በኢትዮጵያ ድህነትና ስራ አጥነትን በመቀነስ የነዋሪዎችን ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ካሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች መካከል በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ እንዱ ነው። ይህም የዜጎችን ፍትሃዊ ኢኮኖሚው ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያግዛል።
በተለይ በስራ እድል ፈጠራው የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮቻቸውን ለመቅረፍ እንዲቻል መንግስት ከፍተኛ ወጪ በመመደብ እየሰራ ነው። ለወጣቶች የተዘዋዋሪ ብድር ማቅረብን ጨምሮ ተደራጅተው የስራ ባለቤት የሚሆኑበትን ስራም እየተሰራ ነው። በዚህም ሀብትና ንብረት ያፈሩ በርካታ ወጣቶች መኖራቸውም ግልጽ ነው፡፡
መንግስት የሚያቀርባቸው እድገት ተኮር የስራ ዘርፎች ላይ በመሰማራት ጉልበታቸውን ተጠቅመው እንዲሁም በድጋፉ የስራ እድል ተጠቃሚ እየሆኑ ያሉ ወጣቶች እንዳሉ ሆኖ አሁንም በከተማችን ወጣቶች በኩል የሚስተዋሉ ስራ የማማረጥ አባዜ አለ። ይህ መታረም አለበት። በማንኛውም የስራ ዘርፍ ለመሰማራት፤ ሰርቶ ለማደግና ለመለወጥ ብሎም ከድህነት ለመላቀቅ እንዲቻል ወጣቶች ንቁ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለመሆን መዘጋጀት ይኖርባቸዋል።
በ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት በሃገር አቀፍ ደረጃ በመደበኛና በመንግስት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ብቻ ለ734ሺ 226 ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን የፌዴራል የከተሞች የስራ እድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም ለ 11ሺ 232 ኢንተርፕራይዞች ለመስሪያ የሚያገለግሉ 1 ሺ 642 ሼዶችን ማስተላለፍ መቻሉንም የኤጀንሲው መረጃ ያመላክታል፡፡ ይህም መንግስት ዜጎችን የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ የሰራው ስራ ውጤታማነት ማሳያ ነው።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ከለውጡ ጋር በተያያዘ ተግባራዊ እየተደረጉ ባሉ ዘርፈ ብዙ የፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ነዋሪውን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ውጤቶች ለማስመዝገብና የህዝቡን ተሳትፎ ለማሳደግ ሰፊ ጥረቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ። በዚህም የህዝቡን እርካታ በተቀናጀና በተሟላ መልኩ ለማሳካት ለየት ባለ መልኩ ትኩረት በመስጠት ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የተለያዩ ስራዎች እየተከናኑ መሆኑ ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው።
ከእነዚህ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ባለሀብቱን አሳትፎ ለወጣቱ የስራ እድል እየተፈጠረባቸው ካሉ ፕሮጀክቶች መካከል ደግሞ የሸገር ዳቦና የዳቦ ዱቄት ፋብሪካ ይገኝበታል፡፡ የግንባታ ሂደቱ እየተጠናቀቀ ያለውና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን የሰነቀው ይህ ፋብሪካ ወደ ስራ ሲገባም ለ20ሺ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥርም ታምኖበታል፡፡
ዝቅተኛ ኑሮ ላይ ያለውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ከማድረግ ጎን ለጎን ወጣቶችን የስራ እድል ባለቤት የሚያደርጉ መሰል ፕሮጀክቶች ሲጠናከሩ ሁሉም ሀላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣም ይገባል፡፡
ባለፉት ጊዜያትም የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች በአስሩም ክፍለ ከተሞች ከወጣቶች ጋር ባደረጉት ውይይት ‹‹የሥራ እድል ይፈጠርልን›› የሚለው የወጣቶች ዋነኛ ጥያቄ ነበር፡፡ ይህንን ተከትሎም በብዙ ሺ ለሚቆጠሩ ወጣቶች የስር እድል እንደሚፈጥር የከተማ አስተዳደሩ ቃል መግባቱ ይታወሳል፡፡ ይህ የሸገር ዳቦና ዱቄት ፋብሪካ ፕሮጀክትም አንዱ በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ በዚሁ ቀጥል የሚል ማበረታቻም ይገባዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በጀመረው ለውጥና ሰፊ የሥራ እድል ፈጠራ እንቅስቃሴ የከተማው ነዋሪዎች በንቃት መሳተፍ አለባቸው። ወጣቶቼም ስራ ሳይመርጡ ራሳቸውን ለመቀየር መጣር ይገባቸዋል። መንግስት ደግሞ እንደ ሸገር የዳቦና የዳቦ ዱቄት ፋብሪካ አይነቶቹ ኢንቨስትመንቶች ማበረታታት አለበት። ለስራ እድል ፈጠራም አጋዥ ናቸውና።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ሆነ የፌዴራል መንግስቱ ዜጎች የስራ እድል ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያደርጉት ጥረት አጠናክረው መቀጠል አለባቸው። ወጣቶችም በተገኙት አማራጮች ሁሉ ወደ ስራ በመግባትና ራሳቸውን ከሁኔታዎች ጋር በማመቻቸት የስራ ፈጣሪም ሆነው የሀብት ባለቤት ለመሆን መዘጋጀት አለባቸው፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 20/2012