የሰው ሀብትን ወደ ሀገራዊ አቅም የሚቀይረው የክህሎት ልማት

የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ለሀገር ጠቃሚ የሆኑ ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎች የሚሠሩበት ቢሆንም በማህብረሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ ግን እዚህ ግባ የማይባል እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ያነሳሉ። ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ግን መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ በመጀመሩ ለውጦች መታየት ጀምረዋል። ይህም በዘርፉ ያሉ አካላትን በክህሎት የዳበረና ለሀገር ጠቃሚ የሆኑ ፈጠራዎች እንዲሠሩ ከማድረግ ባለፈ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ በክህሎት እውቅና እንዲኖራት አድርጓል ነው ያሉት።

ይህን ዘርፍ ወደ ተሻለ ደረጃ ከሚያሸጋግሩት ቀዳሚ ተቋማት መካከልም አንዱ የኢፌዴሪ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ነው። ኢንስቲትዩቱ ከትናንት በስቲያ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያ ዲግሪ (ሌቭል 6) እና በሁለተኛ ዲግሪ(ሌቭል 7) ያሰለጠናቸውን ሁለት ሺህ ሰልጣኞች አስመርቋል። በወቅቱ ንግግር ያደረጉት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ፤ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዘርፍ ወሳኝ ነው። መንግሥት ዘርፉን በማጠናከር ዓለም የደረሰበት ደረጃ ለማድረስ ባለፉት ዓመታት በርካታ ተግባራት አከናውኗል ነው ያሉት።

ይህንን ተከትሎም ዘርፉ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ማግኘቱን ጠቅሰው፤ በ2017ዓ.ም የዓለም አቀፍ የክህሎት ህብረተሰብ አባል መሆን የተቻለበት ውጤታማ ዓመት መሆኑንም አንስተዋል። ዘርፉ ኢትዮጵያ ለጀመረችው ራስን የመቻል ጉዞ ወሳኝ በመሆኑ በቀጣይ የተገኘውን ውጤት ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት ይሠራልም ሲሉም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ እና ራስን የመቻል ትልሟ የሚሳካው ብቁ ሙያተኞችን በማፍራት ዘርፉን በማዘመን ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ተመራቂዎች ይህ ሀገራዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በቀጣይ ዓመት በሌቭል 8 የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርት ለመጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸው፤ ይህም ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ እንደሚያስችል አመልክተዋል።

መንግሥት ባለፉት ዓመታት ለቴክኒክና ሙያ ስልጠና ሥርዓቱ ልዩ ትኩረት በመስጠት ዘርፉን ሳቢና ለሀገራዊ የልማት ፍላጎት ምላሽ ሰጪ ለማድረግ የሚያስችሉ የሪፎርም ሃሳቦችን በመቅረፅ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል። በዚህም እሴት አካይ፣ ተስፋ ሰጪና ተጨባጭ ውጤቶች መታየት ጀምረዋል ሲሉ ገልፀዋል።

የክህሎት ልማት ዘርፉ ካሉን በርካታ የልማት ፀጋዎች አንዱና ዋነኛው የሆነውን የሰው ሀብት ወደ ተጨባጭ ሀገራዊ አቅም ከመቀየር አኳያ ሚናው የላቀ ነው። ኢትዮጵያ የጀመረችው ራስን የመቻል እና ኢኮኖሚያዊ ነፃነት የመጎናፀፍ ብርቱ መሻትና ጥረት በእናንተ የነቃ ተሳትፎ የሚረጋገጥ መሆኑ እምነቴ የፀና ነው ብለዋል።

ለዚህም ባለፉት ዓመታት ተኪ ምርቶችን ለመሥራት የተጀመሩ ጥረቶችና የተገኙ ውጤቶች ራስን የመቻል ጉዟችን መሳካቱ እንደማይቀር ህያው ማሳያዎች ናቸው። በዘርፉ እየተመረቁ የሥራ ገበያውን የሚቀላቀሉ ባለሙያዎች የኢትዮጵያን መሻት እውን ለማድረግ ምቹ ሁኔታን የሚጠብቁ ሳይሆን ተግዳሮቶችን ወደ መልካም አጋጣሚነት ለመቀየር እውቀቱ፣ ክህሎቱና ብቃቱ ያላቸው ዜጎች ናቸው ሲሉ አመልከተዋል።

ለተመራቂዎች ይህ ምዕራፍ የመጀመሪያችሁ እንጂ የመጨረሻችሁ አይደለም። ከሁሉ በላይ ሀገርን የመገንባትና የመሥራት ሃላፊነት የተሰጣችሁ በመሆናችሁ ለቀጣዩ ምዕራፍ የምትዘጋጁበት እና ጉዟችሁም የተሳካ እንዲሆን ከልብ እንደሚመኙ ገልጸዋል።

የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ተቋሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚሰጣቸውን ስልጠናዎች እያሳደገ ይገኛል። በክህሎትና በእውቀት ብቃት ያላቸውን ዜጎችን ለማፍራት ወቅቱን ያገናዘቡ እና የገበያ ፍላጎትን ያማከሉ ስልጠናዎች ተሰጥቷል። ኢንስቲትዩቱ በምሥራቅ አፍሪካ ተመራጭ የልህቀት ማዕከል ለመሆን እየተጋ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ዘንድሮ በመጀመሪያ ዲግሪ አንድ ሺህ 880 በሁለተኛ ዲግሪ 120 በአጠቃላይ ሁለት ሺህ ተማሪዎች በቂ የንድፈ ሃሳብና የተግባር ስልጠና በመውሰድ ለምረቃ መብቃታቸውንም ገልፀዋል። በቀጣይ በሰባት አዳዲስ የትምህርት ዘርፎች ትምህርት ለመስጠት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገበው የዋንጫ ተሸላሚ የሆኑት ተማሪ ባንቴ ዘላለም እና ሀብታም ሞላ በትምህርት ቆይታቸው በንድፈ ሃሳብና በተግባር የታገዘ ትምህርት ማግኘታቸውን ገልጸው፤ በቀጣይም በተማሩበት ዘርፍ ሥራ ፈጣሪ በመሆን ለሌሎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ኢንስቲትዩቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የሙያ ክብር ሽልማት የዳን መስራች ለሆኑት ለኢንጂነር ዳንኤል መብራቱ አበርክተዋል። ሽልማቱ ላለፉት 55 ዓመታት በቴክኖሎጂ ሽግግርና ሥራ ፈጠራ ላይ ላደረጉት ትልቅ አስተዋጽኦ የተበረከተ መሆኑ ታውቋል።

ዳግማዊት አበበ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You