መሰረተ ልማት የሚለውን ጥምር ቃል ፍቺ ቃላቱን ቦታ በማቀያየር “የልማት መሰረት” ብሎ መበየን ይችላል። የመሰረተ ልማት ዋነኛ ግብ ለየትኛውም አይነት ልማት መደላድል መፍጠር ነው። መሰረት ልማት በርካታ ፉርጎዎች ባሉት ባቡር ይመሰላል። አንድ ባቡር ከኋላው በርካታ ፉርጎዎችን እንደሚጎትት ሁሉ መሰረተ ልማትም ዘረፍ ብዙ ልማቶችን ያስከትላል።
ይህን የዘርፉን ቁልፍ ሚና የተረዳው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት “መሰረተ ልማት” ስለኢትዮጵያ በሚል መሪ ሀሳብ ያሰናዳው 20ኛው ስለኢትዮጵያ የፓናል ውይይት ከሳምንት በፊት በድሬዳዋ ከተማ ተካሂዷል። በመድረኩ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው እና የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) እንዲሁም ጥሪ የተደረጋላቸው ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።
በመድረኩ ሦስት መነሻ ሀሳቦች የቀረቡ ሲሆን ተሳታፊዎች ያነሷቸው ጥያቄዎች ተጨምረው የኢትዮጵያ የመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተካሂዷል። ለመሆኑ ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት ዋና ዋና በሚባሉት በመንገድ፣ በኋይል አቅርቦት እና በቴሌኮም መሰረተ ልማቶች ያስመዘገበችው እድገትና ያጋጠሟት ተግዳሮቶች በተዳሰሱበት በዚህ መድረክ እንዴት ያሉ ሀሳቦች ተራመዱ ?
የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ተደራሽነት እና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት በሚል ርዕሰ ጉዳይ የውይይት መነሻ ሀሳብ ያቀረቡት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው እንደሚናገሩት፤ ከለውጡ በፊት በኢትዮጵያ የነበረው የመንገድ መሰረተ ልማት 26 ሺህ ኪሎ ሜትር ገደማ ነበር። ባለፉት ሰባት ዓመታት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በተሰራው ሰፊ ሥራ የነበረውን የመንገድ መሰረተ ልማት በስድስት እጥፍ በማሳደግ ወደ 175 ሺህ ኪሎ ሜትር ማሳደግ ተችሏል።
መሰረተ ልማት ኢኮኖሚን በማሳለጥ ረገድ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመው፣ የትራንስፖርት መሠረተ ልማት ሌሎች ወሳኝ መሠረተ ልማቶች ትስስር የሚፈጥር ጭምር በመሆኑ አንድምታው ሰፊ መሆኑን ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ መኪኖችን በመጠቀም፣ የብስክሌት መሰረተ ልማትን በመዘርጋት፣ የባቡር መሰረተ ልማትን በማዘመን እና ትናንሽ መኪኖችን ወደ ብዙኃን ትራንስፖርት በማሳደግ የካርቦን ልቀትን በመከላከል ረገድ የአጀንዳ 2063 እያሳካች እንደምትገኝ ገልጸዋል። ሆኖም አሁንም የሚቀሩ ነገሮች አሉ ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ በተለይ ክልልን ከክልል፤ ከተማን ከከተማ እና የገጠር መንገዶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል ብለዋል።
ኢንጂነር ዮናስ ከኮንስትራክሽን ግብዓቶች ጋር በተያያዘም በተለይ ሲሚንቶ ከፍተኛ ችግር እንደነበር ጠቅሰው፣ በአሁኑ ጊዜ የሲሚንቶ አቅርቦት መሻሻሉን በመጥቀስ፤ ሌሎች የስሚንቶ ፋብሪካዎችም ለመገንባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ከውሃ፣ ከነፋስ እና ከጂኦተርማል የኢነርጂ ምንጮች 45 ጊጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ትችላለች። ይህም መላ አፍሪካን የኤሌክትሪክ ኃይል ሊያዳርስ የሚችል ነው ያሉት። ሆኖም አሁን እየመነጨ ያለው ከ6 ነጥብ 4 ጊጋ ዋት ኃይል አይበልጥም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ለዘርፉ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ ከነፋስ ኃይል ብቻ እስከ 150 ጊጋ ዋት ኃይል አቅም እንዳላት በመግለጽ፤ ሆኖም እየተጠቀምን ያለነው በጣም ትንሹን ነው ብለዋል። ጂኦተርማል ኃይልን በተመለከተም ወደ 10 ጊጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ቢኖራትም የተጀማመሩት ጥቂት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያን ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማዳረስ አንዱ ማነቆ የሕዝቡ የተበታተነ አሠፋፈር መሆኑን ያነሱት ሚኒስቴር ዴኤታው፤ ይህም ከኃይል ፍላጎት ባሻገር ትልቅ ወጪ የሚጠይቅ ነው። ኤሌክትሪክ ማዳረስ ያልቻልነው የኃይል ማስተላለፊያ መሰረተ ልማቱን በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ማድረስ ባለመቻላችን እንጂ በኤሌክትሪክ ኃይል እጦት አይደለም። