“ለራሳችን የምንሰጠው ግምት – ከስኬት፣ አልያም ከውድቀት ይጥለናል” – ፍራኦል ቶሎሳ በአዲስ አበባ ከተማ የይግባኝ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት

ፍራኦል ቶሎሳ ትባላለች። በሀገረ- አሜሪካ ዲፕሎማት መሆን የሚፈልጉ ወጣቶችን በሚያሰለጥን ‹‹ፊዩቸር ዲፕሎማት ፎረም›› ሀገሯን ወክላ ከ89 ሀገራት ከተውጣጡ የወደፊት ዲፕሎማቶች ጋር በውድድር ተሳትፋለች። ውድድሩ በግላቸው ከፍለው መሰልጠን የሚፈልጉትን ጭምር የሚያሳትፍ ቢሆንም እርሷ ግን በነጻ የስልጠናው ተሳታፊ ከሆኑት መካከል ነች።

አጋጣሚውን ተጠቅማም ስለ ሀገሯ ፍላጎትና አቋም በዓለም አደባባይ መናገር ችላለች። በተለይም ከባሕር በር ጋር ተያይዞ ሀገሯ የምትከተለውን መንገድ በሚገባ አስረድታለች። የባሕር በር ጥያቄዋ ለሀገሪቱ ምን አይነት ትርጉም እንዳለው በማስረዳትም በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ልቦና ተጽዕኖ ለማሳረፍ ሞክራለች።

የፍራኦል የሀገር አበርክቶ እንዲህ በአደባባይ ይገለጥ እንጂ ጅማሮው ከዩኒቨርሲቲ ቆይታ ይነሳል። ይህም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ስትቀላቀል ‹‹ሀገር የምትፈልገው ሰላም ነው›› በሚል የሰላም ክበብ ብስጥ በመግባት የሰራችው ሥራ ነው።

ፍራኦል ውልደቷ በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል በኦሮምያ ክልል ሆሮጉድሩ ወለጋ ፊንጫ አካባቢ ነው። ነገር ግን አዲስ አበባ ስትገባ ከተማው እምብዛም አልከበዳትም። ይልቁንም በቀላሉ ተለማምዳው የተሻሉ ውጤታማ ሥራዎችን አከናውናበታለች። አንዱ ደግሞ ከላይ እንዳነሳነው በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሰራችው ተግባር ነው። ቤተሰቦቿ እንዳስተማሯት ትምህርቷን ሕይወቷ አድርጋ ጎን ለጎን ስለ ሀገሯ ሰላም ሰርታለች። የሰላም ግንባታ ሥራ ካሉበት አካባቢ እንደሚጀምር ታውቃለችና በእነርሱ ጊዜ ዩኒቨርሲቲዎች በከባድ ግጭት ውስጥ ሲወድቅ ለመፍትሄው ተፋጥናለች። የሰላም ክበቡ አስተባባሪ ስትሆን ደግሞ የተለያዩ የመወያያ መድረኮችን እያዘጋጀች በግቢው ውስጥ ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንዲፈጠር የድርሻዋን አበርክታለችም።

ለቤተሰቦቿ የበኩር ልጅ የሆነችው ፊራኦል፣ ያደገችበት ሁኔታና ማኅበረሰቡ ለእርሷ የሚሰጣት ትኩረት ሁሌም ‹‹እችላለሁ›› ባይ እንድትሆን አድርጓታል። በዚህም ያሰበችውን ከማሳካት ወደኋላ አትልም። ይህ ልምዷ ደግሞ በተለይ መድረኮችን ስትይዝ ስለ ሀገሯ መናገር እንድትችል አግዟታል። ስለ ሰላም መመስከር ልምዷ እንዲሆንም ምክንያት ሆኗል።

