ወራሪው የኢጣሊያ ጦር ዶጋሊ ላይ በራስ አሉላ አባ ነጋ በሚመራው የኢትዮጵያ ጦር ድባቅ ተመቶ የመጀመሪያውን ሽንፈት የቀመሰው ከ134 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 18 ቀን 1879 ዓ.ም ነበር።
ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፣ “አፄ ዮሐንስ እና የኢትዮጵያ አንድነት” በተሰኘ መጽሐፋቸው የዶጋሊን ጦርነት ታሪክ እንደሚከተለው ተርከውታል። ራስ አሉላ የጣሊያኖች የወረራ አያያዝ ወሰን እንደሌለው የሚናገሩትም የሚጽፉትም ሁሉ ሐሰት የሞላበት መሆኑን በመረዳት የጦርነት ዝግጅታቸውን ሳይተው ከአስመራ ወደ ጊንዳ በሚጓዙበት ጊዜ ቀጥሎ ያለውን ደብዳቤ ጻፉ።
“የተላከ ከራስ አሉላ ይድረስ ከጄኔራል ካርሎ ዤን … ሰላምታ … በናይብ መሀመድ የላኩብኝ ቃል መልካም ነው። እንግዲህ ወዳጅ ከሆንን ጦር ሠራዊትዎን ከዊዓ ያስነሱ፣ ነጋዴውም በአድገዴ (ሐባብ) በኩል መሆኑ ቀርቶ ለመሸጥም ለመግዛትም ከጊንዳዕ በኩል ይመላለስ፣ ዊዓ ያለው ጦርዎ እስከ ጥር 13 ቀን ድረስ ይልቀቅ። ዙላ ያለው ወታደርዎ ከአንድ ወር በኋላ ይውጡ። ወዳጅነት ከፈለጉ ይህ መፈጸም አለበት። ያለዚያ ግን ወዳጅነት መቅረቱን ይወቁት። ጥር 5 ቀን 1879 ዓ.ም። ”
ለዚህ ደብዳቤያቸው ጄኔራሉ እንደዚህ ሲል ይመልሳል። “በ 5 ጥር የተጻፈውን ደብዳቤዎን ናይብ መሀመድ ሰጥቶኝ አነበብኩት። ወዳጅነት እንደምፈልግ ደጋግሜ ነግሬዎታለሁ። ዊዓ የሚቀመጡት ወታደሮች ይህን ወዳጅነት አይቃወሙም። ወታደሮቹ ዊዓ የሚቀመጡት ለአገሩ ጸጥታ ሲባል ነው። እንደውም ከማናቸውም ወገን ውጊያ ቢገጥማቸው እንዲቋቋሙ ከቀድሞ በበለጠ አጠናክሬያቸዋለሁ። ይህንንም የምሎት የኢጣሊያ መንግስት ሌሎችን ሲያከበር ራሱም መከበር እንደሚፈልግ እንዲያውቁት ብዬ ነው። የኛ ወዳጅ እስከሆኑ ድረስ እኔም ወዳጆ ነኝ። “
በዚህ ጊዜ የኢጣሊያ ወታደር ምጽዋ ከገባ ሁለት ዓመት ሆኖታል። … ራስ አሉላ ጄኔራል ካርሎ ዤን የእምቢታና የማስፈራሪያ ቃል ከጻፈላቸው በኋላ 5 ሺ የሚደርስ ጦራቸውን አስከትለው በጥር ወር አጋማሽ 1879 ዓ.ም ላይ ከጊንዳ ቁልቁል ወደ ሰሐጢ መጥተው ወደ ምሽጉ ለመድረስ አምስት ኪሎ ሜትር ሲቀራቸው ሠፈር አደረጉ። በዚህ ጊዜ በሰሐጢ የሁለት ኮምፖኝ የነጭ፣ 300 ያገር ተወላጅ ወታደር ይዞ መሽጎ የተቀመጠው ማዦር ቦርቲ ከምሽጉ ወጣ ብሎ ጦርነት እንደገጠመ ሁኔታው አደገኛ መሆኑን ሲረዳው ከነጦሩ ወደ ምሽጉ ተመለሰ። ራስ አሉላም ተጠግተው በተደረገው ውጊያ ከኢጣሊያኖች ወገን ፌዶሪኩዎም የሚባለው የመቶ አለቃ ከሁለት የኢጣሊያና ከሶስት ያገር ተወላጅ ወታደሮች ጋር ሞተ። ይሁን እንጂ በምሽጉ ውስጥ ተገን ይዘው የሚዋጉት የኢጣሊያ ወታደሮች በውጭ ያለምንም ተገን በሚዋጉት በኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ብዙ ጉዳት ማድረሳቸውን ራስ አሉላ ሲመለከቱ ፣ የሰሐጢን ምሽግ ትተው ወደታች ወደ ዶጋሊ ወርደው ሠፈሩ።