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የኃይል እጥረት የለም። እንዲያውም እያመረትን ካለነው ኃይል ውስጥ ለገበያ ብናቀርበውም ገዢ ባለመኖሩ 15 ፐርሰንቱ ጥቅም ላይ አልዋለም። የኃይል መሠረተ ልማት ካልተስፋፋ በቀር የሕዳሴ ግድብ ከተመረቀ በኋላም እንኳን ቢሆን ኤሌክትሪክ ያላገኘው ሕዝባችን በሙሉ የኃይል ተጠቃሚ ይሆናል ማለት አይደለም። ነገር ግን ሀገራችን በፍጥነት እያደገች በመሆኑ የምትፈልገው ኃይልም እያደገ ይሄዳል። በዚያ ልክ ተንቀሳቅሰን በቀጣይ ዓመታት ተጨማሪ ማመንጫዎች ካልገነባን የኃይል እጥረት ሊገጥመን እንደሚችል መታሰብ አለበት ነው ያሉት።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ኢትዮጵያ ውስጥ በመሰረተ ልማት ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ከምን ጊዜውም በላይ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። አንድ ኢትዮጵያዊ ከአንድ ጫፍ ተነስቶ ወደ ሌላኛው የኢትዮጵያ ጫፍ በትራንስፖርት ሲንቀሳቀስ ከአንድ ቀን ሊወሰድበት አይገባም። ለዚህም ጥናቶች ተደርገው ታቅዶ እየተሠራ ነው። ይህን ለማሳካት ሁነኛው መፍትሔ የፍጥነት መንገዶችን ማስፋፋት ነው። በነዚህ መንገዶች ልማት ላይ ባለሃብቶች መሳተፍ አለባቸው ብለዋል።
የመሰረተ ልማቶች መናበብ የኢኮኖሚ ሽግግሩን እንደሚያሳልጥ የጠቆሙት ሚኒስትሯ፣ በዚህ ረገድ የመንገድ መሰረተ ልማቶች የተሻለ ውጤት ተመዝግቦባቸዋል። የመንገድ ትራንስፖርት መሰረተ ልማት ማስፋፋት ላይ ከካሳ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ጫና እየፈጠሩ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሯ፤ በአንዳንድ ቦታዎች ለካሳ የሚከፈለው ገንዘብ ለመንገዱ ግንባታ ከተመደበው ልቆ የሚገኝበት አጋጣሚ እንደሚኖር ነው የገለጹት። የመንገድ መሰረተ ልማት እንዲስፋፋ ሕዝቡ በሚያነሳው ጥያቄ ልክ ለግንባታው ተባባሪ ባለመሆኑ እና ደህንነቱን በመጠበቅም በኩል ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ ጠቅሰው፣ መንግሥት ለመንገድ መሰረተ ልማት ትልቅ ትኩረት እንደሰጠው
ከዚህ ቀደም በነበሩ አሰራር ክፍተቶች ምክንያት መሰረተ ልማት ላይ የሚሰሩ ተቋማት በተናጠል በመንቀሳቀሳቸው ከፍተኛ የሀገር ሀብት ሲባክን ነበር። አለመናበብ በርካታ መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት አድርሷል። በአሁኑ ወቅት በተለይም ኮሪደር በተሠራባቸው አካባቢዎች የተናበበ አካሄድ በመከተላችን በተቋማት አለመናበብ ምክንያት መሰረተ ልማቶች ላይ የሚደርሰው ጉዳት ቀንሷል ሲሉም አክለዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የሚሰሙ የመሰረተ ልማት ስርቆቶችን እና ጉዳቶችን “አሳዛኝ” ብለው የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ሚዲዎች እና የሚመለከታቸው አካላት በዚህ ዙሪያ በትኩረት እንዲሰሩ ነው የጠየቁት።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በቴሌኮም መሰረተ ልማት ዝርጋታ የተመዘገበውን ዕድገት ሲገልጹ፤ በፋይበር እና ከተሞችን በምናገናኝበት ሜትሮ በምንለው ወደ 34 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሆን የቴሌኮም መሰረተ ልማት መዘርጋት ችለናል። የፋይበር ባክቦናችን ወደ 21 ሺህ ሜትሮ የምንለው ደግሞ 13 ሺ ኪሎ ሜትር ደርሷል። ከዚህ ባሻገር ወደ ሁለት ነጥብ አራት ቴራባይት የሚሆን በአምስት ኮሪደሮች ኢትዮጵያን ከሌሎች አለማት ጋር የምናገናኝበት ኢንተርናሽናል ጌት ዌይ የምንለው የቴሌኮም መሰረተ ልማት ዝርጋታ አለን። በኬኒያ፣ በሶማሌ፣ በጅቡቲ እንደዚሁም ደግሞ በሱዳን ኢትዮጵያን ያገናኘንበት ነው ብለዋል።
