የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለ2020 ቶኪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅትና ለተለያዩ የልማት ሥራዎች ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ አስቧል። በተያዘው ዓመት መጨረሻ በሚካሄደው የቶኪዮ ኦሊምፒክ በመድረኩ ትልቅ ስምና ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ በተለያዩ ስፖርቶች ተሳታፊ ትሆናለች። ለዚህ የሚሆነውን ዝግጅት የሚመራ ብሔራዊ የዝግጅት ኮሚቴም በቅርቡ ተዋቅሮ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ይገኛል። ኮሚቴው እያደረገ ከሚገኘው ዝግጅት መካከልም ለውድድሩ እንዲሁም ሌሎች የልማት ሥራዎች የሚውል አንድ ቢሊዮን ብር ለማሰባሰብ እንዳሰበ ጠቁሟል። ለዚህም ከ12 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የኦሊምፒክ ደጋፊ ማህበር አባላትን በማፍራት፣ የአትሌቶች ሽኝትና ሽልማት እንዲሁም በመድረኩ የአገሪቷን መልካም ገጽታ ለመገንባት ማቀዱን አሳውቋል።
ለቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ‹‹ከቶኪዮ እስከ ቶኪዮ›› በሚል ርዕስ ከተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመስራት ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል። በትናንትናው ዕለትም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር በከተማዋ ከሚገኙ የግልና የመንግሥት ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች ከተውጣጡ ርዕሰ መምህራንና የትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል። በመድረኩም ላይ የኦሊምፒክ መርሆችና እሴቶች እንዲሁም አገሪቷ ከሜልቦርን እስከ ሪዮ ኦሊምፒክ የነበራት ተሞክሮ ላይ ገለጻ ተደርጓል። በቶኪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅት ዙሪያም ከትምህርት ቤቶችና ከማህበረሰቡ ምን ይጠበቃል በሚል ውይይት ተካሂዷል። ውይይቱም የኦሊምፒክ እሴቶችን በተማሪዎች ማስረጽ፣ የትምህርት ቤት ማህበረሰብን የኮሚቴው አባል ለማድረግ እንዲሁም ለኦሊምፒኩ ሽኝት የትምህርት ቤት ማህበረሰብ ተሳታፊ እንዲሆን አልሞ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።
በመድረኩ ላይም የዝግጅት ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ፣ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዳኘው ገብሩ እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳዊት ትርፉ ተገኝተዋል።
ዶክተር አሸብር የውይይት መድረኩን ሲከፍቱ በቀደመው ወቅት የስፖርት እንቅስቃሴ መነሻ የሆኑት ትምህርት ቤቶች በርካታ ውጤታማ አትሌቶችን ማፍራት እንደቻሉ በማስታወስ፣ ስፖርቱን ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ እንዲሁም በእኔነት ስሜት ሁሉም ተሳትፎ እንዲያደርግበት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በመድረኩ ላይ ተሳታፊ የሆኑ የከተማዋ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህራን እንዲሁም ከየክፍለ ከተማው የትምህርት ቢሮ የተውጣጡ ተሳታፊዎች በበኩላቸው እንቅስቃሴው የዘገየ መሆኑን ጠቁመዋል። በትምህርት ቤቶች ያለው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ባለመበረታታቱ መቀዛቀዝ አሳይቶ የቆየ መሆኑን ያነሱት አስተያየት ሰጪዎች፤ ከዚህ ቀደም እንደነበረው እንዳይሆን ድጋፍ መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል። አያይዘውም የትምህርት ቤት ማህበረሰብ ለዚህ እንቅስቃሴ ዝግጁ መሆናቸውንና አብረው ለመስራት እንደሚፈልጉም አረጋግጠዋል።
የብሔራዊ ኦሊምፒክ ዝግጅት ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አባዱላ ገመዳ፤ እንቅስቃሴው ሁለት ዓላማዎች ያሉት መሆኑን ይገልጻሉ። የመጀመሪያው ለቶኪዮው ኦሊምፒክ ዝግጅት በማድረግ አገሪቷን የሚያኮራ ሥራ ማከናወን እንዲሁም ለቀጣይ ኦሊምፒኮች መነሻ የሚሆን የልማት ሥራ (የብሔራዊ ቡድን ዝግጅት የሚደረግበት ማዕከል ግንባታ) ለማከናወን መሆኑን ጠቁመዋል። ለዚህ የሚሆን ገቢ ለማሰባሰብም ሰፊ የሕዝብ እንቅስቃሴ በመፍጠር ማህበረሰቡ የዝግጅቱ አካል የሚሆንበትና መሠረተ ልማቱ ላይ የሚሳተፍበት እንደሚሆን ተናግረዋል። ይህም ከአዲስ አበባ ከተማ የሚጀመር ሲሆን፤ ተማሪዎች ደግሞ በስፋት ተካፋይ እንዲሆኑ ለማድረግ መታሰቡን አብራርተዋል።
ኦሊምፒክ ትውልድ ተሻጋሪ እንቅስቃሴ እንደመሆኑ አዲሱ ትውልድ ባለቤት በመሆን ችቦውን እንዲለኩስ ለማድረግ በእቅድ ተይዟል። ለዚህም የካቲት 08/2012ዓ.ም ከአዲስ አበባ በመጀመር በአገሪቷ የሚዞር የኦሊምፒክ ችቦ መዘጋጀቱ ታውቋል። ከዚህ ባሻገር በእንቅስቃሴው ሁሉም የእኔነት ስሜት እንዲኖረውና የኮሚቴው አባል እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ሰብሳቢው አስረድተዋል። በቀጣይም ለዚሁ አላማ የሚውልና በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚዘጋጅ የገቢ ማሰባሰቢያ የእራት መርሃ ግብር እንደሚኖር ይጠበቃል። በዚህም ፕሮግራም ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚሳተፉ ሲሆን በመላው አገሪቷ በርካቶች የሚካፈሉበት መሰል እቅድም ተይዟል። እቅዱም ከአንድ አካባቢ ብቻ ገንዘብ ማሰባሰብ ሳይሆን ሁሉም ‹‹የራሴ›› የሚለውን አንድ የኦሊምፒክ መንደር እስከ መገንባት ይዘልቃል።
በኦሊምፒኩ ዝግጅት ዙሪያ ቢሮውና ኮሚቴው አብረው መስራት የጀመሩት ቀደም ብለው እንደሆነ የሚገልጹት ምክትል ቢሮ ኃላፊው አቶ ዳኘው፣ በውይይቱም ለቶኪዮው ኦሊምፒክ ብቻም ሳይሆን ለሌሎችም ኦሊምፒኮች መርሁን ለማስረጽ እንደታሰበ ተናግረዋል። አሁን ለሚወዳደሩት አትሌቶች አቅምና ጉልበት መሆን እንዲሁም ተተኪ አትሌቶችን መፍጠርም ዋነኛ ዓላማው መሆኑን አብራርተዋል። ትምህርት ቤቶች በባለሙያ፣ በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዲሁም ለስፖርቱ ፍላጎት ያላቸው ታዳጊዎች ያሉበት በመሆኑ መርሆቹንና እሴቶቹን ለማስረጽ ምቹ ስፍራዎች መሆናቸውንም አክለዋል። በመሆኑም የካቲት 8 ለተያዘው ቀጠሮ እንደ ትምህርት ቢሮ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 20/2012
ብርሃን ፈይሳ