በዚህ ጊዜ ማዦር ቦረቲ መከበቡን ገልጦ የጦር እርዳታም ስንቅም ባስቸኳይ እንዲላክለት ያንለቱን ከሰዓት ወደ ጄኔራል ዤኒ በግስጋሤ ልኮ ነበረ። ጄነራሉም ምንኩሉ ለሰፈረው ለሶስተኛው ባታዬ የእግረኛ ጦር አዛዥ ለኮሎኔል ቶማስ ክሪስቶፎርስ ወታደርም የጦር መሳሪያም በበቅሎና በግመል ጭኖ በቶሎ ወደ ተከበበው ወደ ሰሐጢ ምሽግ እንዲዘምት አዘዘ።
ኮሎኒል ክሪስቶፎሪስ ትዕዛዙ ከሰዓት በላይ እንደ ደረሰው ሌሊቱ ጭምር ሲዘጋጅ አድሮ ሲነጋ 540 የነጭ፣ 50 የአገር ተወላጅ ወታደር ሁሉም በደንብ የታጠቁ አሥር የሚሆኑ መድፎች ከምንኩሎ ተነስተው ከጠዋቱ በሁለት ሰዓት ተኩል ዶጋሊ አጠገብ ሲደርሱ ፣ ራስ አሉላ ወታደሮቻቸውን ግራና ቀኝ ሥፍራ ሥፍራ አስይዘው ይጠባበቁ ነበር። ጣሊያኖቹ ግን፣ ሁል ጊዜ የኢትዮጵያን ጦር በመናቅ መንገድ ለመንገድ ሲመጡ፣ “ራስ አሉላ እነርሱን በጥሩ አይተው ወደ ጊንዳ እንደሚሸሹ የጦር መኮንኖቹ አምነው ይኸንኑ በጉዞ ላይ ይጨዋወቱ ነበር” ይባላል። ይሁን እንጂ፣ የራስ አሉላን አመጣጥና የጦራቸውን ብዛት የሰሙ አንዳንድ በጣልያኖቹ ውስጥ የተቀጠሩ ፓሽ ባዙቆች ከጉዞ ላይ ሰረቅ እያሉ ወደ ጫካ በመግባት የጠፉ ቢኖሩም፣ በቅርብ የመጣውም መቀደም ብሎ የነበረውም የነጭ ወታደር ወደ ፊት ሲገሰግስ ሳለ ሳያስበው ከራስ አሉላ ጦር የእሩምታ ተኩስ ላይ ወደቀ።
ኮሎኔል ክሪስቶፎሪስ ወታደሩ በቶሎ የመከላከያ ሥፍራ እየፈለገ በመያዝ እንዲመክት ለየሹማምንቱ ትዕዛዝ ወዲያው ሰጥቶ ወታደር ከወታደር እየተታኮሰ ውጊያው በተጋጋለበት ሰዓት ዕርዳታ እንዲደርስለት ወደ ካርሎ ዤኒ በጥድፊያ መላክተኛ ላከ። ዳሩ ግን፣ ተኩሱ በሚጋጋልበት ሰዓት ኢትዮጵያውያኑ እያደር ዙሪያውን እንደ ቀለበት ከበው ጠላቶቻቸውን መውጫ መግቢያ አሳጧቸው። ጣልያኖቹም በያለበት መከበባቸውን ሲያውቁት ጠንክረው ይዋጉ ጀመር። ነገር ግን፣ ከያዙት የጦር መሣሪያ ግማሹ በተለይ መድፉና መትረየሱ ከግብፆች በውርስ ይሁን በግዥ ያገኙት አሮጌ መሣሪያ ስለነበረ በመካከሉ አልሠራ እያለ አስቸገረ። ጥይቱም አለቀባቸው። ወደ ዤኒ የተላከው መልዕክተኛ ጣልያኖቹ አደገኛ ሁኔታ ላይ መገኘታቸውን አስረድቶ በአራትና በአምስት ሰዓት መካከል ደርሶ ዕርዳታው ተዘጋጅቶ ከመላኩ በፊት ራስ አሉላና ወታደሮቻቸው ከወዲህ የድል አድራጊነት ሥራቸውን አከናውነው ጨረሱ። ውጊያውም ያለቀው በመጨረሻ ላይ በጨበጣ ጦርነት ነበር።
በውጊያው ላይ ዋናው አዝማች ኮሎኔል ቶማስ ደ ክሪስቶፎሪስ ከ22 የጦር መኮንኖቹ ጋር በጦሩ ሜዳ ላይ እየተዋጋ ወደቀ። ከመሞቱም በፊት ሻምላውን በቀኝ እጁ ይዞ፣ ‹‹ጣሊያን ህያው ትሁን ጣልያን ህያው ትሁን፣ ወደ ፊት ቅደም፣ በለው፤›› እያለ በመጮኽ የጀግንነት ሙያ ለማሳየት ሞክሮ እንደነበር በቁስለኞቹ አንደበት የተነገረው፣ በኋለኛው ጊዜ በወገኖቹ በጣልያኖቹ ዘንድ የመደነቅ ታሪክ አግኝቷል። ያልተናገረውንም በመጨማመር ቆስሎ ከመውደቁና ሕይወቱ ከመጥፋቱ በፊት በሕይወት ላሉት 12 ወታደሮች በውጊያ ወድቀው ለተረፈረፉት ወታደሮች ‹‹የብረት ሰላምታ ሰጡ›› የሚል ቃል ወርውሯል እየተባለ በየጊዜው ሲጻፍና ሲታመን የቆየውን የዛሬው ተመራማሪ ጸሐፊ አንጀሎ ደልቦካ የፈጠራ ወሬ አድርጎታል።
