«በአንድ ገጽ ወረቀት ጀምሬ አቤቱታ፣
ስንት ዓመት በሸንጎ ልኑር ስንገላታ።
አንተ የበላይ ሹም የእኔ መፍትሔ ሰጭ፣
ዶሴዬን መርምረው አይሁን ተቀማጭ።
እንዲታይ ነው እንጂ ወደ በላይ ቀርቦ፣
መች እንዲቀመጥ ነው መዝገብ ቤት አጣቦ።»
እነዚህ የዜማ ስንኞች ከተዜሙ ቢያንስ ወደ ግማሽ ክፍለ ዘመን ይጠጋል። ዜማው የተደረሰው የንጉሡን ዘመን ቢሮክራሲ ለመሄስ ነበር። ከዚያ ወዲህ የደርግና የኢህአዴግ ሥርዓቶች የወጡበት መሰላል ተሰባብሮ ፍጻሜያቸው ሳያምር ተንኮታኩተው አሸልበዋል። ሥርዓቶቹን እንደ ወጋግራና ማገር የደገፉት የየሥርዓቱ ሹመኞች ዕጣ ፈንታም ምን እንደነበር በታሪክ ድርሳናትና በዓይናችን ምስክርነት ፍጻሜያቸውን አስተውለናል።
«የባሰ አለና ሀገርህን አትልቀቅ» እንዲል አባባሉ እነዚህ ስንኞች ዛሬም ቢዜሙ ከችግሩ ግዝፈት የተነሳ መልዕክታቸው ይደበዝዛል የሚባል አይደለም። ለምን ቢሉ ግጥሙ የሚወቅሰው የመዝገብ ቤቱን ግልገል ቢሮክራት እንጂ የዝሆን ያህል የገዘፈውን ሹመኛ አይደለም። ከሹሙ ዘንድ ያቺ ብሶት ያረገዘችው ደብዳቤ ብትቀርብ መፍትሔ ብጤ እንደማይታጣ ዜመኛው በስሱ ጠቁሞናል።
የንጉሣዊ መንበረ ሥልጣኑን ከሥሩ ገርስሶ ዙፋኑ ላይ ፊጥ ያለው የደርግ መንግሥት «ከበሮ በሰው እጅ ያምር፤ ሲይዙት ያደናግር» እንዲሉ ከወደቀው ንጉሣዊ ሥርዓት በበለጠ በእኩይ ተግባሮቹ መንስኤነት እርሱም በተራው የግፉ ዋንጫ ሞልቶ የአገዛዙ ህልውና ምዕራፍ ተዘጋ።
ኢህአዴግም ንጉሡንና ደርግን እያብጠለጠለና እየተፋለመ ከኖረበት የጫካ ትግል በአሸናፊነት ወጥቶ የአራት ኪሎን መንበር ከተቆናጠጠ በኋላ በምድሪቱና በሕዝቦቿ ላይ ሲፈጽም የኖረው የግፍ ዶፍ በፈራጁ አምላክ ርትእ ፍጻሜው ምን እንደሆነ የትናንት ጀንበር ያሳየችንን አይተን አፋችንን በመያዝ ተደንቀናል። የውልብታ ያህል የተገለጠው ክፉ ስዕሉ ወደፊት በአግባቡ እየተገላበጠ ሲሄድ ብዙ ጉድ ለማየት ዕድሜውን ያድለን።
ከመጋቢት 2010 ዓ.ም ጀምሮ ኢህአዴግን የተካው የሪፎርሙ ሥርዓት እጅግም ቀዳሚዎቹን ሥርዓቶች በነጋ በጠባ ሲኮንንና ሲያብጠለጥል ባለማየታችን አሹ በማለት አነጋገሱንም፣ ነጋሲዎቹንም፣ አተገባበራቸውንም በተመለከተ «እኛም ወደናል ይሁን!» ብለን በዕልልታ ተቀብለን ነበር። የሪፎርሙ ተቀዳሚ ሪፎርሚስት ነግቶ በጠባ ቁጥር የአዋጅ ያህል ስለ ሰላም፣ ስለ ይቅርታ፣ ስለ ፍቅር (እሳቸው ሦስቱን ተወዳጅ ማሕበራዊ አማላይ እሴቶች ሰይፍ በማለት በአጽርኦተ ቃል መጥራታቸውን ልብ ይሏል) ባለመሰልቸት በውስጣችን ለማስረጽ እየሞከሩ እንዳሉ እየሰማንም እያየንም ነው። ዛሬም ቃላቱ ተሰለቹ ብለው ከአንደበታቸው አላራቋቸውም።