ፍራኦል ይህ መሰሉ ባኅርይ በሀገሯ ጉዳይ ለመሟገት፣ በዜጎች ደህንነት ዙሪያ ለመሥራት የሚያስችላትን የሕግ ትምህርት እንድትመርጥም ማነሳሳቱን ትገልጻለች። ዘርፉን በመምረጧም የተሻለችና የማዕረግ ተመራቂ እንድትሆን እድል አግኝታለች። በተሰማራችበት የሥራ መስክም ውጤታማ ለመሆን በቅታለች።

የኦሮምኛ ቋንቋ ፍራኦል በአማርኛው ደግሞ ከዘመድ በላይ የሚል ትርጉም የተሰጠውን ስያሜ የያዘችው ባለታሪካችን፣ በሁሉ ነገር ቀዳሚና ቅድሚያ የሚሰጣት ልጅ ለመሆኗ መሰረቶቿ ቤተሰቦቿ እንደሆኑ ትመሰክራለች። በተለይም የዛሬ ብቃቷን ያጎናጸፋት የአባቷና የእናቷ ቁጥጥርና ክትትል እንደሆነ አትዘነጋውም። በጥብቅ ዲስፕሊን እንድታድግና በእውቀትም የተሻለ አቅም እንዲኖራት በጥንካሬ ቀርጸዋታል። ይህ ምግባሯና ‹‹እችላለሁ›› ባይነቷ ደግሞ ዛሬ ድረስ በራሷ ተማምና በገባችበት ሁሉ አሸናፊ እንድትሆን አስችሏታል።

‹‹እኔ አስተማሪ ነኝ የማወርስሽ ገንዘብ ሳይሆን እውቀትና ነገሽን የሚያነጋ መልካም ሥነምግባር ነው›› ትባል እንደነበር የምታነሳው ፍራኦል፤ እኔ ያደኩት ምንም እንደሌለኝ በማመን ነው። ነገየን ለማንጋት ምርጫዬ ደግሞ በርትቼ መማር ብቻ ነበርና አድርጌዋለሁ ትላለች። በተለይ ከሴትነት ጋር ተያይዞ የምትሰማቸው ምክሮች ዛሬም ድረስ ከአዕምሮዋ አልጠፋም። ከነዚህ መሀል አንዱ ‹‹ከባለቤታችሁ እኩል ለመሆንና ያሻችሁን አግኝታችሁ ቀሪ ሕይወታችሁን ለመቀጠል መማርና የተሻለ ሆኖ መገኘት የግድ ነው›› የሚለው ቃል እንደነበር ታስታውሳለች።

በትምህርቷ በጣም ጎበዝና የደረጃ ተማሪ የነበረችው ፍራኦል፤ መሆን የምትፈልገው ልክ እንደቤተሰቦቿ መምህር ነው። በተለይም የሥነጽሁፍ ችሎታዋ በጣም የላቀ ስለነበርና ልጅ እያለች ሕልሟ ጋዜጠኝነት ነበር። ከፍ ስትል ደግሞ ከቤተሰቦቿ ብዙ የተማረችው ነገር በመኖሩ ዕቅዷ ወደ መምህርነቱ ተቀየረ። ይህም በነበረበት አልቀጠለም። ምክንያቱም ሌላ የተሻለና ማኅበረሰቡን በሚገባ ማገልገል የምትችልበት አማራጭ ስላየች ነበር። ይህም የፖለቲካ ልሂቅ መሆን ነው። በዚህም የሕግና ፖለቲካ ሙያን መርጣ ማጥናት ጀመረች። በሁለቱም ትምህርቶች ከፍተኛ ውጤት በማምጣትም የማዕረግ ተመራቂ ሆና አጠናቀቀች።

ፍራኦል በሥራው ዓለም የመጀመሪያ ሕልሟን አሳክታዋለች። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከእርሷ የበለጠ ውጤት ያላቸውም ሆኑ እርሷ በማዕረግ ቢመረቁም በጊዜው በዚያው መቅረት የሚል ነገር አልነበራቸውምና በውድድሮች በመሳተፍ ወደ ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ አቅንታለች። እንደ እናትና አባቷ ተማሪዎችን በብቃት ለማፍራት በመምህርነት ብዙ ባትቆይበትም ሥራን አሀዱ ብላለች።

