ነጻነት፡- ታላቁ የሰው ልጆች ሃብት
ነጻነት ፈጣሪ ለሰው ልጆች ከሰጣቸው ውድ ስጦታዎች ሁሉ የሚበልጥ ነው። ለዚህም ትልቅ ማሳያ የሚሆነው ፈጣሪ ሌላውን ፍጥረት ሁሉ የፈጠረው ሰውን እንዲያገለግሉ በሰው ቁጥጥር ሥር እንዲኖሩ አድርጎ ሲሆን ሰውን ግን በውዴታ ካልሆነ በቀር እንኳንስ ለፍጡር ለእርሱ ለራሱ ለፈጣሪውም ቢሆን ያለ ፍላጎቱ እንዳይገዛ ሙሉ ነጻነት ሰጥቶ የፈጠረው መሆኑን በታላቁ መጽሃፍ ውስጥ በግልጽ ተጽፎ መገኘቱ ነው። የፍጥረት አመጣጥ በሚተነተንበት የመጽሃፍ ቅዱስ ክፍል፤ በዘፍጥረት ምዕራፍ 1 ቁጥር 26 ላይ ቃሉ እንዲህ በግልጽ ተቀምጧል፤ “እግዚአብሔርም አለ፡- ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር፤ የባህር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፣ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፣ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ። ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። እግዚአብሔርም ባረካቸው፣ እንዲህም አላቸው፡- ብዙ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዟትም። የባህር ዓሦችና የሰማይን ወፎች፣ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ግዟቸው። ሰውን ግን አንድ ነገር ብቻ ነበር የከለከለው-ዕጸ በለስን እንዳይበላ፤ እርሱንም ሞትን እንዳይሞትበት አስቦ እንጅ ሊጎዳው አልነበረም። ፈጣሪ የሁሉም አለቃና ገዥ አድርጎ የፈጠረውን ሰው ሁሉንም እንዲያደርግ ነጻነት ሰጥቶታል፤ የሚገድለውን ነገር ግን ከልክሎታል። የነጻነት ትልቁ ሚስጥር ያለውም እዚሁ ላይ ነው፡- ለሞት ከሚዳርገው በቀር ሁሉንም ነገር ለማድረግ ነጻ መሆን የሚቻልበት ድንቅ ሚስጥር፣ ታላቅ ስጦታ! ይህን ያዙልኝና አሁን ምድር ላይ ወዳለው የነጻነት ጽንሰ ሃሳብ ምን ዓይነት መልክ እንዳለው እንመርምር። የነጻነት ትርጉምና «አከራካሪነት»
ነጻነት ከላይ በተገለጸው መሰረት “ወደ ሞት ከሚያመራው መንገድ” በቀር ሰው በመረጠው መንገድ እንዲኖር ከፍጡር ሁሉ ተለይቶ ለእርሱ ብቻ የተሰጠው ታላቅ የፈጣሪ ስጦታ ቢሆንም ሁሌም ራሱን ብቻ እያዳመጠ ራሱን እያሳተ መኖር የሚወደው ራስ ወዳዱ የሰው ልጅ ግን ዛሬም እንደ ትናንቱ ነጻነትን በአግባቡ መጠቀም ሲሳነው ይስተዋላል። ሁሌም “እኔ ብቻ ትክክል” ማለትን ባህሉ ያደረገው ሰው የሚባለው አሳዛኝ ፍጡር በትህትና ተቀራርቦ እውነቱን መርምሮ ትክክለኛውን የነጻነት ትርጉም ፈልጎ በእርሱ ላይ ተስማምቶ በስጦታው ከመጠቀም ይልቅ ሁሉም በየፊናው ለራሱ ብቻ የሚመቸውን ትርጉም እያበጀ ጎራ ለይቶ ሲናከስ ይውላል። በእርግጥም በፖለቲካ ፍልስፍናው ዘርፍ ለአንድ ህብረተሰብ እጅግ አስፈላጊ ነገር ግን በከፍተኛ ደረጃ እርስ በእርሳቸው የሚጣረሱ ሁለት ፅንሰ ሃሳቦች አሉ ከተባሉ የዜጎች ነጻነትና ማህበራዊ ህግና ሥርዓት የሚሉት ናቸው። በሁለቱ ፅንሰ ሃሳቦች መካከል የማይታረቅ የሚመስል ተቃርኖ መኖሩን የዘርፉ ምሁራን ይገልጻሉ። እስከ ዛሬ ድረስ ምሁራን በጎራ ተከፋፍለው እልህ አስጨራሽ ሙግት ያደርጉባቸዋል። እንደ ታዋቂው የአስራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንግሊዛዊ ፈላስፋ ጆን ስቱዋርት ሚል ዓይነቶቹ የፍጹማዊ ነጻነት አቀንቃኞች “ማንም በፈለገው መንገድ የፈለገውን ለማድረግ የሚያስችል ፍጹም የሆነ ነጻነት ሊኖረው ይገባል” በማለት ነጻነት ገደብ አልባ መሆን አለበት ብለው ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከራሉ። ወግ አጥባቂዎቹ በበኩላቸው “የለም ህግና ሥርዓት በሌለበት ነጻነት ሊኖር አይችልም፤ ጆን ስቱዋርት ሚልና ደቀ መዝሙሮቹ የህግና ሥርዓት ትርጉም አልገባቸውም” በማለት የፍጹማዊ ነጻነት አቀንቃኞችን ይወርፏቸዋል።
እናም ትልቁ የሰው ልጆች ሃብት ነጻነት ዛሬም እንደ ጥንቱ ሞትን የሚያመጣ ዕጸ በለስ ሆኖ በአዳም ልጆች ላይ ጥፋትን የሚያስከትልባቸው አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ ይስተዋላል።በእኛ አገር በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ እያጋጠመ የሚገኘው ችግርም ይሄው ነው። ለውጡን ተከትሎ ህዝቡ ለረጅም ጊዜ ያጣውን ፖለቲካዊ ነጻነት እያገኘ መሆኑ በረጅም ዘመን አኩሪ ታሪኩ ላይ አንድ ሌላ ወርቃማ ታሪክ ለመጻፍ የሚያስችለው ጊዜ ላይ ነው። ይሁን እንጅ የፖለቲካ ሳይንስ ሊቁ ሩሰል ኪርክ እንዳለው የተገኘው ነጻነት በህግና በሥርዓት እስካልተደገፈና ከለውጡ መሪዎች መካከል አንዱና ዋነኛው የሆኑት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ለማ መገርሳ እንዳሉትም ነጻነትን መሸከም የሚችል ትካሻ እስካልፈጠረ ድረስ በነጻነት ስም ወንጀል መፈጸም ይችላል። ከለውጡ ማግስት ጀምሮበተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች የተፈጠሩት ሰውን በድንጋይ መውገርና ዘቅዝቆ እስከ መስቀል የደረሱ አረመኔያዊነት የተቀላቀለባቸው የደቦ ፍርዶችለዚህ ጥሩ ማሳያዎች ናቸው። የራስን ርካሽ ፖለቲካዊ ጥቅም ለማሟላት ፍጹም አግባብነት በሌለው ከህጋዊነት ብቻ ሳይሆን ከሰብዓዊነት በወጣ አኳኋን እንደ ግዑዝ ዕቃ ለ “መደራደሪያነት” በሚል በኃይል ታፍነው ተይዘው በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ የማይታወቁና የህዝብ እንባ እያፈሰሱ ያሉ ሴት ተማሪዎችም በነጻነት ስም እየተፈጸመ ስላለ አደገኛ ወንጀል ዋና ማሳያ ናቸው።