በአንጻሩ አንዳንድ በጎ ነገሮችን ጠል የሆኑ ግለሰቦችና አክራሪና ተቃዋሚ ቡድኖች ከዚህ በታች የተጠቀሰውንና በደርግ ዘመን ይፈከርበት የነበረውን የግድያ ቀረርቶ ሪፎርሚስቱ መሪ ደግመው እንዲያቅራሩና እንዲተገብሩ ፋታ ነስተው እየጎተጎቷቸው እንደሆነ እየሰማንም እያስተዋልንም ነው።
«የፍየል ወጠጤ ትከሻው ያበለጠ፤ ልቡ ያበጠበት
እንዋጋ ብሎ ከነበር ላከበት፣
የማትረባ ፍየል ዘጠኝ ትወልዳለች፣
ልጆቿም ያልቃሉ እርሷም ትሞታለች»
ሪፎርሚስቱ መሪ ከጨለማ ዋሻ ወደ ብርሃናማ አዲስ የዴሞክራሲ አውላላ ሜዳ የሕዝቡን ልብ ማርከው ሊወስዱ ቢሞክሩም የፈተናቸው ጋሬጣ በየሁኔታው ሊያደናቅፋቸው እየሞከረ ሲያስቸግራቸው እያስተዋልን ነው። እንዲያውም ጨለምተኞቹ የጎን ውጋቶች በፈነጠቀው የተስፋ ብርሃን ገበናቸው እንደሚገለጥ ስለሚያውቁ የለውጡ ጉዞ እንዲሰናከል የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ ቆሽታችን ቢያርም በትዝብት እያስተዋልን ነው።
ያም ሆነ ይህ በለውጡ ጎዳና ላይ የመሠናክል ጥርብ ድንጋይ ለማኖር ለሚሞክሩ የጥቅምና የሥልጣን ህልመኞች፤
ያቅታል እንጂ ቁም ነገር መሥራት፣
በጣም ቀላል ነው ሌላውን ማማት፤
ለየብቻ ናቸው መሥራትና ማውራት።
የሚለውን የከረመ የዜማ ስንኞች ማስታወሱ አይከፋም።
መቼም በሀገሪቱ የፈነጠቀው የለውጥ ጨረር እንዲደበዝዝ የሚፈልጉ ጥቂት ግለሰቦችና የተደራጁ ቡድኖች መኖራቸው የአደባባይ ምሥጢር ቢሆንም፤ አብዛኛው ሕዝብ ወደ አለፉት ሥርዓቶች ላለመመለስ በራሱ እጅ የራሱን እጅ እየጠበጠበ በነፍስ ወከፍ የመሃላ ኪዳን መግባቱን ያስተዋሉ አይመስሉም።
እንደዚህም ሆኖ ግን የለውጡን እርምጃ የምንደግፈው አሰርና ገሰሱ እንቅፋት እንዳይሆን እየመከርን እንጂ እንዲያው በጭፍን «ንሴብሆ» እያልን ሥርዓቱን በወረብ ሽብሸባ ለማዳመቅ በመፈለግ ብቻ ሊሆን እንደማይገባ የጸሐፊው የጸና አቋም ነው። ስለዚህም አንዳንድ ስጋቶቻችንን ለሚመለከተው ሁሉ ያለስስትና ያለ ፍርሃት በግልጽነት ማጋራቱ ከዜጎች ሁሉ የሚጠበቅ «የጽድቅ ሥራ» እንደሆነ ማመኑ ተገቢ ነው።
ይህ ጸሐፊ ነፍሱን ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ መንግሥታዊ ሥርዓቶች ቢንኮታኮቱም እንኳ በጭራሽ ለውጥና መሻሻል የማይታይበትን የስብሰባ ልማድ ሲያስብ ከመገረምም አልፎ ቆሽቱ እያረረ በብዕሩ ያነባባቸው ጊዜያት በርካታ ናቸው። ያውም ከዘመነ ደርግ ጊዜ ጀምሮ። «ልማድ ውሎ ሲያድር ባህል ይሆናል» እንዲሉ የስብሰባ ልማዳችን ዛሬም መሠረቱ የጠነከረና የማይነቃነቅ የባህላችን አካል ሆኖ ከደማችን ጋር በመዋሃዱ አይነኬ ወደ መሆን ደረጃ ተሸጋግሯል። ጊዜን በአግባቡ ተጥቅሞ ውጤት ማስመዝገብ እየተቻለ ለምን በትንሹም በትልቁም ጉዳይ ከስብሰባ ጋር መቁረብ እንዳስፈለገ ግራ የሚያጋባ ነው። እንደ ወንዞቻችን በከንቱ የፈሰሰው ጊዜ የሚታፈስበት ሰው ሠራሽ ቴክኖሎጂ ቢኖር ኖሮ ዝቀን በማንገፋው የባከኑ ጊዜያት ክምችት የዓለም መሳቂያና መተረቻ በሆንን ነበር።