በዩኒቨርሲቲው ከአንድ ሴሚስተር በላይ መቆየት ያልቻለችው ፍራኦል፣ ቦታው ከአዲስ አበባ ራቅ ያለ በመሆኑና ለመማርም ሆነ ሌሎች የተሻሉ የሥራ አማራጮችን ለመፈለግ ምቹ ስላልነበረ የተሻለ ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰች። አዲስ አበባ እንደገባችም መንገላታት አልገጠማትም። ብቃት ያላትና የማዕረግ ተመራቂ በመሆኗ ‹‹ለእኔ ለእኔ›› የሚላትን አላጣችም። የእርሷ ምርጫ በአንዱ ላይ አረፈ። የአዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ። በኩባንያው በዋናነት የሕግ ክፍሉን በመያዝ ሥራዋን ታቃናው ያዘች። በተጨማሪ ደግሞ የመምህርነት ፍላጎቷ በዋዛ የሚጠፋ ስላልሆነ በማታ መርሀግብርና በቅዳሜና እሁድ በኮሌጆች የማስተማር ሥራን ታከናውን ገባች።

ፍራኦል ወደ አዲስ አበባ የመምጣቷ ሁኔታ የሥራ አማራጭ ማግኘት ብቻ ሳይሆን የመማር እድልን በስፋት ማግኘትንም ያለመ በመሆኑ ይህንን ሕልሟን አሳክታለች። ለዚህ ደግሞ በጥሩ ውጤት መመረቋ በእጅጉ አግዟታል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥሩ ውጤት የነበራቸውን ሴቶች ለይቶና አወዳድሮ የትምህርት እድልን ሰጥቶ ነበርና እርሷ አንዷ ሆነች። በዚህም የሁለተኛ ዲግሪዋን በቢዝነስ ሕግ የትምህርት መስክ እንድትማር አስችሏታል።

ለውጡ እንደመጣ አካባቢ ብዙ ቦታዎች ላይ የመሳተፍና አቅሟን የማሳየት እድሉ የነበራት ፍራኦል፣ በብዙዎች ዐይን በመግባቷ ዛሬ ላለችበትን ቦታ እንድትደርስ አጋጣሚ ፈጥሯል። ይህም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት የሆነችበት ነው።

በገባችበት ሁሉ ለውጦችን ልምድ ያደረገችው ባለታሪካችን፣ ‹‹ማንኛውም ሥራ የብቻ ስኬት የለውም። በቡድን ጥረትና ትጋት ውስጥ የሚታይና የሚገለጥ ነው›› የሚል አቋም አላት። ከዚህ አንጻርም እኔ ብቻ ሰራሁት የምትለው ነገር የላትም። በዚህም በተቋሙ ውስጥ ለመጡት ለውጦች የእርሷ ብቻ አሻራ እንዳልሆነ ትናገራለች። በጥምረት ሰርተን ካመጣናቸው ለውጦች መካከልም የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች ስልጣንና ኃላፊነቶች ውስንነትና በሌላ መወሰዳቸውን የተመለከተው ጉዳይ እንደሆነ ታስረዳለች።

እንደ እርሷ ማብራሪያ፣ ፍርድ ቤቶቹ አንዳንድ ስልጣኖቻቸው ተወስደው ለፌደራሉ ተሰጥቶ ነበር። በተጨማሪም ውስን ኃላፊነቶች ስለነበራቸው ውሳኔ የማይሰጡባቸው ጉዳዮች በርካታ ናቸው። ስለዚህም እነዚህ ጉዳዮች እንዲፈቱ በብዙ ደክመናል። ድካማችን ግን መና አልቀረም ፍሬውን አይተንበታል። ለፌደራል ፍርድቤቶች የተሰጠው ስልጣን ወደ ከተማ አስተዳደሩ ተመልሷል። በተጨማሪም አዳዲስ ኃላፊነቶች ለከተማ አስተዳደሩ ፍርድቤቶች ተሰጥተዋል።