ከሰሞኑ ደግሞ የዓለም የሰላምና የመቻቻል ከተማ ተብላ በዓለም ህዝብ ድምጽ በተመረጠችው በጥንታዊቷና በታረካዊቷ የፍቅር ከተማ ሐረር የጥምቀት በዓል በተከበረበት ዕለት በባንዲራ ምክንያት ግጭት ተፈጥሯል። የግጭቱ መነሻም ባንዲራ ይሁን እንጅ በነጻነት ሰበብ የአንድን ቡድን ፍላጎትና ዓላማ በሌላው ላይ አስገድዶ ለመጫን መሞከር ነው። ነጻነት ፍቅር ነው። የራሱን ወድዶ የሌላውን አይጠላም፣ በእርሱ ላይ ሊያደርጉበት የማይፈልገውን በሌላው ላይ አያደርግም፤ ይተባበራል እንጅ አይፎካከርም። ለራሱ ጥቅምና ፍላጎት ብሎ የህዝብን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ አይጥልም። ለሃገርና ለህዝብ ሰላምና ደህንነት ሲል በህግና በሥርዓት ይንቀሳቀሳል።
ነጻ ሲወጡ ከእውነት የወጡ አካላት የፈጠሩት ቀውስ በጣም የሚያሳፍረውና የሚያሳዝነው ደግሞ አገሪቱና ህዝቦቿ በዚህ ደረጃ ሰላማቸውን እያጡ ያሉት በህዝብ ትግል ነጻ ወጥተው በአገራቸው መሬት በነጻነት የሚንቀሳቀሱ ታህተ ሰብዕ ፖለቲከኞች እና ዋነኛ የዲሞክራሲ መገንቢያ በሆኑት የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት አማካኝነት መሆኑ ነው። መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ የተፈጠረውን አገራዊ ለውጥ ተከትሎ ለውጥ ከመጣባቸው ዘርፎች መካከል አንዱና ዋነኛው ሚዲያው መሆኑን በርካቶች ይስማማሉ። ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በሚዲያው ዘርፍ ለውጥ መኖሩን የሚያሳዩ ተጨባጭ ማሳያዎች ካለፉት ዓመታት በማነጻጸር የሚገልጹት ብዙዎች ናቸው። ጋዜጠኞች በተናገሩት ነገርና በጻፉት ጽሁፍ ይታሰሩ ነበር ብቻ ሳይሆኑ በእነርሱ አማካኝነት አስተያየት የሚሰጡና ሃሳባቸውን የሚገልጹ ሰዎችም ጭምር በልዩ ልዩ መንገዶች ተፅዕኖ ይደረግባቸው ነበር።
ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ሲ.ፒ.ጀ ከ1984 እስከ 1994 ዓ.ም ባሉት አስር ዓመታት “አስሩ የዓለማችን ፕሬስ ጠላቶች” በሚል ያወጣውን መረጃ በአስረጅነት መጥቀስ ይቻላል። በመረጃው መሰረትም የዓለም ሃገራት መሪዎች ዝርዝር ሟቹ የቀድሞው ኢትዮጵያ አስሩንም ዓመት ከዓለም የፕሬስ ጠላቶች መካከል አንዷ ሆነና ስሟ መካተቱ ነው። ይህም በአገሪቱ ውስጥ የነበረው የፕሬስ ነጻነት ምን ያህል አደጋ ውስጥ ገብቶ እንደነበር ያመላክታል።
ከለውጡ በኋላ ግን ሙሉ በሙሉም ባይሆን አንጻራዊ ነጻነት ይታያል። ማንም ሰው የፈለገውን የመናገርና የመጻፍ መብት አለው። እስከ አሁንም በተናገረው ነገር ወይም በጻፈው ጽሁፍ ምክንያት የተከሰሰ ወይም የታሰረ ጋዜጠኛ አለመኖሩን ዓለም አቀፍ ተቋማት ሳይቀር መግለጻቸው ይታወሳል። ድንበር የለሹ የሪፖርተሮች ቡድን የዘንድሮውን የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን አስመልክቶ የዓለም አገራት የሚገኙበትን ደረጃ የሚጠቁም ዝርዝር ባወጣበት መግለጫው ይህንኑ መስክሯል። ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አርባ ደረጃዎችን በማሻሻል በዘርፉ ከፍተኛ ዕድገትን ማሳየቷንም አድንቋል። በዚህም ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ከነበረችበት የአንድ መቶ ሃምሳኛ ደረጃ ወደ አንድ መቶ አስረኛ ከፍ ብላለች። የፕሬስ ነጻነትን በሚመለከት ለአገራት የተሰጠው ደረጃ ስድስት ዋና ዋና መመዘኛዎችን መሰረት ያደረገ ነው። እነዚህም የሚዲያዎች የተለያዩ ሃሳቦችን በእኩልነት የማስተናገድ አቅምና የብዝሃነት ደረጃ፣ ገለልተኝነት፣ ሚዲያዎች የሚገኙበት ሁኔታ ምቹ መሆንና አለመሆንና በዚህም ለግለ ሳንሱር የሚያስገድድ ሁኔታ መኖር አለመኖር፣ ሊያሰሩ የሚችሉ የህግ ማዕቀፎች መኖር፣ ግልጸኝነት እንዲሁም መረጃዎችን ለመሰብሰብና ዜናዎችን ለማዘጋጀት የሚያግዝ ደረጃውን የጠበቀ መሰረተ ልማት መኖርን የሚመለከቱ ናቸው። ይህም ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ይሆናል ተብሎ የማይታሰብ ትልቅ ለውጥ መሆኑን በርካቶች የሚመሰክሩት ሃቅ ነው።
ይሁን እንጂ ለውጡ የሚደነቀው ከነጻነት አኳያ ነው እንጂ የሃገሪቱ ሚዲያዎች የቆየው ችግራቸው ገና ሙሉ በሙሉ ሳይለቃቸው ለውጡን ተከትሎ ሌላ አደገኛ ችግር(ስህተት ቢባል ይቀላል) ውስጥ ገብተዋል። ይኸውም መንግስት በፈቀደው የነጻነት መንገድ ተጠቅመው በተለይም ከውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ሥራ የጀመሩና በአገር ውስጥም ቢሮ የከፈቱ አዳዲስ መገናኛ ብዙኃን የሙያውን ሥነ ምግባርና ዓለም አቀፋዊውን አደረጃጀት ትተው የፖለቲካ ዓላማ ይዘው በዘርፉ መሰማራታቸው ነው። ከዚህም ባሻገር ዲሞክራሲን ይገነባሉ ተብለው የሚታሰቡት ሚዲያዎች እንደ ፖለቲካ ፓርቲዎቻችን በብሔር እየተደራጁ መሆናቸው አገር ከመገንባት በተቃራኒው መቆማቸውን ያመላክታል። በዚህ ረገድ የክልል ሚዲያዎችም ተጠቃሽ ናቸው። እናም አሁን ላይ በብሔር ላይ የተመሰረተ በተለይም በጥላቻ ፖለቲካ በተሞሉ ጽንፈኛ ፖለቲከኞች የሚመሩ ሚዲያዎች ለራሳቸው የፖለቲካ ጥቅም ሲሉ ህዝብን ከህዝብ፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት በማጋጨት ሥራ ላይ ተጠምደዋል። በህዝብ ትግል ነጻ የወጡ ወይም ነጻነት በመኖሩ ከአለመኖር ወደ መኖር የመጡ ሚዲያዎች የህዝብን ሰላም በሚበጠብጥ አፍራሽ ድርጊት መጠመዳቸው እጅግ ያሳዝናል።