አሁን ላይ ባጠቃላይ እንደ ሀገር ወደ 92 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎች በቴሌኮም አገልግሎት ተደራሽ በመሆን መተሳሰራቸውን ጠቅሰውም፤ ወደ 52 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ናቸው። ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የቆዳ ስፋት ኢትዮቴሌኮም ወደ 86 በመቶ ተደራሽነት አለው። ከሕዝብ ቁጥር አንጻር ደግሞ ወደ 99 ነጥብ በመቶ ተደራሽነት አለው። በዚህም ከመቶ ሰው 76 ሰው የቴሌኮም አገልግሎት የሚያገኝበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ስለዚህ ባጠቃላይ የዘረጋነው መሰረተ ልማት ዜጎቻችንን ከማገናኘት አንጻር እዚህ ደረጃ ላይ ይገኛል ነው ያሉት።
አያይዘውም በአዲስ አበባ የተወሰኑ ቦታዎች የተጀመረው የ4ጂ አግልግሎት ዛሬ ከሰባት መቶ ከተሞች በላይ ተዳርሷል። የ5ጂ አገልግሎትን በአፍሪካ በጣም ጥቂት ሀገራት ናቸው እየሰጡ ያሉት። 25 የሚሆኑ ከተሞቻችን የ5ጂ አገልግሎት ተጠቃሚ ናቸው። በርካታ የቴሌኮም መሰረተ ልማቶች ግንበታን አካሂደናል። 10 ሺህ የሚጠጉ የሞባይል ጣቢያዎች አሉን፤ እነዚህን ለመገንባት ረጅም ጊዜ ወስዷል። ያለፉት አምስት ዓመታት ደግሞ በመሰረተ ልማትና አገልግሎትን በማስታጠቅ በማምጣት በመተግበር በርከት ያሉ አዳዲስ አገልግሎቶችን ተግባራዊ አድርገናል። ይህም ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚያስችል ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ እንደሚናገሩት፤ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ሌሎች ዘርፎች አስቻይ ሁኔታን የሚፈጥር ነው። ከፋይናንስ አንጻር ካየነው በጣም ባጠረ ጊዜ ከ10 ሚሊየን በላይ ተጠቃሚዎች እስካሁን ሆኖ በማያውቅ ሁኔታ ከ22 ቢሊየን በላይ ብር ባጠረ ጊዜ ማግኘት ችለዋል። ለዚህ ነው የቴሌሎኮምና የዲጂታል መሰረተ ልማት አስቻይ ሚና ይጫወታል የሚባለው። ቀደም ሲል በቀጭኑ ሽቦ ሃሎ ሃሎ የሚባል ሲሆን ዛሬ ኢኮኖሚን የሚያስችል የሚያሳልጥ የሚያሳድግ ትልቅ ሚናን ላይ ደርሷል። ዘመናዊነትንም ከግለሰብ ጀምሮ እስከ መንግሥት ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎት ለማዘመንና ማቀላጠፍ የሚያስችል ነው።
ቴክኖሎጂው የማይገባበት ቦታ ስለሌለ በዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞ ውስጥ ከሚሳኩት አንዱ ምርታማነትን ውጤታማነትን በሁሉም ተቋማት ማምጣት መሆኑን ጠቅሰው፣ እንደ ምሳሌ በግብርናው ዘርፍ ጥራትን መጨመርና ምርቶችን ማሳደግና የተመረቱ ምርቶችን ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ወደሚፈለገው ቦታ ማድረስ እንደሚቻል ገልጸዋል።
ሀሳባቸውን ሲያጠቃልሉም፤ መሰረተ ልማቶቻችን የዘመነ አስተዳደርን ይፈልጋሉ። የውሃችን ፍሰት የመብራታችን ፍሰት ስማርት ቴክኖሎጂን ይጠይቃሉ፤ ፍሰታቸውን መቆጣጠር ይኖርብናል። አጠቃላይ ከተማን ለኑሮ ምቹ ከማድረግ አንጻር ቴክኖሎጂን ተጠቅመን ማዘመንም ሆነ በርካታ እሴቶችን መጨመር እንችላለን። ስለዚህ እስካሁን በመጣንበት ርቀት የተረጋጋና ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚ ከመገንባት አንጻር የቴሌኮም መሰረተ ልማት ቁልፍ ሚና ተጫውቷል። ሰዎች ስለዲጂታል ኢትዮጵያ ሲያስቡ ቀድሞ የሚመጣላቸው ፍጥነት ቅለትና ተደራሽነት ነው። ጥቂት ቦታ ላይ ተወስኖ የነበረው አገልግሎት በመላው ሀገሪቱ ሲሆን ማየት የዲጂታል ኢትዮጵያ ትሩፋት ነው ብለዋል።
“መሰረተ ልማት” ስለኢትዮጵያ በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው 20ኛው ስለኢትዮጵያ የፓናል ውይይት የአንድን ሀገር ልማት ተሸካሚ ለሆኑት ምሰሶዎች ትልቅ ትኩረት የተሰጠበት፤ በቀጥታ የሚመለከታቸው ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዘርፍ ምሁራን እና ሙያተኞች የተሳተፉበት፤ ፍሬያማ ውይይት የተካሄደበት እንዲሁም ጠቃሚ ምክረ ሀሳቦች የቀረቡበት ሆኖ ተጠናቋል።
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2017 ዓ.ም