጥሯል። ይሁን እንጂ እነዚህ ወጣቶች በተለይ በአምራች ዘርፉ ላይ የተሰማሩት ከፍተኛ የገበያ እጦት እንደገጠማቸው በተለያዩ መድረኮች እየተናገሩ ይገኛሉ። በየደረጃው ያሉ አመራሮች የሚፈጥሯቸው የሥራ ዕድሎች ካለፈው ጊዜ የተሻለ ቢሆንም በአምራች ዘርፉ ለተሰማሩ ማህበራት እና ኢንተርፕራይዞች የገበያ ትስስር አለመፈጠሩ የሥራ ዕድል ፈጠራው ትልቅ ፈተና ሆኖበታል፤ ማሳያዎቹን እንመልከት።
በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በማዕድን ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶች ሥራቸውን የጀመሩት በብድር መሆኑን ገልፀው፤ ነገር ግን ያመረቱትን የማዕድን ምርት ገበያ አቅርበው መሸጥ አለመቻላቸውን አስታውቀዋል።
በዚሁ ክልል በዝንጅብል ምርት የተሰማሩ ወጣቶችም ያመረቱትን የዝንጅብል ምርት የሚሸጡበት ገበያ አለመኖሩን ይናገራሉ። በአማራ ክልል በከብት እርባታ በተለይ ደግሞ በወተት ሀብት ልማት የተሰማሩ ወጣቶች ምርታቸውን የሚረከብ ባለመኖሩ በገበያ እጦት ምርታቸው ለብክነት እንደተዳረገ አመልክተዋል። እነዚህ ማሳያዎች ቢሆኑም
በመላ አገሪቱ በገጠር የሥራ ዕድል ፈጠራው የተሻለ ትኩረት ቢሰጠውም በገበያ ትስስር ረገድ የተሰራው ሥራ እጅግ አነስተኛ በመሆኑ የሥራ ዕድል ፈጠራው በገበያ እጦት ፈተና ውስጥ እንዳለ ማሣያ ነው። ስለሆነም ይህንን ችግር መፍታት ይገባል።
በሚፈጠረው የሥራ ዕድል ልክ የገበያ ትስስር አለመፈጠሩ ችግሩ ብዙ ነው። ወጣቶቹ ሥራቸውን የጀመሩት በብድር በመሆኑ ያመረቱትን በመሸጥ ብድራቸውን ከፍለው ወደ ተሻለ ደረጃ ለመሸጋገር እንቅፋት ይሆንባቸዋል።
በተለይ በተዘዋዋሪ የገንዘብ ፈንድ ተበድረው ሥራ የጀመሩት ማህበራት እና ወጣቶች ለሌሎች ሥራ አጥ ወገኖቻቸው ዕድሉን ማመቻቸት የሚችሉት ተጨማሪ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር የሚያደርጉት ብድራቸውን በወቅቱ መክፈል ሲችሉ ብቻ ነው። ይህ ደግሞ የሚሆነው ምርቶቻቸውን ገበያ አውጥተው ሲሸጡ ነው።
ይህ ችግር ይበልጥ ችግር ሆኖ እንዳይቀጥል ልዩ ትኩረት ይፈልጋል። በተለይ በግብርና ሚኒስቴር 10 ዓመት መሪ እቅድ ላይ እንደተቀመጠው በሚቀጥሉት አስርት ዓመታት 10 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የመፍጠር ጠንከር ያለ ራዕይ አስቀምጧል። በዚሁ እቅድ ግን የገበያ ትስስር ብዙም ትኩረት የተቸረው ሆኖ አይታይም።
በእርግጥ መንግሥት የሥራ ዕድሉን መፍጠር እንዳለበት ቢታመንም በገበያ ትስስሩም እኩል መጓዝ ካልቻለ ችግር ሆኖ ይቀጥላል። ማህበራቱ ወይም ወጣቶቹ ምርቶቻቸውን በገበያ ማስተሳሰር ብዙ አገራዊ ጉዳዮችን ያቃልላል።
በከተሞች ያለውን የምርት እጥረት ለማሟላት፣ለኢንዱስትሪ ግብዓት መሆን፣ በተለይ ደግሞ በማዕድን ዘርፍ እሴት ጨምሮ በጌጣጌጥ ሽያጭ የተሻለ ገቢ መፍጠር ያስችላል። በሌላ መልኩ ደግሞ ገበያ መፍጠር መንግሥትን ብቻ የሚመለከት ጉዳይ አለመሆኑን ተገንዝበው ማህበራቱም ገበያ መፍጠር ላይ ሊሰሩ ይገባል። ስለሆነም የሥራ ዕድል ፈጠራው በገበያ እጦት እንዳይደናቀፍ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
አዲስ ዘመን ጥር 21/2012