ድርጊታቸው በሃገርና በህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን በየለቱ የምንታዘበው ሃቅ ነው። ለዚህም ትልቁ መንስኤ ጥቅምን ብቻ አጋባሽ የሆኑት ሚዲያዎቻችን በነጻነት ስም ከእውነትና ሙያው ከሚጠይቀው ሥነ ምግባር መውጣታቸው ነው። ሚዲያዎች የውይይትና የነጻ ሃሳብ መንሸራሸሪያ በመሆን ዲሞክራሲያዊ ባህልን መዳበርና ለሃገር ግንባታ ዋነኛ መሳሪያዎች ቢሆኑም አሁን ላይ በተቃራኒው ቆመዋል። ወገንተኝነታቸው ለህዝብ መሆኑ ቀርቶ ለጥቅም ሆኗል። የሚመሩት በሙያው ሥነ ምግባር ሳይሆን በፖለቲካ ነጋዴዎች ርካሽ ምግባር መሆኑን በግልጽ እየተመለከትን ነው። ይህ ሃገርን ሊያፈርስ የሚችል አደገኛ አካሄድ ነው። በዚህ ላይ ወቅቱ ሃገሪቱ ከበርካታ ችግሮች ጋር ሆኖ ሃገራዊ ምርጫ ለማድረግ እየተቃረበች ያለችበት ጊዜ ላይ በመሆናችን ነጻነትን ለጥፋት የሚጠቀሙ “መገናኛ ብዙሀኖቻችን” ከ “መለያያ ብዙሃንነት” ወደ “መገናኛ ብዙሃንነት” መምጣት ያለባቸው መሆኑን በአጽንኦት እናሳስባለን።
እንደ መገናኛ ብዙኃኑ ሁሉ በአገሪቱ ውስጥ የተፈጠረውን ለውጥ ተከትሎ የህዝብ ትግል ነጻነት ካስገኘላቸው አካላት መካከል ዋነኞቹ “ፖለቲከኞች” ናቸው። በዚህም በህዝብ ትግል በመጣው ለውጥ የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋቱን፣ የሲቪክ ማህበራት እንቅስቃሴን የሚገድቡ የህግና የፖሊሲ ማዕቀፎች እንዲሁም የመናገርና ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብትን የሚያፍኑ ጨቋኝ ህጎች መሻሻላቸውን ተከትሎ ብዛት ያላቸው ፖለቲከኞች ከስደት ተመለሱ። በርካቶች ከእስራት ተፈቱ። ይሁን እንጅ ህዝባቸውን ከተቀላቀሉ ፖለቲከኞች መካከል አንዳንዶቹ የነጻነት ትርጉም ያልገባቸው ነበሩ ማለት ይቻላል። ምክንያቱም ነጻነትን እንደ ልብ ተንቀሳቅሰው፣ ሃሳባቸውን በነጻ ገልጸው፣ በሃሳብ አሸንፈው የበለጠ ነጻነትንና ዲሞክራሲን ለማምጣት ሳይሆን እየታገሉበት ያለው ያለ ምንም ገደብ የራሳቸውን ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስ ነው። ያለ ምንም ገደብ አፍራሽ ሃሳባቸውን ለማስፋፋትና በህዝብ ስም የራሳቸውን ጥቅም ለማሳካት ነው ነጻነትን እየተጠቀሙበት ያለው። በዚህም ያለ ማንም ከልካይ ጥላቻን ይሰብካሉ፣ ህዝብን በህዝብ፣ ሃይማኖትን በሃይማኖት፣ እንዲሁም ህዝብን በመንግስት፣ መንግስትን በህዝብ ላይ ያነሳሳሉ። ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ሲነገራቸው “ነጻነታችንን ተገደብን” በማለት ከሳሽ ሆነው ይቀርባሉ። እናም በእኔ ዕይታ ለውጡ ከመጣ ወዲህ እስካሁን ድረስ ባሉት ሁለት ዓመታት በሃገሪቱ ውስጥ ለተፈጠሩትና እየተፈጠሩ ላሉት ችግሮች ሁሉ ዋነኞቹ ተጠያቂዎች በነጻነት ስም ወንጀል እየፈጸሙ በነጻነት እየኖሩ ያሉት እነኚሁ የፖለቲካ ነጋዴዎች ናቸው።