የሀገራችን የቢሮክራሲ እስትንፋስ በስብሰባ ላይ የተመሠረተ እስኪመስል ድረስ በመንግሥታዊ መዋቅሮች ሥር ባሉ ተቋማት ስብሰባ ሳይካሄድ ከዋለና ካደረ ኃላፊዎቹና ሹማምንቱ ጤና አግኝተው የሚሰነብቱ አይመስለኝም። ይህ የጸሐፊው የጸና አቋም ነው። ምናልባትም የስብሰባ ባህል ከተጓደለ እንደ ቡና ሱስ ውል የሚላቸውና የሚያፋሽኩ እንደማይጠፉም እንጠረጥራለን።
ሪፎርሚስቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሥልጣን በያዙ ሰሞን የቢሮክራሲው የስብሰባ ጊዜያት ወይ ከሥራ ሰዓት በኋላ አለያም ከሥራ ቀናት ውጭ እንደሚፈጸም የመሃላ ያህል አስረግጠው ነግረውን ነበር። የእርሳቸው ካቢኔም የሚሰበሰበው ከሥራ ቀናት ውጪ እንደሚሆን አስታውቀውናል። መቼም እርሳቸው ለገቡልን ተስፋና ቃል ታማኝነታቸውን ለማሳየታቸው ባንጠራጠርም በእርሳቸው አጠገብና ዝቅ እያሉ በተደራጁ መዋቅሮች ውሣኔው ተግባራዊ ሊሆን ቀርቶ እንዲያውም ችግሩ እንደተባባሰ እኛን ቢጠይቁን ከነማስረጃው ለማቅረብ ዝግጁ ነን። በስብሰባ ፍቅርና ሱስ የወደቁ ብዙ ኃላፊዎች ስላሉ እከሌ ለማለት እኛ ተራ ተገልጋዮች ችግር የለብንም።
ደረጃቸው ዝቅም ይበል ከፍ የሀገራችንን ቢሮክራሲ የሚዘውሩ ኃላፊዎችንና ሹማምንትን በቢሯቸው ፈልጎ ከማግኘት ይልቅ ወደ ፀባዖት አንጋጦ ዙፋኑን ወደ ዘረጋው ፈጣሪ መጮኹ የተሻለ አማራጭ ብቻም ሳይሆን ፈጣን መልስም ሊያስገኝ ይችላል ባይ ነን። ምክንያቱም እነርሱ ስብሰባ ስለሚናፍቃቸው የሥራ ወንበራቸውን አያስታውሱትም።
የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በሙያችን ጣልቃ ገብታችሁ በጨዋ ገለጻ ትንታኔያችንን አታጉድፉ ብለው እንዳይገስጹን ብንፈራም የሀገራችንን ኢኮኖሚ አዚም ከነዙበት ምክንያቶች አንዱ በኃላፊዎች የሚመለከው የስብሰባ ዛር እንደሆነ ከገባን ውለን ማደራችንን ሳንሳቀቅ እንመሰክራለን።
አብዛኞቹ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የባለጉዳይን እንባ ለማበስ ንፉግና ስስታም መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ለበታቾቻቸው ሙሉ ውክልና ሰጥተው ባለጉዳይ እንዳይጉላላ አደራ እንደሚሰጡ እንኳ እንጠራጠራለን። አብዛኞቹን የሀገራችን ሹመኞች ሕዝቡ በሁለት ባህርይ እንደፈረጃቸው ቢያውቁት አይከፋም። አንዱ ስብሰባ ወዳድና ውክልና ጠል መሆናቸው ከላይ የተዘረዘረ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በየስብሰባው ላይ የፊት ወንበር ይዞ በሚዲያ የመታየት ጥማታቸው ነው። በቅርቡ በእኔ ላይ የተፈጸመን አንድ ጉዳይ ደጋግሜ ባሰብኩ ቁጥር ውስጤ በሀፍረትም በፀፀትም እየተቀጣ ተቸግሬያለሁ።