ፍራኦል የአስተዳደር ሥራውን በዋናነት በተሰጣት ኃላፊነት ልክ ብታከናውንም በአንድ ሥራ ብቻ ታጥራ መቀመጥን አትወድም። ከዚሁ ጎን ለጎን በሰበር ሰሚ ችሎቶች እየገባች የዳኝነትን አገልግሎት ትሰጣለች። ዋና ተግባሯም ሰብሳቢ ዳኛ መሆን ነው። ከዚህ አንጻርም በአስተዳደሩም ሆነ በዳኝነቱ ሥራዋ እርሷን ፈልጎ የሚመጣ ሁሉ አግኝቷትና የሚፈልገውን አሳክቶ በሥራ ባልደረቦቿና ተገልጋዮች ዘንድ መልካም ስም አትርፎላታል።

ለፍራኦል ትርፍ የሚባል ጊዜ የለም። ሁሉ ነገር በሥራ ያልፋል። ለምሳሌ ከተቋሙ ሥራ በተጨማሪ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት ዋነኛ ተግባሯ ነው። ይህ ደግሞ በተለያየ መልኩ ይመነዘራል። በትልልቅ መድረኮችና ወርክሾፖች ላይ በመሳተፍ አለያም ጥናታዊ ጽሁፎችን በማቅረብ ሊሆን ይችላል። ወርክሾፖችን በማስተባበርና የተለዩ ሀገራዊ ፋይዳዎች እንዲኖሩት በማድረግም ይሆናል። በተለይም ከሰላም ግንባታ አንጻር የሚነሱ ጉዳዮች ካሉ ወደኋላ አትልም። ይህ ተግባሯ ከበጎ ሥራዋም ባሻገር የሚታሰብና እንደ ሥራም የሚወሰድ እንደሆነ በጭውውታችን ወቅት ነግራናለች።

ፍራኦል በአብዛኛው የሴት ልጅ ችግሮች የሚመነጩት ከማኅበረሰብ የተዛባ አስተሳሰብ መሆኑን ታምናለች። ንቃተ ሕሊናው አሁን ላይ ተሸሽሏል በሚባልበት በዚህ ዘመን ሳይቀር ሴቶች ላይ የሚፈጠረው ጫና ከማኅበረሰቡ የራቀ አይደለም። ስለዚህም ሥራዎች ሲከናወኑ ከቤተሰብ በጀመረ መልኩ መሆን እንዳለበት ታስገነዝባለች። ምክንያቱም እርሷን የሰሯት ቤተሰቦቿ እንደሆኑ በሚገባ ታውቃለችና።

ሴትነት ጥንካሬ ነው። ለፈተና እጅ ሳይሰጡ የተሻለው ሁሉ ይገባኛል ማለት ነው። የተሻለውን በመፈለግ ውስጥ ደግሞ ራስን ብቁና ንቁ አድርጎ መገኘት ነው። ለራሳችን ያለን ግምትንም ማስተካከል ነው። ምክንያቱም ለራሳችን የምንሰጠው ግምት ወይ ስኬት ላይ ወይም ደግሞ ውድቀት ላይ ይጥለናልና። ስለሆነም ቤተሰቦች፣ ከዚያም ትምህርት ቤቶችና የአካባቢ ሰዎች ይህንን አውቀው እነዚህን ተግባራት እውን ያደርጉ ዘንድ ሊያግዟቸው ይገባል ትላለች።

በሰፈር፣ በወረዳና በዞን እንዲሁም በክልልና በሀገር ብቻ የተወሰነች ሴት እንዳትኖር ካሰብን የእኛ አስተሳሰብ ዓለም አቀፈፋዊ መሆን አለበት። ዘመኑን የዋጁ አስተሳሰቦችን ማዳበር ይኖርብናል። ይህንን ካደረግን እንደ ሴት ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር አሸናፊ እንሆናለን ስትልም መልዕክቷን ታስተላልፋለች።

