የምግብ ነክ ምርቶች ለፀሀይ መጋለጥ የሚኖረው የጤና ጠንቅ

ዜና ሀተታ

አሁን አሁን ከተላላፊ በሽታዎች ይልቅ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በሀገራችን በስፋት እየተስተዋሉ ብሎም ሞትን እያስከተሉ ይገኛሉ። ለእነዚህ በሽታዎች መስፋፋት ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን አለመከተል ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ የጤና ባለሙያዎች ያስረዳሉ። ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ ሲባል ጤናማ አመጋገብን ያካትታል የሚሉት ባለሙያዎቹ አሁን አሁን የታሸጉ ምግቦችን አብዝቶ መጠቀም እየተለመደ በመምጣቱ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ያለው የተጋላጭነት ደረጃ እጨመረ እንደሚገኝ ይገልፃሉ።

የአዲስ አበባ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሙሉእመቤት ታደሰ እንደሚሉት፤ ምግብ ከእርሻ እስከ ጉርሻ ደህንነቱ የተጠበቀ ሊሆን ይገባል። በተለይ የታሸጉ ምግቦች የሙቀትና የቅዝቃዜ መጠን ለምግቡ ደህንነት ወሳኝ ነው። እነዚህ ምግቦች ሲመረቱ በተለጠፈው የመጠቀሚያ ጊዜ ልክ ደህንነታቸው ተጠብቆ የሚቆየው ተመጣጣኝ ሙቀት ሲያገኙ መሆኑንም ይጠቁማሉ።

ነገር ግን ብዙ ጊዜ የምግብ አምራቾችም ሆኑ ቸርቻሪዎች ምርቶቹን ለፀሀይ ተጋላጭ ያደርጉና መልሰው ደግሞ በጣም ቀዝቃዛ ወደ ሆነ ቦታ የማፈራረቅ ሁኔታ እንዳለ ያስረዳሉ። ይህም ምግቡን ለካንሰር አምጪ ኬሚካሎች እንደሚያጋልጥ ብሎም ከፍተኛ የጤና ጠንቅ እንደሚያመጣ ይናገራሉ። በተለይ ለፀሀይ ተጋላጭ የሆኑ ምግቦች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ሳያልፍ ወደ ሻጋታነት ብሎም ወደ መርዛማነት እንደሚቀየሩ ይጠቅሳሉ። በመሆኑም ባለስልጣኑ የምግብ ነክ ምርቶችን የፀሀይ ተጋላጭነት ለመከላከል በስፋት እየሠራ እንደሚገኝ ያስረዳሉ።

የፀሀይ ተጋላጭነትን የመከላከሉ ሥራ የምግብን ደህንነት ከማስጠበቅ እንዲሁም የህብረተሰቡን ጤና ከመጠበቅ አኳያ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ እየተወጣ ያለው ማህበራዊ ኃላፊነት መሆኑንም ይጠቁማሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ የብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ ያልተሰጣቸውን ተቋማት ሳይቀር እንደሚቆጣጠሩ ገልፀው፤ ከዚህ በፊት የአዲስ አበባ ደምብ ማስከበር በመደበኛነት ሲሠራው መቆየቱን ያስታውሳሉ።

በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ አካላት ከመነገዱ በዘለለ የምግቡን ደህንነት መጠበቁ ላይ የሚታይባቸው ችግር እንዳለ ያነሱት ሥራ አስኪያጇ፤ አንዳንዶች ምርቱን ውጪ ላይ አድርገው ለፀሀይ በማጋለጥ መኖሩን ለመጠቆም እንደሚጠቀሙት ይገልፃሉ። ጎዳና ላይ ፍራፍሬ የሚሸጡና ሌሎችም ፍቃድ ለመስጠት የሚሸጡበት ቦታ ራሱ ደረጃውን ያላሟላ በመሆኑ ፍቃድ የማይሰጣቸው ተቋማት ይህ ችግር እንደሚታይባቸው ይጠቁማሉ። ነገር ግን በሚዛናዊነት ያንኑ የሥራ እድል እንዳያጡት ሲባል የከፋ የጤና ጉዳት በሚያደርሱ ጉዳዮች ላይ ብቻ ርምጃ እየተወሰደ መሆኑንም ይገልፃሉ።

በቀጣይም የጎዳና ላይ ምግብ አሻሻጥን በተመለከተ የወጡ ደንቦች ተግባራዊ ሲሆኑ እንዲሁም በባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ከፀሀይ ተጋላጭነት ነፃ የሆኑ አካባቢዎችን እየፈጠሩ የሚሄዱበት እቅድ ወደ ሥራ ሲገባ የቁጥጥር ሥርዓቱ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ያስረዳሉ።

በባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የቁጥጥር ባለሙያ የሆኑት አቶ ሞላ ታደለ በበኩላቸው፤ ምግብ ነክ ምርቶችን ለፀሀይ ተጋላጭ አድርገው የሚገኙት አብዛኞቹ የሸቀጥ ሱቆችና ሚኒ ማርኬቶች መሆናቸውን ይገልፃሉ። በዚህ ዓመትም ለ410 መሰል ተቋማት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ይገልፃሉ። በተመሳሳይ 65 ተቋማት ደግሞ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ባለመታረማቸው የማሸግ ርምጃ እንደተወሰደባቸው ያስረዳሉ። ነገር ግን አብዛኛው ተቋማት ምግብ ነክ ምርቶችን ለፀሀይ አጋልጠው ሲገኙ ግንዛቤ በመስጠት የሚታረሙበት አግባብ ላይ እንደሚሠራ ይጠቁማሉ።

ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ እኔም ለጤናዬ ባለስልጣን ነኝ በሚል መሪ ቃል የባለድርሻ አካላት ፎረም ማቋቋሙን አስታውሰው፤ ፎረሙ የቁጥጥር ሥርዓቱ ላይ አዎንታዊ ለውጥ ማምጣቱን ይገልፃሉ። ህብረተሰቡ በባለቤትነት እንዲሳተፍ አስተዋፅኦ ማድረጉንም ጠቁመዋል።

ነፃነት አለሙ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You