ለዚህም በቅርቡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ የሰጡት ምስክርነት የሚያሳየው ለውጡ ከመጣ ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አገሪቱ ውስጥ በተፈጠሩ የፖለቲካ ግጭቶች መሆናቸው ነው። አገሪቱን ለከፍተኛ ችግር እያጋለጡ የሚገኙ እነዚህ ፖለቲካዊ ግጭቶች የሚፈጠሩት ደግሞ በማን እንደሆነ በአደባባይ የሚታይ ሃቅ ነው። ሃገሪቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር በግጭትና በመፈናቀል እንድትታወቅና ህዝቦቿም ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰላም እንዲያጡ እያደረጉ ያሉት ፖለቲካዊ ግጭቶች የሚፈጠሩት በህዝብ ትግል ነጻ ወጥተው መልሰው ህዝብን እያባሉ የሚገኙ ጡት ነካሽ የፖለቲካ ነጋዴዎች ናቸው።
የነጻነት ወንጀለኞችን ለመከላከል እንደ መፍትሔ
በህዝብ ስም የህዝብን ደህንነት አደጋ ላይ እየጣሉ ባሉ ራስ ወዳድ ጥቅመኛ ፖለቲከኞች የተማረረው የኢትዮጵያ ህዝብም “ችግሩ የመንግስት ነው፤ በነጻነት ስም ማንም በአገሪቱ ላይ ብጥብጥና ችግር መፍጠር የለበትም፣ መንግስት ህግና ሥርዓትን ማስከበር አለበት” ሲል በተደጋጋሚ ቢገልጽም መንግስት በበኩሉ ነጻነት ይቀድማል በሚል ቅድሚያ ለነጻነት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ሲናገር ይሰማል።
ከሰሞኑ በሃረር እንደሆነው ሁሉ ከባንዲራ ጋር ተያይዞ በአንድ ወቅት በአዲስ አበባም ተፈጥሮ የነበረውን ችግር አስመልክቶ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፤ “የሰው ችግር ያሰበውንና የፈለገውን እንደ ዜጋ በነጻነት መናገር ነው። ለዚህ ነው መገናኛ ብዙሃንን የከፈትነው፤ ለዚህ ነው መድረኩን ክፍት ያደረግነው” በማለት ቅድሚያ ህዝቡ ያጣውን ነጻነት ለማጎናፀፍ እየተሰራ መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል። ይሁን እንጂ ይሄ ያልገባው የትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ወይም ኃይል ካለ መቼም አሸናፊ አይሆንም በማለት የተገኘውን ነጻነት ህዝቡን ለመለያየት የሚፈልጉ ኃይሎች ሃሳባቸው እንደማይሳካ አውቀው ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢያሳስቡም ከራስ ጥቅም ውጭ ህዝብ ምን ማለት እንደሆነ ያልገባቸው ኃይሎች ዛሬም ከክፉ የመለያየት ሥራቸው አልተቆጠቡም።
እናም አሜሪካዊው የፖለቲካ ምሁርና የሞራልና የማህበራዊ ሂስ ሊቅ ሩሰል ኪርክ፤ እንዳለው በህግና በሥርዓት ካልተመራ በቀር በነጻነት ስም ወንጀል ሊፈጸም ይችላልና፤ ነጻነት ልቅነት የመሰላቸው የእኛም ጅሎች ይህንኑ እያደረጉ ነውና በነጻነት ስም እየተፈጸሙ ካሉ ወንጀሎች ራሳችንን ለመጠበቅ የመጨረሻው አማራጭ የህግ የበላይትን ማስፈን ነው እንላለን።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 20/2012
ይበል ካሳ