
በሶሪያ ዋና ከተማ ደማስቆ ውስጥ በሚገኝ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ በተፈጸመ የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት ዜናው እስተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ቢያንስ 22 ሰዎች ሲገደሉ 63 ሰዎች መቁሰላቸውን የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው አንድ ግለሰብ እሁድ ምሽት በድዋይላ ሰፈር በሚገኘው በነቢዩ ኤልያስ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ በመግባት ልብሱ ላይ የታጠቀውን ፈንጂ ከማፈንዳቱ በፊት ተኩስ ከፍቷል። ጥቃት አድራሹ ከጂሃዳዊው ኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ቡድን ጋር ግንኙነት እንዳለው ተገልጿል። ቡድኑ ግን ለተፈጸመው ጥቃት ኃላፊነቱን አልወሰደም ተብሏል።
የዐይን እማኝ የሆነው ሎውረንስ ማማሪ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደገለጸው፤ “አንድ ሰው ከውጭ የጦር መሳሪያ ይዞ ”ወደ ቤተክርስቲያኗ” በመግባት ተኩስ ጀምሯል። ቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ የነበሩ ሰዎች “ጥቃት አድራሹ]“ራሱን ጭምር ከማፈንዳቱ በፊት ለማስቆም ሞክረዋል” ብሏል። በአቅራቢያ በሚገኝ ሱቅ ውስጥ የነበረ ሌላ ሰው ደግሞ በመጀመሪያ የተኩስ ድምፅ፣ ቀጥሎም የመስታወት ስብርባሪዎች እንዲፈናጠሩ ያደረገ ፍንዳታ እንደሰማ ተናግሯል። ዚያድ፤ “በቤተክርስቲያኗ ውስጥ እሳት መኖሩን እና የእንጨት አግዳሚ ወንበሮች እስከ [ቤተክርስቲያኗ] ደጃፍ ድረስ ሲወረወሩ አየን” በማለት እማኝነቱን ሰጥቷል።
እስላማዊ መራሽ አማጺ ኃይሎች በሽር አል-አሳድን ከሥልጣን ካወረዱ በኋላ እና 13 ዓመታትን ያስቆጠረውን አውዳሚ የእርስ በርስ ጦርነት ካስቆሙ በኋላ ደማስቆ ውስጥ እንዲህ አይነት ጥቃት ሲፈጸም ይህ የመጀመሪያው ነው። መጀመሪያ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የቦምብ ፍንዳታው የተከሰተው በቤተክርስቲያኑ መግቢያ ላይ ሲሆን በዚህም ምክንያት በሕንፃው ውስጥ እና በአቅራቢያው የነበሩ ሰዎች ተገድለዋል።
ፓትርያርኩ፤ የሶሪያን ጊዜያዊ ባለስልጣናት “በቤተክርስቲያኖች ቅድስና ላይ ጥሰት በመፈጸም ለተፈጸመው እና አሁንም እየተከሰተ ለቀጠለው ነገር ሙሉ ኃላፊነት እንዲወስዱ እና የሁሉም ዜጎች ጥበቃ እንዲያረጋግጡ” ጥሪ አቅርበዋል። የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር አናስ ካታብ ድርጊቱን “የተወገዘ ወንጀል” ብለው የገለጹትን ሲሆን ጉዳዩን የሚመለከቱ የልዩ ባለሙያዎች ቡድን ምርመራ መጀመሩን ተናግረዋል።
“እነዚህ የሽብር ድርጊቶች የሶሪያን መንግሥት የሲቪል ሰላም ለማምጣት የሚያደርገውን ጥረት አያስቆሙትም” ብለዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሶሪያ ልዩ መልዕክተኛ ጌር ፔደርሰን፤ ጥቃቱን በማውገዝ ሶሪያውያን “ሽብርተኝነትን፣ አክራሪነትን፣ ትንኮሳን እና ማንኛውንም ማኅበረሰብን ዒላማ የማድረግ ተግባርን ለመቃወም አንድ እንዲሆኑ” አሳስበዋል።
የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ቶም ባራክ በበኩላቸው፤ ‘እነዚህ አስከፊ የፈሪነት ድርጊቶች ሶሪያውያን ለማሳካት እየጣሩ ባሉትን አዲስ የተቀናጀ የመቻቻል እና የአቃፊነት ሂደት ውስጥ ቦታ የላቸውም” ብለዋል። ጊዜያዊ ፕሬዚዳንቱ አልመህ አል ሳሃራ የሱኒ እስላማዊ ቡድን የሆነውን ሃያስ ታህሪር አልሻም የተባለ ቡድን የሚመራ ሲሆን ይህ ቡድን ከዚህ ቀደም ከአል ቃኤዳ ጋር ግንኙነት የነበረው እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት፣ በአሜሪካ እና በዩናይትድ ኪንግደም አሸባሪ ቡድን ተብሎ የተፈረጀ ነው።
ፕሬዚዳንቱ በሃይማኖት እና በብሔር ሕዳጣን የሆኑ ቡድኖችን ለመጠበቅ በተደጋጋሚ ቃል ገብቷል። ይሁን እንጂ ሶሪያ በቅርብ ወራት ውስጥ ሁለት የሰዎች ሕይወት የተቀጠፈባቸው ማንነት ተኮር ግጭቶችን አስተናግዳለች። አይ ኤስ ሶሪያ ውስጥ ክርስቲያኖችን እና ሌሎች ሕዳጣን የሃይማኖት ቡድኖችን በተደጋጋሚ ዒላማ አድርጓል። ቡድኑ እ.አ.አ በ2016 በደማስቆ ደቡባዊ አካባቢ በሚገኘው የሺያ ሙስሊም ሳይዳ ዘይነብ መቅደስ አቅራቢያ ተከታታይ ፍንዳታዎችን በመፈጸም ከ70 በላይ ሰዎችን መግደሉን ተገልጿል።
አይኤስ በአንድ ወቅት ከምዕራብ ሶሪያ እስከ ምስራቅ ኢራቅ ድረስ የተዘረጋን 88 ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር መሬት በመያዝ ስምንት ሚሊዮን ገደማ ሰዎችን በጭካኔ የተሞላበት አኳኋን ሲገዛ ነበር። ምንም እንኳ ቡድኑ በ2019 ሶሪያ ውስጥ ወታደራዊ ሽንፈት ቢያጋጥመውም፤ አይኤስ እና ተባባሪዎቹ የፈጠሩት ስጋት ከፍተኛ ሆኖ እንደሚቀጥል የተባበሩት መንግሥታት አሳስቧል።
የካቲት ላይ የታተመ አንድ ሪፖርት፤ ቡድኑ የሶሪያን የሽግግር ወቅት እንደ እድል ተጠቅሞ ጥቃቶችን ሊጨመር እና ሀገሪቱን አዲስ የውጭ ተዋጊዎችን ምልመላ ማዕከል ሊያደርግ እንደሚችል አስጠንቅቋል። አይ ኤስ፤ በሶሪያ እና በአጎራባቿ ኢራቅ ከ1 ሺህ 500 እስከ 3 ሺህ 000 የሚደርሱ ታጣቂዎች እንዳሉት ይገመታል። የቡድኑን ቁልፍ አመራሮችን ጨምሮ አብዛኞቹ ታጣቂዎች በሶሪያ ግዛት ውስጥ መስፈራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2017 ዓ.ም