በውጊያው ላይ ራሱ ኮሎኔል ክርስቶፎሪስ ከ22 የጦር መኮንኖች ጋር ሲወድቅ 418 ወታደሮች ሞተዋል። ‹‹ከነዚህም ውስጥ ቆስለው ወደ ምፅዋ እንደርሳለን ብለው በሌሊት ጉዞ እያቃሰቱ በመንገድ የሞቱ ምፅዋ ደርሰው ነፍሳቸውን ያተረፉም ይገኛሉ። አንዳንዶቹም ምፅዋ ሆስፒታል እንደተገኙ ለየዘመዶቻቸው በጻፉት ላይ፣ ሹማምንቶቻችን ያለምንም ጥናትና ድርጅት ከጦርነት ላይ አጋፍጠውን ‘ጣልያን ህያው ትሁን ወደ ፊት ግፋ’ ብለው በመጨረሻ እኛን ጥለውን እነሱ ሸሹ የሚል ሮሮ ያቀረቡ ነበሩ። ከተረፉት የጦር መኮንኖች መካከል ካፒቴን ሚሸሊኒ የሚባለው የመድፈኛ የጦር መኮንን እንደ ቆሰለ ሳይሞት የሞተ በመምሰል ከሬሳ ጋር ድምፁን አጥፍቶ ውሎ ሲጨልምና ፀጥ ሲል ከጥቂት ጓደኞቹ ጋር በሌሊት የችግር ጉዞ ተጉዞ ምጥዋ ከገባ በኋላ፣ እንደ ቀሩት ቁስለኞች በራስ ሙዱር ሆስፒታል ታክሞ ከዳነ በኋላ ወደ አገሩ በሕይወት ለመመለስ ችሏል።
በኢትዮጵያ ፣ የጦርነት ዝክረ ነገር በመዝገብ ይዞ ለትውልድ ማቆየት እምብዛም ስላልተለመደ፣ በዶጋሊ ጦርነት ከኢትዮጵያ ወገን የሞቱትንም፣ የቆሰሉትንም የሹማምንቱንም ፣ የወታደሩንም ቁጥር በትክክል አይታወቅም። ደልቦካ በመጽሐፉ ከራስ አሉላ ወገን የሞተውም የቆሰለውም እስከ አንድ ሺሕ መድረሱን ያመለክታል።
ምንም እንኳን በዶጋሊ ጦርነት በጣሊያን በኢትዮጵያ እንዲሁም እንግሊዝ መካከል ብዙ የፖለቲካና የጦርነት ውዝግብ በመፈጠሩ በአጼ ዮሐንስ ዘንድ ቅሬታ ተፈጥሮ ራስ አሉላ ከጦር ጠቅላይ መሪነት ቢገለሉም በዶጋሊው ጦርነት የራስ አሉላ የጉብዝና ወሬ በመላው ኢትዮጵያ ተሠራጭቷል። በጣሊያኖቹም በኩልም ከማናቸውም የአጼ ዮሐንስ መኰንን የበለጡ የታወቁና በየመጽሐፉ የሚታወሱ ናቸው። ከዶጋሊ ጦርነት ወዲህ በየጊዜው እንደዚህ እየተባለ ተገጥሞላቸዋል።
አባ ነጋ አሉላ የደጋ ላይ ኮሶ
በጥላው ያደክማል እንኳንስ ተቀምሶ
ጣልያን ሰሐጢ ላይ እግሩን ቢዘረጋ
በብረት ምጣዱ በሰሐጢ አደጋ
አንገርግቦ ቆላው አሉላ አባ ነጋ
ተው ተመከር ጣልያን ይሻላል ምክር
ሰሐጢ ላይ ሆነህ መሬት ብትቆፍር
ኋላ ይሆንልሃል ላንተው መቃብር
ይቺ አገር ኢትዮጵያ የበዝብዝ አገር
ምንም አትቃጣ እንዳራስ ነብር።
ደርግ የዶጋሊ ድል በዓልን ሕዝባዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር በማድረግ በዶጋሊ የመታሰቢያ ኀውልት እንዲቆም አድርጎ ነበር። የሕዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ሕግሓኤ) ደርግን አሸንፎ ኤርትራን ሲቆጣጠር ኀውልቱን አፍርሶታል። ጣሊያኖችም በጦርነቱ ለተሰው ወታደሮቻቸው ሮም ላይ የመታሰቢያ ኀውልት አቁመውላቸዋል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 20/2012
የትናየት ፈሩ