አንድ ከፍተኛ ሥልጣን የተሰጠው የመንግሥት ተቋም በዓለምና በሀገር አቀፍ ደረጃ በጋራ የሚከበር ዓመታዊ ቀን አስቦ ለመዋልና ለውጤታማ ተቋማት ሽልማት ለመሸለም ሞቅና ደመቅ አድርጎ በአንድ ታላቅ ሆቴል ውስጥ አንድ መርሃ ግብር አዘጋጅቶ ነበር። በፕሮግራም ዝግጅቱ ውስጥ ይህ ጸሐፊ በተዘጋጀው መስፈርት መሠረት ተሸላሚዎችን አወዳድሮ ለሽልማቱ ለማብቃት ጥቂት ሰዎች በተካተቱበት የበጎ ፈቃደኞች ኮሚቴ ውስጥ ተመድቦ ስለነበር ተልዕኮው የሚጠናቀቀው በዚያ ስብሰባ ላይ ነበር።
እንደ አጋጣሚ ስብሰባውን ለመታደም የተቀመጥኩት በኋለኛው መደዳና በመጨረሻዎቹ ወንበሮች አካባቢ ነበር። በፕሮግራሙ ላይ መጠነኛ ድርሻ እንደነበረኝ የሚያውቁት የፕሮግራሙ አዘጋጆች ከኋላ ወንበር ተነስቼ ወደፊት እንድሄድ በተደጋጋሚ ጊዜያት እየተመላለሱ ይጎተጉቱኝ ጀመር። ግዴለም ቦታው ተመችቶኛል ብዬ ብማጠንም ሊሰሙኝ ስላልቻሉ ለአምስተኛ ጊዜ ግድ ሲሉኝ ፈቃዳቸውን ልሙላ በማለት እየመሩ ወስደው በሦስተኛ መደዳ ላይ በተያዘልኝ ወንበር ላይ አስቀመጡኝ።
በአዲሱ የእንግድነት ወንበሬ ላይ ገና አረፍ ከማለቴ አንድ ሰው ሲንደረደሩ መጥተው «ወንድሜ ይሄ ወንበር የእኔ ነው ተነሳልኝ?!» በማለት ከግር እስከ ራሴ በግልምጫ ላጡኝ። ቀና ብዬ ሳያቸው በቴሌቪዥን መስኮት ለዓመታት ያህል ስመለከታቸው የኖሩ «የተከበሩ የፓርላማ አባል» ነበሩ። እንደ እውነቱ ከሆነ እኒህን ሰው በተከበረው የፓርላማ ወንበር ላይ ተቀምጠው ከማስተዋል ውጪ አንድም ቀን አስተያየት ሲሰጡ አስተውዬ አላውቅም። ምናልባትም የቴሌቪዥኖቻችን የካሜራ ባለሙያዎች የመታየቱን ዕድል ነፍገዋቸው ሊሆን ይችላል።
«ተነስ ብለው ላፈጠጡብኝ የተከበሩ የሕዝብ ተመራጭ» እምቢታ እንደማያዋጣ ስለተረዳሁ ማስታወሻ መጻፊያ ደብተሬን እንኳ በአግባቡ ሳልሰበስብ በመቶ የሚቆጠሩ ዓይኖች እያፈጠጡብኝ ፕሮግራሙ እንደተጀመረ በእፍረት አንገቴን ደፍቼ ስብሰባውን አቋርጬ ለመውጣት ተገድጃለሁ። የፊት ወንበር ወዳጁና የሸላሚው ተቋም ኃላፊዎች ይህንን መራራ ትዝብት ማንበባቸው ስለማይቀር ምላሻቸውን ባደምጥ አይከፋም። ለፊት ወንበር ግብግብ የማይፈጥሩ «መሪዎችን» ፈጣሪ እንዲያድለን አጥብቄ መጸለይ የጀመርኩት ከዚያ ክስተት ማግስት ጀምሮ ነው።