‹‹ሴትን ልጅ ከፍ ማድረግ ሀገርን ከፍ ከማድረግ የማይተናነስ ነው። ምክንያቱም ብዙ ቁጥር የያዝን ስለሆንን የሀገራችን ፍላጎት ሁልጊዜ በሀገር ደረጃም ሆነ በዓለም ላይ መግለጥ እንችላለን። ለምሳሌ እኔ በቤተሰቦቼ እገዛ ዓለምአቀፉን መድረክ ስይዘው የሀገሬ ወቅታዊ ጥያቄ ምንድነው የሚለውን በሚገባ መናገር ችያለሁ። የሀገራት አመለካከት ምን መሆን እንደሚገባውም በሚገባ አስገንዝቤያለሁ። እንደእኔ አይነት ሴቶች በዚህ መልኩ መውጣት ቢችሉ ዓለማቀፋዊ ተቀባይነታችን ከምንም በላይ ማየሉ የማይቀር ነው›› ትላለች።

ኢትዮጵያ በርካታ ሕዝብ ይዛ የባሕር በር የሌላት በመሆኗ በርካታ ችግሮች ይገጥሟታል። በየዓመቱ የጅቡቲን ወደብ ለመጠቀም ብዙ ገንዘብ ማውጣቷ ደግሞ አንዱ ማሳያ ነው። ስለዚህም የባሕር በር ጉዳይ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጉዳይ መሆኑን ለማስገንዘብ ሴቶች የግድ ያስፈልጋሉ። ቁጥራቸው ደግሞ ይህንን ግንዛቤ ለማስጨበጥ ከፍተኛ እድል ይሰጣል።

ሴቶች በተለይም መለያየትን አጥፍቶ አንድነትን ለመስበክ የማይተካ አስተዋዕጾን ያበረክታሉ። ምክንያቱም ‹‹ሴት የላከው›› እንዲሉ ነውና እናት የመከረችው ልጅ ከዚህ ሀሳብ አይወጣም። ስለሆነም በዓለማቀፍ መድረኮች ላይ ተገኝቶ ፍላጎትን ከመንገር ባሻገርና በዲሎማሲያዊ መልኩ ሂደቱ እንዲቀጥል ከማድረግ በተጨማሪ በሀገር ውስጥም ሀሳቡን ከማስረጽ አኳያ ሴቶችን ተጠቅሞ መሥራት እንደሚያስፈልግ ትመክራለች።

‹‹ለእኛ የባሕር በር ማግኘት የተለየ ትርጉም አለው። ኢኮኖሚያችንን ከማሳደጉም በላይ፤ ለወደብ የምናወጣውን ወጪ ይቀንስልናል፤ ሰላማችንን አረጋግጦ ጠንካራ የሆነች ሀገርን እንድንመሰርት ያግዘናል። ከዚህ አንጻርም አሁን የሁላችንም አጀንዳ የባሕር በር ጥያቄያችን መልስ ያግኝ ነው›› የምትለው ፍራኦል፣ ሴቶችን በዚህ አጀንዳ ውስጥ በስፋት ማሳተፍ ጥቅም ከፍ ያለ ስለመሆኑም ታወሳለች።

ፍራኦል ‹‹ ሴት ልጅ ሰፊ እይታ አላት። ሀገሯ ለእርሷ ልዩ ትርጉም የሚሰጣት ነች። ምክንያቱም በእርሷ ሰላም ማጣት ውስጥ መጀመሪያ የችግሩ ገፈት ቀማሽ ሴቷ ስለሆነች። ስለዚህም እያንዳንዱ ተግባር ላይ እርሷን ማሳተፍ የዛሬን ደስታን ማለምለምና የነገዋን ያደገች ሀገር መገንባት ነውና ልብ ይባል›› ባይ ነች። እንቅፋት የሚሆናትን ሁሉ በማስተዋልና በጥበብ የምትመልሰዋን ሴት በሀገር ገጽታም ሆነ የሰላም ግንባታ ውስጥ እናሳትፋት ስትልም ምክሯን ትለግሳለች።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You