ረቂቅ አዋጁ የዜጎችን መብት ደህንነትና ዘላቂ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችል እንደሆነ ተጠቆመ

– የሥራ ስምሪቱ ሙሉ ለሙሉ ዲጂታል በሆነ ሥርዓት ይካሄዳል

አዲስ አበባ፡- የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅ የዜጎችን መብት፣ ደህንነትና ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ረቂቅ አዋጁ ግልጽና ከሰው ንክኪ ነፃ የሆነ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ረገድ የሚደረገው የሥራ ስምሪት አገልግሎት በዲጂታል እንደሚከናወን ገልጿል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በላከው መግለጫ፤ የውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት ረቂቅ አዋጁ የዜጎችን መብት፣ ደህንነት፣ ክብርና ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችል እንዲሆን ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ገልጿል፡፡ ሆኖም ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ ተገቢነት የሌላቸው መረጃዎች በተለያዩ የመገናኛ ብዘሃን አውታሮች እየተሰራጩ እንደሆኑ አመልክቷል፡፡

ረቂቅ አዋጁ ግልጽና ከሰው ንክኪ ነፃ የሆነ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ረገድ የሚደረገው የሥራ ስምሪት፣ የስልጠና ምደባ፣ የብቃት ምዘናና የአየር ትኬት መቁረጥን ጨምሮ ሁሉም አገልግሎት ዲጂታል በሆነ ሥርዓት እንዲሰጥ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁሞ፤ ለዚህም የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ለውጭ ሀገር ሥራ ስምሪቱ አገልግሎት የሚሰጥበት ብቸኛው ሥርዓት ነው ብሏል፡።

ረቂቅ አዋጁ በዜጎች መብት፣ ክብርና ደህንነት ላይ በመደራደር ሀብት ያጋብስ የነበረውን ሃይል ከመግታት ባለፈ፤ በየደረጃው የዜጎችን እና የሀገርን ጥቅም ሲጎዱ የነበሩ ሕገ ወጥ የጥቅም ማጋበሻ ሰንሰለቶችን በመበጣጠስ ሕጋዊ አሠራርን የሚያሰፍን እንደሆነ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አብራርቷል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በሥራ ላይ የሚገኘው የሕግ ማሕቀፍ (አዋጅ ቁጥር 923/2008 ካለው ነባራዊ ሁኔታ በተለይም የዜጎችን መብት፣ ክብርና ደህንት ከማስከበር አንጻር በርካታ ክፍተቶች የሚስተዋልበት መሆኑን ገልጿል፡፡ አብዛኛው ኤጀንሲዎች የዋስትና ገንዘብ ሕጉ በሚፈቅደው መልኩ የማያስቀምጡ በመሆናቸው፤ ለሥራ ያሠማሯቸው ዜጎች ችግር በሚገጥማቸው ጊዜ በወቅቱ ተገቢውን ምላሽ እንዳያገኙ ተግዳሮት ሆኖ መቆየቱን እንደ አብነት ተነስቷል፡፡ በዚህም ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ሀገራት በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ዜጎች ከፍተኛ እንግልት ሲደርስባቸው እንደነበር አስታውሷል፡፡

በዘርፉ የተደረገውን ሪፎርም ተከትሎ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በሰጠው ትኩረት ዜጎችን ወደ ተለያዩ ሀገራት በሕጋዊ መንገድ ለመላክ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነቶችን ከመፈራረም እና የመዳረሻ ሀገራት ከማስፋት ጀምሮ ሀገር ውስጥ ያሉ የሕግ እና የአሠራር ክፍተቶችን ለመሙላት ሲሠራ ቆይቷል፡፡

የተሻሻለው የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 1246/2013 የዜጎችን መብት፣ ደህንነት፣ ክብርና እና ዘላቂ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፤ በዘርፉ የሚስተዋሉ ሕገ ወጥነቶችን መግታት እና ሀገራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ የረቂቅ አዋጁ ዋና ዋና ዓላማዎች መሆናቸውን ጠቅሷል፡፡

በአዋጁ የፍቃድ አሰጣጥ ሥርዓት ላይ ማሻሻያ መደረጉ የተገለጸ ሲሆን፤ ነባሩ የሕግ ማሕቀፍ ግን ሁሉንም በአንድ ምድብ የሚመለከት ነበር፡፡ በተሻሻለው ረቂቅ አዋጁ ኤጀንሲዎች ያላቸውን ደረጃ በሚያሰማሩት የሰው ኃይል ብዛት፣ ክህሎት፣ የሙያ ዘርፍ፣ መነሻ ካፒታል እንዲሁም ተያያዥ መስፈርቶችን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ኤጀንሲዎች በባንክ ዝግ አካውንት እንዲያስቀምጡ የሚገደዱትን ዝቅተኛ ገንዝብ ከ100 ሺህ ወደ 50 ሺህ ዶላር ዝቅ እንዲል ያደረገ ሲሆን ፤ ሌላኛው በረቂቅ አዋጁ የተደረገ ማሻሻያ መሆኑን አብራርቷል፡፡

ይህም ኤጀንሲዎች ለዋስትና የሚያሲዙት ገንዘብ በካሽ በባንክ እንዲቀመጥም ያስገድዳል፡፡ ይህ ገንዘብ የዜጎችን ደህንነት ለማስከበር የሚውል ሲሆን ኤጀንሲዎች ለላኳቸው ዜጎች ተገቢውን ኃላፊነት እንዲወስዱ እና ዜጎችም ችግር ውስጥ በሚገቡበት ጊዜ ያለ ምንም ውጣ ውረድ ክብራቸው ተጠብቆ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ሙሉ ወጪን ለመሸፈን የሚውል መሆኑ ተቀምጧል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አዋጁን በማዘጋጀት ረገድ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በተለይም የውጭ ሥራ አገናኝ ኤጀንሲዎች አስፈላጊውን ውይይት ያደረገ ሲሆን ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ ተገቢነት የሌላቸው መረጃዎች በተለያዩ የመገናኛ ብዘሃን አውታሮች እየተሰራጨ መሆኑን በመግለጽ ፤ ሚኒስቴር መሥሪያቤቱ አዋጁን ከማሻሻሉ በፊት በትግበራ ሂደት ከተገኙ ክፍተቶች ባለፈ ኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ፊሊፒንስ ካሉ ሀገራት ተሞክሮዎችን በመውሰድ በዝርዝር ማየቱን ገልፀዋል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በውጭ ሀገራት የሚሠሩ ኢትዮጵያውያንን መብት፣ ደህንነት እና ዘላቂ ጥቅም ለማስጠበቅ ያለመ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅ በሚኒስትሮች ምክርቤት ጸድቆ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማሳለፉ ይታወሳል፡፡

ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁን መርምሮ ለሰው ሃይል፣ ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳች ቋሚ ኮሚቴ የመራው ሲሆን፤ ረቂቅ አዋጁ አስፈላጊውን የሕግ ሒደት አልፎ ሲፀድቅ በስምሪቱ የዜጎችን መብት፣ ደህንነትና ዘላቂ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል፡፡

መክሊት ወንደወሰን

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You