የስብሰባና የፊት ወንበር ወዳድነት ባህላችን አብቦ የጎመራው በመንግሥት ቢሮክራሲ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ ፓርቲ አባላት ዘንድም እንደሆነ እንደ እኔ አንባቢው ሳይታዘብ የቀረ አይመስለኝም። ወደፊት የምርጫ ቀናት እየተቃረቡ ሲሄዱ በስፋትና በተከታታይ የምናያቸው የስብሰባ አበዛዞች ለሀገሬና ለኢኮኖሚያችን ይብላልኝ እያልኩ መስጋቴም አልቀረም።
መቼም እንደ ደርግና እንደ ኢህአዴግ በስብሰባ ተወልደው በስብሰባ የሞቱ ሥርዓቶችን ታሪካችን አስተናግዶ ስለማወቁ እርግጠኛ አይደለሁም። በዚህኛው የዘመነ ብልፅግና አገዛዝ የተንዛዙት ስብሰባዎቻችን መልክ ይይዛሉ ብለን ስንጎመጅ ጭራሹኑ ስብሰባ የዕለት ቀለብ ሲሆን ስናስተውል ድንጋጤ እየወረረን ነው። ከኢህአዴግ ማህጸን ውስጥ የተወለደው የብልፅግና ፓርቲ ለአስራ ሰባት ያህል ቀናት ከፍተኛ አመራሮቹና ሹማምንቱ ለሥልጠና በአንድ አዳራሽ ተከማቹ ማለትን በቀደም ስንሰማ ተስፋችን መውደቅ ጀምሯል።
ከሚኒስትሮች ጀምሮ በሁለትና በሦስት እርከኖች ዝቅ የሚሉ ሹመኞችን የሚመለከተው የከፍተኛ አመራሮቹ ስብሰባ ለምን አስራ ሰባት ቀናት እንደተቆረጠለት ግር ብሎናል። ስብሰባው ይካሄድ አይካሄድ ብሎ መወሰን የእኛ የተራ ዜጎች ውሳኔ እንዳልሆነ ይገባናል። እኛ ስብሰባው ተንዛዛ እያልን የምናላዝነው በሹማምነቱ ባዶ ወንበሮች የሚሸማቀቀው አንካሳው የሀገራችን ኢኮኖሚ አንደኛውን በእንብርክክ እንዳይሄድ ስለምንሰጋ ነው። መፍትሔ የሚፈልጉትና በየወንበሮቻቸው ላይ ያሉት የሕዝብ ጉዳዮችም ከስብሰባው ጋር አብረው እንዳይታገቱ ስለምንሰጋ ጭምር። ውክልና ለመስጠት ያለውን ንፍገት ከላይ ስለጠቀስኩ አልደግሞውም።
ተወዳጁ የኢህአዴግ «አሥራ ሰባት ቁጥር» በብልፅግና ፓርቲ ስብሰባ መደገሙ በራሱ ትንሽ ግርታ ፈጥሮብናል። ኢህአዴግ የደርግን የአሥራ ሰባት ዓመታት ዘመነ ሥልጣን እየዘፈነበት ኖሮ በአሥራ ሰባት ቀናት የግምገማ ስብሰባ ግባ መሬቱ እንደተፈጸመ አንዘነጋም። «የዘሬን ብተው ያንዘርዝረኝ» እንዲሉ ብልፅግናም ለአሥራ ሰባት ቀናት የሚቆይ የስብሰባ መርሃ ግብር መንደፉ የፖለቲካ ባህሉ ግድ ስለሚል ይሆንን ብለን ለእውቀት ያህል እንጠይቃለን። ስብሰባው የፈለገውን ቀናት ያህል ቢፈጅ ላያገባን ይችላል፤ ነገር ግን የምንጮኸው የኢኮኖሚውስ ጉዳይ? የዳቧችንስ ጉዳይ? በእጃቸው ያለው ጉዳያችንስ እንዴት ይሆናል እያልን ነው። «ስብሐት ለሚሰሙኝ ሁሉ!» በማለት ጽሑፌን ላሳርግ ስሞክር ሳሎኔ ውስጥ ከተገሸረው ቴሌቪዥኔ የሚከተለው ዜማ መንፈሴን ሰርቆ ለአፍታ ገታኝ፤
ምን ጥልቅ አርጎኝ፤ በሰዎች ነገር፣
ምንስ አቅብጦኝ እኔ እምናገር፤ እኔ እምናገር።
ያልተሰጠኝን የሰውን ሥራ፤ የሰዎችን ሥራ፣
አለሁ አውቃለሁ ብዬ ሳወራ ሁልጊዜ ሳወራ፣
የሚያስደንቅ ነው ለሰሚው ግራ ለሰሚውም ግራ።
ሰላም ይሁን!!
አዲስ ዘመን ጥር 20/ 2012